
ከእግዜርጋ ቀጠሮ ያዝን:: ቦታውም የዕድሜ
አውቶቡስ በምታልፍበት ፌርማታ ላይ። ሰዓቴን
ሳላዛንፍ እንዲያውም አንድ አስር ደቂቃ ቀደም ብዬ
ተገኘሁ። ፈንጠር ብሎ አንድ ሽማግሌ ዓይነ ስውር
ነዳይ ምጽዋት ይለምናሉ።
ገና ከመድረሴ ነዳዩ:- “የኔ ልጅ ተዘከረኝ ቀኑ
የጨለመብኝ ሌቱ …” አላስጨረስኳቸውም “እግዜር
ይስጥልኝ አባቴ”
ስንገናኝ ምን እደንምለው ምን እንደምጠይቀው
ምን እንደምወቅሰው እያሰላሰልኩ ጥበቃዬን
ተያያዝኩ።
የዕድሜ አውቶቡስ ዝም ብሎ ያልፋል።
“የሚመራኝ ልጅ ጠዋት እዚህች ድንጋይ
ላይ የጎለተኝ ነኝ። ምን ሆኖ እንደሁ አላውቅም
ያለውትሮው ዘገየብኝ። ከነጋ እህል ባፌ አልዞረም”
አሉ ለማኙ
አልመለስኩላቸውም።
“አንዳች የሚበላ ነገር ይዘህ ይሆን?”
“አባቴ ይቀልዳሉ ልበል?”
“አትበል። ቀልዴን አይደለም። ”
“ሲያዩኝ ርዳታ ማስተባበሪያ መስላለሁ እንዴ?”
“ይቅርታ ልጄ አትቆጣ። እንዲያው አፍ
የሚያካፍት ስላገኘሁ ደስ ብሎኝ ነው። ዓይኔ ታወረ
እንጂ ልሳኔ አልተዘጋም። ለምን እንደሁ እንጃ ግን
ሰው አያወራኝም። ” ያዘኑ መሰሉ።
እኔ ምናገባኝ ታዲያ አልኩ በሆዴ።
“አንዱ ስላንዱ ማሰብ ተው። ፍቅር ቀዘቀች።
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም ገጽ 9
ዓለም አቀፍ
መዝናኛ
የብዕር ጠብታ
ለምን ይመስልሃል ልጄ?”
“እንጃ!”
“ምክንያቱም ስግብግቦች ስለሆንን ነው።
ሆዳሞች ስለሆንን ነው። ”
ሰዓቴን አስር ጊዜ አያለሁ።
ምነው እግዜር አረፈደ?። . . .
የዕድሜ አውቶቡስ ዝም ብሎ ያልፋል።
“ግን የአምላክ ዓላማ እንዲያ አልነበረም። ” አሉ
አዛውንቱ “የሱማ ዓላማ ፍቅር ነበር። እርስ በርሳችን
ስንዋደድ ነው መንግሥቱን የምናሰፋ። እኛ ግን
እርስ በርስ ጦር እንሳበቃለን። ሠይፍ እንማዘዛለን።
ለጊዜያዊ ጎጇችን ዘላለማዊ ቤታችንን እናፈርሳለን። ”
ትግስቴ አለቀ። ከዚህ በላይ መጠበቅ
አልቻልኩም። ግን ቆይ ምናልባት እግዜር እንደ አበሻ
ሊሆን ስለሚችል ትንሽ ልጠብቀው።
የዕድሜ አውቶቡስ ዝም ብሎ ያልፋል።
“ምን እየጠበክ ነው ታዲያ?” አሉ ሽማግሌው።
“መቼም አባቴ አንድ ሰው ፌርማታ ከተገኘ
አውቶቡስ እንጂ ዶሮ አይጠብቅ”
ፈገግ አሉ። ድምጻቸውን እንደመሞረድ አረጉና
“ሰማህ ልጄ” አሉ “ሰማህ የዕድሜ አውቶቡስ
በፌርማታ ሲያልፍ እንጂ መቼ ሲቆም ታይቶ
ያውቃል?”
“ታዲያ ፌርማታ ለምን ተሠራ?”
“እግዜርን መጠበቂያ ነዋ። እግዜርና ሰው ቀጠሮ
የሚይዙት ከእድሜ አውቶቡስ ፌርማታ ነው።
አንተም ከእግዜርጋ ቀጠሮ ይዘህ የመጣህ መስሎኝ”
“ልክ ነዎት። ግን እንዴት አወቁ?”
“ብዙ ሰው እንዳንተ ከግዜርጋ ቀጠሮ አለኝ
እያለ በየጊዜው ይመጣል። እኔ ደሞ ሽቀላዬን እዚቹ
ፌርማታ ስር ተቀምጬ ስለሆነ ምሸቅለው በዚህ
አውቃለሁ”
“ታዲያ እንደተቃጠሩት እግዜር በሰዓቱ
ይመጣላቸዋል?”
“አዎ። ግን ብዙዎቹ ትተውት ይሄዳሉ። ”
“እንዴት?”
“አላውቅም። ይቀጥሩትና በሰዓቱ ሲመጣላቸው
ትተውት ይሄዳሉ”
“ታዲያ ለኔ ለምን በሰዓቱ አልመጣልኝም? . . .
ይሄው አሁን እንኳ ግማሽ ሰዓት አለፈው”
ሽማግሌው ፈገግ አሉ።
“እኮ የታል እግዜር?”
“እንግዲህ እኔ ዓይን የለኝ እንዳላፋልግህ። ዞር
ዞር እያልክ ፈልገዋ ልጄ”
የዕድሜ አውቶቡስ ዝም ብሎ ያልፋል።
እንዳሉኝ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ዞር ዞር እያልኩ
እግዜርን ፈለኩት። ባካባቢው ከኔና ከዓይነሥውሩ
ለማኝ በቀር ማንም የለም።
ወደ ቤት ልመለስ ተነሳሁ።
“በቃ ተስፋ ቆርጠህ ልትሄድ ነው?” አሉ ነዳዩ
“ምንም ማድረግ አልችልም። ከዚህ በላይ
የምጠብቅበት ትግስት የለኝም። ከመጣ ግን ጠብቄው
ጠብቄው ጠብቄው . . . ተስፋ ቆርጬ እንደሄድኩ
ይንገሩልኝ”
እቤት ስደርስ ስልኬ አቃጨለ። እግዜር ነው።
“ምነው? ምናረኩህ? ምንበደልኩህ? ምን
አስቀየምኩህ? ምን አጠፋሁ እግዜር?”
“ምን ሆነሃል?”
“ጭራሽ ምንሆነሃል? ትለኛለህ?! . . . አንድ ሰዓት
ሙሉ አስደግፈኸኝ?”
“አላስደገፍኩህም። ቀድሜህ ነው የተገኘሁት።
አንድ ሰዓት ብቻ ሳይሆን ዕድሜ ልክ ነበር የጠበኩህ።
እጠብቅሃለሁም። ”
“ጭራሽ ቀድሜህ ትለኛለህ? ጭራሽ ዕድሜ ልክ
ጠበኩህ ትለኛለህ?. . . አንተም እንደሰው ትቀልዳለህ
እንዴ እግዜር?”
“እረ በፍጹም። ”
“ታዲያ በቀጠሯችን ቦታ መች ተገኘህ?”
“እዚያው ነበርኩኮ። ስላልፈለከኝ ነው። ”
“እኮ የቱጋ? . . . አስታውሳለሁ አጠገቤ
ከነበሩት ዓይነስውር ለማኝ በቀር በስፍራው ማንም
አልነበረም”
“ታዲያ ዓይነ ስውሩ ለማኝ እኔ አልነበርኩ
እንዴ?”
“ምናልክ?”
“ሰምተሃል። ”
***
(ከዳዊት ወርቁ አጫጭር የልቦለድ ስብስቦች
የተወሰደ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም