አዲስ አበባ፡– ኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን መስመር ለማስያዝ የተጀመሩ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ። የተቀዛቀዘውን የጫት የወጪ ንግድ ለማስተካከልና የንግድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ገበያዎችን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ገለጹ።
ሚኒስትሩ ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ የኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አለ። አንዳንድ ነጋዴዎች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር እያንቀሳቀሱ ለመንግሥት ምንም ግብር አይከፍሉም። በሚያዙበት ወቅት ደግሞ ነገሮችን ፖለቲካዊ ዕይታ በማስያዝ ለማምለጥ ይሞክራሉ።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱና የግብር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ እየተሠራ ነው ፤ በመርካቶ የተጀመረውም ይኸው ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መርካቶ ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ ይዛባል ፤ይህንን ለማስተካከል የተጀመረው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጫት ገቢ ከቡና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ከዘርፉ የሚጠበቀው ገቢ እየተገኘ እንዳልሆነ አመልክተዋል። አርሶ አደሩ ሆነ ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን የፌዴራል መንግሥት ገበያ የማስፋት ሥራዎችን
እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመንግሥት በኩል የጫት ኬላዎች እንዲነሱ ቢወሰንም የተለያዩ ሰበቦች እየተፈለጉ 283 ሕገ ወጥ ኬላዎች በመላው ሀገሪቱ አሉ ያሉት ሚኒስትሩ ፤ እነዚህ ኬላዎች የምርት ነጻ ዝወውርን የሚገድቡ፤ የሎጀስቲክ መቀላጠፍን የሚያደናቅፉ፤ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ርምጃ እንዲወስዱ ማሳወቃቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት በጫት የወጪ ንግድ አራት ሺ 900 ነጋዴዎች ፈቃድ አውጥተው የነበረ ቢሆንም የሚልኩት ከ300 ያልበለጡ ነበሩ ያሉት ሚኒስትሩ ፤ ብዙዎቹ ፈቃዳቸውን የሚጠቀሙበት ለኮንትሮባንድ ማስተላለፊያነት ነበር። ይህንንም ለመቅረፍ የንግድ ፈቃድ ቅድመ ብቃትን ያረጋገጠ መሆን አለበት ተብሎ ባለፈው ዓመት 347 ፈቃድ አውጥተው እንዲሠሩ ተደርጓል ብለዋል ።
አሁን ላይ ስድስት መቶ የሚደርሱ ነጋዴዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ለማስቀጠል የንግድ ፈቃድ እድሳት መመሪያው ለእድሳት የአንድ ወር ጊዜ ቢያስቀምጥም ዘንድሮ ከሀምሌ ጀምሮ እስከ ህዳር ሰላሳ 2017ዓ.ም ድረስ እየተከናወነ ይገኛል። የኮታ አሠራር መቆሙ ለጫት የወጪ ንግድ ተጨማሪ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
የሰንበት ገበያን በተመለከተ ሚነስትሩ በሰጡት ማብራሪያም ፤ በሩብ ዓመቱ 59 የቅዳሜና አሁድ ገበያዎች እንዲመሠረቱ ተደርጓል ፤ እንደ ሀገር የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አንድ ሺህ 134 እንዲደርሱ ተደርጓል። እነዚህ ገበያዎች ከአስር እስከ ሰላሳ በመቶ የዋጋ ቅናሽ ያለባቸው ናቸው። የጥራት ጉድለት ላለባቸው ገበያዎችም ደረጃ በማዘጋጀት ነባር ገበያዎች ወደ ተዘጋጀው ደረጃ እንዲያድጉ፤ አዳዲስ ገበያዎች በደረጃው መሠረት እንዲገነቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አንዳንድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተነሳሽነት ወስደው እየሠሩ ይገኛል ፤ አዲስ አበባ መስተዳድር በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በመመደብ በለሚኩራ እና በኮልፌ የግብርና ምርት ማቅረቢያ ማአከላት ገንብቷል። አማራ ክልልም 450 ሚሊዮን ብር በመመደብ የአንደኛ ደረጃ የግብይት ማእከላትን በመገንባት ላይ ይገኛል። እነዚህ ማእከላት ከደላላ ውጪ ግብይት እንዲፈጸም የሚያስችሉ ፤ ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ሚኒስትሩ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ ለአንድ ቀን በተደረገ አሰሳ ካሉት 120 ማደያዎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበረው ስድስት ብቻ ሲሆኑ ስልሳ ስምንቱ ነዳጅ እያላቸው የለም ሲሉ መገኘታቸውን አስታውቀዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ በየቀኑ ላለፉት 125 ቀናት የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ በዚህም በመላው ሀገሪቱ ከ105 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል። ከዚህ ወስጥም ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት በእስራት እንዲቀጡ መደረጉን አንስተዋል ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም