ሀዋሳ:- ሲዳማ ባንክ ባለፈው የሂሳብ ዓመት 71 ነጥብ 6 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ፤
ባንኩ የባለ አክሲዮኖች 3ኛ መደበኛና 3ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሀዋሳ ትናንት ተካሂዷል።
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ማርሻሎ የባንኩን ያለፈውን በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 45 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ 71 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም ከእቅዱ አንጻር 58 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ በተቀማጭ ሀብት አሰባሰብ፣ አዳዲስ ደንበኞች ምልመላ፣ ኮርፖሬት ደንበኞች በማፍራት እና ከክልሉ መንግሥት ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት በማጠናከር በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
የተመዘገበው ትርፍ ባንኩ አዲስ ከመሆኑና ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የብድር ማስፋፊያ ጣሪያ ከነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች አኳያ ሲታይ አበረታች ሊባል የሚችል መሆኑንም ነው አቶ አብርሃም የገለፁት።
በሁሉም ቅርንጫፎች አማካይነት ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተደረገው ጥረት ፈታኝ የነበረ ቢሆንም የባንኩን አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን አንድ ነጥብ 22 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉን ጠቁመው፤የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም ሁለት ነጥብ 62 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ98 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክተዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 799 ነጥብ 29 ሚሊዮን ብር ብድር ለደንበኞቹ በመስጠት አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠን ወደ አንድ ነጥብ 17 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በበጀት ዓመቱ በደንበኞቻችን ላይ የተከሰተው የንግድና ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ በተበዳሪ ደንበኞች የብድር አመላለስ እና በማሰባሰብ ሂደት ላይ ተፅዕኖ ቢፈጥርም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድና የስራ አመራሮች በወሰዱት ስትራቴጂካዊ የስራ አመራር የባንኩ ጤናማ ያልሆኑ ብድሮች መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ጣሪያ በታች ሁለት ነጥብ 96 በመቶ እንዲሆን መደረጉንም አንስተዋል፡፡
የባንኩን ቅርንጫፎች አድማስ እና ተደራሽነትን ለማስፋትም በበጀት ዓመቱ 8 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈት መቻሉን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፤ አጠቃላይ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥር ወደ 39 ከፍ ማለቱን ገልፀዋል።
የባንኩ ባለአክሲዮኖች በተጨማሪ አክሲዮን በመግዛት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ተፈለገው የካፒታል መጠን መድረስ እንዲቻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃም ማርሻሎ ጠይቀዋል።
በመደበኛ አስቸኳይ ጉባኤ ለቀጣይ ዓመታት የሚያገለግሉ የዳይሬክተሮች ቦርድ በባለ አክሲዮኖች ተመርጠዋል።
አበበች ማቴዎስ
አዲስ ዘመን እሁድ ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም