ንባብ የዕውቀትን ውስንነት በማስወገድ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ አምራች ዜጋ ማፍራት የሚቻልበት ነው የሚሉት የንባብ ባህልን ለማነቃቃት ማረሚያ ቤት የተገኙት ደራሲ ገዛሃኝ ሀብቴ፤መጽሐፍት በተለይ ማረሚያ ቤቶች በተለያየ መንገድ የመጡ የሕግ ታራሚዎች የንባብ ባህል የሚያዳብሩባቸው ናቸው፡፡ ንባብ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢገደብ እንኳን ከመላው ዓለም ጋር ግንኙነት መፍጠር የሚቻልበት መሣሪያ እንደሆነ ያብራራል፡፡
አሁን ላይ በማረሚያ ቤቶች ያለው የንባብ ልምድ ታራሚዎች ለቀሪው ዘመናቸው የሚያገለግላቸውን መሠረት መጣል የሚችሉበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሞት ፍርድ የተፈረደበት አንድ ሰው መጽሐፍ እያነበበ ሲታይ ባለው ጊዜ የመኖርን ትርጉም የሚስረዳ መሆኑን ይናገራል።
በፌዴራል ማረሚያ ቤት የትምህርትና ሥልጠና ዋና ዳይሬክተር አቶ አዝመራ አብደታ በበኩላቸው በማረሚያ ቤቶች መጻህፍትን የሕይወት አንዱ አካል አድርጎ ማንበብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በሀገርና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ላይ እንደሀገር ውጤት በቀነሰበት ጊዜ ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች ቀጥሎ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል የሚሉት አቶ አዝመራው፤ ይህም የንባብ ባህል ከማዳበርና ለንባብ ቅድመ ሁኔታዎች በማቻቸት የመጣ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ዋናው ተልዕኮ የሕግ ታራሚዎችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝና ውሳኔ ተቀብሎ የተጠናከረ የጥበቃና ደህንነት፣ የመሠረታዊ ፍላጎት አቅርቦት፣ የምክር እንዲሁም የተለያዩ የትምህርትና ሥልጠና አገልግሎቶችን መስጠት ስለመሆኑ ያመላክታሉ።
እንደ አቶ አዝመራው ገለጻ፤ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አምራች፣ ሕግ አክባሪ፣ ወንጀል ጠል ዜጋ ለመፍጠር እና ከማህበረሰቡ ተቀላቅለው ማህበረሰቡን እንዲክሱ የማስቻል ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም ነው፡፡ ታራሚዎች በሀገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከጎልማሶች የመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በርቀት ከዛም ባለፈ በቴክኒክና ሙያ አጫጭርና የደረጃ ሥልጠናዎች ውስጥ አልፈው የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል፡፡
በቀጣይም የፌዴራል ማረሚያ ቤቱ የተሻለና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ብሎም ይበልጥ ውጤት እንዲመጣ ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ታራሚዎች ከጥፋት ድርጊታቸው ታርመውና በአመለካከትና በአስተሳሰብ ተሻሽለው አምራች ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ማረሚያ ቤቱ የተለያዩ የሥልጠና መርሃ-ግብሮችን በማዘጋጀት እየሠራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዝዋይ ታድሶ ልማት ማረሚያ ቤት ዳይሬክተር ፍቅሬ አቢዩ ናቸው፡፡
ለሕግ ታራሚዎች የሚቀርቡ የቀለምና የክህሎት ሥልጠናዎች በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ያሉ ሲሆን፤ ለሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የማንበብ ልምድ ማዳበራቸው ለሀገርና ለወገን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ታራሚዎች መጽሐፍ ማንበባቸው አስተሳሰብን ከመቀየርና አምራች ዜጋነትን ከማጎናጸፍ ጎን ለጎን ለተለያዩ ሥነ-ልቦናዊ ጫና እንዳይጋለጡ የሚያስችል ነውም ባይ ናቸው፡፡
መጻህፍት ለሰው ልጆች በጊዜና በወቅት የማይናወጽ ወዳጅነት የሚያጎናጽፉ ናቸው፡፡ እጁን ታጥቦ ለሚቀርባቸውም በገበታ የቀረቡ ማዕድ ናቸው፡፡ በተለይም ንባብን የሕይወቱ አካል ለሚያደርግላቸው ደግሞ የተለየ ትሩፋት ይለግሳሉ፡፡
ማንበብ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን መመልከቻ መስታወት ነው፡፡ ሀገርን ለመገንባት ለሚታትሩ ወገኖች አቀበት ቁልቁለቱን የሚያልፉበት ምርኩዝም ጭምር፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል የሚለው አባባል በወረቀት ላይ የሚቀር ሳይሆን ከሰው ልጆች የሕይወት እስትንፋስ ጋር የተለወሰ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
መጽሐፍትን ማንበብ እና ዘወትር የሕይወት አካል ማድረግ ለማነኛውም ዜጋ አስፈላጊ ቢሆንም በማረሚያ ቤቶች ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ መጻሕፍት በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ታራሚዎች አመለካከታቸውን፣ ሥብዕናቸውን፣ ክህሎታቸውን፣ እውቀታቸውን የሚቀርጹበት እንዲሁም ጣፋጭ የሕይወት ውሃ ቀድተው የሚጨልፉበት ምንጭ ነው፡፡
ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት “የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሃሳብ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ያለመ የንባብ ሳምንት ሰሞኑን በዝዋይ ታድሶ ልማት ማረሚያ ቤት ተከፍቷል፡፡ በንባብ ሳምንቱ ማስጀመሪያ ላይም የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት፣ ለዝዋይ ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤትና ለባቱ ከተማ ዋጋቸው 700 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ መጻህፍት አበርክቷል፡፡
መጻህፍቶቹ የታራሚዎችን ሥብዕናና አመለካከት ለመቀየር እንዲሁም በማረሚያ ቤት ቆይታቸው አምራች ዜጋ ሆነው እንዲወጡ የሚያስችሉ መሆናቸውን በርክክቡ ወቅት ተገልጿል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም