ብሪክስ እና ወጣቶች

የአባል ሀገራቱን የመጀመሪያውን ፊደል ይዞ የተመሠረተው ብሪክስ ምህጻረ ቃል ነው፡፡ ምህጻረ ቃሉ መጠሪያ ሆኖ ያገለገለው፤ ብራዚልን፣ ሩሲያን፣ ሕንድን፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን አካቶ ነው:: መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ይህን ስያሜ የሰጡት እ.ኤ.አ በ2001 የጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል እንደሆኑ ይነገራል::

በወቅቱ የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና ኢኮኖሚ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቱን ተከትሎ፤ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚለውጥ አቅም እንዳለው በመገንዘባቸው በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበት ነበር::

ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የባለብዙ መድረኩ ብሪክስ አባል ሀገራት የዓለምን ሕዝብ 45 በመቶ እና የዓለምን የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት 31 ከመቶ ይሸፍናሉ:: የብሪክስ ዋናው ግብ ቀጣይነት ያለው፣ ፍትሃዊ እና ለሁሉም የሚጠቅም እድገትን ለማስፈን በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ፣ ማጠናከር እና ማስፋት እንደሆነም ይነገራል::

የአባላቱ ድምር ምጣኔ ሀብት ከ28 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ አለው። ከዓለም ኢኮኖሚ 28 በመቶውን ማለት ነው። ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በአባልነት የሚያካትተው የብሪክስ አገራት ቡድን 44 በመቶ የሚሆነውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ያመረትበታል። ቡድኑ የምዕራባውያን አገሮች እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ያሉ እንዲሁም ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደሚቆጣጠሩ ይከራከራሉ።

ከዚህ አንጻር በመልማት ላይ ያሉ አገራት “የበለጠ ድምጽ እና ውክልና” እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እ.አ.አ በ2014 የብሪክስ አገራት መሠረተ ልማትን ለማሳደግ የሚያግዝ ገንዘብ የሚያቀርብ አዲስ ልማት ባንክ አቋቁመዋል። እ.አ.አ በ2022 መገባደጃ ላይ ለአዳዲስ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የባቡር መስመሮች እና የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች 32 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለአገራት አቅርቧል።

ሦስት ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ የሚኖረው በጥምረቱ ሀገራት ውስጥ ነው። በአንፃሩ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ተብለው የሚታወቁት ምዕራባውያን ሀገራት ከዓለም ጠቅላላ ምርት ድርሻቸው 30 ነጥብ አምሥት በመቶ ነው። ይህ የሚያሳየው የብሪክስ ሀገራትን ከፍተኛ አቅም ነው።

ኢትዮጵያም ይፋዊ ጥያቄ አቅርባ ይህን ጥምረት ባለፈው ዓመት መቀላቀሏ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት ያገኘው ከሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ 20 ከሚበልጡ ሀገራት ጋር ጠንካራ ፉክክር አድርጋ የተሻለች ሆነ በመገኘቷ ነው:: ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ተቋማት በአባልነት እና መስራችነት የረጅም ጊዜ ታሪክ እና ልምድ ያለት ሀገር መሆኗ በ‹‹ብሪክስ››ም ዘንድ ተፈላጊ አድርጎታል።

ብሪክስ የተቋቋመበት አንዱ ዓላማም ኢኮኖሚዊ ዕድገትን የተመለከተ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ መሆኗ እና ተከታታይ እድገት እያስመዘገበች ያለች መሆኗ የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት ከተሰባሰቡበት ዓላማ ጋር የተሰናሰለ መሆኑ ወደ ብሪክስ ላደረገችው ጉዞ አቅም እንደሆነት ይታመናል::

ይህ የብሪክስ ጥምረት በቅርቡ በሩሲያ ካዛን ከተማ የጥምረቱ የወጣቶች ምክር ቤት ስብሰባ አድርጓል። ኢትዮጵያም በስብሰባው ተሳትፎ አድርጋለች። በስብሰባው ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት እና ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተውጣጣ የልዑክ ቡድን ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤትን በመወከል የምክር ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ በስብሰባው ተሳተፊ ነበር። ወጣት ይሁነኝ ከጉባኤው መልስ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበረው ቆይታ ጉባኤው በብዙ መልኩ የተሳካ እንደነበርና የኢትዮጵያ ወጣቶችን ፍላጐትና አቅም ለማስረዳት ዕድል የተገኘበት ስለመሆኑ ተናግሯል።

በጉባኤው የጥምረቱ መሪዎች የደረሱባቸውን ስምምነቶችና መግለጫዎች መሠረት በማድረግ እነርሱ ላይ ውይይት በማድረግ ነው ጉባኤው ጅማሮውን ያደረገው የሚለው ይሁነኝ፤ በአባል ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አንድነታቸውን ለማጠናከር ምን አይነት ሥራዎች መሥራት ይጠበቅባቸዋል በሚሉ ጉዳዮች ሰፊ ውይይት በማድረግ የወጣቶች ጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ እንዳሳለፈ ይናገራል።

የእያንዳንዱ አባል ሀገር ተወካይ ወጣቶች ሀገራቸው በጥምረቱ አማካኝነት ማግኘት ስላለባቸው ጥቅም የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት ውይይት ስለማድረጋቸው የሚናገረው ይሁነኝ፤ ኢትዮጵያም በዚህ ሕብረት መቀላቀሏ እንዳለ ሆኖ ማግኘት ስለምትፈልገው ጥቅም በማንሳት የኢትዮጵያ ፍላጐት እንዲሰማ ጥረት እንደተደረገ ይናገራል።

በተጨማሪም የሀገራቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያድግ የሚያግዙ ውይይቶች ስለመካሄዳቸው የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ የጥምረቱ አንዱ ዓላማ በአባል ሀገራቱ ሕዝቦች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወጣቶች ስለሚኖራቸው ሚና በማንሳት የተደረጉ ውይይቶች ሀገራቱ ከኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፈ ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ናቸው ይላል።

የጥምረቱ ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ ጥምረቱ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን የወጣቶች ሚና ጉልህ ነው፡፡ ነገ የብሪክስ መሪዎች እና በጥምረቱ ውስጥ የሚቋቋሙ ተቋማትን የሚመሩት ወጣቶች ናቸው፤ ይህንን ኃላፊነት መውሰድ ከወጣቶች ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ጉባኤው የጥምረቱ አባል ሀገር ወጣቶች እራሳቸውን ብቁ እንዲያደርጉ መልዕክት የተላለፈበት እንደሆነ ይገልጻል።

የአባል ሀገራቱ ወጣቶች እየተጋፈጡ ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው የመፍትሔ ሀሳብ ለማምጣት ውይይት እንደተደረገ የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በተለይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ ይናገራል።

ወጣት ይሁነኝ፤ በትምህርትና ስልጠና፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጤናና ሰው ሰራሽ አስተውሎት መስክ ያሉብንን ውስንነቶች ለመሙላት በዘርፉ የላቀ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ከደረሱ እንደ ቻይና፣ ሩሲያና ሕንድ ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይቶች አድርገናል ይላል፡፡ እነዚህ ውይይቶች እየዳበሩ ሄደው የኢትዮጵያን ወጣቶች ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉ ይናገራል።

‹‹አሁን በይፋ የማልገልፃቸው ግን በጥምረቱ አባል ሀገራት ተግባራዊ የሚደረጉ ከ10 በላይ ፕሮጀክቶች አሉ›› የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ “እኛም ሀገርን ወክሎ በጉባኤው ተሳታፊ እንደሆነ ወጣት ከተሳትፎ ባሻገር እነዚህ በእቅድ ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ እንዲተገበሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርገናል፤ በተጨማሪ በዚህ ስብሰባ ምን ማሳካት አለብን የሚለውን እቅድ አውጥተን ነው ወደ ሩሲያ ካዛን የተጓዝነው፤ ከዚህ አኳያ ቆይታችንም የተሳካ ነበር ይላል።

ወደ እዚህ ጥምረት ለመቀላቀል እንደ መንግሥት የተወሰደው ውሳኔ የሚደነቅ ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወደፊት እንደርስበታለን ብለው ላቀዱት ብልፅግናና እድገት እንደ ብሪክስ ወዳሉ ሀገራት ጥምረት ተቀላቅሎ የንግድ አማራጮችን ማስፋት ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን ይናገራል።

ብሪክስ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በዓለም ላይ ትልቁ ጥምረት ይሆናል፡፡ ብዙ ሀገራት ወደ ጥምረቱ ለመቀላቀል ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ከ120ሚልዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ከፈለገች ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማጠናከርና ወዳጅ ማብዛት የውዴታ ግዴታዋ ነው ይላል።

እንደቻይናና ሩሲያ ያሉ ሀገራት በቴክኖሎጂ ልማት ከፍተኛ የሚባል የእድገት ደረጃ ላይ የደረሱ ሀገራት ስለመሆናቸው የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በዘርፉ እድገት ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ዛሬ የላቀ ብልፅግና ላይ የደረሱ ሀገራት ምን አይነት መንገድ ተከትለው በመጓዝ ውጤታማ መሆን ቻሉ የሚለው ተነስቶ ልምድ የሚቀሰምበት መድረክ በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ይላል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መሆኗ፣ በአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባሕር ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት። ይህ በዚህ ሕብረት ለመቀላቀሏ ምክንያት ነው የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ይህንን መልካም አጋጣሚ ደግሞ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ማዋል እንደሚያስፈልግ ይናገራል።

ወጣት ይሁነኝ እንደሚናገረው፤ ጥምረቱ የአንድ ወገን የበላይነትን በመገዳደር ሚናው ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ እያደገች ያለች ሀገር እንደመሆኗ ወደዚህ ጥምረት መግባቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርግላታል:: ከፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው፤ በተጨማሪም ሀገሪቱ ወደውጭ ለምትልካቸው ምርቶች ተጨማሪ የገበያ አማራጭ ያስፈልጋታል። በእነዚህ እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች የጥምረቱ አባል መሆን ጠቀሜታው እንደ ሀገር ከፍተኛ ነው።

ጥምረቱ የራሱ የመገበያያ ገንዘብ ይፋ በማድረግ ከዶላር ጥገኝነት ነፃ የሆነ የዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚናገረው ይሁነኝ፤ በተጨማሪም በጥምረቱ ውስጥ የተካተቱ ሀገራት እርስበርስ በሚኖራቸው የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በየራሳቸው ሀገር ገንዘብ መገበያየት እንዲችሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለሚገዳደራቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ትልቅ ተስፋ ነው ይላል።

እንደኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ከቻይናና ሩሲያ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይቶችን ስለማድረጋቸው የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በሀገሪቱ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሰፊ ገለፃ በማድረግ ሂደት የካዛን የብሪክስ ወጣቶች ምክር ቤት ጉባኤ ውጤታማ እንደነበር ይናገራል።

ለኢትዮጵያ ወጣቶች የተለያዩ የስልጠና ዕድሎች እንዲፈጠሩ ጥረት ተደርጓል የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ኢትዮጵያ በምትፈልገው መስክ የትምህርትና ስልጠና ዕድል እንዲያገኙ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ የክህሎት ክፍተትን በመሙላት ኢትዮጵያ ለመለወጥ በምታደርገው ጉዞ አጋዥ እንደሚሆን ተነግሯል።

ወጣት ይሁነኝ እንደሚናገረው፤ የዓለም ፖለቲካ እና አሰላለፉ እየተቀያየረ እየሄደ ነው:: በተፈጥሮውም ተቀያያሪ ነው:: በአንድ ቦታ የሚቆም አይደለም፤ ተለዋዋጭ ነው:: በዚህ ተለዋዋጭ የዓለም ፖለቲካ ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የምትችልበትን አማራጭ ሁሉ መጠቀም አለባት፤ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ ሕብረት በማድረግ የሚፈለጉ ብሔራዊ ጥቅሞች ማሳካት የሚቻል አይደለም ይላል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት እንደ ተቋም የኢትዮጵያ ወጣቶች በጥምረቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ዕድሎች መጠቀም እንዲችሉ ጥረት ያደርጋል የሚለው ይሁነኝ፤ ከዚህ አኳያ ወጣቶች በተለይ ቴክኖሎጂን መረዳት የሚችሉ ሆነው እራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You