ማህበራት የዋጋ ንረቱን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዳማ፦ በመዲናዋ የህብረት ሥራ ማህበራት የዋጋ ንረቱን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ምርት አምራች እና አቅራቢዎች የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትና ተግዳሮቶቻቸው ላይ የሚወያዩበት መድረክ ትናንት አካሂዷል።

በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንተባ ዣንጥርራ ዓባይ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ የህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡን ችግር በማቃለልና የሸቀጦች ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል። ማህበራቱ በከተማዋ በተገነቡ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ ነው፡፡

የተራዘመውን የግብይት ሰንሰለት ለማሳጠርና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት ማህበራቱን ማጠናከር እንደሚገባ አውስተው፤ ይህም ማህበራቱ በተመጣጠኝ ዋጋ ምርቶችን ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ምቹ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት ከመደበኛው ነጋዴ በዋጋም ሆነ በምርት ጥራት የተሻሉ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በከተማዋ ባሉ የገበያ ማእከላትም ለእነዚህ ማህበራት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ባደረገው ሪፎርምም ከዚህ በፊት በህብረት ሥራ ማህበራት ላይ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቀነስ መቻሉን አቶ ዣንጥራር ተናግረዋል።

የክልሎች የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርት አቅራቢዎች ከከተማ አስተዳደሩ ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩም ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ልእልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ የግብርና ምርቶችን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን፣ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማው ነዋሪ ለማቅረብ ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ በማስተሳሰር የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩም ኅብረት ሥራ ማህበራት አቅማቸውን ለማጠናከር እና ያጋጠማቸውን የፋይናንስ ዕጥረት ለመፍታት ለዋና ዋና የግብርና እና ለተመረጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማቅረቢያ የሚሆን አንድ ቢሊዮን የተዘዋዋሪ ፈንድ ብር በማመቻቸት ምርቶችን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንዲችሉ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ሳይቋረጥ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ሕገወጥ የምርት አቅራቢዎችን ለመከላከል የህብረት ሥራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ ሕገወጥነትን ለመከላከል በህብረት ሥራ ማህበራት መሀከል ቀጣይነት ያለው ትስስር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ልእልቲ የምርት አቅርቦት ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋፋት የተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ሕገወጦችን በመከላከልና ማህበረሰቡ ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቀነስም የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You