ትክክለኛውን የአትሌቲክስ መሪ ለማግኘት ከማን ምን ይጠበቃል?

ስፖርት ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አትሌቲክስ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚሳሳለት ስፖርት ነው፡፡ አትሌቲክስ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በዓለም መድረኮች ከመገንባት ባለፈ ለሀገር ያለው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ስፖርቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደራራቢ መሰናክሎች ውስጥ ለማለፍ ተገዷል፡፡

የተለመደ ውጤት ያልተመዘገበበትን የፓሪስ እኤአ 2024 ኦሊምፒክን ጨምሮ በሌሎች ውድድሮች ለገጠሙት የውጤት ማሽቆልቆልና ይህንን ተከትሎ ለተነሳው ውዝግብ በርካታ ምክንያቶች ቢቀርቡም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ግን ይበልጥ ሚዛን የሚደፉ ይመስላሉ፡፡

ይህንን በፌዴሬሽን ውስጥ የሚታይ አስተዳደራዊ እንከን ፈር በማስያዝ አትሌቲክሱ በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ የሚያደርግ ሁነኛ አመራር የግድ ይላል፡፡

ይህ አይነቱ የስፖርቱ አመራር ደግሞ ፌዴሬሽኑ በየአራት ዓመቱ በሚያደርገው የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ላይ የጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ አግኝቶ ስልጣን መያዝ ይኖርበታል፡፡

እንደሚታወቀው በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱበት የስራ ዘመኑን ያገባደደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሳምንታት በኋላ በሚካሄደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ በአዲስ ይተካል፡፡ ይህም ስፖርቱን ከገባበት የቁልቁለት ጉዞ መንጭቆ የሚያወጣው አዲስ አመራር የሚመጣበት ትክክለኛው ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ብዙዎች ተስፋ አድርገውበታል፡፡

አትሌቲክሱን ለመምራት ወደ ኃላፊነት የሚመጣው አዲስ አመራር እንዳለፈው ጊዜ የስፖርት ቤተሰቡን ላለማሳዘን፣ የአትሌቶችን ጥያቄ ለመመለስ እንዲሁም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ምን ዓይነት ስትራቴጂ እቅዶችን ይዞ ሊቀርብ ይገባል? ለስፖርቱ ሁነኛ ሰው በመምረጥ ረገድ ትልቅ ዋጋ ያለው ድምፅና ኃላፊነት የተሸከሙት የጉባኤ አባላትስ ምን ይጠበቅባቸዋል? የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ከወዲሁ አነጋጋሪ ሆነዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አትሌት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴ፤ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈጻሚነት የሚቀርቡ ሰዎች በደንቡ የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላታቸው ቀዳሚው ነገር መሆኑን ይናገራል፡፡

ከመስፈርት ባለፈ ግን በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉና የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ የሚችሉ፣ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠልና ያልተነኩትን(የአትሌቶች ልማት፣ የህጻናት አትሌቲክስን መሰል ጉዳዮች) ማስጀመርን የመሳሰሉ ብቃቶች ሊኖሯቸው ይገባል ባይ ነው፡፡

ለስራ አስፈጻሚነት የቀረቡት እጩዎች ስፖርቱ በዚህ ዘመን የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት ማሟላት የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁሙት ደግሞ የስፖርቱ ምሁርና የአትሌቲክስ አሰልጣኙ ብዙአየሁ ታረቀኝ(ዶ/ር) ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ስልጠና እስከ ሦስተኛ ደረጃ የደረሱትና የጥሩነሽ ዲባባ የስልጠና ማዕከልን ጨምሮ በበርካታ ክለቦች በአሰልጣኝነት የሰሩት ብዙአየሁ ታረቀኝ(ዶ/ር)፣ አትሌቲክስን መምራት በዚህ ወቅት ትልቅ አቅምን ይጠይቃል ይላሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወዳዳሪነቱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ጥቂት ምርጥ ፌዴሬሽኖች(ተቋማት) ጋር ነው፡፡ መገንባት ያለበት በእኩል መፎካከር የሚችል ፌዴሬሽን እንደመሆኑ በምርጫው የቀረቡት እጩዎች በዚህ ደረጃ ላይ መገኘት የሚችሉ ናቸው የሚለውን መመዘን አስፈላጊ ነው›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

እንደ አሰልጣኝ ብዙአየሁ ገለፃ፣ ቀድሞ እንደነበረው ጥቂት ልምድ ብቻውን የስፖርቱ መሪ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይልቁንም አትሌቲክስ እውቀት የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ ስለዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በእኩል መነጋገር የሚችል ባለሙያና ስትራቲጂካዊ እይታ ያለው ሰው የግድ ነው፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን የሚቀላቀሉ ሰዎች በቅንነት ከባለሙያዎች ጋር በቅርበት በመስራትና በትምህርት እንዲሁም በልምድ የካበተ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ያካተተ ጠንካራ ቴክኒካል ኮሚቴ በማዋቀር የሚፈለገውን ነገር ማሟላት ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በሚቀጥሉት ዓመታትም የአትሌቲክሱ ውጤት ይበልጥ እያሽቆለቆለ የስፖርት ቤተሰቡም እያዘነ መቀጠሉ አይቀርም ብለዋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት በተጨማሪ በስፖርቱ ዕድገትም ይሁን ውድቀት ትልቅ ሚና ያላቸው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ‹‹ስፖርቱን መምራት ይችላሉ›› ተብለው ለምርጫ ወደ እጩነት የሚያቀርቡት በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወካይነት ነው፡፡ ስለዚህ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተገቢውን ሰው በመወከል ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ በምርጫው ድምጽ የሚሰጡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላትም ለስፖርቱ ለሚበጀው ትክክለኛ ሰው ብቻ ድምፅ የመስጠት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ኮሚሽነር ማርቆስ እጩዎችን ከመላክ አስቀድሞ ክልሎች እነማንን መወከል እንዳለባቸው በተገቢ ሁኔታ ማጤን እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ ለስፖርቱ እድገት እነማን በተሻለ ሁኔታ ይሰራሉ የሚለውን መዝነው ካሳወቁ በኋላም ድምጽ የመስጠት ሂደቱ በጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ይላል፡፡

ስፖርቱን በትክክልና በሃቀኝነት ሊያገለግል የሚችለውን እጩ መለየት የግድ መሆኑንም ያብራራል፡፡ በቅርቡ በኦሊምፒክ የታየው መጥፎ ሁኔታ በአትሌቲክሱ እንዳይደገምም መራጮች የስፖርትን መርህ በመከተል ለአትሌቲክስ እድገት ለሚበጀው አካል ድምጽ መስጠት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

አሰልጣኝ ብዙአየሁ በበኩላቸው፣ የክልሎች ቀዳሚ ስራ ያቀረቧቸው እጩዎች እነማን ናቸው? የሚለው መሆን አለበት ይላሉ፡፡ አክለውም፣ ለስፖርቱ የሚጠቅም ሃሳብና ራዕይ ያለው እንዲሁም ስፖርቱን ከወደቀበት በማንሳት ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ የሚችልን እጩ ስለማቅረብ አስቀድመው መስራት ይገባቸዋል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ በምርጫው ድምጽ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ጠቅላላ ጉባኤው የእጩዎችን ሃሳብና ዕቅድ እንዲሰማ ቢደረግ መልካም ይሆናል ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ብዙአየሁ ከሕግ አንጻር ሲታይ በድምጽ አሰጣጡ ላይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ ብለው ያምናሉ፡፡ በተለይ የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት አትሌቶችና አሰልጣኞች የሚመራቸውን አካል መምረጥ የሚያስችላቸው የድምጽ ብዛት ሊታሰብበት ይገባ ነበር ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ ስፖርቱ ‹‹ባለህበት እርገጥ›› እንዳይሆን በቀጣዩ ምርጫም ቢሆን ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት ሊሰራ የሚችለውን እጩ በትኩረት በመለየት ድምጽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

እጩዎችም ቦታውን ለመያዝ ብቻ ሳይሆን አትሌቲክሱን ለማሳደግ በተቆርቋሪነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስቀምጠዋል፡፡

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን ተሻሽሎ የቀረበው መመሪያ፣ ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመራጭ የሚሆኑ አካላትን መስፈርት ይዘረዝራል፡፡ በዚህም መሰረት ተመራጮች የስፖርት ፍቅር ያላቸው፣ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡና በጽናት የሚቆሙ፣ ከሙስና የጸዱ እና በስፖርቱ ማህበረሰብ ተቀባይነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ያመላክታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ስፖርቱን በሀብቱ፣ በእውቀቱና በሙያው መደገፍ የሚችሉ እንዲሆኑም ያሳስባል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You