ትምህርት ቤቶች ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክቱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስተባበር በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሰሞኑን በድረገጹ ያሰራጨው መረጃ እንደሚጠቁመው ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚመሩ አካላት ከትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሀመድ አህመዲንም በመጪው መጋቢት ወር በመቀሌ ከተማ የሚካሄደውን 3ኛውን አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር በማስመልከት በትምህርት ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ የትምህርት ዘርፉ 30 ሚሊዮን ዜጎችን ያቀፈ በመሆኑ ለስፖርቱ ዘርፍ ዕምቅ አቅም ይሆናል፡፡ የስፖርቱን ዘርፍ በኃላፊነት የሚመሩ አካላት የተተኪ ስፖርተኞች ማፍሪያና የዘርፉ ትልቅ አቅም ከሆኑት የትምህርት ዘርፍ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ለዘርፉ እድገት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከመጋቢት 14 እስከ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በመቀሌ በሚካሄደው 3ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ውጤታማ እንዲሆንም የዘርፉ አካላት ተቀናጅተው በትኩረት መስራት እንደሚጠ በቅባቸው ያስገነዘቡት አቶ መሀመድ፤ የትምህርቱ ዘርፉ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት በየደረጃው ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት በዋነኛነት ከሚያከናውነው ሥራ ባሻገር፤ እንደየትኛውም የትምህርት መስክ ለስፖርት ዘርፉ ዕድገት የድርሻውን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው፤ ስፖርት ለሁሉም፣ ስፖርት ህዝባዊ መሠረት ይኑረው ከተባለ ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያለውን መዋቅር መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የስፖርት ኮሚሽንም ሆነ ሁሉም የስፖርት ተቋማት ከትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው ከሚገኙ የዘርፉ አካላት ተቀናጅቶ በመስራት በዘርፉ አገሪቱ የምትፈልገው ውጤት እንዲመዘገብ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የስፖርቱ ዘርፍ ባለድርሻዎች በመቀሌው በሚካሄደው 3ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ የ20 የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ከስፖርት ኮሚሽን የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬትና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ 5ኛው የአማራ ክልል የተማሪዎች ስፖርት ውድድር ትኩረት እንደሚሰጠው በድረ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ጠቁሟል፡፡ በዚህ መሰረትም በተያዘው አመት የየካቲት ወር የክልሉ የተማሪዎች ውድድር በደብረብርሀን ከተማ እንደሚካሄድ አመልክቷል፡፡
4ኛው የአማራ ክልል የተማሪዎች ስፖርት ውድድር በ2007 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ለብዙ አመት ተቋርጦ የቆየው የተማሪዎች ስፖርት ውድድር በዛው ዓመት በአማራ ክልል አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡
5ኛው የተማሪዎች ስፖርት ውድድር በ2009 ዓ.ም ለማካሄድ ቀጠሮ ቢያዝለትም ወድድሩን ለማካሄድ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ስላልነበር አልተካሄደም፡፡
ሰሞኑን በደብረታቦር ከተማ ውድድሩን አስመልክቶ በየደረጃው ካሉ የትምህርትና የስፖርት መዋቅር አካላት ጋር በተደረገ ውይይት፤ በአጠቃላይ ተማሪዎችን በስፖርት ውድድር በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በመደበኛ ክፍለ ጊዜ የሚሰጠውን የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በተግባር እንዲያስደግፉ ያግዛቸዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የሀገራቸውን ስም የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ለማስቻልና የተማሪዎቹን የዕርስ በዕርስ ግንኙነት በማጠናከር ክልላዊና ሀገራዊ ስሜትን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ያለመ ነውም ተብሏል፡፡
በውይይቱም በ4ኛው የተማሪዎች ስፖርት ውድድር የነበረውን አፈፃፀም በመገምገም 5ኛውን የተማሪዎች የስፖርት ውድድር እቅድ ትውውቅ ተደርጎ ውድድሩን በተገቢው መልኩ ለመምራት የሚያስችል ስምምነት ተደርሷል፡፡ የስፖርት ውድድር ደንብም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በክልሉ ትምህርት ቢሮና ስፖርት ኮሚሽን በጋራ የሚመራው የተማሪዎች ስፖርት ውድድር የተሳካ እንዲሆን በትኩረት እንሰራለን ያሉት የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዱኛ ይግዛው በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ውድድሩ በዞን ደረጃ እስከ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ. ም የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ በክልል ደረጃ በየካቲት ወር በደብረ ብርሀን ከተማ ይካሄዳል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ከመጋቢት ወር በመቀሌ ለሚካሄደው ውድድር ብቁ ስፖርተኞችን ለመመልመል ያግዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎ በታል፡፡