ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፉ በሽታዎች ትኩረት እንደሚሹ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፉ ኤች አይ ቪ ኤድስ ፣ ቂጥኝ እና ሄፒታይተስ ቢ አሳሳቢ የጤና ስጋት እየሆኑ በመምጣታቸው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ የማስጨበጥ ኃላፊነታቸውን በትኩረት እንዲወጡ ጥሪ አቅረበ።

በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ክፍል ኤክስፐርት አቶ ሙለጎ ሻፊ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ከእናት ወደልጅ የሚተላለፉና አሳሳቢ የጤና ችግሮች ተብለው በተለዩት በኤች አይ ቪ ኤድስ ፣ በቂጥኝ እና በሄፒታይተስ ቢ በሽታዎች ዙሪያ ሚዲያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሰፊ ስራ መስራት አለባቸው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥናት እ.አ.አ በ2024 በሀገራችን 13 ሺ 312 ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ነፍሰጡር እናቶች መኖራቸውን ያመለከቱት አቶ ሙለጎ፤ ይህ አሀዝ ቀድሞ ከነበረው 16 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 8 ነጥብ 64 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥሩ በተፈለገው ልክ የወረደ ባለመሆኑ ግንዛቤው ላይ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ከኤች አይ ቪ ኤድስ ነጻ የሆነ ትውልድን ለመፍጠር ከተቀመጠው ግብ አኳያ፤ የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መ ምጣቱ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በማፍራት ሂደት ውስጥ ስጋት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የቂጥኝ በሽታ በነፍሰ-ጡር እናቶች ላይ ሲከሰት 80 በመቶ ያህል በጽንሱ ጤና ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ሙለጎ ፤ ጥናታዊ አሀዝ እንደሚያመለክተው የበሽታው ስርጭት በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝና በአሁኑ ጊዜም ከዜሮ ነጥብ 6 በመቶ ወደ 5 ነጥብ 1 በመቶ ከፍ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የሄፒታይተስ ቢ በሽታም አሁን ላይ አሳሳቢ የሚባል የጤና ችግር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ይህ በሽታ በሀገራችን 4 ነጥብ 8 በመቶ ያህል ሽፋን አለው፡፡ በሽታው በእናቶች ላይ በተከሰተ ጊዜ የሚያደርሰውን የከፋ ጉዳት በመገመትም ከፍ ያለ ክትትል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ሂፒታይተስ ቢ በተለይ ኤችአይቪ ባለባቸው እናቶች ላይ ታክሎ ሲመጣ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አቶ ሙለጎ ገልጸው፤ ለዚህም የጤና ሚኒስቴር ዕቅድ ይዞ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከበርካታ ተላላፊ በሽታዎች በላይ ለሶስቱ የተለየ ትኩረት የተሰጠው የመተላለፊያ መንገዳቸው ተመሳሳይ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ሙለጎ ፤ ሁሉም በሽታዎች የሚተላለፉት በግብረ-ስጋ ግንኙነት ነው፡፡ እናቶች በነዚህ በሽታዎች ከተጠቁ በኋላ የሞትና ህመም ምጣኔያቸው ከፍ ያለ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

ነፍሰ-ጡር እናቶች በጊዜና በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በሽታዎቹ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፉ ማድረግ እንደሚቻል የገለጹት አቶ ሙለጎ፤ በሽታዎቹ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የእናቶችንና የህጻናትን ጤና በመጠበቅ ሂደት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በበሽታዎቹ ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሙለጎ፤ ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነት ከፍያለ ነው ብለዋል። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ከመገናኛ ብዙኃን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል በሚደረገው ትግል ሚዲያዎች ተገቢውን መረጃ ለህብረተሰቡ የማድረስ ሚናቸውን ሊወጡ፤ በተለይ ከእናት ወደልጅ በመተላለፍ የጤና ችግሮች በሆኑት ሶስቱ በሽታዎች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You