‹‹ አምቦ አሁን የሰላምና የልማት ማዕከል ሆናለች ›› – አቶ ሀጫሉ ገመቹ የአምቦ ከተማ ከንቲባ

አዲስ አበባ፡– በትግል ማዕከልነት የምትታወቀው አምቦ አሁን የሰላምና የልማት ማዕከል መሆኗን የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀጫሉ ገመቹ አስታወቁ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የሚከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአምቦ ከተማ ዛሬ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀጫሉ ገመቹ በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው የባዛርና ኤግዚቢሽን መክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ አምቦ ከተማ ከትግል ማእከልነት ወደ ልማትና ሰላም ማእከልነት እየተሸጋገረች ነው፤ ከተማዋ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ስላላት በክልል ደረጃ የሚከበረውን 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንድታስተናግድ መመረጧን አስታውቀዋል፡፡

የምንገኘው በብዙ ፈተና ተከበን ነው ያሉት ከንቲባው፤ በዚህም ምክንያት ጆሯችን ብዙ ያልተረጋገጡ ነገሮችን ይሰማል፡፡ ከርቀት ሆነው አምቦና አካባቢውን የግጭትና የብጥብጥ ማዕከል አድርገው የሚመለከቱ አሉ፡፡ እውነታው ግን አምቦ ከተማም ትሁን መላው ምዕራብ ሸዋ ዞን የግጭት ሳይሆኑ የልማትና የሰላም ማዕከል ናቸው ብለዋል።

በክልል ደረጃ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአምቦ ከተማ የሚከበር መሆኑም አካባቢው ሰላም እንደሆነ ለዓለም ምስክርነት የሚሰጥ እንደሆነ ያመለከቱት ከንቲባው፤ ምእራብ ሸዋና አምቦ ከተማ በተረጋጋ ሰላም ውስጥ እንጂ በጦርነት ውስጥ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ከውጭና ከውስጥ የገጠመንን ፈተና ሁሉ ተቋቁመን ልትፈርስ ጫፍ ላይ የደረሰችን ሀገር መታደግ ችለናል። ለዚህም የአዳዲስ አመራሮች መምጣትና የብልጽግና ፓርቲ መመስረት አስተዋጽኦ ከፍያለ እንደነበር ገልጸዋል። የክልሉ አመራሮች የኦሮሞ ሕዝብን አሳታፊ ያደረገ ፍኖተ ካርታ በማስቀመጥና ታግለው በማታገላቸው ትልቅ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ሃይማኖቶችንና ቋንቋዎችን የያዘች ትልቅ ሀገር ነች ያሉት አቶ ሀጫሉ፤ እነዚህን ልዩነቶች አቻችላ ጠላቶቿን በጋራ ክንድ በመመከት ህልውናዋን አስጠብቃ ኖራለች፡፡ አባቶቻችን በዚህ መልክ አስከብረው ያቆይዋትን ሀገር እኛም ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ ትናንታችንን በትውስታ፤ ዛሬያችንን በሥራ ማሳለፍ ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

ዓመት በዓሉን በማስመልከትም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የልማት ሥራዎች መጎብኘታቸውን፤ የደም ልገሳና የጽዳት ሥራዎች መከናወናቸውን ፤ እስከ በዓሉ እለት ድረስ የሚቆይ ባዛርና ኤግዚቢሽን መከፈቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ከተለያዩ የክልሉ ዞኖች የመጡ የባዛሩ ተሳታፊዎችም የንግድ ልውውጥ ከማድረግና ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር የአምቦን የሰላምና የልማት ገጽታ የሚያስተዋውቁ አምባሳደሮች እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎችም የእንግዶቻቸውን ደህንነት ጠብቀውና በክብር አስተናግደው እንዲሸኟቸው ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You