በአሁኑ ወቅት የጤና መድህን ተጠቃሚው ቁጥር ከ53 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ይህን የጤና መድህን አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንዳለም መረጃው ያሳያል፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አገልግሎቱን ለማዳረስም በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አኳያም በክልሎች ያለው የጤና መድህን አገልግሎት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማንሳት ተሞክሯል፡፡
በሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ የህክምና አሰጣጥ ስራ ሂደት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኢማን ዘይዳን እንደሚሉት፤ በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት መተግበር የጀመረው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የተሻለ አፈፃፀም እያሳየ መምጣቱን የገለፁት ኃላፊዋ፤ በ2016 ዓ.ም ክልሉ ላይ ባሉት ዘጠኙም ወረዳዎች መተግበር ተችሏል ይላሉ፡፡ 46ሺ 196 አባዎራዎችንም አባል ማድረግ እንደተቻለ ይገልፃሉ፡፡
በዘጠኙም ወረዳዎች አንዳንድ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት መድኃኒቶችን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግና ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ እንደነበር አንስተው፤ ጥሩ አፈፃፀም እንደነበረ ጠቁመዋል። አቅም የሌላቸውን 7ሺ 478 የህብረተሰብ ክፍሎች ከየወረዳው በመለየት በጊዜውና በወቅቱ ወደ ክልሉ ፋይናንስ ቋት በማስገባት ያለምንም እክል አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉንም ያስረዳሉ፡፡
የጤና መድህን ዋና አላማው ከመታመም አስቀድሞ በመክፈል እርስ በእርስ መረዳዳትን ማዳበር ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ በክልሉ ያሉ ባለሀብቶችና የግሉ ዘርፍ በየዓመቱ የተለያየ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡ በ2016 ከተሰበሰበው 24 ሚሊዮን ብር ወደ 2 ሚሊዮን የሚሆነው የግል ባለሀብቶች ድጎማ መሆኑን አስታውሰው፤ የእነሱ ትብብር ክልሉን የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
የአባልነት መታወቂያ ዕድሳቱ ላይ በዘመቻ የሚሰጠው የተፋጠነ አገልግሎትም አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።፡ ነገር ግን እንደሀገር የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያለው ክፍተት አባላቱ ላይ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑ ተግዳሮት እንደሆነባቸውም ገልፀዋል፡፡
በሱማሌ ክልል ጤና ቢሮ የጤና መድህን አስተባባሪ የሆኑት አቶ በድሪ አብዲ በበኩላቸው፤ የ2017 ዓ.ም የጤና መድህን ንቅናቄ በክልሉ መጀመሩን ገልፀው፤ በዚህ ዓመት እንደተያዘው አርባ አዳዲስ ወረዳዎችን ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በህዳር ወርም አዳዲስ አባላትን የመመልመል ስራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
አዲሱን የቁርጥ ክፍያ አከፋፈል ለመተግበር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የገለፁት አስተባባሪው፤ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ተብሎ በገቢ መጠን መሰረት የሚከፈል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ከአንድ መቶ አርባ ጤና ጣቢያዎችና ከ18 ሆስፒታሎች ጋር ውል መፈራረማቸውንም ያስረዳሉ፡፡
በክልሉ ያለው የጤና መድህን ተጠቃሚ ቁጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሶስት ሺህ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ ዓመት ደግሞ አንድ ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመዋል። በገንዘብ ደረጃም አምና አርባ ሚሊዮን እንደተሰበሰበ ገልፀው፤ በቀጣይ ሰባ ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
ዲጂታል የማድረግ ስራም በአንድ ወረዳ እንደተጀመረ ይገልፃሉ፡፡ ከዛ ባሻገር አገልግሎቱ ከሌሎች ክልሎች ዘግይቶ የተጀመረ መሆኑና ማህበረሰቡ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚተዳደር መሆኑ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡
በ2016 በከተማ አስተዳደሩ የተሻለ አፈፃፀም እንደነበረና ተጠቃሚውን ወደ 78በመቶ ለማድረስ መቻሉን የገለጹት ደግሞ ወ/ሮ ሜሪ አብዱ በድሬዳዋ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አስተባባሪ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለፃ 50ሺ 985 አባዎራዎችን አባል ማድረግ ተችሏል፡፡ በ2016 ዓ.ም ወደ 58ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም አስታውሰዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩም ለ10ሺ 908 አባወራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው፤ ለዚህም ወደ 10 ሚሊዮን ብር ከአስተዳደሩ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ አስራ ስድስት ጤና ጣቢያዎች ሁለት ሆስፒታሎች፣ አንድ የቀይ መስቀል ፋርማሲ ፣ ሶስት የሕዝብ መድኃኒት ቤቶች መኖራቸውን የገለፁት አስተባባሪዋ፤ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ ለጤና ጣቢያዎች የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ስላለ የተሻለ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር አስችሏል ይላሉ፡፡
ከዚህ በፊት የነበረውን የመድኃኒት ቤቶቹን በየሶስት ወሩ መጠየቂያ እየላኩ መጠየቂያው ተተንትኖ አቅርቦቱ የመዘግየቱን ስራ እንዳስቀረም አስረድተዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር አንዱ ጋር የሌለውን መድኃኒት ከአንዱ እንዲያገኙ የማድረግ ስራም እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመትም አዲሱን የቁርጥ ክፍያ አከፋፈል ለመተግበር እየተወያዩ እንዳለ አብራርተዋል፡፡
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም