ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ጀርባ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሚና ጉልህ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደረሰበት ስኬት የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የጀርባ ደጀን በመሆን ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የተቋቋሙበትን 80ኛ ዓመት ከህዳር 30 ቀን እስከ ታህሳስ ሶስት ቀን 2017 በተለያዩ ፕሮግራሞች ያከብራል፡፡ የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ እንደገለጹት፤ እ.ኤ.አ. 1944 በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ ሃምሳሁለት ሀገራት በተሳተፉበት ጉባዔ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሲቋቋም ከአፍሪካ ከተሳተፉ ሶስት ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መመሥረት በቀናት ልዩነት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት በሚል ስያሜ መመሥረቱን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ደንጌ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት መቋቋምን ተከትሎ በዓመቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋቋመ፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዘመናት ጉዞው ለደረሰበት ስኬት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከጀርባ ጠንካራ ደጀን በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡

ከአየር መንገዱ ስኬቶች ጀርባ የባለሥልጣኑ ሚና ጉልህ እንደሆነ ገልጸው፤ በአንድ ሀገር ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም ከሌለ ጠንካራ አየር መንገድ ሊኖር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ በበኩላቸው፤ የአቪዬሽን ዘርፉ በሀገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በተለይ ለቱሪዝምና ንግድ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኝ ዘርፍ ነው፡፡ የአየር መንገዱ በየዓመቱ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው፤ ከእድገቱና ከስኬቱ ጀርባ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የአየር ትራንስፖርት ደህንነቱ ተጠብቆ ዘለቄታ ባለው ሁኔታ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኘ ተናግረው፤

አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 17 ሚሊዮን መንገደኞችና ከ 750 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ እቃን የማመላለስ አቅም ፈጥሯል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሀገራት ጋር በሚያደርጋቸው ስምምነቶች መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ 141፤ በሀገር ውስጥ ደግሞ 23 መዳረሻዎች እንዳሉት አስታውቀዋል፡፡

በአምስት አውሮፕላኖች የተጀመረው አየር መጓጓዝ ሂደት አሁን ላይ 240 የሚሆኑ አውሮፕላኖች ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገራችን አምስት የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋማት አሉ ያሉት አቶ ጌታቸው፤ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ፈቃድ የተሰጣቸው ከስድስት ሺህ በላይ ፓይለቶች አሉ፡፡ እንዲሁም ብቃታቸው ተረጋግጦ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን እውቅና የሰጣቸው አውሮፕላን ጠጋኞች ከስምንት ሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ለአቪዬሽን ዘርፉ በተለይ ደግሞ ለብሔራዊ የአየር መንገድ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You