ማዕከሉ የተደራጁ ወንጀሎችን በመመርመር ለፍትህ ሥርዓቱ አጋዥ መረጃዎች ይሰጣል

አዲስ አበባ፡- የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል እንደሀገር ሊፈጸሙ የሚችሉ የተለያዩ የተደራጁ ወንጀሎችን መመርመርና ለፍትህ ሥርዓቱ አጋዥ የሆኑ መረጃዎችን የመስጠት አቅም እንዳለው የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። ማዕከሉ ለጎረቤት ሀገራት አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከሉ በቀጣዩ ዘመን እንደሀገር ሊፈጸሙ የሚችሉ የተለያዩ የተደራጁ ወንጀሎችን መመርመርና ለፍትህ ሥርዓቱ አጋዥ የሆኑ መረጃዎችን የመስጠት አቅም ያለው ነው፡፡

የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከሉ የፎረንሲክ አቅምን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም በሚያስችል መልኩ ተደራጅቷል ያሉት ጀነራል መስፍን፤ በዘመኑ በሚስተዋሉ የወንጀል አይነቶች ላይ ምርመራዎችን ማካሄድ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተሟልተውለታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ወንጀልን መከላከል የሚያስችል ጠንካራ የምርመራ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው፤ በማዕከሉ ወደ ውጭ ተልኮ ሲከናወን የነበረውን የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ በሀገር ውስጥ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ለክልልና ለፌዴራል ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ለሚገኙ የሌሎች ሀገራትም ጭምር አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ብለዋል፤ ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት

ማዕከሉን እንደራሳቸው መጠቀም የሚችሉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወንጀልን በጋራ መከላከል ካልተቻለ ወንጀለኞች በሀገር አጥር የሚገደቡ አይደለም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ የማዕከሉ አደረጃጀት፣አሰራርና አቅም እየተገነባ ያለው ለሁሉም ማገልገል በሚያስችል መልኩ ነው ብለዋል፡፡

ፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የፎረንሲክና የምርመራ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ሆኖ በቀጣይነት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት በመደበኛ፣ ሥልጠናዎች፣ በአጫጭር ፕሮግራሞች እያሰለጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የማዕከሉን ባለሙያዎች የማሰልጠን ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ሁልጊዜ እያደገ ከሚሄደው ቴክኖሎጂ ጋር አዳዲስ ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎች እየተጨመሩለት እንደሚሄድ በመግለጽ፣ተጨማሪ ማሽኖችንና የሰው ኃይል በማስገባት አቅምን ማሳደግና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ቅርንጫፎችን የማስፋት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ህዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You