የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት- ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሠራች መሆኑ ተደጋግሞ ይገለጻል፡፡ ለዚህም የአረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ የተለያዩ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ቀርጻ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡

የትራንስፖርት ዘርፉ ከ10 እስከ 15 በመቶ ለአየር ብክለት መንስኤ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህን ችግር ለመፍታትም ዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን

እውን ለማድረግ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገ የትራንስፖርት ዘርፍ መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ይገለጻል።

ከህዳር 13 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ኤግዚቢሽን እና ሲምፖዚየም መክፈቻ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ግንባታ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት፣ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ከታለሙ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው፡፡

ሚኒስቴሩም የታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች የማድረግና ምቹ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ አበክሮ እየሠራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ያላት ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ ይህን እድል በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፈር ቀዳጅ ለመሆንና የትራንስፖርት መልክዓ-ምድሯን በማሻሻል ላይ ትገኛለች፡፡ የ 10 ዓመት የትራንስፖርት እቅድም ለሞተር አልባ የትራንስፖርት ስትራቴጂዎች፣ ለሕዝብ ትራንስፖርት ፖሊሲዎችና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

ለዚህም አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ማሟላትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሠን በበኩላቸው፣ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ረገድ ሰፊ እቅድ ይዛ እየሠራች ነው። በትራንስፖርት ዘርፍ የኤሌክትሪክ መኪና ምርትን በማፋጠን የነዳጅ ወጪን ለመቀነስና አረንጓዴ ከባቢን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚመጡት 10 ዓመታት ከ 432 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ እንደሚሆኑ አመልክተው፤ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግሥት ከፍተኛ እገዛና ክትትል እያደረገ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰጠኝ እንግዳው በበኩላቸው፤ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ላለፉት ስምንት ዓመታት የደረቅና ፈሳሽ ጭነት መኪኖችን በሀገር ውስጥ ሲያመርት ቆይቷል፡፡ ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ መገጣጠም ተሸጋግሯል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር 216 የሚደርሱ ከ15 ሰው በላይ የሚጭኑ የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችን ገጣጥሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ቬሎሲቲ የተባለ እህት ኩባንያ አቋቁሞ በ20 ሚኒባሶች እና ሁለት አውቶብሶች አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ተቋሙ ቀደም ሲል ሚኒባሶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችንም ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ እስካሁንም 10 ያህል አውቶብሶችን ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡

እንደሀገር የሚስተዋለውን የመኪና ቻርጀር ችግር ለመቅረፍም ከ60 እስከ 160 ኪሎ ዋት ያላቸው ፈጣን የኤሌክትሪክ ቻርጀሮችን አስመጥቶ ለገበያ ማቅረቡንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ ከፍተኛ ወጪ ስታወጣ መቆየቷ አንስተው፤ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም እንደሀገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ትልቅ አቅም ፈጥራል፡፡ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትም ያስችላል ብለዋል፡፡

የካኪ ሞተርስ አቶ እንግዳ ሰው ደምሴ በበኩላቸው፤ ካኪ ሞተርስ ከሃያ ዓመት በላይ የተለያየ የጭነት መኪኖችን በስፋት ሲያቀርብ የቆየ ተቋም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የአይሱዙ መገጣጠሚያ ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደሀገር ለታዳሽ ኃይል የተሰጠውን ትኩረት ለማሳካት እንዲቻል በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር እያስመጣ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ነው ይላሉ፡፡

በቀጣይነትም ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድተው፤ ይህም እንደ ሀገር የተያዘውን ከካርበን ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ያሉት፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You