አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምድር ፈውስ – የልማት መድሀኒት

በዓለማችን የኢንዱስትሪው አብዮት ከታወጀ ወዲህ የአየር ንብረት ባህርይ ተቀያይሯል:: በሂደት ቀድሞ የነበረው ይዞታ እየተለወጠ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል:: በየግዜው ጎርፍ፣ የሰደድ እሳት፣ ከመጠን ያለፈ ሙቀት፣ ድርቅ እና የመሳሰሉት አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰቱ የዓለማችን መገለጫ ሆኗል:: ይህ አይነቱ ክስተት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በአፍሪካና በሌሎች አህጉራት ላይ እያሳደረ ያለው ጫና፣ የፍጥረታት ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም እለት ከእለት እያሳየ፣ እያሰማን ነው::

በአሁኑ ሰዓት የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል:: የአየር ንብረት ለውጥ እንደዋዛ በቀላሉ የሚነገርለት ቃል አይደለም:: በየግዜው በሕይወታችን ያለ ስጋትና እየጎዳን የሚገኝ መሆኑን ጭምር የዓለም ሕዝብ ተረድቶታል:: ምናልባትም እያደረሰ ያለው ጉዳት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ዓለማችን በሙቀት፣ በጎርፍ፣ በበሽታ፣ በድርቅ ምክንያት ከጦርነቶች ሁሉ በላቀ ደረጃ ልትጠቃና ልትወድም እንደምትችል ሳይንቲስቶች ይተነብያሉ::

ሳይንቲስቶቹ ለዚህ ለዓለማችን የጉዳት ቁንጮ ለሆነው ችግር እንደሁነኛ መፍትሄ እየመከሩ ያሉት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከፍ ማድረግንና መገንባትን ነው:: አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራትን ይጠይቃል:: የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ፕሮግራም /ዩኤንኢፒ/ በየዓመቱ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች መሰረት ከውሀ፣ ከንፋስ፣ ከፀሀይ፣ከእንፋሎትና ከመሳሰሉት ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚገኝን ታዳሽ ኃይል መጠቀም፣ለአየር ንብረቱ ተስማሚና ሙቀት አማቂ ጋዞችን የሚቀንሱ አረንጓዴ ግንባታዎችን መገንባት፣ ወሳኝነት አለው:: ለአየር ንብረት ተስማሚነት ቀጣይነት ያላቸውና አስተማማኝ የሆኑ እንደ የኤሌክትሪክ መኪና፣ ብስክሌትና የመሳሰሉትን መጓጓዣዎችን መጠቀም የግድ ይላል:: እንዲህ መሆኑ የውሃ አጠቃቀምንና አጠባበቅን፣ የቆሻሻ አወጋገድን፣ የመሬት አጠቃቀምና አጠባበቅን በአግባቡ ለማስተዳደርና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያግዛል::

እነዚህን መሰረታዊ ግብዓቶች የሚያሟሉ ሀገራት በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ውስጥ መኖራቸው እንደሚረጋገጥም መረጃው ይመሰክራል:: እኤአ ከ2007 በኋላ ዓለማችን ላይ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ኢንቨስት ተደርጓል:: አሁን ደግሞ ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ በግልፅ ይታያል:: በተለይ በፀሀይ፣ በንፋስ፣ በእንፋሎትና በውሃ ኃይል ላይ እየተደረገ ያለው ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ልብ ይሏል::

በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት እየደረሰ ያለው ጉዳት በጉዳዩ ላይ አመኔታ ያልነበራቸው ሀገራት ጭምር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትኩረት እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው ጥናቶች ያመለክታሉ:: ለምሳሌ 63 ከመቶ የአውሮፓ ሕብረት ነዋሪዎች፣ 59 በመቶ የሚሆኑ እንግሊዛውያን፣50 ከመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን እና 60 ከመቶ የሚሆኑ ቻይናውያን በአረንጓዴ ኢኮኖሚው እናምናለን እያሉ ነው:: እነዚህ ሀገራት ለዓለም ሙቀት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ቢሆኑም ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚያምኑ አልነበሩም::

በዓለም ሙቀት መጨመር ሳቢያ አህጉረ አፍሪካ ደግሞ ባልበላችው ዳዋ እየተመታች ትገኛለች:: ብዙ ችግሮችም እየደረሱባት የምትገኝ አህጉር ናት:: አፍሪካ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የምትከተል ከሆነ ለወጣቶቿ የስራ እድልን ከመፍጠር ጀምሮ ብዙ ጥቅሞችን እንደምታገኝ ዕሙን ነው:: በአፍሪካ እስካሁን በተተገበረ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ብቻ ሶስት ሚሊዮን ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል:: እርግጥ ነው በአፍሪካ በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ወጣቶች ስራ ፈላጊዎች ናቸው:: እነዚህ ወጣቶች በስራ ለመሰማራት ብቁ ናቸው ተብሎ ይታሰባል:: እኤአ እስከ 2030 አፍሪካ ውስጥ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ መሰረት ሊሆን እንደሚችል ይተነበያል::

በኦክስፎርድ ጥናት መሰረት ዓለማችን የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ብቻ 3 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች:: ይህ ቁጥር እኤአ በ2050 ደግሞ ወደ 10 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ይጠበቃል:: በአመዛኙ ይህ ዘርፍ የትኩረት አቅጣጫ ከሚያደርጋቸው ነጥቦች መካከል ምቹ የስራ ሁኔታን ለዜጎች ከመፍጠር አልፎ ስራ አጥነትን እስከ መቀነስ ብሎም የተረጋጋ ሀገራዊ ምርትን እስከማስቀጠል ይደርሳል ተብሎ ይገመታል::

በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ከ73 ሚሊዮን በላይ ስራ የሌላቸው ወይም ስራ እየፈለጉ ያሉ ወጣቶች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህንን የዓለማችን ችግር ለመፍታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: በተግባራዊነቱም በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ ከመገኘቱ ባሻገር ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው:: ሀገራት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትኩረት የሚሰጡ ከሆነ ለወጣቶቻቸው ትልቅ የስራ እድል ይፈጥራሉ፤ኢኮኖሚያቸውንም ያነቃቃሉ::

ሀገራችን ኢትዮጵያም ከዓመታት በፊት በጀመረችው አረንጓዴ አሻራን የማኖር ተግባር አረንጓዴ ኢኮኖሚን የመገንባት አቅም ታላቅና ሰፊ እንደሚሆን ታምኖበታል:: የዘርፉ ምሁራንም በምግብ ራስን ከመቻል እስከ ግዙፍ ኢኮኖሚ ግንባታ ድረስ ሚና ያለውን ተግባር እንደሀገር አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን ያሳስባሉ::

ባለፉት ስድስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንደባህል ፀንቶ እየተካሄደ ይገኛል:: የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣የድርቅ፣የጎርፍና የረሀብ አዙሪትን ጥሶ ለመውጣት የታቀደ መርሀ ግብር ነው:: በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ2011 እስከ 2014 ወደ 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል:: በሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያው ዓመት በ2015 ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል:: በድምሩ በሀገራችን በነዚህ ዓመታት ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል:: ባለፈው ዓመት በ2016 ዓ.ም ደግሞ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከእቅዱ በላይ ተፈፅሟል::

የባለፉት ዓመታት ክንውኖች ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፋይዳዎችን በወጉ መረዳቷን ያመላክታሉ:: ሂደቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መርሀ ግብር መሆኑና ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ምርቶችን እንደሚሰጥ ታምኖበትም እየተሰራበት ይገኛል:: እስካሁን ከተተከሉት ችግኞች መካከል 60 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው እነ ማንጎ፣ፓፓያ፣አቡካዶና የመሳሰሉት ፍራፍሬዎች ናቸው:: የእንስሳትን የወተት ምርት ለማሳደግ፣ ለመኖና ለንብ ማንቢያ ምቹ የሆኑ የዕፀዋት ዝርያዎች ተተክለዋል:: ከዚህ አኳያ ተጨማሪ ምርቶችን በማስገኘት ስርዓተ ምግብንም በማሻሻል የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም::

በኢትዮጵያ በተተገበሩ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች እንደ ሀገር የተቀመጡ የልማት ግቦች እንዲሳኩ መሰረት ተጥሏል:: የአረንጓዴ ልማት ተግባራት ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው:: እይታችን የሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ሲሆን ደግሞ ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚለው አካሄድ ሁለንተናዊ የሆነውን ሀገራዊ አቅም ማሳደግ ላይ የሚኖረው ጥቅም ከፍ ይላል::

የአረንጓዴ አሻራ ጉዞ የተመጣጠነ ዝናብን ከመስጠት ጀምሮ ለምነትን ለመመለስ ጥቅሙ ግዙፍ የሚባል ነው:: በኢኮኖሚው ላይም ትልቅ አወንታዊ አስተዋፅኦ ያሳርፋል:: የተስተካከለ ዝናብ ሲኖር አፈር እንዳይሸረሸር ይከላከላል፣ የሰው ንብረት እንዳይወድም ስለሚያደርግ ምርታማነት ይጨምራል:: ምርታማነት በጨመረ ቁጥር የሀገር ኢኮኖሚ እያደገ ይሄዳል:: ለውጡ ወዲያው የሚታይ ላይሆን ቢችልም ቆይቶ ተጨባጭ የሚባሉ ለውጦች መመዝገባቸው አይቀሬ ይሆናል::

በ2016 ዓ.ም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በአንድ ቀን ብቻ 615 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል:: ይህ እውነት ስንተባበር ምን ማድረግ እንደምንችል አንዱ ማሳያ ነው:: እነዚህን ችግኞች መትከላችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሆነ ለመላው ዓለም ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው:: እኛ ዘመናችን ላይ ቆመን አያት ቅድመ አያቶቻችን እንደምናመሰግነው ሁሉ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችንም ነገ ከነገወዲያ ያመሰግኑናል:: በእኛ ግዜ ካወደምነው የደን ሽፋን 3 በመቶ ያህሉን ሸፍነናል:: እንዲህ ይባል እንጂ ቀደምቶቻችን ደግሞ ተገቢውን ግዴታ ከውነው አልፈዋል::

በቀደመው ጊዜ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ ይደርስ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ:: በ 1980ዎቹ በተደረገ ጥናት የደን ሽፋኑ አዘቅዝቆ 3 በመቶ መድረሱን አመላክቷል:: ይህንን አስጊ ሁኔታ ለመቀየር ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የደን ሽፋኑ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ ተችሏል:: የኢትዮጵያ ዓላማ የደን ሽፋኑን ቢያንስ 40 በመቶ ማድረስ ነው::

እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው ሀገር የደን ሽፋኑ 3 በመቶ ብቻ መሆኑ እጅግ አስጊ ነው:: በሀገራችን ምዕራብ በኩል የሰሀራ በረሀ ስጋት ‹‹መጣሁ መጣሁ›› እያለ ከሱዳን ጥግ ደርሷል:: በምስራቅ በኩልም የሱማሊያ መልከአ ምድር አሸዋማ፣ በረሀማ ቦታ ነው:: በስተሰሜንም የአረብ በረሀን እናገኛለን:: በበረሀዎች የተከበበች ሀገር 3 በመቶ ብቻ የደን ሽፋን ካላት ምንያህል እንደምትጎዳ ግልፅ በመሆኑ ስጋቱን ተጨባጭ ያደርገዋል::

አሁን ላይ ግን ይህን ታሪክ እየለወጥነው እንገኛለን:: ነገ ከነገወዲያ ደግሞ በደን ልማታችን የምንታወቅና ከደን ሀብታችንም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የምናፍስ ይሆናል::

በተደጋጋሚ እንደሚሰማው ብራዚል ከደን ልማቷ ‹‹ሬድ ብላስ›› ከሚባለው ፕሮጀክት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ ቆይታለች:: ትልልቅ የሚባሉ የአውሮፓ ሀያላን ሀገራትም ለብራዚል ደኖች የሚከፍሉት ክፍያ አለ:: ይህ ማለት ብራዚል ለአየር ንብረቷ መስተካከል ከደኗ ከምታገኘው ጥቅም ባሻገር ደን ስላላት ብቻ የምታገኘው ጥቅም አላት ማለት ነው::

ኢትዮጵያም እየሄደችበት ባለው መንገድ የምትቀጥል ከሆነ እንደብራዚል ከሌሎች ሀገራት ክፍያ ማግኘቷ የማይቀር ነው:: የሜትሪዮሎጂ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ኮንጎ ያለው ደን ወይም ዛፍ ኢትዮጵያ ላይ ለሚጥለው ዝናብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው::ልክ እንደ ኮንጎ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የሚገኝ ደን የሰሜን አፍሪካ፣የምዕራብና የምስራቅ አፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የአውሮፓ ሀገራት ድረስ ይተርፋል:: ሀገራችን ይህን አስተዋፅኦው በማበርከት የምታገኘው ገቢ ከመኖሩ በላይ ተግባሩ ኢትዮጵያን ሊያስመሰግን የሚገባ ነው::

ይህ የደን ልማት ተግባር ዓለማችንን አንድ ትሪሊዮን ዛፎችን እንስጣት /እናልብሳት ‹‹ዋን ትሪሊዮን ትሪ ኢንሼቲቭ›› የሚባል ተነሳሽነትን ፈጥሯል:: የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በዓለማችን እስከ 3 ትሪሊዮን የሚደርሱ ዛፎች አሉ:: በእርግጥ እነዚህ ዛፎች በአብዛኛው ሰፋፊና ትልልቅ በሚባሉና ወደ ሰሜን ዋልታ የሚጠጉ ሀገራት ውስጥ ይገኛሉ:: ዛፎቹ እንደሩሲያ፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ አሜሪካና የመሳሰሉት ሀገራት የሚገኙ ናቸው::

በደቡብ ዋልታ ግዙፍ ደን ያላቸው ሀገራት እምብዛም አይገኙም:: ከምድር ወገብ ወደ ላይ ስንወጣ የአማዞንና የኮንጎ ጥቅጥቅ ደኖች ሊገኙ ይችላሉ:: ነገር ግን ወደታች እየወረድን ስንሄድ የምናገኘው ደን አይኖርም:: ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ እየከወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ደን እንዲኖር የምታደርገው አንዱ ጥረት ነው ማለት ይቻላል::

በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች የአርሶ አደሩን ማሳ ምርታማነት በማሳደግም ጉልህ ድርሻ አላቸው:: የአፈሩ መከላትና በጎርፍ መሸርሸር የግብርናው ዘርፍ ትልቁ ችግር ሆኖ ቆይቷል:: ከዝናብ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ምንም ልባስ የሌለው ማሳ ላይ ዝናብ ሲጥል አፈሩ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚሸረሸር ይህንን ለመከላከል የተተከሉ ችግኞችም አሉ:: እነዚህ ችግኞች የአፈር ለምነት የማስጠበቅ፣ የማሳደግ፣ አፈሩ በጎርፍ እንዳይሸረሸር በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ያሳድጋሉ::

ለምሳሌ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሲጀመር የበቆሎ ምርት በሔክታር 25 ኩንታል ይመረት ነበር:: አሁን ላይ በሔክታር 42 ኩንታል ደርሷል:: በእርግጥ ይሄንን አረንጓዴ አሻራ ብቻ ያመጣው አይደለም:: ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የተሻለ አስተራረስ መጠቀም ጭምር አስተዋፅኦ አበርክቷል:: ይሁን እንጂ የአፈር ለምነት መጨመሩ የአየር ሚዛኑን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ ተችሏል:: በስንዴ ምርትም ከ19 እና 20 ኩንታል አሁን ላይ በሔክታር ወደ 36 ኩንታል ሊያድግ ችሏል::

በስራ እድል ፈጠራውም አስተዋፅኦው የጎላ ነው:: የግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ሶስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ያስገኘውን የስራ እድልና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ባደረገው ጥናት ወጣቶች ተደራጅተው ችግኞችን በማፍላት፣ በመንከባከብ ስራ ላይ በመሰማራታቸው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል:: 800 ሺህ የሚጠጋ የስራ እድል ተፈጥሯል:: ይህ የሚያሳየው በመርሀ ግብሩ መተግበር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ማለቱን ነው::

የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ የደን ሽፋንን በመጨመር፣ የተፈጥሮ ብዝሀ ሕይወት ሚዛንን ለማስጠበቅ በሚደረግ ጥረት የደን ሽፋንን መጨመር ዋንኛው የመርሀ ግብሩ ተልዕኮ ነው:: የአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣው አማቂ ጋዞችን በአካላቸው የሚይዙ እፀዋት ባለመኖራቸው፣ የተራቆቱ ተራሮችና አካባቢዎች በመፈጠራቸውና የሚዘንብ ዝናብ በምድር ላይ ጎርፍ ሆኖ በመሄዱ ምክንያት ነው::

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያን ደን ሽፋን ከዓመታት በኋላ ከፍ እንዲል አስችሏል:: ከዚህም ባሻገር በርካታ ለምግብነት የሚውሉ ዛፎች በመተከላቸው ምክንያት ዜጎች ለምግብነት አገልግሎት የሚውሉ እፅዋቶችን በቀላሉ እንዲያገኙና ሸጠውም የገቢ ምንጭ እንዲሆናቸው አስችሏል::

እናም በሚደረገው የአረጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሀገራችን የወጠነችው የልማት ግብ ማሳኪያ መንገድ መሆኑን ተረድተን ለስኬቱ ይበልጥ በጋራ መቆም ይጠበቅብናል:: ሀገርን በማልማት ፈጣን ጉዞ ለየቅል ዕሳቤ መኖር የለበትም:: በ2030 እንደርስበታለን ተብሎ የተቀመጠው የ30 በመቶ ሀገራዊ የደን ሽፋን በአግባቡ ይሳካ ዘንድ ዜጎች በልማቱ ላይ በሚደረገው ያላሰለሰ ርብርብ ከፍተኛ ተሳትፎና ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል:: ይህ እውነታ በተግባር በተመሰከረ ቁጥር የምንፈልገውን ሀገራዊ እድገት ማስመዝገብ ይቻለናልና::

ታሪኩ ዘለቀ

 አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You