አዲስ አበባ፡ በአማራ ክልል በቀጣዩ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያልተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ኮሚሽኑ ገለጸ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከታሕሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እንደሚካሄድም ጠቁሟል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕሮፌሰር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል በወረዳ ደረጃ ተሳታፊዎችን የሚያስመርጡ ከሁለት ሺህ 200 በላይ ተባባሪዎች ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
በክልሉ በብዙ ወረዳዎች ተባባሪ አካላት ተሳታፊዎችን በመለየት አስመርጠዋል ያሉት ዋና ኮሚሽነር ፤ በቀጣዩ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቀሪ የምክክር ሥራዎችን ለማካሄድ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ለዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት ላይ መሆኑን ያመላከቱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ሥራው በ9 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች መጠናቀቁን አውስተዋል፡፡
ከታሕሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከ350 በላይ ወረዳዎች ከሚመጡ ከሰባት ሺህ 700 በላይ ተሳታፊዎች እና ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የክልሉን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡
እንደ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ገለጻ፤ ቀሪ ዓበይት ሥራዎች የፌዴራል ባለድርሻ አካላትን በመሰብሰብ አጀንዳ እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት አጀንዳቸውን እንዲልኩ እና በሚሰጣቸው ቀመር መሠረት ተሳታፊዎችን እንዲልኩ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሥራውን 80 በመቶ የተሟላ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ትግራይ ክልል በመሄድ አንዳንድ ባለድርሻ አካላትን ማነጋገሩን አስታውሰው፤ በክልሉ በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋርም ጥሩ የሚባል ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ኮሚሽኑ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ለመነጋገር በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸው ፤ በክልሉም በኩል ምላሹ መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ እና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር አብረው መሥራት ላልጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጥሪ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ሁኔታ እንደሚያስቀምጡ እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ በኮሚሽኑ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ምክንያቱ አሳማኝ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ኮሚሽኑ አሁን ላይ ከ50 በላይ ከሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየሠራ እና የሚሠራውን ሥራ ፓርቲዎቹ እየተመለከቱ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሁሉንም ማሳተፍ ስላለበት በትጥቅ ትግል ላይ ካሉ አካላት ጋር ቅርበት ሊኖራቸው ከሚችል የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ አካላት ጋር በተቻለ መጠን አሁንም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሁሉም በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም