“የቅማንት ታጣቂ ቡድን” የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ለመቀበል ስምምነት ላይ ደረሰ

ራሱን “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” ብሎ የሚጠራው ሃይል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት መስማማቱ ተገለጸ።

አሚኮ በምዕራብ ጎንደር ዞን የፀጥታ ምክር ቤት አስተባባሪ ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ መሃመድን ጠቅሶ እንደዘገበው በሀገር ሽማግሌዎች አገናኝነት በተደረገው ውይይት “የቅማንት ታጣቂ ቡድን” የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት ተስማምቷል ።

በቀጣይም በሥራቸው ያሉ እስከ 250 የሚደርሱ አባሎቻቸውን ይዘው መንግሥት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንደሚመለሱም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ታጣቂዎቹ ከሕዝባቸው ጋር በመቀላቀል ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከቀበሌ መሪዎች እና ከመንግሥት አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቋል።

ታጣቂዎቹ ከሕዝባቸው ጋር በመቀላቀል ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከቀበሌ መሪዎች እና ከመንግሥት አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ገልጿል።

በቀበሌው የሚከናወኑ የመንግሥት ተግባራት ከምን ጊዜውም በላይ እንዲሳለጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክቷል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብም ታጣቂዎችን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት በልዩ ልዩ መንገድ ለመደገፍ እንደሚሠሩ ገልፀዋል።

በውይይቱ የምዕራብ ጎንደር ዞን የጸጥታ ምክር ቤት አስተባባሪ ብርጋዴየር ጄኔራል አብደላ መሐመድ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አንዳርጌ ጌጡ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እያሱ ይላቅ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደግነት አበበ፤ የመተማ ወረዳ መሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የታጣቂ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You