በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በአሠልጣኝነት ገናና ስም ካላቸው ጥቂቶች አንዱ አስራት ኃይሌ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ። የእግር ኳስ ቤተሰቡ “ጎራዴው” በሚል ቅፅል ስም የሚያውቀው አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ ከበርካታ ታላላቅ የኢትዮጵያ ክለቦች እስከ ብሔራዊ ቡድን በዘለቀ የአሠልጣኝነት ሕይወቱ “አንቱ” ያስባለውን ሙያዊ አበርክቶ በውጤታማነቱ አስመስክሯል።
ይህ የእግር ኳስ ባለውለታ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ባበረከቱት ልክ ባይዘመርለትም። ያለውን ትልቅ አቅም በተለይም በእድሜው የመጨረሻ ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ አንጠፍጥፎ አለመጠቀሙ የብዙዎች ቁጭት ቢሆንም ሥራው ከመቃብር በላይ ህያው ሆኖ በትውልዶች ሲታወስ ይኖራል።
አስራት ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት የዘለቀው የረጅም ዓመት የእግር ኳስ ሕይወት በሰፈር ውስጥ መስከረም ኮከብ የተባለ ቡድን እንደተጀመረ በሕይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። በ1953 ዓ.ም በዳርማር ህጻናት ከተጫወተ በኋላ ችሎታውንና ለስፖርት ያላቸውን ፍቅር በማየት በወቅቱ የድሬዳዋ ጥጥ ማህበር ወይንም ኮተን አሠልጣኝ የነበረው ታሪካዊው ሉቻኖ ቫሳሎ በ1963 ክለቡን እንዲቀላቀል አድርጎታል። በኮተን ቆይታው ባሳየው ብቃትም ለሐረርጌ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ አስችሎታል። በኮተን ቆይታው ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ክለቦች ቻምፒዮና ፤ የሀረርጌ ክፍለ ሀገር ምርጥ ቡድን ጋር አንድ ዋንጫ አንስቷል።
1968 ዓ.ም አስራት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣበት ነበር። ለ 3 ዓመት በተጫዋችነት እንዲሁም በአምበልነት ቆይታ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም ለዋናው ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ ለ 9 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን፣ በ 1968 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ 4ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አስተዋፅኦ ነበረው።
ከዚህ በኋላ ፊቱን ወደ አሠልጣኝነት ያዞረው ጎራዴው በመጀመሪያ ለትግል ፍሬ ቡድን በአሠልጣኝ ተጫዋችነት በ 1972 ዓ.ም የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን ቻምፒዮን እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በመቀጠል ለህንፃ ኮንስትራክሽን 50 ክለቦች በአዲስ ሲዋቀሩ ጥሩ 10 ክለቦች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ሲያልፉ ክለቡን አራተኛ ደረጃ እንዲይዝ በማድረግ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ማሳደግ ችሏል።
የአሠልጣኝነት ችሎታውን በማጎልበት በተጫዋችነት ያገለገለውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ 1983-1992 ዓ.ም ያሠለጠኑ ሲሆን በቆይታውም የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በ1975 ዓ.ም ቡድኑ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ከማሳደግ ጀምሮ በ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ፤ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፤ የፀባይ ዋንጫ ጠራርጎ በማሸነፍ ኮከብ አሠልጣኝ ሲሆን ከክለቡም ኮከብ ተጫዋች አስመርጧል።
የቀድሞው የመስከረም ኮከብ፣ ዳርማር፣ ድሬዳዋ ጥጥ ማህበር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ትግል ፍሬና ለሌሎች ክለቦች ድንቅ የተከላካይ ቦታ ተጫዋች ወደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት የመጣው የተስፋ ቡድን አሠጣልጣኝ በመሆን ነበር። ቀጥሎም የዋናው ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ በመሆን በኢትዮጵያ በተደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ ዋንጫ በማንሳት ብቸኛ የሆነበትን ታሪክ አኑሯል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨማሪ በክለብ አሠልጣኝነት ሕይወቱም በመከላከያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ፤ በመብራት ሃይል ሲቲ ካፕ ዋንጫ ያሳካ ሲሆን የኢትዮጵያ መድህን ከአንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳድጓል።
በመጨረሻም በደደቢት ስፖርት ክለብ ከአማካሪነት እስከ አሠልጣኝነት በነበረው ቆይታ በፕሪሚየርሊጉ ዋናው በሁለተኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ አድርጓል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሠልጣኞች ማህበር መሥራችና አባል በመሆን፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሠልጣኞች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግሏል፡፡ በአጠቃላይ በአሠልጣኝነት ሕይወት ዘመኑ ከ 30 በላይ ዋንጫዎችን ማሳካትም ችሏል፡፡ ልምድና ሙያውን ያለ ስስት አጋርቷል፤ በርካታ ተተኪዎችን ፈጥሯል፤ በመገናኛ ብዙሃን በጨዋታ ትንታኔ ሙያዊ እውቀቱን አካፍሏል።
ሃይለኛ፣ ደፋር፣ ቀጥተኛ፣ አልሸነፍ ባይ፣ እጅ የማይሰጥ፣ የሰላ፣ ስኬታማ በመሆኑ “ጎራዴው” የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ ለረጅም ጊዜ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት ልክ የዛሬ ሳምንት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም