በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አራተኛ ዘመን የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ማመላከታቸው ይታወሳል። ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስብሰባው ደግሞ የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ተመስርተው ላነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ምላሾችንና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሾችና ማብራሪያዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
በመጀመሪያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ቆይቶ ከነበረው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት አንፃር ሪፎርም እያካሄድን መቆየታችን ይታወቃል። ሪፎርሙ ያልነካው ሴክተር የለም። እነዛ ሪፎርሞች ያስገኟቸው ውጤቶች፣ የተገኘባቸው ትምህርቶች፤ ቀሪ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ለዚህ ለተከበረው ምክር ቤት መግለጽ የምፈልገው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሀገራዊ ማንሰራራት የምንጀምርበት ዓመት ነው።
ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን ሀገራዊ ማንሰራራት የምንጀምርበትና በታሪካችን አይተን የማናውቃቸውን ውጤቶች እያየን ለትውልድ የማፅናት ሥራ የምናሸጋገርበት ዘመን መጀመሪያ ነው። በሪፎርም ዓመታት የማፍታታት፤ ሕግ አስከባሪ ተቋማት፣ የፖለቲካ ሥርዓታችን፣ የኢኮኖሚ ሥርዓታችን፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ትክክለኛ የፌዴራል ሥርዓት ሆኖ ክልሎች በራሳቸው የመፈጸም አቅም ኖሯቸው ሥራቸውን እንዲሰሩ የማድረግ፤ ሴክተራል ሪፎሪም የማካሄድ የማፍታታት ሥራ ስንሰራ ቆይተናል።
በመጨረሻ ይዞን የቆየው የኢኮኖሚ ሪፎርም በሚመለከትም በቅርቡ በተሟላ ሁኔታ መጀመራችን ይታወቃል። ከዚህ ዓመት ጀምሮ የማንሰራራት ዓመት ይሆንልናል። በዚህ የማንሰራራት ዓመት ውስጥ በርካታ ውጤቶች ይጠበቃሉ። ከዚያ የሚቀጥለው ደረጃ የማፅናት ይሆናል። ያንን ትውልድ የሚያስቀጥለው ይሆናል።
የማንሰራራት ዓመት ይሆንልናል ስንል እንዲሁ ዝም ብሎ ሃሳብና ምኞት ሳይሆን ባለፉት ዓመታት በታየው መልክ መንግሥታችን የማይነጥፍ ሃሳብ ይዞ ይነሳል፤ ሃሳቦቹም ሃሳባዊያን እንደሚያደርጉት ውይይት ሆኖ እንዳይቀር በተግባር ሃሳቡን የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ለማድረግ ይተጋል። አንዳንዴ ከትጋት በኋላ የሚጠበቅ ውጤት በበቂ ደረጃ ካልመጣም ሊያዘነጋ ሊያዳክመን ይችላል። በእኛ ሁኔታ ግን አስደናቂ ውጤቶች እናገኛለን።
ሃሳብ አለን፣ ተግባር አለን፣ ውጤት እያገኘን እንገኛለን። እነዚህን በማፍጠን፣ በማስተሳሰር ሪፎርሙ በሁሉም ቅርፅ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዓመት በ2017 የምንጀምረው ይሆናል። ይህንን አብረን በጋራ የምናየው ይሆናል። ከዚህ ቀደም ትፈርሳለችሁ ሲሉን አንፈርስም እንዳልነው አንሰራርተን ደግሞ በጋራ የምናይ ይሆናል። ይህ በጣም ቁልፍ መልዕክት ነው። በትናንትናው እሳቤ፣ በትናንትናው ለቅሶ፣ በትናንትናው ሃሳብ ውስጥ ያላችሁ ሰዎች እሱን ጨርሰን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ተሸጋግረናል።
ምዕራፉን ገብቷችሁ ካልተከተላችሁ እናንተ አሁንም ትናንትና ውስጥ እንዳትሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የማንሰራራት ዓመት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በኮሪደር፣ በግብርና በሁሉም በሚቆጠር መንገድ በፍሬ የሚታይ ይሆናል። ባለፈው ዓመት ዓመታዊ የGDP እድገት ከአቀድነው በላይ 8.1 በመቶ አሳክተናል። ይሄ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት ታርታ ኢትዮጵያን የሚያስገባት ነው፤ በብዙ ሀገራትም እውቅና አስገኝቶለታል። ከብዙ ሀገራት ጋር በምናደርገው ግንኙነት የተገኘው እድገት ለማመን የሚቸገሩና ‹‹ምን አግኝታችኋል ነዳጅ አገኛችሁ ወይ?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በጣም በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ።
ለማየት የፈለገ ሰው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢንቀሳቀስ የሚጨበጥ፣ የሚታይ፣ ለውጥና እድገት አለ። በዚህ በያዝነው ዓመት 8.4 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ጠበቅ ያለ እቅድ ተይዟል። ባለፉት ሶስት ወራት ያየናቸው ምልክቶች እንደሚያመለክቱት ከዚያ በላይ እድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ያመለክታል። አምና ከነበረው እድገት 8.4 በጣም ትልቁ ነው። በአፍሪካም ከፍተኛው እድገት ነው። ነገር ግን ከዚያ በላይ እድገት ሊመዘገብ እንደምችል ያለፉት ሶስት ወራት እንቅስቃሴዎች ያሳያሉ። 8.4 በመቶ የGDP እድገት እናረጋግጣለን ስንል ጥቅል እሳቤ ሳይሆን በሴክተር ከፍለን እያንዳንዱ ሴክተር ምን አይነት እድገት ሊያመጣ እንደምችልም ታቅዶ፣ አስፈላጊው ግብዓት ተዘጋጅቶ ሥራ ተጀምሮ ነው።
ለምሳሌ ግብርናን ብንወስድ፤ ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ መነቃቃት እንደመጣ ይታወቃል፤ በዚህ ዓመት 6.1 በመቶ እድገት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። የግብርና ሴክተር 6.1 በመቶ እድገት ያመጣል ስንል አምና በነበረው መሠረት ቢሆን ይሄ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል። መሠረታችን እየሰፋ ሲሄድ ከዚያ ውስጥ የምናመጣው እድገት በቁጥር እያነሳ ስለሚሄድ የግብርና መሰረት ከመስፋቱ የተነሳ 6.1 በመቶ እድገት ያስገኛል ተብሎ ቢጠበቅም በንዑሳን ክፍሎች ስንመለከት እጅግ ከፍተኛ ውጤት የመጣባቸው ሴክተሮች አሉ።
ለምሳሌ ሰብል፣ ጥጥ፣ ሆርቲካልቸር ተደምሮ ክረምት ከበጋ ሰላሳ ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 1.4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት እንሰበስባለን፤ ይሄ ትልቅ ዜናና ይሄን ምክር ቤት ልያኮራ የሚገባ ተግባር ነው። ሰላሳ ሚሊዮን ሄክታር ክረምት ከበጋ እናርሳለን ሲባል ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት ከ15 ሚሊየን ሄክታር በታች ነበር የምናርሰው። ያረስነው መሬት ደብል አድርጓል፤ በመሬት ስፋት ብቻ ሳይሆን በጋን በስፋት የመጠቀም በመስኖ የመጠቀም በኩታ ገጠም የመጠቀም ልምምዳችን በማደጉ በሰብል ምርት 6.6 በመቶ እድገት ይጠበቃል። በግብርና አጠቃላይ 6.1 ብዬአለሁ በሰብል ደግሞ 6.6 ገደማ እድገት ይጠበቃል።
ሁለተኛው ሌማት ነው። በንፅፅር ዘግየት ብለን የጀመርነውና በግብርናው ዘርፍ ትልቅ እምርታ የሚጠበቅበት ሴክተር አንዱ ሌማት ነው። ሌማት (በአርቴፊሻል አንስምሌሽን) በጣም በርካታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች የማዳቀል ሥራ ተሰርቷል። ዶሮ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ስንጀምር በዓመት ኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን ጫጩት ተዘጋጅቶ ነበር፤ በዚህ ዓመት 150 ሚሊዮን ጫጩት ተዘጋጀለች፤ ይሄን ብቻ በማየት የሌማት ትሩፋት ምን አይነት እምርታ እያመጣ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።
በዚህ ዓመት 12 ቢሊዮን ሊትር ወተት እንደምናገኝ ታቅዷል፤ 218 ሺህ ቶን የዶሮ ሥጋ እንደምናገኝ ታቅዷል፣ 8 ቢሊዮን እንቁላል እንደምናገኝ ታቅዷል፣ 297ሺህ ቶን ማር እንደሚገኝ እንዲሁ በእቅድ ተይዞ ባለፉት ሶስት ወራት በርካታ ውጤት ተገኝቶበታል፤ ዓሳ 2.28ሺህ ቶን የዓሳ ምርት ይገኛል። ሌማት በድምሩ 5.4 በመቶ እድገት ይጠበቃል።
በግብርና ውስጥ በንፅፅር የሌማት እድገት ከሰብል ያነሰ ነው፤ ምክንያቱም የሌማት ትሩፋት ከጀመርን ጥቂት ጊዜያችን ስለሆነ፤ የአረንጓዴ ዐሻራን በምንወስድበት ጊዜ የደን ልማት ጥምር ደን፣ አትክልትና ፍራፍሬ በሁሉም መስክ በጣም ከፍተኛ የሆነ እምርታ መጥቷል። ጥቂቶችን ለምሳሌ ስናነሳ፦ ቡና ባለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት እድገት አግኝተናል፤ በካቻምናና በአምና መካከል የቡና ምርት እድገት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ዘንድሮ ከብራዚልና ከቬትናም በስተቀር በቡና ምርታማነት ኢትዮጵያን በዓለም የሚበልጣት ሀገር አይኖርም። በርካታ ሀገራት አልፈን መጥተን አሁን የቀረን ብራዚልና ቬትናም ናቸው። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የጀመርነውን ጉንደለና ችግኝ ተከላ አጠናክረን ከቀጠልን ከብራዚል በስተቀር በቡና ምርት ኢትዮጵያን የሚበልጣት ሀገር እንዳይኖር ታቅዶ እየተሰራ ነው። ከቬትናም ጋር ያለንን ልዩነት እናውቀዋለን በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በምንሰራቸው ሥራዎች ከዚያ ያላነሰ ምርት ልናመርት እንደምንችል ይጠበቃል ዘንድሮ ግን ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ሀገር ናት። ባለፈው ዓመት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ከቡና ኤክስፐርት አግኝተናል። በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊየን ዶላር ገደማ ይጠበቃል።
የቡና ምርት እያደገ ስለመጣ በሀገር ውስጥ ያለው ተጠቃሚነት ያደገ ቢሆንም ለውጭ ገበያ የምናቀርበውም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። ዘንድሮ ከአራት መቶ ሀምሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ቶን ድረስ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። አራት መቶ ሀምሳ ሺ ቶን ማለት የዛሬ አምስት ዓመት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ቶን አይሞላም ነበር። ይህ እድገት በቡና ብቻ ሳይሆን በሻይም ምልክት መታየት ተጀምሯል። ሻይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በስፋት ተተክሏል በጣም አስደናቂም ውጤት እያገኘንበት ነው።
ሻይ ግን በባህሪው እንደ ቡና ለቅመን የምንሸጠው አይደለም። ሻይ ቅጠል ከተሰበሰበ በኋላ ፕሮሰስ መደረግ ይፈልጋል። አሁን ከተክለነው የሻይ ምርት ሶስት እጥፍ የማብዛት የመሬት እና የችግኝ ዝግጅት ያደረግን ቢሆንም አሁን የተከለነውን ራሱ በጣም በርካታ ፋብሪካዎች ካልተከልንና ፕሮሰስ ማድረግ ካልጀመርን በስተቀር አርሶ አደሩ እኛን አምኖ የተከለው ሻይ ገበያ ሊያጣ ይችላል። በመሆኑም ከግል ባለሀብቶች ጋር በመነጋገር እና አንዳንድ ሀገራት ጋር በጉብኝት በማድረግና ልምድ የመቅሰም ሥራ ተሰርቶ በቅርቡ ከግል ሴክተር ጋር ቢያንስ ሀያ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ለመትከል ተስማምተናል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተከልን ስለሆነ ሀያውም በቂ ስለማይሆን አሁንም በጣም በርካታ ፋብሪካዎች ይፈልጋል። በስፋት ፋብሪካዎቹን አብዝተን የችግኝ ተከላውን ከቀጠልን የሀይላንድ ሻይ በጣም ተፈላጊ ስለሆነ በሻይ መስክም ስመ ጥር አምራች ሀገራት ተርታ ለመግባት ያለን እድል በጣም ሰፊ ነው።
ስንዴን በሚመለከት የተከበረው ምክር ቤት በደንብ እንደሚያውቀው በቅርቡም ወደ ምርጫ ክልላችሁ ስትሄዱ እንዳያችሁት በዚህ ዓመት ክረምትና በጋ ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ይሸፈናል። በከፍተኛው ደረጃ በሄክታር አርባ ኩንታል ቢመረት ቁጥሩ ከፍ ይላል። ነገር ግን አሁንም ኮንሰርቫቲቭ መሆን አስፈላጊ ስለሆነ ቀንሰን ከአርባ በታች እንደሚገኝ አስበን ብንሄድ ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር በትንሹ ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በዚህ ዓመት ይመረታል። ሰላሳ ሺ ቶን ስንዴ ይመረታል ማለት ነው። ሰላሳ ሺ ቶን ስንዴ ማምረት ማለት በአፍሪካ ሁለተኛው አምራች ከሰሶት እጥፍ በላይ ማምረት ማለት ነው። ሁለተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ዘጠኝ ሺህ ቶን ገደማ ነው የሚያመርተው። ይህም ማለት ቢያንስ የዚህን ሶስት እጥፍ ምርት እንሰበስባለን ማለት ነው።
ስንዴ እንዴት እየተቀለደበት እንደተጀመረ ሁላችሁም ታውቃላችሁ አሁን ሁሉም የሚቀበለው እየሆነ መጥቷል። ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በዚህ ዓመት ማሳካት ከቻልን ለዛ በቂ ገበያና የእሴት መጨመር ሥራ ከሰራን ለማሳደግ ያለን አቅም በዛው ልክ እየሰፋ ይሄዳል። በዚህ ሳይወሰን ሰሊጥ ለውዝ አኩሪ አተር ቦሎቄ ቀድሞ ከነበረን በእጅጉ አድጓል። ሰሊጥ ድሮ ከምናመርተው ከእጥፍ በላይ እየተመረተ ነው። በሁመራ አካባቢ የሚታወቀው ሰሊጥ በወለጋ አካባቢ በስፋት ማምረት ተችሏል። በሎቄም በተለይ ለውዝ በሀረርጌ አካባቢ በጣም በስፋት የተመረተ ሲሆን ለውዝ ብቻ ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ ማምረት ተችሏል። እነዚህ በግብርና ዘርፍ የመጡ ውጤቶች ያገኘናቸውን ድሎች ጠብቀን ስንሰራ እና የገጠሙንን ድካሞች አርመን፤ አርቀን እያስፋፋን መሄድ ብንችል አሁንም ሰፊ መሬት በጣም ሰፊ ውሃና የሰው አቅም ስላለን የማደግ እድሉ በጣም ሰፊ ነው።
በዚህ ረገድ በተለየ መልኩ ሥራ የሚፈልገው ማዳበሪያን በተመለከተ ነው። እስካሁን በጅምላ አንድ አይነት ማዳበሪያ እንገዛና ለሁሉም መሬት የምንጠቀመው የተቀራረበ ማዳበሪያ ነበር። በዚህ ዓመት እንደ መሬቱ ጸባይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ሥራውን ስንጀመር የምርጥ ዘር አቅማችን በጣም ውስን ነበር። ምርጥ ዘር አልነበረንም በስንዴ እና በበቆሎ መቶ በመቶ ባልላችሁም በምርጥ ዘር ከፍተኛ እድገት እየመጣ ነው። ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም።
መስኖና በበጋ የማምረት አቅማችንም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ማሸነሪና ፓምፕ መጠቀመም ጨምሯል። ማሽነሪም ፤ ምርጥ ዘርም፤ ማዳበሪያም ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋሉ። እነዚህን በመሥራት ሁለት ቁልፍ ተግባራት ከፊታችን እንደ ፈተና ይጠብቁናል። አንደኛ ጥራት፤ ሁለተኛ አምራችነትን ማሳደግ ይገባል። ቡና ጥራት ላይና ምርታማነት ላይ ሥራ ይፈልጋል። ስንዴም ጥራትና ምርታማነት ላይ ሥራ ይፈልጋል። ይህም ማለት በአንድ ሄክታር አርባ ኩንታል የምናገኝ ከሆነ አርባ አምስት ማድረስ ይቻላል ማለት ነው። ማለትም መሬት ሳይጨመር ባለበት ላይ ምርትን ለማሳደግ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቃል። በድምሩ ግብርና ስድስት ነጥብ አንድ እድገት በማረጋገጥ ስምንት ነጥብ አራት በመቶ ለማደግ ያለንን ጥረት ለማሳካት አጋዥ ሆኖ የሚቆም ይሆናል። ይህ ሴክተር እንደተለመደው ትልቅ እምርታ የመጣበትና ወደፊትም ተስፋ የሚጣልበት ነው።
ሁለተኛው ሴክተር ኢንዱስትሪ ነው። ከኢንዱስትሪ በዚህ ዓመት አስራ ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት ይጠበቃል። ከዚህም በየዘርፉ ስንመለከት ማኑፋክቸሪንግ አስራ ሁለት በመቶ እድገት ይጠበቃል። ከኮንስትራክሽን አስራ ሁለት ነጥብ ሶስት በመቶ ይጠበቃል። ኢንዱስትሪ በዚህ ዓመት ከፍተኛ እድገት እንደሚያመጣ የተጠበቀበት ዋነኛው ምክንያት ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ የጀመርነው ሥራ የሚጨበጥ ፍሬ እንደሚያመጣ ስለሚጠበቅ ነው።
ባለፉት ዓመታት ኢንዱስትሪን በዘርፍ ከፍለን ስንሰራ ቆይተን ባለፈው ዓመት መጨረሻና በዚህ ዓመት መጀመሪያ ደግሞ በፕላን ደረጃ እያንዳንዱን ከፍ ከፍ ያለ ፋብሪካ ምን ችግር እንዳለው? ምን ብናግዘው ምርታማነቱ ሊያድግ እንደሚችል በጋራ ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። አንደኛ ከፋብሪካዎች ጋር የሚያያዝ የመብራት ችግር ከሞላ ጎደል ተፈትቷል። ከቴሌ ጋር የሚያያዝ ችግር ከሞላ ጎደል ተፈትቷል። ከባንክ ጋር የሚያያዝ ችግር ተቀርፏል። ብዙ መሰራት ያለበት ሥራ ቢኖርም ከፍተኛ ለውጥ አለ። ከመሬት አቅርቦትና ከእኛ አሰራር ጋር የሚያያዙ በርካታ ጉዳዮች መፍትሔ እያገኙ መጥተዋል። አሁንም ተጨማሪ ሥራ የሚያስፈልገንና ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ የሚፈልጉት ከጉምርክ ጋር የሚያያዝ ሥራ ነው። እሱም ለብቻ ተይዞ ሥራ ተጀምሯል። በሁሉም ሴክተር የኢንዱስትሪ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችል ደረጃ ከላይ እስከታች ተሳስረን መሥራት እንዳለብን አይተን፤ ለይተን ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ሰፋፊ ጥረቶች ተደርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ዓመት ቢያነስ ቢያነስ ሰባ ሁለት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ፋብሪካ ቢባሉም አንዳንዶቹ ከፋብሪካም በላይ የሆኑ ሥራ ይጀምራሉ ወይንም ወደ ገበያ ይገባሉ። ከእነዚህ ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች፤ ምግብና መጠጥ አርባ አንድ ፕሮጀክቶች፤ ኮንስትራክሽንና ኬሚካል አራት ፕሮጀክቶች፤ ቴክኖሎጂ አስራ አምስት ፕሮጀክቶች፤ የሚሊተሪ ፋብሪካዎች፤ ትልቅ ገበያ ሊያመጡ የሚችሉ ሶስት ፋብሪካዎች በዚህ ዓመት ማምረት ይጀምራሉ። ከመከላከያ ጋር ተያይዞ በጣም በርካታ ስንገዛቸው የነበሩ ጉዳዮች አሁን ወደ ማምረት እየገባን ስለሆነ ቀጣዩ ሥራ በአፍሪካ ገበያ እያፈላለጉ ተጨማሪ ገንዘብ ማምጣት መጀመር ይሆናል። እነዚህ ሰባ ሁለት ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ ቀድመው ከነበረው በተጨማሪ ተጨማሪ ምርት፤ ተጨማሪ ሀብት እንደሚያመጡ ይጠበቃል።
ከኢንዱስትሪያል ፓርክ ጋር ተያይዞ እንደሚታወቀው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ መሳተፍ እምብዛም ስላልተፈቀደና ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ስላልተፈቀደ ችግር ነበር። ከሪፎርሙ በኋላ ሰፊ ለውጥ ተደርጎ ሀምሳ በመቶ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተይዟል። በተኪ ምርቶች ደረጃም ከፍተኛ እመርታ አምጥተዋል። አጠቃላይ ኢንዱስትሪው ግን ከነበረበት ሀምሳ ዘጠኝ በመቶ በዚህ ዓመት ቢያንስ ስልሳ ሰባት በመቶ የምርት እድገት ይጠብቃል። ከዚህ ቀደም አርባ ውስጥ ነበር። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በሌሎች ሀምሳ ዘጠኝ ደርሷል። አሁን አዲሶቹን ጨምሮ ስልሳ ሰባት በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል። በዚህ የሀገር ውስጥ ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚያድግ የገቢ ምርትን በመተካት ረገድ ብዙ እምርታ ይጠበቃል።
ማዕድን በሚመለከት በወርቅ፣ ብረታ ብረት፣ የድንጋይ ከሰል አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ። የወርቅ ፋብሪካዎች ሲሰራባቸው የቆዩ በዚህ ዓመት ምርት የሚጀምሩ አሉ። ሲሚቶን ብንወስድ የለሚ ሲሚንቶ ብቻ በዓመት 450 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል። አሁን ያለውን የሲሚንቶ ምርት 16 በመቶ እድገት ሀገር ውስጥ ያመጣል። እነዚህ ፋብሪካዎች በተሟላ አቅም እየሰሩ ሲሄዱ የኢንዱስትሪው እና የማዕድን ዘርፉ ተደምሮ ከፍተኛ እምርታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ሲሚንቶን በሚመለከት አንዳንድ የአሰራር ችግሮች እንዳሉ እንገነዘባለን። እነሱን ለመፍታት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ተጨማሪ የውጭ ኢንቬስተሮች ፍላጎት አሳድረዋል። አዳዲስ ፋብሪካዎች ለመክፈት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን እያደገ እንደሚሄድ በመተማመን ብዙ ፍላጎቶች አሉ፡፡
ሁለተኛ ለሲሚንቶ ምርት የሚያግዙ ሁሉም ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ ስለሚገኙ፤ አዳዲስ ፍላጎቶች አሉ እነሱን እያስፋፋን በሚቀጥሉት ዓመታት የምንቀጥል ይሆናል። የኢንዱስትሪ ሴክተር እያንዳንዱ ሴክተር ባስቀመጥነው መንገድ ሰርቶ የ12 ነጥብ 8 በመቶ ካረጋገጠ፤ ለስምንት ነጥብ አራት በመቶ እድገታችን ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡
እዚህ ጋር ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ግብርና ስድስት ነጥብ አንድ ነው ድርሻው፤ ኢንዱስትሪ 12 ነጥብ 8 ነው ሲባል ኢንዱስትሪ ከግብርና ይበልጣል ማለት አይደለም። ግብርና መሰረቱ በጣም የሰፋ ስለሆነ በየዓመቱ የምናመጣው እድገት በቁጥር ደረጃ ይቀንሳል፤ በአጠቃላይ እድገቱ ግን የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሶስተኛው ዘርፍ አገልግሎት ነው። በዚህ ዓመት አገልግሎት ሰባት ነጥብ አንድ በመቶ እድገት ይጠበቃል። አገልግሎት በዋና ዋና አንጓ አንጓ ዘርፎች ብንመለከት፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ 124 አዳዲስ አውሮፕላን አዟል፡፡
በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን አየር መንገድ በእጥፍ የሚበልጥ አቅም እየፈጠረ ነው ያለው። 124 አውሮፕላን ማዘዝ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለን ኤርፖርት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች በዓመት ማስተናገድ የሚችል ቢሆንም፤ በቂ ስላልሆነ ከ100 እስከ 130 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች ማስተናገድ የሚችል ኤርፖርት ለመገንባት ጥናት ተጠናቋል፡፡
ይህ ኤርፖርት አሁን ካለን ኤርፖርት በአየር ርቀት ከ40 ኪሎ ሜትር የሚያንስ ሆኖ፤ ሁለቱ ኤርፖርቶች በባቡር የሚገናኙ ስለሆነ ሁለቱንም በጋራ ለመጠቀም ሰፊ እድል ይፈጥራል። በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ትልቁ ኤርፖርት ይሆናል ማለት ነው። ሜጋ ፕሮጀክት ነው፤ ሰፊ ሥራ እየሰራን ነው። ይሄን ውጤት ካመጣን አየር መንገዳችን ከነበረው ክብር፣ ከነበረው ዝና በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጨበጥ ውጤት እያመጣ የሚቀጥል ተቋም ይሆናል፡፡
እንደኛ ወደብ አልባ ለሆኑ ሀገራት እንደዚህ አይነት ተቋማት፤ የገበያ ብቻ ሳይሆኑ ስትራቴጂክ ናቸው። በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ መጠንከር፤ መገንባት አለባቸው። ለዚህ ነው ለቁጥር ለማመን በሚከብድ ደረጃ ሰፋፊ የአውሮፕላን እና የኤርፖርት ልማቶች የተጀመሩት፡፡
ይሄ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ ነው። አራት ሳይሆን 124 አውሮፕላን ማዘዝ ቀላል ነገር አይደለም። በዚያው ልክ ፓይለት፣ በዚያው ልክ የጥገና ቦታ፣ በዚያው ልክ በጣም በርካታ ዝግጅቶች ስለሚፈልግ። ሁለተኛው ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ነው። ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ኤልቲ፣ ፎር ጂ፣ ፋይቭ ጂ ኢንተርኔት ወደ ማስፋፋት ገብቷል። ከአዲስ አበባ ወጥቶ የክልል ከተሞች እያስፋፋ ይገኛል፡፡
የሞባይል መኒ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይሄዳል። ኢትዮ ቴሌኮም ከማገናኘት አልፎ በኢ- ኮሜርስ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚጫወት ተቋም ሆኗል። ኢ-ኮሜርስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያድግ እንደ ዋና ሥራው ወስዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ የሶቭሬን ዌልዝ የተቋቋመው ተቋም አብዛኛው የመንግሥት ኩባንያዎች፣ ተቋማት ትርፋማ መሆን አቅቷቸው በድጎማ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን አብዛኞቹን እራሳቸውን እንዲችሉ እና ትርፋማ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
ስኳር ብንወስድ በጣም በብዙ ድጎማ የሚንቀሳቀስ ኮርፖሬሽን ነው። በስኳር ሴክተር ላይ በተሰራው ሪፎርም ሁሉም የስኳር ፋብሪካዎች ባይባልም፤ በርካቶቹ እራሳቸውን ችለው እንዲሄዱ፣ ትርፋማ እንዲሆኑ፣ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ማድረግ አስችሏል፡፡
ኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በታሰበለት መንገድ ድጋፍ እያገኘ ከሄደ፤ በመንግሥት ስር የተቋቋሙትን ትላልቅ ኩባንያዎች ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ግን ያልተመሩና፣ አክሳሪ የነበሩ ውጤታማ እንዲሆኑ በእጅጉ ያግዛል፡፡
የካፒታል ማርኬት መጀመራችን ይታወቃል፤ ብዙ ሀብት፣ ብዙ እውቀት ለመሰብሰብ እና ዜጎች ኢንቬስት አድርገው ትርፋማ እንዲሆኑ፣ የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓት እንዲያድግ፣ መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን በሕግ ብቻ እንዲያስተዳድር በእጅጉን የሚያግዝ ልምምድ ለኢትዮጵያ የሚያመጣ ነው። በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ሽያጭ ማካሄዱ ይታወቃል፤ በቀሩትም ኩባንያዎች መሰል ሥራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ቱሪዝም በሚመለከት ባለፉት ሶስት ወራት ከ20 የማያንሱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተካሂደዋል። አምና ዓመቱን ሙሉ 20 አላካሄድንም። ዘንድሮ በሶስት ወራት ብቻ 20 ተካሂዷል። በሚቀጥለው ሳምንትም በዛኛው ሳምንትም ይቀጥላል። በርካታ ጉባኤዎች እየሳብን እንገኛለን። ምክንያቱ አንዱ ኮሪደር ነው። ሁለተኛ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አውድ ከውጭ ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጉባኤ እንዲያካሂዱ እግረ መንገዳቸውን ኢትዮጵያን ለማየት ፍላጎት እያሳደሩ ስለመጡ ነው፡፡
ቱሪዝም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቅድም ሲገለጽ እንደነበረው በተለያዩ የገበታ ስሞች የግል ዘርፍ በማስተባበር ሁላችሁም አግዛችሁ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል አሁን ውጤት ማየት የጀመርንበት ጊዜ ነው። ያን አጠናክረን በመቀጠል ልማቱንም ጎን ለጎን የምናስፋፋ ይሆናል፡፡
የችርቻሮና ጅምላ ንግድ መከፈቱም በጣም ብዙ እድል ይዞ ይመጣል። በዚህ ምክንያት የአገልግሎት ኢንዱስትሪው ሰባት ነጥብ አንድ በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 12 ነጥብ 8 በመቶ፣ ግብርናው ስድስት ነጥብ አንድ በመቶ በማደግ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የጂ ዲ ፒ እድገት ስምንት ነጥብ አራት በመቶ ይሆናል በሚል ታቅዷል፡፡
አሁን የሶስት ወር እንቅስቃሴያችን የሚሳየው ግን ከዚያ በላይ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ነው። በሁሉም ዘርፍ ያለው አበረታች ውጤት ከዚያ የተሻለ እድገት ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታል። ለምሳሌ ግብርና ሁላችሁም እንዳያችሁት የተለመደው አይደለም። የዘንድሮ የግብርና ምርት። በጣም ከፍተኛ ምርት ነው ያለው በየቦታው። ይሄን ስትወርዱ ያያችሁት ይመስለኛል፡፡
አርሶ አደሩ ከምርቱ መያዝና ማማር የተነሳ የሰላም ያድርግልን እያለ ነው ከልምምዱ እና ከባህሉ ከፍተኛ ምርት በቡናም፣ በስንዴ፣ በሰሊጥ የሚጠበቅበት ዓመት ነው። የዝናብ ሁኔታ እስካሁን ባለው ሁኔታ አስቻይ ነገር ስለፈጠረ። ከዚህ በኋላ ትንሽ ገብ ማለት ቢጠበቅበትም። እነዚህ ሶስት ዘርፎች ተደምረው የኢትዮጵያን የጂ ዲ ፒ እድገት ስምንት ነጥብ አራት በመቶ እና ከዛ በላይ ማሳካት ከቻልን የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን በሚጨበጥ ሁኔታ እውን ይሆናል፡፡
ከሪፎርም ጋር ተያይዞ በቅርቡ ያካሄድነው ኦፕን አፕ ምን ችግር ስለነበረ ነው፤ ምን ፋይዳ አስገኘ ለሚለው እኛ ሪፎርም የጀመርነው በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንድ ነው። በቅርቡ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለት ብለን እንደጀመርን ይታወቃል። አሁን እነዚያ ሪፎርሞች የቋጨንበት ቀሪ ሥራዎች መቋጫ ያበጀንበት የመጨረሻው የሪፎርሙ አካል ነው እንጂ አሁን የተጀመረ ሪፎርም አይደለም፡፡
ይሄ ሪፎርም እውነት ለመናገር ቀድሞ መጀመር ነበረበት። በጣም ነው የዘገየው፤ ኢትዮጵያን አይመጥንም። በዓለም ላይ በጣም ጥቂት ሀገራት ሸቀጥና ካፒታል ዝውውር ከዓለም ጋር የማያደርጉ፣ መረጃቸው በግልጽ የማይታወቅ፣ የንግድ ሥርዓታቸው የማይታወቅ ጥቂት ሀገራት ካልሆኑ በስተቀር እኛ በነበርንበት አይነት የኢኮኖሚ ሥርዓት በአፍሪካ ውስጥ እንኳን ብዙ ሀገራት አይገኙም፡፡
ተቆላልፎ የተቀመጠው እና ሪፎርሙ አንዱ ያፍታታው ይሄን ነው። በዛ ምን እንዳጣን በመረጃ እናየዋለን፤ ምን ማግኘት እንደጀመርን ስናይ ይበልጥ የተገለጠ ይሆናል። ምንድነው ዋና ጉዳቱ ያላችሁ እንደሆነ አንደኛ ኤክስፖርት ይቀንሳል፣ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት መድረስ ከነበረበት አነስተኛ ያደረገው ኢኮኖሚክ ሪፎርሙ በበቂ ደረጃ ባለመሰራቱ ነው።
ሁለተኛ ምርቶች በሀገር ውስጥ በበቂ ደረጃ እንዳይመረቱ ያደርጋል። ተኪ ምርት አምራቾችን የሚያበረታታ ስላልሆነ ማለት ነው። ሶስተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በስፋት ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ያደርጋል። የውጭ ምንዛሪ ሂደቱ አስጊና ትርፍን ለማውጣት አስተማማኝ ስላይደለ የውጭ ኢንቨስተሮች የበለጠ ተማምነው ሀገር ውስጥ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ያደርጋል፡፡
አራተኛ በዶላር ግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ትይዩ ገበያ የተራራቀ ያደርገዋል። ይሄም በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚፈጥርና ሰዎች ተማምነው ሀብታቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ራሱን የቻለ እንቅፋት አለው። ተቀባይነት አይኖረውም ማለት ነው። ይሄ ሁሉ ችግር ነው። ጥቅምስ ነበረው ወይ ያላችሁ እንደሆነ ጥቅም ያላቸው አካባቢዎች አሉ ለምሳሌ ሸቀጥ ከውጭ አምጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ በፈለጉት ዋጋ ለሚሸጡ ሰዎች የውጭ ሸቀጥ ለሚያራግፉ ሰዎች ጥቅም አለው። ኤክስፖርት ለማድረግና ኢንፖርት ለመተካት ግን በጣም ጉዳት አለው።
ራሱ ሥርዓቱ ኤክስፖርትን የሚጎዳ ኢንፖርት ተኪዎችን የሚጎዳ ሸቀጥ አራጋፊዎችን የሚጠቅም ነው። በዚህ ውስጥ ፍራንኮቫሎታ አንዱ መንገድ ነው። ባለፉት ጥቂት ወራት ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ከወሰናቸው አብረው ከማይሄዱ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ፍራንኮ ቫሎታ ነው። ያን የወሰንበት ምክንያት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩን። አንደኛው በውጭ ያለ ሀብት ከዚህ ቀደም የሸሸ ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት የሚችል ከሆነ እድል ለመስጠት ሁለተኛ ባንኮቻችን አሁን በጀመርንው ኢኮኖሚክ ኦፕን አፕ በቂ ልምምድ እስኪያደርጉ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች እንዳያንሱ እና የኑሮ ውድነትን እንዳያባብሱ ጉዳት ቢኖረውም ከፈት እናድርግ የሚል እሳቤ ነበረን።
ያየነው ውጤት ከዚህ በላይ መሸከም ተገቢ እንዳልሆነ የሚያሳይ በመሆኑ በቅርቡ ፍራንኮ ቫሎታን በሚመለከት ማስተካከያ እንደሚደረግ ይጠበቃል። አጠቃላይ ኢኮኖሚክ ኦፕንአፕ ኢትዮጵያን ማንሰራራት፣ የኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የምታደርገውን ጉዞ መሰረት ሆኖ የሚያገለገል ይሆናል። ከምንጠብቃቸው አንኳር አንኳር ድሎች መካከል አንደኛው ገቢ ነው። እናንተም እንዳነሳችሁት ገቢ ባለፉት ሶስት ወራት 180 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገብተናል። ይሄ መቶ ፐርሰንት እቅዳችንን ነው ያሳካነው። ምንም ከእቅዳችን የጎደለ ነገር የለም። ሪፎርሙን ተስታኮ በታቀደው እቅድ መሰረት የተገኘ ገቢ ነው።
የተከበረው ምክር ቤት ቀለል ባለ መንገድ እንዲገነዘበው ግን ሁለት ሺህ አስራ አራት የዛሬ ሁለት ዓመት በሶስት ወር ያስገባነው ገቢ 70 ቢሊዮን ብር ነበር። 2015 አቻምና 93 ቢሊዮን ብር ነው ያስገባነው። 2016 ያለፈው ዓመት ያስገባነው 109 ቢሊዮን ብር ነው። አሁን 170 ቢሊዮን ብር አስገባን ስንባል 2014 ያስገባነው 70 ቢሊዮን በአምናና በዘንድሮ ሶስት ወር መካከል ባለ ዲፍረንስ ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው። ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ መስከረም ያስገባነው 170 ቢሊዮን 109ኙ የአምና ሆኖ ከዛ የተረፈው 71 ቢሊዮን ቢወሰድ ከ2014 ሶስት ወር ገቢ እኩል ይሆናል ትርፉ ብቻ፡፡
ከዓመት ደግሞ ልታወዳድሩ ከፈለጋችሁ ሪፎርም ሲጀመር በ2010 የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ እንደ ሀገር ያስገባነው ዓመታዊ ገቢ 176 ቢሊዮን ነበር የዓመቱ። 2010 ዓመቱን ሙሉ ያስገባነው 176 ቢሊዮን ብር ነው። አሁን ሶስት ወር ያስገባነው 180 ቢሊዮን ብር ነው። ይሄ ሶስት ወር ከ2010 የዓመት ገቢ ይልቃል። ታዲያ በዚህ ደረጃ ካደገ ችግሩ ምንድነው ያላችሁ እንደሆነ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ካላት አቅም፤ ካላት ጂዲፒ አንጻር የታክስ ጂዲፒ ሬሾ የሚጠበቅ መስፈርት አለ። በዚህ መሰፈርት ከፍ ያሉት እስከ 40፣ 44 የደረሱ ሀገራት አሉ ምዕራቡ። አፍሪካ ውስጥ ኬንያን ብንወስድ 16 ፐርሰንት ገደማ ናት። ደቡብ አፍሪካ 24 ገደማ ናት። ሞሮኮ ትበልጣለች፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በጀመርንው ሪፎርም ዘንድሮ ሁለት ፐርሰንት እንኳን ማሻሻል ብንችል የምንደርሰው 8.5 ፐርሰንት ከጂዲፒአችን የኬንያ ግማሽ ማለት ነው። ልናስገባ ከሚገባን በጣም ሩቅ ነን። ከ10 በታች አይደለም። እኛ አሁን በሪፎርሙ ያቀድነው በትልቁ 8.5 ለመድረስ ነው። እዛ ብንደርስስ የኬንያን ግማሽ እንሆናለን። ኢትዮጵያ ታክስ ከማይሰበስቡ ሀገራት ተርታ ናት። ይሄ የተከበረው ምክር ቤት በደንብ መገንዘብ አለበት። ታክስ አይሰበሰብም። አብዛኛው ኢንፎርማል ማርኬቱ በብዙ መንገድ ስለሚሰራ በህጋዊ መንገድ ታክስ የመክፈል ልምምዱም አነስተኛ ነው። ይሄንን ማሳካት ችለን ዘንድሮ በፌደራል መንግሥት 9 መቶ ቢሊዮን ገደማ፣ በክልል 6 መቶ ቢሊዮን ገደማ ማስገባት ብንችል እንደ ሀገር 1.5 ትሪሊየን ብር ገቢ እንሰበስባለን። ይሄን ካሳካን እምርታ ነው። በቂ አይደለም ግን እድገት ነው፡፡
1.5 ትርሊየን የፌደራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ገቢ በዚህ ዓመት ይጠበቃል። ይሄ አሁን ካለንበት በተወሰነ ደረጃ እንድንሻሻል ያደርገናል። የታክስ ጂዲፒ ሬሾ እሳቤ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ያግዛል። ይህ እንዲሆን የታክስ ሕጎች፣ የታክስ አስተዳደር ኦውቶሜሽን፣ የታክስ አስተዳደር የሚሰራ አቲትዩድ፣ ሪፎርም፣ በጣም በርካታ ትጋትና ጥረት የሚጠይቁ ሥራዎች አሉ። ብሔራዊ ታክስ አቁሞ በማክሮ የሚመራ ገቢን ብቻ በቅርበት የሚመራ ቲም አለን ያን ይዘን እንደምናሳካው ተስፋ እናደርጋለን። እድገቱን ግን የማይካድ የቁጥር እድገት ስላለ እሱን እንዳለ ተቀብለን አድርገን ያ እድገት ከሚታሰበው አኳያ ዝቅተኛ ስለሆነ ወደሚገባው ደረጃ እንዲያድግ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ከሪፎርም በኋላ የመጡ ውጤቶችን በጥቂቱ ነካ ነካ በማድረግ የሪፎርሙን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ለማድረግ እሞክራለሁ። አንደኛ ሪዘርቭ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለክፉ ቀን ብላ የምታስቀምጠው ሪዘርቭ ባለፉት 3 ወራት 161 በመቶ አድጓል። የናሽናል ባንክ ሪዘርቭ 161 ፐርሰንት አድጓል። የግል ባንኮች ሪዘርብ 29 ፐርሰንት አድጓል። ይሄ ድንገተኛ ነገር ሲያጋጥም በእጅጉ የሚያግዝ እና አንዳንድ መንግሥታት ሊያሟሉ እየፈለጉ ከሚጨንቃቸው ኤሪያ አንዱ ነው። እኛን ጨምሮ ሪዘርባችንን ከፍ ማድረግ አሁንም ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል።
ሁለተኛው ሬሚታንስ ነው። ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የሬሚታንስ ገቢ ባለፉት 3 ወራት 24 ፐርሰንት እድገት አምጥቷል። ከዚህ በላይ ማደግ አለበት ተጨማሪ ሥራ ብንሰራ ግን ቢያንስ 24 ፐርሰንት እድገት አምጥቷል። ባንኮች 652 ሚሊዮን ዶላር ገዝተው 1 ቢሊዮን ገደማ ዶላር ሸጠዋል። በባንኮች የተደረገው የዶላር ትራንዛክሽን በሽያጭም ፤በግዢም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ኤክስፖርትን ብቻ ብንወስድ ቅድም ሪፎርሙ ኤክስፖርት ይጎዳል ብያችሁ ነበር። ኤክስፖርት እኛ ባለፉት 3 ወራት ያቀድነው 1.1 ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ነው። ያስገባነው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ነው። ምን ማለት ነው 1.5 ቢሊዮን ዶላር በ3 ወር ማለት ያላችሁ እንደሆነ ይሄንን ካስጠበቅን በዓመት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ልናስገባ እንችላለን ማለት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የፖለቲካ መነቃቃት የታየው 1997 ዓመተ ምህረት ነው። ሁላችሁም የምታስታውሱት ከ97ቱ ምርጫ በኋላ በ98፣ በ99 ዓመተ ምህረት ከዚያ ሁሉ ግር ግር በኋላ የኢትዮጵያ የአንድ ዓመት ኤክስፖርት 1 ቢሊዮን ብር ነበር። ዘንድሮ በሶስት ወራት ብቻ 1ነጥብ 5 አስገብተናል፡፡
የሚታይ የሚጨበጥ ውጤት ነው ያለው። በሶስት ወር አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር አስገብተን በዓመት ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ ካስገባን እንደምታውቁት የመጨረሻው ጣራ በሪፎርም ዘመን ያሳካነው አራት ቢሊየን ዶላር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አምስት ቢሊየን በላይ ዶላርን ኤክስፖርት ማድረግ አይታሰብም። በ2000 ዓ.ም እኔ እዚህ እያለሁ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር አልደረስንም እና እድገቱን በደንብ በእውነታነት ማወቅ ያስፈልጋል። መዘናጋት አያስፈልግም። የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ አምስት ቢሊየን ዶላር ማለት ውድቀት ነው። 50 እና 100 ቢሊየን ዶላር ብለን ማሰብ አለብን፤ አቅሙ ስላለ። ከነበርንበት አረንቋ አንፃር ነው እንጂ የምናየው መድረስ ካለብን አንፃር አሁንም ገና ነን።
በቅርቡ የሄድኩባት ማሌዥያ ከፓልም ዘይት ብቻ 25 ቢሊየን ዶላር ታገኛለች። እኛን ጨምሮ ያው የፓልም ዘይት ገዢዎች ነን ከፍተኛ ምንዛሪ ያገኛሉ። ኢትዮጵያ ዘንድሮ ሁለት ቢሊየን ዶላር ኤክስፖርት በቡና ካሳካች ቡና የሪፎርም ወራት 750፣ 760 ሚሊየን ዶላር ነው ከፍተኛ የነበረው። ያንን እጥፍ አድርገን አምና አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ደርሰናል። ዘንድሮ ሁለትም ቢሊየን ከገባን ባለፉት ስድስት ዓመታት ከሁለት እጥፍ በላይ የቡና ኤክስፖርት ካደገ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ከፍ አለ ማለት ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ በሚጨበጥ መንገድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ አደረገ ማለት ነው።
በርግጥ ዘንድሮ ቡናና ወርቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። የወርቅም እንደሚታወቀው ለመጀመሪያ ከቡና በላይ ትልቁን ድርሻ ይዟል። ምን ያህል ወርቅ ስንዘረፍ እንደነበረ ማሰብ ይቻላል። አምስት መቶ ሚሊየን ዶላር ገደማ ወርቅ ባለፉት ሶስት ወራት ማግኘት ተችሏል። ባልተገባ መንገድ ከምንዘረፍባቸው 1001 አካባቢዎች ጥቂቶቹ ምላሽ እያመጡ ነው። ገና ብዙ ነው። የምንበዘበዝበት ብዙ ቀዳዳዎች አሉ። ከነሱ ውስጥ አንዱ ወርቅ ነው መልስ እየሰጠ ይገኛል።
ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ኤክስፖርት ትልቁን ድርሻ ይዟል። የሚገርመው ግን ባለፉት ሶስት ወራት የአገልግሎት ኤክስፖርት የሚባለው አንድን ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ነው። የእቃ ኤክስፖርት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር ነው ለመጀመሪያ ጊዜ እቃ አገልግሎትን በልጧል። ይህ በጣም የምንመኘው የሪፎርሙ ፍሬ ነው።
አምስት ትላልቅ ኤክስፖርት ከምናረጋቸው ዘርፎች አንዱ ኤሌክትሪክ ነው። ከአምስቱ አንዱ ወርቅ ቡና ብላችሁ አምስት ስትደርሱ መብራት ታገኛላችሁ። ማምረት ብቻ አይደለም ብር እያመጣ ነው። ኢምፖርት ላይ ደግሞ በአንድ ነጥብ ሶስት በመቶ ገደማ ቀንሷል። ተኪ ምርቶች ሸቀጥ እያመጡ የሚያራግፉት ቀንሰዋል። የሀገር ውስጥ ምርቶች ደግሞ የተሻለ ገበያ አግኝተዋል። ይሄ መጠናከር አለበት። ምክር ቤቱ ከፍተኛ ኩራት ሊሰማው ይገባል። ቀላል ውጤት አይደለም አያወራሁ ያለሁት። ትልቅ እምርታ ነው። ይህን አናይም አንሰማም ማለት አይቻልም። አፍ አውጥቶ ይናገራል። ልክ እንደቦሌ መንገድ ነው እየጮኸ የሚናገረው።
ነገር ግን እንደዚህ አይነት እድገት ያመጡ ሀገራት አላደግንም ችግር አለብን መሞከር አለብን የሚባል ዜና በቻይናም በሲንጋፖርም በማሌዥያም ባጠናናቸው ጥናቶች በኮሪያም የተለመደ ልምምድ ነው። ሀገር እየተቀየረ ሲሄድ የማይቀየሩ ሰዎች አሉ። እኛን የከበደን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቀየር ሳይሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተቀየረ እንደሆነ ማንበብ የማይችሉ ሰዎችን መቀየር ነው ያስቸገረን። ይሄ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመለከት እንዳይመስላችሁ እኛ ብልጽግናዎችን ነው በዋናነት የሚመለከተው። አልተቀየረም፤ ጭንቅላታችን እያመጣን ያለነውን ድል ለመጠበቅ ለማስቀጠል የሚያስችል እምነታችን ተጨማሪ ሥራ ያስፈልገዋል። ለምሳሌ በኋላ እመጣበታለሁ ከጎፋ እና ከአርባ ምንጭ አካባቢ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ የአርባ ምንጭ ሕዝብ በጣም ሰላማዊ እና የፍቅር ሕዝብ ነው ታውቁታላችሁ። በጣም ሲደክመኝ፤ በጣም ሲጫጫነኝ ሄጄ እረፍት የማገኝበት ቦታ አርባ ምንጭ ነው። የሚገርም ሕዝብ ነው። ቁጫን ይጨምራል። ዘይሴን ይጨምራል። ሁሉንም ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ባሕል ካላቸው ሰው ከሚወዱ እና ፍቅር ከሚዘሩ ሕዝቦች መካከል አንዱ የዛ አካባቢ ሕዝብ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥያቄ ሕዝቡን የሚጠይቅ አይደለም። እኛን የሚጠይቅ ነው። እኛ አመራሮች እንዴት ነው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የምንይዘው። እሱን በጣም ማየት ያስፈልጋል። እንዳለ ጥያቄያችሁ ገደል ይግባ ካልናቸው አናድግም ማለት ነው፤ መፈተሽ ጥሩ ነው። የተጋነነ ሊሆን ይችላል ሰው ሳይሞት ሊሆን ይችላል። መፈተሽ ግን ይጠቅመናል። ችግር የለም ብለን ከሄድን በየቦታው ያለ አመራር በሙሉ ዴሞክራሲያዊነት ተላብሶ ከችግር ወጥቷል ማለት ነው። እንደዛ አልደረስንም። ለምሳሌ ባለፉት አራት ዓመታት ሄዶ አለማወያየት በሁለት መንገድ ይታያል። በአንድ በኩል ከነሱ ድክመት በሌላ በኩል እኛ ገዢ ፓርቲ ስለሆንን በነፃነት መጥተው እንዳያወያዩን እንቅፋት እንፈጥራለን ማለት ነው። እነሱ ሲናገሩ የጋሞን ሕዝብ ደግነት ፍቅር የሚነካ ከሆነም መታረም አለበት። የእኛ አስተዳደር ግን ችግር አይፈጥርም የሚል መከራከር ውስጥ መግባት ሳይሆን መፈተሽ ነው ያለብን።
እንደዚያ ካደረግን እናድጋለን። እኛ ብዙ ስለሆንን ማዳፈን እንችላለን፤ ግን አይጠቅመንም። የሚጠቅመን ውስጣችንን እያየን እያረምን መሄድ ነው። በእነርሱ በኩል የጋሞ ሕዝብን ጥያቄ ያነሳሉ ብዬ አልገምትም ምክንያቱም ከዚያ አንዱ ስለሆኑ። ለምሳሌ ሰላም በር ሄድን ነበር። የቁጫ በር የተባለው ማለት ነው በጣም የምታምር አነስተኛ ከተማ ናት። ያው በሻሻ ማለት ናት፡፡
ባለፈው ምርጫ ዘመን ሕዝቡ እኛን አልመረጠንም። ልክ እንደ ባሕር ዳር እኛን አልመረጠንም። እኛ ግን ስንመረጥ ቃል የገባነው የመረጠንንም ያልመረጠንንም ማገልግል ስለሆነ ልክ ባሕር ዳር ድልድይ እንደሰራነው በሰላም በር ከተማ ደግሞ አስፓልት ሰርተናል። ከተማዋ አስፓልት አልነበራትም። ይሄ ግዴታችን ነው። እርሶ የዚያን ቀን ከእኛ ጋር ቢሄዱ ጥሩ ነበር። በሚቀጥለው ሲሄድ አስታውሼ ይዤዎት እሄዳለሁ፡፡
ጋሞ ማለት እኮ እዚህ ቡራዩ ላይ ሰዎች አደጋ ሲደርስባቸው መጥቶ ያስታረቀ ሕዝብ ማለት ነው። ጋሞ ማለት እኮ ትግራይ ሄጄ ካላስታረቅኩ ያለ የሀገር ሽማግሌ ያለበት ሕዝብ ነው። እዚያ አካባቢ ያለው በጣም የሚገርም ማህበረሰብ ነው። ደግሞ አቃፊ ነው። የሌለ ብሔር የለም። ያንን እንጠብቃለን፤ እናደንቃለን። እኛ የምንፈጥረው ችግር ደግሞ እናርማለን። በዚያ መንገድ ብናየው ይሻላል፡፡
ወደ ኢኮኖሚ ጉዳይ ለመመለስ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ባለፉት ሦስት ወራት 6 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል። ከለውጡ በኋላ በጣም ከፍተኛ ፍላጎት መጥቷል። በሚቀጥሉት ቀናት እንደምትሰሙት ከብዙ ሀገራት ኢንቨስት እናድርግ እንስራ የሚል ጥያቄዎች እየመጡ ነው። በእኛ በኩል ኢዝ ኦፍ ዱይንግ ቢዝነስ ላይ ተጨማሪ ሥራ መሥራት ይኖርብናል። የጀመርነውን ሥራ ማጠናከር፤ ኦቶሚሽን ላይ የሲቪል ሰርቪስ ሥራችን ላይ መሬት አቅርቦት ላይ በጣም ብዙ ማረቅና ማረም የሚገቡን ነገሮች አሉ። እነርሱን በማድረግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚያድግ ይጠበቃል። አብዛኛው ምክንያት ተመልሷል ዋናው ችግር የፋይናንሻል ሥርዓቱን የምንመራበት መንገድ ነበር ያ መፍትሔ ስላገኘ ብዙ ኢንቨስትመንት እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡
ኢንቨስትመንት እንደሚመጣ የሚጠበቅበት ዋናው ምክንያት ለተከበረው ምክር ቤት ግልጽ መሆን ያለባቸው ጥቂት ጉዳዮች አሉ። በአፍሪካ ውስጥ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ በፈለገው ደረጃ ቢስፋፋም ኢትዮጵያን የሚያክል ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚባል ሀገር እምብዛም የለም። አንድ መሬት ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ስለሆነ አንድ ኢንቨስተር አሳማኝ ኢንቨስትመንት ሲያመጣ ጥቂት ሊዝ ከፍሎ ነው ኢንቨስት የሚያደርገው። ይህንን ሌላ አፍሪካ ሀገር ውስጥ ማድረግ አይችልም። መሬት የግል ስለሆነ ገዝቶ ነው የሚያደርገው።
ሁለተኛ ለኢንዱስትሪ ወሳኝ ዘርፍ ኢነርጂ ነው። ኢነርጂ ብቻ ሳይሆን ንጹህ ኢነርጂ ነው። በምዕራቡ ዓለም ፋብሪካ ሲያቋቁሙ ኢነርጂውን ንጹህ ባለመሆኑ ተጨማሪ ካሳ እንዲከፍሉ ይጠይቃሉ። እኛ ጋር ንጹህ ነው፤ ካሳ የለም። ርካሽ ነው ፤ ንጹህ ኢነርጂ ነው፡፡
ሦስተኛ ሙስና ነው። ጠፋ ብላቸው እንዳትሸወዱ አለ። አፍሪካ ውስጥ ካለው ጋር ግን አይወዳደርም። በዚህ ምክንያት የውጭ ኢንቨስተር ለመሳብ ሰፊ እድል አለ። ችግራችን ቢሮክራሲው አናቂና ዘጊ መሆን፣ የፋይናንሻል ሥርዓት ክፍት አለመሆን ነበር። የፋይናንሱ ፈተናል ሪፎርሙን ካጠናከርን በእጅጉ አዳዲስ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚያስችል የተሻለ የሰው ኃይልም በዚያው ልክ አቅም አለ።
የትይዩ ገበያው በጥቁር ገበያና በባንክ ያለው ምንዛሪ ከአምስት በመቶ በታች ዝቅ ብሏል። ይሄ ተቀባይነት ያለው ሬት ነው። ሁለቱም ገበያ መካከል ያለው ክፍተት ሰፊ እንዳይሆን ተሰርቷል። ዩኒፊኬሽኑ ውጤት አምጥቷል ማለት ነው። ዩኒፊኬሽንን በሚመለከት አንዳንድ በሽታ ያላቸው ሰዎች ጥቂት ግንዛቤ እንዲወስዱ የምፈልገው ኢትዮጵያ በቅርቡ በዌርልድ ባንክና በአይ ኤም ኤፍ የባንከርስ ዋሽንግተን ላይ በነበረው ግብረ መልስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋለች ብሏል። ዝቅተኛ ዝግጅት አድርጋለች አልነበረም የተባለው። ሁለት ሦስት ዓመት እንደምታውቁት ኮሙኒዝም ደማችን ውስጥ ስላለ ወደ ነፃ ገበያ ለመሄድ በከፍተኛ ስቃይና ትጋት ብዙ ሕጎች፣ ፖሊሶዎች እና አሰራሮችን አሻሽለን ነው የገባንበት። ዘለን አልገባንበትም። ሆም ግሪዝ ዋንን ጨርሰን ሆም ግሪዝ ቱን እያገባደደን ነው የገባንበት። በዚያ ምክንያት ዩኒፌኬሽኑ ከሞላ ጎደል በጣም የተሳከ በሚል ምስክርነት ያገኘ ነው። አሁንም በቅርብ አመራር ይጠብቃል ይፈልጋል። ካልተመራ አንዴ ከሾለከ ችግር ስላለው፡፡
ባለፈው ዓመት 2016 ሦስት ወር ውስጥ ከውጭ ያመጣነው ሀብት 400 ሚሊዮን ዶላር ነው። በተለያየ ስም በርዳታ፣ በብድር አምና ሦስት ወር ያገኘው 400 ሚሊዮን ዶላር ነው። ዘንድሮ በሦስት ወር ያገኘው 3ነጥብ4 ቢሊዩን ዶላር ነው። ይህ ስንት እጥፍ እንደሆነ አስቡት። በለውጥ ዘመኑ 27 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይጠበቃል። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቀነስና ተጨማሪ ሀብት አግኝተን ልማት እንድናለማ በእጅጉ የሚግዝ ነው።
እዳን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ እዳን ማቃለል የለውጡ አንዱ አንኳር ሥራ እንደሆነ ይታወቃል ። ለውጥ ሲመጣ የሀገር ውስጥ ሳይጨምር ውጭ እዳ ብቻ 30 ነጥብ6 በመቶ የጂዲፕ ሼር እዳው ይወስደው ነበር። እንደምታወቁት አብዛኛው ኮመርሻል ሎን ነው። እድገት ሲባል የነበረው ያንን ብድር እያመጣን በምንረጨው ፕሮጀክት ነበር ኢትዮጵያ ውስጥ እድገት አለ ሲባል የነበረው። በፋይናንስና በኮመርሻል ሎን በሚመጣ ሀብት። ባለፉት ስድስት ዓመታት አንድ ዶላር ኮመርሻል ሎን አልወሰድንም። ይሄ ትልቅ ርምጃ ነው። በኮመርሻል ሎን ሳንወስድ እድገት ማስቀጠል መቻል፣ በኮመርሻል ሎን ሳንወስድ የነበረን እዳ መቀነስ መቻል ትልቅ እምርታ ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ያለባት እዳ፣ የውጭ 13.7 ፐርሰንት ነው። ከ30 ከግማሽ በታች ወርዷል። በሚቀጥሉት ዓመታት ከ10 በታች ማድረግ ነው የእኛ እቅድ። ከ10 በታች ከሆነ፣ እዳን ሳይሆን ምንዳን እናሸጋግራለን። እኛ እዳ ነው የወረስነው። እዳ ነበረብን፤ እንደገባን ኤክስፖርት በምናደርገው ልክ በየዓመቱ እንከፍል ነበር። በየዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንከፍል ነበር። ባለፉት ስድስት ዓመታት 13 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የመንግሥት (የአየር መንገድና ቴሌን ሳይጨምር) ተከፍሏል። ያን በማድረግ እዳችንን ከ30ቢሊዮን ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ አድርገናል። አሁን ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ከአበዳሪዎች ጋር የውጭ ሀገራት መንግሥታት፣ ባንኮች፣ ባለሀብቶች፣ አበዳሪዎች ጋር ድርድር እያካሄድን ነው። ከተሳካ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሽግሽግ ይፈጠራል። ይህ ከፍተኛ የኢትዮጵያን እዳ የሚቀንስ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ሪፎርም በጣም ተጠቃሚ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ነው። በሕዳሴ፣ በቦንድ ምክንያት በጣም አስጊ ጉዳይ ውስጥ ከነበሩ ተቋማት አንዱ ንግድ ባንክ ነው። ይህ ሪፎርም ባይሰራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፈርስ ነበር። ያለበትን እዳ በቀላሉ የሚቆጣጠረው አልነበረም። በዚህ ሪፎርም 900 ቢሊዮን ብር የተራዘመ ቦንድ አግኝቷል። ባንኩ በከፍተኛ ደረጃ የነበረበትን አስቸኳይ ችግርና አደጋ መከላከል የሚችልበትን ሀብት አግኝቶ ሥራ ጀምሯል። ንግድ ባንክ ወደቀ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ 30ዎቹም ባንኮች ወደቁ ማለት ነው። ዋናው የኢትዮጵያ ባንክ ንግድ ባንክ ነው። እሱን ማዳን የባንክ ሴክተሩን ማዳን ነው። 900 ቢሊዮን ብር የተገኘበትን መንገድ ብንነጋገር በጣም ብዙ አስደሳች ጉዳዮች አሉበት፤ ግን አላነሳውም። በጣም ጠቃሚ በሆነ ድርድር የተገኘ ውጤት ነው። የፋይናንስ ዘርፉን ለማነቃቃት ይውላል።
የፋይናንስ ዘርፉ በ2010 ያለው አጠቃላይ ሀብት 1.3 ትሪሊዮን ብር ነበር። አሁን ባንኮች ያላቸው ሀብት 3.5 ትሪሊዮን ብር ነው። በሀብት ደረጃ ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ አድገዋል። የባንኮች ቁጥር 18 ነበር፤ አሁን 32 ደርሰዋል። በቁጥር አድገዋል፤ ይህ ቁጥር ምን ያህል ጠንካራ ያደርጋቸዋል የሚለው ጉዳይ ተጨማሪ ሥራ የሚፈልግ ነው። የሞባይል ባንኪንግ አልነበረንም፤አሁን 50 ሚሊዮን ሰው በሞባይል ባንኪንግ ይጠቀማል፤ እየሰፋና እያደገ እንደሚሄድም ይጠበቃል። ከስድስት ዓመታት በፊት ቅርንጫፎች በተደራሽነት 5500 ገደማ ነበሩ፤አሁን 13ሺ ደርሰዋል፤ከሁለት እጥፍ በላይ አድገዋል። 450 ቢሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷል፤ ከዚህ ውስጥ 82 ፐርሰንቱ የተሰጠው ለግሉ ዘርፍ ነው።
ቀደም ሲል ከነበረው ድርሻ አንፃር የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት አለው፤ አሁንም ብዙ ፍላጎት አለ። ከምናበድረው ብድር ውስጥ 15 ፐርሰንት ገደማ አነስተኛና መካከለኛ ለሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥ ነው። ይህም ስታርትአፕ ቢዝነሶች እንዲያድጉ ያግዛል። የባንክ ሴክተሩ እምርታ አለው። መታረም ያለባቸውና ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮችም አሉ።
የኢኮኖሚ ዘርፉ በገቢ፣ በኤክስፖርት፣ በሬሚታንስ፣ በመጠባበቂያ/ተቀማጭ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት እድገት አምጥቷል፣ የወርቅና የቡና ኤክስፖርት እድገት አምጥቷል ባልኩት ልክ የምክር ቤት አባላትን ትኩረት የሚሹና ሥራ የሚፈልጉ ዘርፎች አሉ። አንደኛ ባንኮች ናቸው። ባንኮች ኮሚሽን ስለለመዱ፣ በትክክለኛው ህጋዊ መንገድ ከሚሰራው ይልቅ በትይዩ ገበያው ውስጥ መሳተፍ ስለሚጠቅማቸው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳያድግ የሚያበላሹ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ። በባንክ ስም የሚዘርፉ አሉ። እነሱ ላይ ከፍተኛ ክትትልና እርምጃ ይወሰዳል። ባንኮች ሕግና ሥርዓት አክብረው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በሚያረጋግጥ መንገድ እንጂ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ባንክ በሚል ስም የአራጣ ሥራ የሚሠሩ ከሆነ ችግር ነው። ባንክ በሕጋዊ መንገድ የሚወዳደሩበት እንጂ በሕገ ወጥ መንገድ በኮሚሽን ሀብት የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም። ይህ የምክር ቤት አባላትን ትኩረት ይፈልጋል።
ሁለተኛ፣ አንዳንድ ኤምባሲዎች ቀጥ ብለው የኢትዮጵያን ሀብት የመዝረፍና የውጭ ምንዛሪ ቢዝነስ ስራ ይሰራሉ። በእነሱ ላይም ጥብቅ ክትትል ይደረጋል። የማይታረሙ ከሆነ እርምጃ ይወሰዳል። ጤናማ ዝምድና የማያደርግ ኤምባሲ አንፈልግም፤ እኛ የምንፈልገው ጤናማና ህጋዊ ስርዓትን የሚከተልን ብቻ ነው። ያን ስራ የሚሰሩ ነገር እንዳናበላሽ እየታገስናቸው ስራቸው ግን ጥቁር ገበያ ማሯሯጥ የሆኑ ኤምባሲዎች አሉ፡፡
ሦስተኛ ኩባንያዎች ናቸው። በኩባንያ፣ በፍራንኮ ቫሉታ፣ በወርቅ ንግድ ስም የኢትዮጵያን ገበያ የሚያዛቡ ግለሰቦች አሉ። በሾፌሮችና ትንንሽ ሥራዎችን በሚሠሩ ሰዎች ጭምር የኢትዮጵያ ጥቁር ገበያ ዶላር በባቡርና በቅጥቅጥ መኪና ይወጣል። ወርቅና ዶላር ይወጣል። ይህን ዘረፋ መከላከል ያስፈልጋል፤ ሁላችንም ትኩረት ማድረግ አለብን፤ሕገወጥነት፣ ኮንትሮባንድ፣ ዘራፊዎች በውስጣችን ያሉ ሰዎች ተጨምረውበት የሚደረግ ማንኛውም ሕግን ያልተከተለ ዘረፋ መከላከል አለብን።
በዚህ መንገድ ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ እና ኢትዮጵያ ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅሟ አንፃር ጥያቄ ስታነሳ ደግሞ እንደግስላ የሚሆኑ አንዳንድ ሀገራት አሉ። እኛን መዝረፍና የእኛን ብሔራዊ ጥቅም አለማክበር ተገቢ አይደለም። ከእኛ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፣ ለመስጠት ደግሞ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። ያን ማድረግ ላይ ተጨማሪ ሥራ መሥራት ይኖርብናል፤ ገና የሚቀሩ ቀዳዳዎች አሉ። እነሱ ቢደፈኑ ውጤቱ ከዚህ በላይ ያማረ ይሆናል። ሌላው ፍራንኮ ቫሉታ ቅድም እንዳነሳሁት እርማት ይፈልጋል፡፡ፍራንኮቫሉታ ዓላማውን ስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ሀብት ማሸሻ እየሆነ ስለሆነ ለሱ እርማት ማድረግ ያስፈልጋል።
ሌላው የተነሳው ቁልፍ ጉዳይ ግሽበት ነው። የዋጋ ግሽበት የኑሮ ውድነት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ፣አሜሪካን፣ አውሮፓን፣ ብዙ ሀገራትን የፈተነው ኢንፊሌሽን ነው። ደረጃው ቢለያይም ዓለምን የፈተነ ጉዳይ ነው። ይህን ኢንፊሌሽን ልንታገለው ልናስቀረው ከፍተኛ ሥራ ስንሥራ ቆይተናል። በተደጋጋሚ አንስቼዋለሁ።
ዓለም ላይ ያሉ የተዛቡ የንግድ ሥርዓቶች እና የምርት እጥረት ፍላጎትን መመለስ ባለመቻሉ ገበያው ተዛብቷል። ኢኮኖሚስቶች እንደዚህ አይነት ነገር ሲያጋጥም ኢንተረስት ሬት በማሳደግ ብር በመሰብሰብ ኢንፊሌሽን መቀነስ ይቻላል ብለው ያምናሉ። ይህ ባደጉት ሀገራት ይሠራ ይሆናል። ለእኛ ግን አይሠራም፤ ለኛ የሚሠራው ምርት ነው። ማምረት ነው ምርት በሌለበት ሁኔታ ብር ላይ ኢንተረስት ሬት ብንጨምር ብቻውን ኢንፊሌሽንን አይቀንስም። ምንም ሚና የለውም ማለት ግን አይደለም ሚና አለው። ዋናው ግን ምርት ማምረት ነው። ስንዴ ምን ያደርጋል፤ ስንዴ ጊዜው ነው ወይ፤ ስንዴ ለማኝ አይደላችሁም ወይ፤ እየተባልን በአፍሪካ አንደኛ ብቻ ሳይሆን በጣም ከፍተኛ ምርት ከሚያመርቱ ሀገራት ተርታ የገባነው። እናም ምርታማነትን ማሳደግ የግድ ሥርዓትን ማዘመን በጣም በጣም ወሳኝ ነው። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ እጅ አጠር ሰዎችን፣ በቂ ገቢ የሌላቸውን ሰዎች ማገዝ ያስፈልጋል። ዘንድሮ ሪፎርም ስንሰራ ከ300 እስከ 400 ቢሊዮን ብር ድጎማ ነው የደጎምነው።
አራት መቶ ቢሊዮን ብር ማለት በ2010 እና 2011 የኢትዮጵያ አጠቃላይ በጀት ማለት ነው። ይህን በጀት የሚያህል በሀብት ለድጎማ ነው ያዋልነው። ለምን እጅ አጠር ሰዎችን የሚጎዳ ሪፎርም እንዳይሆንና ኢንፊሌሽንን የሚያባብስ እንዳይሆን ነው። አራት መቶ ቢሊዮን ብር ለድጎማ ማስቀመጥ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር በቀላል የሚታይ እንዳልሆነ ማንም ሰው መገመት ይችላል።
እነዚህ ድጎማዎች የት ዋሉ ያላችሁ እንደሆነ አንደኛው ነዳጅ፤ ነዳጅ ባለፉት ሶስት ወራት 35 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ተደጎሟል። በሚቀጥለው ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል። የሚደጎመው ማነው ያላችሁ እንደሆነ አንደኛ ቤንዚን፣ በወር 85 ሚሊዮን ሌትር ቤንዚን እንጠቀማለን እያንዳንዱ ሊትር 25 ብርና ከዛ በላይ ይደጎማል። ናፍጣ 270 ሚሊዮን ሊትር በወር እያንዳንዱ ሊትር ናፍታ 25 ብር ይደጎማል። የአየር 75 ሚሊዮን ሊትር በወር እንጠቀማለን። ይህ ድጎማ የሚደረገው እጅ አጠር ሰዎች በትራንስፖርትና በገበያ ሥርዓት ምክንያት እንዳይጎዱ ለማለት ነው። የእኛን የነዳጅ ዋጋ ብዙ ሀገራት ብትሔዱ አታገኙም። እኛ ልክ ነዳጅ እንደሚያወጡ ሀገራት ነው ነዳጅ የምንሸጠው። ደሃው እንዳይጎዳ ደጎምን ማለት ነው።
ሴፍቲኔት 80 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ለዘይት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ተመድቧል፤ ለማዳበሪያ 53 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፤ ማዳበሪያ ካልደጎምን ምርታማነት አይቀጥልም። ግብርና ስድስት ነጥብ አንድ ማደግ የሚችለው በቂ ማዳበሪያ ደጉመን ማቅረብ ከቻልን ብቻ ነው። የተሳሰሩ ጉዳይ ነው ምርት ካለ ተመልሶ ገበያውን ያረጋጋል። ለመድኃኒት እንደሚታወቀው ለመንግሥት ሆስፒታሎችና መድኃኒት ቤቶች መድኃኒት በርካሽ ለማቅረብ 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ እናደርጋለን። ገበያው ተከፍቷልና በገበያ ዋጋ ግዙ ብለን የለቀቅነው ሳይሆን እጅ አጠር ሰዎችን መደጎም ባለብን ቁልፍ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ከምግብ፣ ከምርትና ከመድኃኒት ጋር በሚያያዝ አካባቢ ከፍተኛ ሀብት መድበናል፡፡
ደመወዝን በሚመለከት እውነት ነው ደመወዝ መጨመር እንዳለበት ተስማምተን ወስነናል። ነገር ግን እንደምታውቁት የደመወዝ ጭማሪው በፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚውል አይደለም። የክልል መንግሥታትንም መደገፍ ይፈልጋል። ከፍተኛ የሆነ የዳታ ችግር ነበረ። በትምህርት ሥርዓት ያለን ተማሪና ለተማሪ ቀለብ ተብሎ የሚጠየቀው ቁጥር አንድ አይደለም። ያን ዳታ ማጥራት ይፈልጋል። ካልጠራ የመንግሥትና ንብረትና ሀብት ባልተገባ መንገድ ስለሚፈስ፤ ያን ማጥራት ቀላል እንዳልሆነ እናንተ ገምቱት። ለምሳሌ የአንዳንድ ክልል ፖሊስ ደመወዝ መጨመር አለብን። እና የፖሊስ ቁጥር ተብሎ የሚነገረን ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ሚሊሻንም ጨምሮ አይሆንም። ሳናጣራ ዝም ብለን ብንሔድ በጣም በርካታ ሀብት ይወድማል። ያንን ሥራ ስንሠራ ቆይተናል። 91 ቢሊዮን ብር መድበናል። ከዚህ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪው ይደረጋል፡፡
እንደዚህ አይነት ሥራ ባይሠራ እናንተ የምትከታተሉት ሀብት ባልተገባ መንገድ የተሳሳተ ቦታ ይውላል። ያንን ጥንቃቄ አድርገን ካልፈጸምን በስተቀር በሌለን ሀብት ካባከንን ሪፎርሙን አናሳካውም። ለዛ ሲባል ጥንቃቄ የተወሰደባቸው ጉዳዮች አሉ። ይህ ብቻ ግን አይደለም። የትምህርት ቤት ምገባ አለ። እሁድ ገበያ ትጠቀማላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምንያህል ውጤት እንዳመጣ ታያላችሁ፤ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር እኮ ዘመን መለወጫና መስቀል መንግሥት እንደ አንድ ሥራው ይሠራል። ምርት ከአርሶ አደሩ ገዝቶ ከተማ ውስጥ ሽንኩርትና ዶሮ አምጥቶ ገበያውን ለማረጋጋት ልክ እንደመደበኛ ሥራው ይሠራል። ምክንያም ደሃው ባልተገባ መንገድ እንዳይመዘበር።
ማዕድ ማጋራት እኔ የናንተን አካባቢ አላቀውቅም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አካባቢ ማዕድ ማጋራት በጣም እየጠቀመ ነው ያለው። በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ እናጋራለን። በዚህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ይጠቀሙበታል። በብዙ መቶ ሺ ደሃ ይታገዝበታል። የመስጠት ባህል እያሳደገ መጥቷል። የማካፈልና የመክፈል ባህል እያሳደገ መጥቷል። ማዕድ ማጋራት ማደግ ያለበት ጉዳይ ቢሆንም እጅ አጠር ሰዎችን ደግፏል። በክረምት የአሮጊቶች፣ የሽማግሌዎችና የመበለቶችን ቤት እናድስ እንጠግን ያልነውን ጉዳይ እንዴት እንደምታዩት አላውቅም።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ደረጃ 249 ሺህ ቤት አዲስ ገንብተናል፤ ጠግነናል። በነፃ ለደሀ የተላለፈ። ለምሳሌ በት ፈርሷል የሚል አለ ትክክል ነው። በኋላ እመጣበታለሁ ግን 249 ሺህ ቤት፤ ሰው አንድ ብር ሳይከፍል ወይ አፍርሰን ሰርተን ወይም ጠግነን አስተላልፈናል። 249 ሺህ ቤትን በሶስት ሰው በአራት ሰው ቤተሰብ አባዙት። ኮንዶሚኒየም አደለም እኮ፤ ግዥ አይደለም የማወራው፤ ጥገና።
በእኛ እንኳን እዚህ አቧሬ የተሰራው እንዳያችሁት በሺህ የሚቆጠር ሰው የቤት ባለቤት ሆኗል። እንደ ቤተሰብ። ይሄ የመንግሥት እቅድ አካል አይደለም። ለምሳሌ ቅድም ሲጠየቅ ‹‹ገበታ ለሀገር ጥሩ ተሰርቷል። እኛም ጋር ይምጣ መንግሥት ምን አስቧል›› የመንግሥት ሀሳብ እኮ አይደለም፤ የመንግሥት በጀት አካል አይደለም። ገበታ ፕሮጀክት እናንተና የግል ሴክተር አግዞ የሚሠራው ሥራ ነው እንጂ የመንግሥት በጀት እቅድ አካል አይደለም። ጥሩ ጅማሮ ነው ይበርታ ትክክል ነው። መንግሥት ምን አስቧል ግን በመንግሥት እቅድ ውስጥ የለም። ምክንያቱም የመንግሥት እቅድ በናንተ ሪሶርስ ነው የሚወሰነው። በሰጣችሁት በጀት ነው የሚወሰነው ማለት ነው። ያስፈልጋል ካላችሁና ካገዛችሁስ፤ የግል ባለሀብት ቀስቅሰን፣ ክልል ቀስቅሰን በጋራ እንሠራዋለን ጠቃሚ ስለሆነ።
የደሀ ቤት፤ 249 ሺህ ሰው ቤት አግኝቷል ማለት እውነት ለመናገር በቂ ግብር አልተከፈለም፤ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በቂ ግብር አልከፈሉም ብለን በምንወቅሳቸው ልክ ደግነታቸውና ምስጋና የሚገባቸው ደግሞ 99 በመቶ ይሄን ቤት የገነባው የኢትዮጵያ ባለሀብት ነው። ለደሀ ቤት ሰርቶ መስጠት ልምምድ ያደረገ የግል ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ነው። ለዚህ ምስጋና ይገባቸዋል። የተከበረው ምክር ቤትም ቢያመሰግንልኝ እፈልጋለሁ።
ምክንያቱም በሚቀጥለው ዓመት ይቀጥላል። ለሠሩት ሥራ ካላመሰገንን በሚቀጥለው መጠየቅ አይቻልም። 249 ሺህ ሰው ቤት አግኝቷል የምላችሁ ባለፉት 15 ዓመታት አዲስ አበባ የተሰራው ኮንዶሚኒየም (ተሰርቶ የቆመውም ያላለቀውም ጨምሮ ) 300 ሺህ አይሞላም። እና እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ይሄ ሁሉ ሆኖ የዋጋ ግሽበት ምን ትሬንድ እያሳየ ነው ያላችሁ እንደሆነ እየቀነሰ ነው፤ እየጨመረ አይደለም። 2014 ዓ.ም 33 በመቶ ነበር ኢንፍሌሽኑ፤ 2015 ዓ.ም 32 በመቶ ነበር፤ አምና 26 በመቶ ነበር፤ ዘንድሮ 17 በመቶ ገብቷል። ይሄ ትልቅ እመርታ ነው፤ ግን ብዙ ሥራ ይፈልጋል። ይሄን ወደ ነጠላ ቁጥር ማውረድ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። ሰዎች ከሚያስገቡት በላይ ወጪ የሚጠይቃቸው ከሆነ ጉዳት ይኖረዋል። የተከበረው ምክር ቤት ግን አንድ ነገር እግረ መንገድ እንድትገነዘቡኝ እፈልጋለሁ።
አንድ ሰው የአንድ ሺህ ብር ደመወዝተኛ ዛሬ ኑሮ ውድ ሆነበት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። የዛሬ 6 ዓመት የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ኢትዮጵያ ውስጥ 37 ሚሊዮን ሰው ሞባይል ነበረው፤ ለምሳሌ በናንተ ቤተሰብ ውስጥ ወይ አባት፤ ቢበዛ አባትና እናት ነበረው። ዛሬ ሳፋሪ ኮምን ጨምሮ በሁለት ሶስት እጥፍ አድጓል ቁጥሩ ታውቃላችሁ፤ 80 ሚሊዮን ደርሷል ሞባይል የሚይዝ ሰው።
አንድ አባት አንድ ሺህ ብር እየበላ አንድ ሞባይል ቻርጅ የሚያደርግ ከነበር የሚከፍለው ኢነርጂ እና ቤት ውስጥ አራት ሞባይል ሲፈጠር የሚከፍለው ኢነርጂ አንድ አይደለም። አንድ ስልክ ሲም ካርድ ሲገዛና ካርድ ሲገዛ አሁን ፌስቡክና ቲውተር ሳያይ የማይውሉ ልጆች ባሉበት ዘመን ለቴሌኮም ዳታ የሚከፍል ከሆነ ከዚያ ሺህ ብር ምን ያክል ኮስት እንደሚያወጣ አስቡት ። ልማታዊ ካልሆነ ማለት ነው።
እራሱ እድገቱ፤ እራሱ ዘመናዊነቱ የሚጨምርብን አዳዲስ ነገር አለ። እሱን እንዘነጋለን፤ ሞባይል እንፈልጋለን፣ ደመወዝ አልጨመረም፣ ገቢ አልጨመረም ሞባይል ስንፈልግ ተጨማሪ ወጪ መሆኑን ማሰብ አለብን። ከድሮው ሽንኩርት ይሻማል ማለት ነው ኢንተርኔት፤ ሽንኩርትን አብዝተህ ትጠላለህ እያሉ ትንሽ እየወቀሱኝ ነው። ሽንኩርት አስፈላጊ ነገር ነው፤ በመጠኑ እንዲሆን ብቻ ነው። እና እንደዚህ አይነት እድገቶች ተጨማሪ በሰው ላይ ጫና ይፈጥራሉ። ልጆቻችን ስልክ ብቻ አይደለም የሚፈልጉት እንደምታውቁት፤ ስማርት ስልክ ይላሉ። ጫናውን ታውቁታላችሁ በየቤቱ ያለውን በዚያ ምክንያት ወላጆች ተጨማሪ ኮስት ተጨማሪ ገንዘብ፤ ለአዳዲስ ሴክተር ለማውጣት ይገደዳሉ። ያም ሆኖ ምርት አሳድገን፣ ንግድ ሥርዓት አዘምነን ለደሀ የማካፈል ልምምዳችንን አስፋፍተን፣ ሕገወጥነት ቀንሰን single digit ማውረድ ይጠበቅብናል፤ ያ ካልሆነ እድገትም ቢኖር ጉዳቱ ቀላል አይደለም።
ድሀ ይጎዳል፤ እኔም ብዙ ድሀዎች ስለማገኝ ችግሩን በደንብ እገነዘባለሁ ። የተከበረው ምክርቤት ብልጽግና ድሀን ይወዳል፤ ለድሀ ይራራል ፤ድህነትን ግን በጣም ይጠላል። አይቀላቀልብን ድህነት እና ድሀን ለይተን ማየት አለብን እና ድህነትን ስለምንጠላ እንበቀለዋለን፤ አሰቃይቶናል። ድሀን ብቻ ነው ምንወደው ምናዝነው ምንራራው ምናካፍለው፤ አንዳንድ ሰው ድህነትን እና ድሀን ይቀላቅል እና የፈረሰ ቤት ለምን ፈረሰ ይላል ፤ አሁን አዋሬ ፈረሰ ይባላል። ፈርሷል እኮ ላስቲክ ቤት እሱ ድህነት ነው እንበቀለዋለን ፤ ድሀን ግን እናግዛለን፣ እንደግፋለን ፣ እንራራለን ፣ እንወዳለን፣ እናቅፋለን ለምን? ድሀ የሆኑ ሰዎች ባለጸጋ መሆን ይችላሉ። ድህነትን አብዝተን ጠልተን ከተበቀልነው ድህነት እና ድሀ ከተቀላቀለብን ግን ብልጽግናን ማረጋገጥ ያስቸግራል።
ኢንፍሌሽንን በሚመለከት እምርታው በጣም ተስፋ ሰጪ ነው። ሰፊ ሥራ ይጠበቅብናል እንዳንዘናጋ አብዝተን ሰርተን ከዚህ በታች ማውረድ አለብን። ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ራሱ ፈተና ነው ሰፊ ሥራ ሠርተን ውጤት እንደምናመጣ ይጠበቃል፡፡
በኢኮኖሚው ዙርያ መጨረሻ የተነሳው የሥራ እድል ነው። የሥራ እድል አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚለው ብዙ ባይሆንም ለተባለው በጣም ብዙ ነው በጣም በጣም ብዙ ነው ። በወር 350 ሺህ ሰው ሥራ ማስያዝ አለብን። አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ማለት እኮ አፍሪካ ውስጥ አስር ገደማ የሚያክሉ ሀገራት ይሄን የሚያክል ቁጥር የላቸውም። በጣም ትልቅ እቅድ ነው ፡፡
ተቋሙ እየጠነከረ ስለመጣ ሴክተሮች እየነካካን ስለሆነ የልማት እንቅስቃሴው ስለሚፋጠን እናሳካዋለን ብለን አቀድን እንጂ ቀላል እቅድ አይደለም። ይሄ የሚሳካው በግብርና 39 በመቶ እናሳካለን ብለን አስበናል፤ ምክንያቱም ግብርና እያደገ ስለሆነ የሥራ እድልም በዛው አብሮ ስለሚያድግ አገልግሎት 31 በመቶ የሥራ እድል ሼር ይኖረዋል። ቅድም እንዳነሳሁት ራሱ እዛ ውስጥ እያደገ ስለሆነ ራሱ እድገት ያመጣል ፤ ኢንዱስትሪ 29 በመቶ እድገት ያመጣል ቅድም እነዳነሳሁት አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ እየጀመሩ ስለሆነ በርከት ያለ ሰው እንደሚቀጠር ተስፋ ይደረጋል ።
በዚህ ዓመት ለውጭ ሥራ ስምሪት ያቀድነው 700 ሺህ ሰው ነው። ባለፈው ዓመት 100 ሺህ የሰለጠነ ሰው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ልከናል ። 100 ሺህ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነው። ይሄን ካጠናከርን 700 ሺህ ሰው ይሳካል። ሁለተኛው በጣም ተስፋ ሰጪ እና አስደሳች የሥራ መስክ ነው። በአውትሶርሲንግ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እዚህ ሀገር ውስጥ ሆነው ለሕንድ፣ ለእንግሊዝ፣ ለአሜሪካ እዚህ ሆነው ይሠራሉ። ባለፉት ጥቂት ወራት 26 ሺህ ሰው ነው ሥራ የያዘው። ወጣቶች እዚህ ሆነው ሥራ የሚሠሩ ለምሳሌ አውሮፓ ላይ ያለው የኳስ ጨዋታ አርሴናል ማንችስተር የሚባለው አናላይሲስ የሚሠራ ቡድን አለ። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኳስ አንችልም እንጂ አናላይሲስ እንችላለን ማለት ነው። ኮዲንግ የሶፍትዌር ኮዲንግ ለህንድ በርካታ ኩባንያ እዚህ የሚጽፉ ልጆች አሉ። እዚህ ጽፈው ይልካሉ ዶላራቸው ይላክላቸዋል ፤ 26 ሺህ ሰው ነው ሥራ ያገኘው በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ ኤሪያ እሱ ነው ። 50 በመቶ ሴቶች 50 በመቶ ወንዶች ሥራ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ፡፡
እዚህ ጋር ሁለት ቁልፍ ነገር አብረን ብናይ ነው ጥሩ የሚሆነው። ተቋሙ እየዘመነ በሪፎርም ራሱን እያጠናከረ ከመጣ በኋላ ያሳካው አንድ ነገር ሥራ መቅጠር ብቻ ሳይሆን የሰለጠኑ ሰዎች ነው ወደ ውጭ ሀገር የሚልከው፤ ሁለተኛ የሚልከው ሚድል ኢስት ብቻ ሳይሆን አውሮፓ መላክ ጀምሯል። ነርሶች እንልካለን አሰልጥነን የሰለጠኑ በመሆናቸው ገቢያቸው ያደገ ደህንነታቸው የጠነከረ ይሆናል። ለኛም የተከበረ የሥራ መስክ ዜጎቻችን እንዲሳተፉ ያደርጋል ። በከተማ እና በገጠር ኮሪደር በጣም በርካታ ሰው ሥራ ያገኛል። መቼም የተከበረው ምክር ቤት አዲስ አበባ ማታ ማታ ስትንቀሳቀሱ ታያላችሁ በፓውዛ ማታ ማታ ማሽን ማንቀሳቀስ አዲስ ፋሽን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ይሄ ፋሽን ግን አድጓል አሁን ጎንደር ገብቷል፤ ባህርዳር ገብቷል ፣ ጅማ ገብቷል አዲስ አበባ ብቻ አይደለም በምሽት መስራት ሌሎች ከተሞችም እያደገ መጥቷል፡፡
ሰዎች ቀን ይሠራሉ ፤ማታ ይሠራሉ፤ መሰረተ ልማት ይገነባሉ፤ ቤቶች ይገነባሉ እዛ ውስጥ ሥራ ያገኛሉ። ሥራ ማስፋት ሰላማችንን ማረጋገጥ ስለሆነ ሥራ ማስፋት ማንሰራራት ላሰብነው ጉዳይ እውን የሚያደርግ ስለሆነ ሥራን ማሳካት ሰዎች በኑሮ ችግር እንዳይቀፈደዱ እንዳይቸገሩ የሚያግዝ ስለሆነ ሥራን ማብዛት ለማኝነት የሚቀንስ ስለሆነ ሥራን መፍጠር ላይ አብዝተን መሥራት ዋናው ተልዕኳችን ነው። ውጤቱ አበረታች ነው፤ ተባብረን የሥራ መስኩን ብናጠናክር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ በእጅጉ የሚያግዝ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ።
ቀደም ሲል በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጊዜ ወስደን ስላየን አሁን በሠላም እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ መጠነኛ ማብራሪያ እሰጣለሁ፡፡
ሠላምን በሚመለከት ሠላምን አስታኮ ለተነሳው ጥያቄ ያለው መሻት፣ ሠላም እንዲኖር ያለው ፍላጎት በጣም ትክክል ነው። ሠላም በጣም ወሳኝ መሠረት ስለሆነ ነው ሁላችንም የምናስበው
የተከበራችሁ አባላትም በዚሁ መንገድ ማንሳታችሁ ተገቢ ነው። እንግዲህ ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት፣ ሰው የሚያመዛዝን ፍጡር ነው። ከፍጥረታት የሚለየው ነገር አመዛዝኖ በዝቅተኛ ወጪ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ነገሮችን ይመርጣል ተብሎ ይታሰባል። ከሚያገኘው ጥቅም የማይስተካከል ከፍተኛ ወጪን አይመርጥም፡፡
ለምሳሌ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከመሞት፣ ከመግደል፣ በሠላማዊ መንገድ መታገል ጊዜም ቢወስድ ውጤቱ የተሻለ ስለሆነ ሰው እንደዚያ አመዛዝኖ ይመርጣል። ከኃይል ይልቅ ሠላም በእጅጉ አዋጭ መንገድ ነው። ኃይል የግልፍተኝነት ስሜት ስላለበት ያልተገባ ጉዳት ያመጣል። መሣሪያ ሲያዝ ብቻም አይደለም ከመሣሪያው ውጪ ቤት ውስጥ ኃይል ሲቀላቀል ያለው ግንኙነትና ከኃይል ውጪ ያለው አንድ አይደለም። እናም ሁሌም ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሠላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛና ተመራጭ ነው፡፡
ነገር ግን በሠላም መኖር በአነስተኛ ኢንቨስትመንት የተሻለ ነገር ማምጣት ተመራጭ የሆነባቸው ሰዎች ከባቢዎች ስብስቦች ቢኖሩም አልፎ አልፎ ያንን አማራጭ የማይመርጡ ሰዎች ደግሞ አሉ። መቶ ፐርሰንት ሰው አመዛዛኝ ስለሆነ ሁሉም ሠላም ይሻል ሠላም ይፈልጋል ማለት አይደለም፡፡
ለዚያ ነው መንግሥታት በዓለም ላይ ለዜጎች መኖሪያ ቤት ይገነባሉ። ማረሚያ ቤትም ይገነባሉ። ምክንያቱም መኖሪያ ቤት መገንባት ብቻውን ሠላም አያረጋግጥም። ሠላም ለልማት ለሥራ መፍጠር በጣም አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ ማረሚያ ቤት መገንባትም ያስፈልጋል። ለዚህ ነው ያደጉትም ሀገራት ጭምር የሚገነቡት። እኛ 249 ሺ የደሃ ቤት ገነባን ባልኳችሁ ቁጥር አብዛኛው መኖሪያ ቤት አብዛኛው የንግድ ቦታ አብዛኛው ለውጥ የሚያመጣ ትንሽም ቢሆን ማረሚያ ቤት ደግሞ ያስፈልጋል። ይህን ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ሰው ሁሉ ሠላም ይፈልጋል። ሰው ሁሉ ለሠላም ይሠራል ብሎ በጥቅሉ መመልከት ያስቸግራል፡፡
ባለፉት ዓመታት ያለው ልምድ የሚያሳየው እንደዛ ነው። እኛ ከምንም በላይ ሠላም እንፈልጋለን። በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት በጣም በልጅነት ወራት ክላሽ ተሸክመን ስለኖርን ክላሽ መሸከም ምን ያህል ጉዳት እንዳለው ይገባናል። ጦርነትን እናውቀዋለን። በወሬ አይደለም በተግባር እናውቀዋለን እና አንፈልገውም። ብዙዎችን ቀጥፎብናል፤ አንፈልገውም። ሁለተኛ ሕልም አለን። በዚህ ሀገር ላይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን። ያንን ለማድረግ ደግሞ ሠላም በእጅጉ ያስፈልጋል። ሠላም በተሟላ ሁኔታ ማረጋገጥ ካልተቻለ የምናስበውን እድገት ማምጣት እንቸገራለን። ሠላም የምንመኘውም የምንፈልገው ጉዳይ እንደሆነ በሁላችሁም ከግምት ቢገባ ጥሩ ነው፡፡
ለምሳሌ የሠላም አማራጭ አትመርጡም ወይ በግልጽ አታውጁም ወይ ለተባለው በተደጋጋሚ ማወጃችን እናንተም ሕዝቡም ያውቀዋል። አገር ሽማግሌዎች ልከን በእንብርክክ መመለሳቸውንም እናንተም እኛም እናውቃለን። ግን አሁንም ለምሳሌ እርሶ በሠላም በኩል እኛና የሚቃወሙትን ሰዎች ማቀራረብ ከቻሉ በሩ ክፍት ነው። እኛ የምንፈልገው ሠላም ስለሆነ አነጋግረው ቢያመጧቸው ደስ ይለናል፡፡
ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁት የተከበረው ምክር ቤት ማወቅ ያለበት ጉዳይ በአማራና በኦሮሚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር አለን። ንግግር የሌለ እንዳይመስላችሁ። ግን ንግግር የሚያደርጉና ሠላም የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት ትነጋገራለህ ከዚህ መንግሥት ጋር ብለው የሚወቅሱ ሰዎች ደግሞ አሉ። እዚህም እዛም አሉ፡፡
እና እነዛ ሠላም ፈላጊዎቹ ትንሽ ደበቅ ይላሉ። እንጂ ንግግር የለም ማለት አይደለም። መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ንግግርም ጀምረናል። ግን ለቀረውስ እርሶም ያግዙን። እኛ የምንፈልገው ሠላም ነው የምንፈልገው። አንድ ወንድም ገድለን ምን እናገኛለን። በዚያ መንገድ ማንም እንደማያሸንፈን እናውቃለን። ማንም ስጋት ኖሮብን አይደለም። ግን ምን ያደርግልናል። እኛ ብንገዳደል ምን ፋይዳ አለው። አይጠቅምም እናም የሚያስፈልገው ሠላም ነው፡፡
ይህ ግን እርሶም እንደሚገነዘቡት ብዙዎቻችሁም እንደምታውቁት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ጥሩ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት ፓርቲ የሚባል እሳቤ የተዋወቅንበት፣ ርዕዮተ ዓለም የሚባል ንትርክ የጀመርንበት፣ ድጋፍም ይሁን ሠላማዊ ሰልፍ የጀመርንበት፣ የፖለቲካ ንትርክ በህቡዕ መደራጀት፣ ፖለቲካል ኢንትሪክ፣ የውሸት ፕሮፖጋንዳ፣ ማጠልሸት በስፋት የተማርንባቸው ዘመናት ናቸው፡፡
ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሽፍታ ነበረ። ሽፍታን በአዲስ መንገድ ስሙን አሻሽለን የትጥቅ ትግል ብለን ደግሞ ከጀመርነው አንድ 50ና 60 ዓመት ይሆነናል። ጥቂት ሽፍቶች በተሰባሰበ ሽፍታ ታጋዮች ተብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 60ና 70 ዓመታት ከየቦታው ከየአቅጣጫው አለ። ይህ ጉዳይ በብዙ መንገድ ጉዳት አምጥቷል። አንደኛው ጉዳት መነሻው የሚያደርገው ኃይል በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ ይላል። ሁለተኛ ፍረጃ ይፈርጃል የፈለገውን ሰው ስም እያወጣ ነው የሚውለው። ሦስተኛ ጥላቻ የሚታገለው ሀገር ለማስተካከል፤ የሚታገለው መንግሥት ለመሆን አይመስልም። በጣም ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት አለ። ይህ አይጠቅምም። ጥላቻና ኃይል ለማንም አይፈይድም። በተግባር ደግሞ አየነው። ፓርቲዎች እኮ ዓይንና ናጫ ሆነው ተጠፋፍተዋል ኢትዮጵያ ውስጥ። የአንድ ትምህርት ቤት ተማሪ፤ የአንድ ቤተሰብ ልጆች ፤ የአንድ ጎረቤት ልጆች፤ የዚህና የዛኛው ፓርቲ ነን ብለው ተጠፋፍተዋል። በእንትን መቃብር ላይ እንትን እንገነባለን፤ ኤክስ ካልሞተና መቃብሩ ካልተሠራ በስተቀር ዋይ አይገነባም ብሎ የሚያስብ በጣም ዳይኮትሚ ላይ ቤዝ ያደረገ ፖለቲካ 50፣ 60 ዓመት አካባቢ ሂደናል። ኪሳራ ነው፤ ጥቅም የለውም። ይሄ ነገር ጥቅም የለውም ሲባል፣ የተከበረው ምክር ቤት በአንክሮ እንዲገነዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ብቻ አይደለም ለዓለም ጥቅም የለውም። ማኦ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሊቀመንበርና የቻይና ከነፃነት በኋላ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆነው ሰው፤ በጣም ሲበዛ ጀግና ሰው ነው። የቻይና ሠራዊት /army/ ተዳክሞ፣ ፈርሶ ሊፈጣ በደረሰበት ጊዜ ያንን ሠራዊት /army/ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ለቀናት ለወራት በእግር ተጉዞ እንዲሄድ አድርጎ፤ መልሶ አደራጅቶ ኮሚንታንግ የተባለውን መንግሥት አሸንፎ በ1949 ቻይናን፣ ከኮሚንታንግ ነፃ ያወጣና ባለፉት 75 ዓመታት አምስት ገደማ መሪዎች ተቀያይረው፤ ከድህነት፣ ከችግር ቻይናን ከፍተኛ ሀብት ያላት ሀገር ያደረገው የመጀመሪያው ሰው ነው።
ማኦ በጀግንነቱ በትግሉ ኮሚንታንግን አሸንፎ ቻይናን ነፃ ያውጣ እንጂ፤ የቻይናን ኢኮኖሚ ማሳደግ ግን አልቻለም። መቀየር አልቻለም። በኛ በአፍሪካ ውስጥ የታንዛኒያው ኔሬሪ በጣም ጀንትል ሰው ነው። ታሪኩን ስታገላብጡ በጣም ጨዋና ጀንትል ሰው ነው። የታንዛኒያን ሕዝብ ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፤ አሸንፏል። የታንዛኒያን ኢኮኖሚ ግን መፍታት አልቻለም። የዛምቢያው ኬኔት ካውንዳ በጣም ተመስጋኝ ነው አፍሪካ ውስጥ። የነፃነት ታጋይ ነው። አሸንፏል፣ ነፃ አውጥቷል። የዛምቢያን ኢኮኖሚ ግን መቀየር አልቻለም።
እንደዚህ በሽፍትነት፣ በትጥቅ የሚመጡ ሰዎች የሀገር ኢኮኖሚ ስታክ እንዲያደርግ ያደርጋሉ። የኛንም ልምድ መውሰድ ትችላላችሁ። ዓለም ላይ ያለው ልምድ በጦርነት አሸንፈናል የሚለው ኃይል፤ በሪፎርም የሀገር ኢኮኖሚ ሲያንሰራራ አይታይም። ለምን ሁሌ በኃይል ይመስለዋል። ሽፍትነት በውጊያ ጊዜ ያግዛል፣ ኢኮኖሚ ግን ጥበብ ይፈልጋል። ሽፍትነት አይፈልግም።
በዚያ መንገድ የመጡ መንግሥታት የትም ቦታ ብትዞሩ ሬር ነው። ከነፃነት በኋላ ኢኮኖሚ ገንብተው፣ ድህነት ቀንሰው አይታዩም። ከዛ ውጭ የመጡት ሳ እነ ሊን ብትወስዱ የሲንጋፖሩ፣ ኮሪያ ብትሄዱ ከሽፍትነት ውጭ የመጡ ሀገር ሲቀይሩ ይታያል። እና በጥቅልም ጥቅም የለውም፣ አሁን ባለው ልምምድም ጥቅም የለውም እና ቢቀር። ወደ ሠላማዊ ትግል፣ ወደ ንግግር፣ ወደ ሃሳብ ቢመጣ ጥሩ ነው። ይህ ስብራት ኢትዮጵያን ጎድቷል። በሄድንበት ሀገር ሁሉ የሚገባን ነገር፤ ምን ያህል ኋላ ቀሮች እንደሆንን ነው። እናንተም ትታዘባላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እኔ በሄድሁበት ሁሉ ታምሜ ነው የምመለሰው። አንዳንድ ጊዜ የማይቻል ቢሆንም፤ 60፣ 70 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ በኮምፒዩተር ቢሆን ተቆርጦ ቢጠፋ ከውስጥ ብዬ አስባለሁ።
አላስፈላጊ መባላት ብቻ። ከሰው ሁሉ ኋላ ያስቀረ ዘመን ነው። ምንም እንትና ከንትና የሚባል የለውም፤ ያው ነው ሁሉም። ስንዴ እንድናመርት፣ ኢኮኖሚ እንዲያድግ፣ ድህነት እንዲቀር አላገዝንም። አሁንም አይጠቅመንም። ከየትኛውም ጫፍ ይምጣ አይጠቅመንም። በዚህ ምክንያት ሠላም በእጅጉ ያስፈልገናል። በምክንያት የሚያስብ፣ ስሜትን ረገብ ያደረገ የፖለቲካ ሂደት፤ ሀሳብ አልቦ ትግል ምንም ፍሬ የለውም።
ተመልከቱ ኦነግን 50 ዓመት፤ 50 ዓመት በኦነግ ትግል የኦሮሞ ሕዝብ ምን ጥቅም አገኘ? ቁጭ ብሎ መገምገም ያስፈልጋል። ድካም፣ ድካም ነው። በሌሎችም ፓርቲዎች። ሰክኖ ሰው ሳይሞት፣ ንብረት ሳይወድም በንግግር በሃሳብ እየተወዳደሩ የሚኬድበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። እኛ ለዛ ብለን ነው እንደመጣን ኑ ብለን ሁሉንም ጠርተን አብረን እንሥራ ያልነው። አሁንም ምርጫችን እሱ ነው። ለምን? ኢትዮጵያ ማደግ አለባት፣ ኢትዮጵያ መበልፀግ አለባት፣ ኢትዮጵያ መቀየር አለባት፣ ልጆቻችን መልሰው ድሃ ሀገር መውረስ የለባቸውም። ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ በዚያ እሳቤ ውስጥ ቢሠራ መልካም ነው። የተነሳው ጥያቄ ከቅንነትና ከሠላም ፍለጋ ስለሆነ አብዛኛውን በዚያ መንፈስ ነው መውሰድ የምፈልገው ጥቂት ጉዳዮች ብቻ ነው ማረም የምፈልገው።
አንደኛ “በሁለት ወር እንቆጣጠራለን ብላችሁ ገብታችሁ” የተባለው ምን እንቆጣጠራለን እኛ እኮ ክልሉን በሕጋዊ መንገድ በምርጫ ያሸነፍንበት ክልል ነው። ምንድነው የምንቆጣጠረው? ከማነው የምንቆጣጠረው? በአንፃሩ ያልተሳካው በሁለት ሳምንት ይሄን አረፋ መንግሥት አባርሬ አራት ኪሎ የአባቶቼን ርስት እወርሳለሁ ያለው አልተሳካለትም እንጂ፤ አማራ ክልል ክልላችን ነው፤ የአማራ ሕዝብ ሕዝባችን ነው። ምንም የምንቆጣጠረው የለም፣ አብረን ነው የኖርነው፣ አብረን ነው የታገልነው፣ አብረን እንኖራለን። እንደዛ አይነት ሁለት ወር፣ ሦስት ወር የሚባል እቅድ ከኛ ሳይሆን እኛን በቀላሉ ገፍትረው ካሰቡት ሰዎች ዘንዳ የነበረ ነው፤ ቦታውን አሳስተው ከሆነ አድራሻውን ብቻ እንዲያስተካክሉ ለማለት ነው። የእርሶ ሀሳብ አብዛኛው የሚያጠነጥነው ሠላም፣ ልማት፣ አንድ እንሁን ነው፤ እሱን መቶ በመቶ ከእርስዎ ጋር ነኝ፤ ለውጥ የለውም።
ሁለተኛው ቢታረም ብዬ የማስበው የአማራ ክልል ባለፈው ዓመታት ሥር ጉዳት፣ ችግር፣ … ያው እንደሰሙት ነው። የቁጫም ችግር ምናምን ነው። የኦሮሞም ሲጠየቅ ችግር ምናምን ነው። ይሄ በቃ የሰፈሩን ብቻ የሚያስብ ኃይል ሁልጊዜ እንደዛ ነው። የራሱን ብቻ ነው የሚያየው። ለምሳሌ እርሶ አማራ ክልል እስረኛ አሉ። ከዛ ደግሞ አንድ ወንድሜ አርባ ምንጭ እስረኛ አሉ። ወለጋም ብንቀጥል እንደዛ ነው ባሕሪው።
ይሁንና እኔ አማራ ክልል ያለኝ ልምምድ ያለፉት ስድስት ዓመታት፤ አማራ ክልልን የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል። ይሄን የማያምን በቁጥር ኮምቦልቻ ሂዶ ይቁጠር። ደብረ ብርሃን ይቁጠር። ባሕር ዳር ይቁጠር፤ ኢቨን ቡሬ ይቁጠር። ጨርቃጨርቅ፣ ሲሚንቶ፣ ማርብል፣ ግራናይት፣ በጣም ብዙ ፋብሪካዎች፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አማራ ክልል አቋቁመናል። የዘይት ፋብሪካዎች ብዙ ብር አግዘን አቋቁመናል። አማራ ክልል የብልፅግና መንግሥት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም ዘመን አግኝቶ አያውቅም። በወሬና በምናምን ስለተደባበቀ እንዳትሸወዱ እውነታው እርሱ ነው። ሁለተኛ መንገድ በመንገድ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነበረ በአማራ ክልል። ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። እንግዲህ ሁሉ ተሟልቷል ብዬ ባላስብም ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ለምሳሌ ባሕርዳር እርሶ እንደሚያውቁት እኛን አልመረጠንም፤ ልክ እንደ ቁጫ፣ ሠላም በር ግን በሥራ ማሳየት ስላለብን በኢትዮጵያ ሠርተን የማናውቀውን ድልድይ የሠራነው ባሕርዳር ነው። 30 ኪሎ ሜትር ገደማ መንገድ የምንሠራው ባህርዳር ከተማ ነው። የኮሪደር ልማት የምናለማው ባሕርዳር ከተማ ነው። ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሠራነው ባሕርዳር ከተማ ነው። ለምን ሕዝባችን ያ ሰርቪስ ይገባዋል ብለን ስለምናምን። እርሶ ይገነዘባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አሁን እኮ ጎንደር ቢሄዱ ያ ስልጡን ሕዝብና ሀገር ከሰባ፣ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ዘወር ብሎ የሚያየው መንግሥት ያገኘው እኮ አሁን ነው ። ፋሲል እኮ ቀንና ማታ ይገነባል ከፋሲል ቀጥሎ ያለው አብዮት አደባባይ አዲስ አበባ ያለው መስቀል አደባባይን በሚያክል መንገድ እየተገነባ ነው ያለው፤ ፒያሳ እኮ እያሸበረቀ ነው ያለው። ጎንደር እውነተኛ ቦታዋን እየያዘች ነው ። መገጭ 18 ዓመት ከቆመ በኋላ ሰባት ቢሊዮን ብር መድበን ቀንና ማታ እየሠራን ነው። እንደምታውቁት ሐይቅ ዘመናችንን በሙሉ የነበረ ነው። አሁን እኮ ነው በገበታ ለትውልድ እየሠራን ያለነው። ጎርጎራን ሠርተን አሳይተናል።
አማራ ክልል ላይ እኛ ልማት ነው እያመጣን ያለነው። ልማቱን እንደ ልባችን እንዳንሠራ ያደናቀፉን ሰዎች ግን አሉ። እሱን እርሶ ያግዙን። ይመለሱ አብረን እናልማ። እዛ የሚፈሰው ጥይት ድካም ተሰብስቦ በጣም ብዙ ቁምነገር ሊሠራ ይችላል። ለምሳሌ እርሻን በሚመለከት እርሶ እንደሚያውቁት ከፈለጉም ዳታ ቼክ ያድርጉ ዘንድሮ ባለፈው ክረምት አማራ ክልል ያሰራጨነው ማዳበሪያ ብዛት ከጥቂት ዓመታት በፊት ካለው በእጥፍ ይበልጣል። በዚህ ልክ ማዳበሪያ ተሰራጭቶ አያውቅም ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልማት ፋሲል ግንብን ማዳበሪያ በየቀበሌ ማድረስን በወታደር እያጀበ የሚሠራ መንግሥት እኮ ነው እንዴት አሳሪ መንግሥት ይባላል። ልማት በወታደር ጠብቆ የሚያሠራ ተቀናቃኝ የሚባለው ደግሞ ልማት የሚያደናቅፍ ፤ ተማሪን የሚያደናቅፍ ይሄንን የአማራ ሕዝብ በደንብ ይገነዘባል፤ ያስተውላል።
ሕዝቡን የእርሶን ያህል ብዬ ባልዳፈርም አውቀዋለሁ አስተዋይ ሕዝብ ነው። ማን እንደሚሠራለት ማን እንደሚያወራለት ያውቃል። ይሄ ይጠፋዋል ብዬ አላምንም። ይልቁንስ ደብረማርቆስ ኮሪደር ጀምረን ትንሽ ማሸብረቅ ጀምራለች ከተማዋ ፤ ግን የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተመንግሥት ጊቢ ገና ሥራ አልጀመረም። ምናለ እርሶ ፓርቲዎን አስተባብረው፣ ባለሀብት አስተባብረው ያንን ቤተመንግሥት ቢያድሱልን። እርሶ እንደሚያውቁት የጮቄ ተራራ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃምን ያገናኛል ። በጣም የሚያምር ተራራ ነው። የውሃ ታንከር ይባላል። የጮቄ ተራራ ለጎጃም ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር እጅግ የውብ ቦታ ነው። ምናለ እሱን አስተባብረው ሀይኪንግ ቢሠሩ እና ቱሪስት ቢስቡልን። ካልሠሩ እኛ ስንሠራ እንዳይቀደሙ ብዬ ነው። እዛ ጋር ብንተባበር ጥሩ ነው።
ሠላሙን እርሶም ሞክረው ጓደኞቻችሁም ሞክረው ቢመጡ፤ ቢመለሱ። ልማቱን ደግሞ እኛ ለምነን ነው የምንሠራው። አዋሬ የገነባነው ለምነን ነው፤ ገበታ ለትውልድ የገነባነው ለምነን ነው። እርሶም ለምነው ተባብረን አማራን ወደ ልማት ብናስገባው አይሻልም ወይ። እኛም ወጪ በዛብን። ጎርጎራን በወታደር ጠብቀን ሠርተን፤ አሁን ፒያሳን የምናድሰው ከኩሃሪ ሲሚንቶ በወታደር ጠብቀን። ከማን ከየትኛው ወራሪ ነው የምንጠብቀው። ጎንደር እንዳይለማ ባሕርዳር እንዳይለማ ወሎ እንዳይለማ የሚያደርገው የዛው ሰፈር ሰው ነው። ይሄ ቢቀር ጠቃሚ ስለሚሆን በዚያ ብንተባበርና አብረን ብንሠራ ጥሩ ይመስለኛል። እኛ የምንፈልገው እሱን ነው። አማራ ካልለማ፣ አማራ ካልተቀየረ ኢትዮጵያ አትቀየርም። እኛ ሞኞች አይደለንም አማራን በኢትዮጵያ ብልፅግና ውስጥ ያለውን ሚና አቅለን የምናይ ሰዎች አይደለንም። አማራ ካልተቀየረ ኢትዮጵያ አትቀየርም። አማራ እንዲቀየር አግዙን። ተጋግዘን እንሥራ። እኛ እየሞከርን ነው። መንገድ እያረስን ነው፤ እርሻ እያስፋፋን ነው፤ እየሞከርን ነው። የሚያደናቅፉን ሰዎች የልማቱን ጊዜ እንዳያራዝሙብን ግን ብንተጋገዝ አይሻልም ወይ።
ጋዜጠኛ፣ የማኅበረሰብ አንቂ … ባሉት ጉዳይ አንድ እግር በሲኦል አንድ እግር በገነት አድርጎ መቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም። ወይም የገነትን ፍሬ መብላት ነው ወይም ደግሞ የሲኦልን እሳት መቅመስ ነው። አንዳንድ ሰዎች እዚህም ሠላም ውስጥ አሉ እዚያም ጦርነት ውስጥ አሉ። ያን ያህል የመረጃ ችግር ያለብን እንዳይመስላችሁ። በጅምላ የፓርላማ አባላት፣ በጅምላ የፖለቲካ ሰዎች የምናስር ከሆነ እርሶንም እናስር ነበረ። ሰው የሚታሰረው በጅምላ አይደለም። በግብር ነው ሰው የሚታሰረው። ያም ቢሆን ግን የግል ምርጫዬን ከጠየቁኝ ቢቀር ነው።
ይቅር ተባብለን፣ ትተን በደለኛም ካለ ክሰን በሠላም ሀገራችንን ብናለማ ነው። ከዚህም ይምጣ፣ ከዩኒቨርሲቲም ይምጣ ከከተማ እስር አይጠቅመንም። በዛ አናምንም ግን መንግሥት ነን። መኖሪያ ቤት እንገነባለን ማረሚያ ቤትም እንገነባለን። ዝም ብለን በመኖሪያ ቤት ብቻ ሀገር ይቀየራል ብለን በሞኛሞኝ መንገድ አናስብም።
አሁን ደግሞ ይናገሩ ያውጁ ባሉት ግን ሁሌ በራችን ክፍት ነው ሞክረናል። የአማራ ክልል ሰዎች አነጋግረን ሽማግሌ ጠይቀን ልከን፤ በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢጋድም ሙከራዎች ይደረጋል። እርሶ ይህን ቢያደርጉ በደስታ፤ በደስታ እንቀበላለን። ሁሌም ሠላምን ነው እኛ የምንፈልገው። በዚያ ቢቀጥል ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው።
ፓርቲዎችን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ውይይቶች ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል። በባለፈው ዓመት ሁለቴ አግኝቼያቸዋለሁ። የኛ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ አግኝተዋቸዋል። በክልል ደረጃ ውይይት ተካሂዷል። ካልበቃ ደግሞ እንጨምራለን። ተሳስተን ተላልፈን የፈጸምነው ስህተት ካለም ደግሞ እናርማለን። እኛ ብፁዓን ነን አንሳሳትም ብለን አንመፃደቅም። ኢንቴንሽናችን ግልጽ ቢሆንም ስንሠራው ካበላሸን እንታረማለን። ያም ሆኖ ግን በቅርርብ በንግግር በውይይት ስለሆነ በጀመርነው መንገድ ውይይቱን ብናጠናክር።
ፓርቲዎችም ጠንከር ብሎ ለማገዝ ሰብሰብ ቢሉ ጥሩ ነው። ለምሳሌ በጎፋ በጋሞ ዞን ውስጥ የቁጫ የሚባል፣ የዘይሴ የሚባል ከሚሆን ሰብሰብ ብሎ ቢባል ጥሩ ይመስለኛል። ያው ለመብት ስለሆነ ትግሉ አብሮ መሆን ቢቻል ጠቃሚ ይመስለኛል። እዛው ቅድም የዘይሴም የቁጫም የተነሳው ቅድም እንዳልኩት እኛ የምንፈትሸው፣ የምናስተካክለው ካለ እናርማለን። በናንተ በኩል ግን እንደምታውቁት ይሄ ምክር ቤት ዛሬውኑ እጅ አውጥቶ ለቁጫ ሕዝብ እንደዚህ ይሁን ብሎ መወሰን አይችልም። ይሄ ሥርዓት አለው። እኛ ደግሞ ሥርዓት እንዲፈጠር ነው የምንፈልገው።
በተጀመረው ሕግ መንገድ ቢሄድ ጥሩ ይመስለኛል። እኔ የግል አስተያየቴ እዚያ አካባቢ ባለኝ እንቅስቃሴ ኮንታም፤ ጎፋም፣ ወላይታም፤ ጋሞም፣ ዳዎሮም አንድ ሕዝብ ነው። አንድ ቤተሰብ ነው። አንድ ቋንቋ የሚናገር፤ አንድ ባሕል ያለው አንድ ሕዝብ ነው። አንድ ሕዝብ ነው ሲባል ይጨፍለቅ፤ ማንነቱ ይደበቅ ማለት አይደለም። ግን የሚያቀራርበው ነገር በጣም ብዙ ነው። ጎፋና ጋሞ ፤ጋሞና ወላይታ አስተርጓሚ አይፈልጉም። ይህንን የሚያቀራርብ ሥራ ብንሠራ ነው የሚጠቅመን ለእኛም ለኢትዮጵያም። እየተበታተንን እየተበታተንን ከመሄድ የሚጠቅመን እርሱ ነው። እኛ በደቡብ ክልል የነበረውን ጥያቄ ፈተናል። ፍትሐዊ ነው ብለን በምናስበው በሠላማዊ መንገድ ምላሽ ሰጥተን አራት ክልል መፈጠሩ ይታወቃል። አሁንም የፌዴሬሽን ም/ቤት ፕሮሰሱን ጨርሶ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሪኮግናይዝ የሚያደርጋቸው ሕዝቦች ካሉ በደስታ ነው ግን ይሄ በቀጥታ የምጠይቀው ጥያቄ አይደለም። እኔ የፌዴሬሽን ም/ቤት አባል አይደለሁም። ፕሮሰሱንም አላቅም። እንዴት እንደሚወሰንም አላቅም። በዚያው በሕግና በሥርዓት ቢሄድ የሚሻል ይመስለኛል። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመግፋት ያለመመቸት ጉዳይ በእኛ ውስጥ ካለ እንፈትሻለን እናስተካክላለን።
ገዥ ትርክትን በሚመለከት የፓርቲ አቋም ነው ወይ? የመንግሥት አቋም ነው ወይ? እንዴት ይገነባል? ለተባለው ገዥ ትርክት አሰባሳቢ ትርክት ነው። ኃይል ይሰበስባል፤ የተሰበሰበው ኃይል ደግሞ ልማት ያፋጥናል። ነጠላ ትርክት ኃይል በታኝ ነው። ልክ እንደ ቅድሙ ዓይነት ማለት ነው። የራስ ሠፈር ብቻ ጎልቶ ሌላ የሚነካ ከሆነ በመካከል ያለ ዝምድና እምነት እየላላ ይሄዳል። ገዥ ትርክት ይኑረን ሲባል የወል ትርክት ሲባል እንደ ሀገር የሚያሰባስበንን ቋንቋ እንጠቀም ለማለት ነው። ይሄም በመደመር መንገድ የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ ነው። በመደመር መንገድ ሲባል ምን ማለት ነው? ያላችሁ እንደሆነ፤ የትናንትና ወረት አለ ይክፋም ይልማም ትናንትና ውስጥ ጠቃሚ ወረቶች አሉ። እነሱን ለይቶ መጠቀም ያስፈልጋል። ዛሬ ደግሞ ፀጋ አለ፣ አቅም አለ፣ ጊዜ አለ መጠቀም ያስፈልጋል። ነገ ደግሞ ተስፋ ነው። የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ጀምሯል ስላችሁ፤ ተስፋ ይኑራችሁ እያልኩ ነው ። እየጠፋን ሳይሆን እየለማን ነው። ለልጆቻችን እንደምንለወጥ እንደምናድግ ትጥቅ እያስታጠቅናቸው ማሳደግ አለብን። እንጂ ተስፋ የለንም እያልን ተስፋ የለኝም ብሎ ያመነ ሰው የጠቀመ ነገር ሊሠራ አይችልም። ተስፋ ያስፈልጋል። በመደመር መንገድ ማለት ትናንትና ዛሬን፤ ዛሬና ነገን አስተሳስሮ ለሀገር ልማት ለሀገር ብልፅግና ማዋል ማለት ነው። ለምሳሌ እዚህ ኢዩቤልዩ ቤተመንግሥት እታች ያለው በጃንሆይ ጊዜ የተሠራ ነው። በጣም ትልቅ ግቢ ነው ከተማ መሐል ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የፊውዳል ቤት ስለሆነ መንግሥታት እንኳን ሊገነቡት ዞር ብለው አላዩትም። አይኖሩበትም አያዩትም። የፊውዳል ይላሉ፤ አንዳንዶቻችሁ አይታችሁ ሊሆን ይችላል ወደፊትም ማየት ትችላላችሁ። ዘንድሮ እድሳት ባይደረግ ኖሮ ያ ምናቀው ታች ያለው ቤተ መንግሥት ይፈርስ ነበር። ይሄን ከእኔ ሳይሆን ሥራውን ከሠራው ቫርኔሮ ከሚባል የጣሊያን ኩባንያን ማረጋገጥ ትችላላችሁ። ወደ ሥራው ሲገባ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። እንደምታውቁት ሥሩ ውሃ ስለሆነ ፍልውሃ ስለሆነ ተበልቷል።
ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት እዛ ቤተ መንግሥት ውስጥ የገነባናቸው አዲስ ግንባታዎች በድምሩ ከነበረው ግንባታ ይበልጣሉ። ምንም ጥርጥር የለውም ይበልጣሉ። ቤተ መንግሥቱን በታሪክ መዝገብ ማጽናት ማቆየት ብቻ ሳይሆን ብዙ ገንዘብ እንድናገኝበት አስውበን ሠርተነዋል። የፊውዳል አልነበረም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ነው የነበረው። እዛ ቤተ መንግሥት ውስጥ አራት መቶ ኪሎ ግራም ወርቅ አሁን ነው መዝነን፣ አጥርተን፣ ኮሚቴ አዋቅረን ወደ ናሽናል ባንክ እያስገባን ያለነው። አራት መቶ ኪሎ ግራም ወርቅ ናሽናል ባንክ አያውቀውም። ሪዘርቭ አያውቀውም። የፊውዳል ፕሮቶኮል ሆኖ ተቀምጧል። የፊውዳል ሳይሆን የኢትዮጵያ ወርቅ ነው።
አሁን ታችኛው ቤተ መንግሥት ሄዶ ያየ ማንም ሰው ማንም ኢትዮጵያዊ ኩራት ይሰማዋል። በምን ያክል ጥራ አስበን እንደሠራን ስለሚታይ። ትናንትና ነውና ገደል ይግባ ሳይሆን አስውበን አሳምረን አልቀን ልጆቻችን እናሻግራለን። የመደመር መንገድ ማለት ትናንትን ከዛሬ የሚያስተሳስረው በዚህ መንገድ ነው። ጠቃሚ ነገር ካለ አጉልቶ በመጠቀም ማለት ነው። የበለፀገች ኢትዮጵያን እንፈጥራለን ደግሞ ሲባል ብልፅግና ማለት ቤትና መኪና ማለት ብቻ አይደለም። መንፈሳዊ ሀብት ያላት መንፈሳዊ ስዕል የጠበቀ በቁስም በመንፈስም በሞራልም ያደገ ማኅበረሰብ ያላት ኢትዮጵያ ማለት ነው።
ለምሳሌ ማዕድ ማጋራት አንድ ሞራላዊ ልዕልና ነው። ድሃን መውደድና ድህነትን መጠየፍ ሌላው ቫልዩ ነው ማደግ ያለበት ። በዚያ መንገድ ነው ብልፅግና መረጋገጥ ያለበት። ናሬሽናችን ይሄንን መገንባት አለበት የምንለው፡፡
ገዥ ትርክት ውቅሮች አሉት። አንደኛው ውቅር ሕገ መንግሥታዊነት ነው። ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የወል ትርክት መገንባት አይቻልም። ሕገ መንግሥታዊ የሆነ የወል ትርክት ሲባል በውስጡ ዴሞክራሲ አለ፣ ፍትሕ አለ፣ እኩልነት አለ፣ አንድ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት አለ። ይሄ ትርክቱ አንድ ውቅር ነው ሕገ መንግሥታዊነት።
ሁለተኛው እናንተም እንዳነሳችሁት ኅብረ ብሔራዊነት ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች የብዙ ባሕሎች የብዙ ቋንቋዎች፣ የብዙ እምነቶች እና የሁለት ፆታዎች ሀገር ናት። ይሄን ተቀብሎ መኖር ያስፈልጋል። ይሄን የማይቀበል ዕሳቤ ገዥ ትርክት አይገነባም። ብዙ ቋንቋ አለ፣ ብዙ ባሕል አለ፣ ብዙ እምነት አለ፣ የተለያየ ፆታ አለ፤ ተቀብለን በትብብር መንፈስ ተከባብረን እንኖራለን ብሎ ማመን ያንን መናገር ያስፈልጋል።
ሦስተኛው ውቅር ብልፅግናን በየደረጃው እያረጋገጡ ድህነትን እየደፈቁ መሄድ ነው። ልማትና ልማታዊነትን ማሳደግ ነው። ይሄም ኃይል ካልተሰባሰበ በስተቀር አይሆንም። አራተኛው ውቅር ማረምና ማስቀጠል ነው። በጣም ብዙ ድካሞች ስንፍናዎች ስህተቶች አሉ። እያረምን እያረቅን እያሻሻልን መሔድ ነው። ትናንትናን እንዳለ መድፈንም አንችልም። ጥላ ነው ያስቸግራል የራሱ ነገር አለበት። ከዚያ እየተማርን እያረቅን መሔድ ከቻልን ግን ለዛሬ ስንቅ ሊሆን ይችላል። አምስተኛው ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው። እንደ ሰው ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ተነጋግሮ የጋራ ሕልም መፍጠር ነው። የበለፀገች ያደገች ኢትዮጵያን ለማየት የጋራ ሕልም መፍጠር ነው።
ይህ ጉዳይ አንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን አንድ ትውልድ ይሻገራል። እንኳን የእኛ ፓርቲ ብቻ ሁላችን ብንደመርም ቀጣዩ ትውልድ ካልሠራበት ብቻውን የሚሆን አይደለም። ከፓርቲም ከትውልድም ይሻገራል። እኛ ፋውንዴሽን እንጥላለን ልጆቻችን አስቀጥለውበት ይገነቡታል ተብሎ የሚታሰብ ነገር ነው። በምን ይገነባል በትምህርት ቤት፤ በካሪኩለማችን፤ የሚያሰባስብ የማይለያይ በታሪክ ትምህርት ውስጥ፤ በእሳቤ ውስጥ ከፋፋይ የሆኑ ሀሳቦችን እያጠፉ ሰብሰብ ማለት። ሁለተኛ ኪነጥበብ በመሳደብ፣ በመቃወም ብቻ ታዋቂነትን ማትረፍ ሳይሆን ማኅበረሰብ በመገንባት፤ እውነትን በመግለጥ፤ ኪነጥበብ ሚናዋን እንድትወጣ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሦስተኛ የእምነት ተቋማት፤ የእምነት ተቋማት ግብር የማይከፍሉት፣ የእምነት ተቋማት በነፃ መሬት የሚወስዱት እንዲሁም ብዙ ድጋፍ የሚያገኙበት ዋናው ምክንያት ማኅበረሰብ ይገነባሉ ተብሎ በማሰብ ነው። ይሄ ጉዳይ የእነሱ ጉዳይ ነው። ከፋፋይ ነገር፣ የሚለያይ ነገር መሥራት አይጠበቅባቸውም። ሚዲያዎች፣ ፓርቲዎች፤ የሚዲያዎች ሥራ መሆን ያለበት ሰብሰብ የሚያደርግና እንደሀገር ካለንበት አረንቋ የሚያወጣ፤ ፓርቲዎች በፕሮግራማቸው፣ በዲስኩራቸው፣ በስብሰባዎቻቸው እንዲሁም በሥልጠናዎቻቸው ማሳየት ያለባቸው የሚሰበስብ እሳቤ ነው።
በብልፅግና ፕሮግራም እንዳያችሁት ይህ እሳቤ እንዳለ አለ። ይሄ ብቻ ሳይሆን ተረትና ምሳሌዎቻችን እንዲሁም ሆያ ሆዬ እና አበባየሆሽ ሳይቀሩ ግጥም መቀየር አለበት። እንጨት ለቅሜ፣ እንጀራ እናቴ የመሳሰሉት መቆም አለበት። መጥፎ መርዝ ነው ልጆች ውስጥ የሚገባው። ያ ግጥም ካልተቀየረ ውስጥ ውስጡን እየገባ እየገባ ሄዶ ጥፋት ያመጣል። ትርክት ስንጠይቅም፣ ስንመልስም፣ ስንሠራም፣ ስንኖርም የምንገነባው ነገር ነው። እኛ አንጨርሰውም ተባብረን ግን ልጆቻችን እንደዚህ በሰፈር ሳይባሉ እንዲኖሩ ማድረግ የሚያስችል ነው።
የቁጫና ዘይሴ መልሼ የኢሊባቡርና የድሬሲንግ ኮድ (የአለባበስ ሥርዓትን) የሚመለከት እግረመንገድ ለማንሳት ኢሊባቡር እንደተባለው ነው፤ በጣም በጣም ውብ ሀገር ነው። ትልቅ አቅም ያለው አካባቢ ነው። ለቱሪስት ብቻ ሳይሆን ለእኛም ለጉብኝት በጣም የሚያጓጓ አካባቢ ነው። ከፍተኛ ጫካ የሚበዛበት በጣም ውብ አካባቢ ነው። ግን ጅማሬዎች አሉ፤ ኤርፖርት እየሠራን ነው፤ መንገዶች እየሠራን ነው እዛ አካባቢ፤ ቅድም ያወራሁት ሻይ፣ ቡና፣ ሩዝ አንዱ የሚሠራው እዛ አካባቢ ነው። እንቅስቃሴዎች አሉ፤ የተባሉት ቦታዎች የሚያጓጉ ናቸው። ወደፊት እየታየ ሲሄድ የልማት አካል እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ። ግን እርስዎ እንደሚያውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ የሚያምር ነገር አለ። ብዙ ከመቶ በላይ፤ እኛ የሠራናት አስር አትሆንም። ያን አንድ በአንድ እየገነቡ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
ቅደም ተከተል ላይ ለምሳሌ የኮሪደር ልማት ላይ የተመለከትን እንደሆነ በፌደራል መንግሥት በእኛ ደረጃ የምንመራውና የመረጥነው ነው። ብዙ ከተሞች ያሉ ቢሆንም ጎንደር፣ ሐረር እና ጅማ ጥንታዊም ስለሆኑ ያን ነገራቸውን ለማውጣት እንዲያስችል በቀጥታ እንመራቸዋለን። አርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ አዳማ፣ ነቀምት ብዙዎቹ ደግሞ ያካሄዳሉ። እነዚህን ጨርሰን ደግሞ ፍላጎት አለ ሁሉም ቦታ ገንዘብና አቅም ግን የለም። እና ቀስ ቀስ እያልን የምንደርስበት ይሆናል።
የድሬሲንግ ኮድ (የአለባበስ ሥርዓት) እና ከእምነት ጋር በሚያያዝ በተሟላ ሁኔታ ምንም አይነት እንከን የለንም ብዬ መናገር አልችልም። ግን ትልቅ እድገት አለ። ለመጀመሪያ ጊዜ በለውጡ በሙስሊምም በክርስትናም በአዋጅ እውቅና የተሰጣቸው ተቋማቶቻቸው እንዲጠናከሩ መንግሥት ያለው ቁርጠኝነት እርስዎ በደንብ ይገነዘባሉ። ከተቋማት አንጻር መሠራት ያለበት ሥራ ካለ እያየን እንሠራለን። እንደእርስዎ አይነት ሰዎች፣ ማስተማር የሚችሉ ሰዎች እግረ መንገድ ቢያስተምሩ ብዬ የማስበው ኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ሳይሆን ሃይማኖተኝነት ነው እያደገ የመጣው። ሃይማኖተኝነት እያደገ ሲሄድ ደግሞ አብሮ አክራሪነት ይፈጠራል። እምነት ነው ማደግ ያለበት። እምነት ምንድን ነው? ሰው መውደድ፣ አለመስረቅ፣ አለመግደል እንዳይባል እሱ እየጨመረ ነው ያለው። ሃይማኖተኛ የሆነ ፓርቲ ፓርቲዚያም ህሳቤ ግን እያደገ ነው ያለው። እሱ እሱን ማስተማር ያስፈልጋል። እርስዎ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ብዙ ተጋድሎ ያደርጋሉ ከጓደኞችዎ ጋር ሆነው እንደዛው በዚህ ጉዳይም ገለልተኛ የሆነ እምነቱን የሚወድ የሚያከብር ሌላውን ግን የማይነካ ማኅበረሰብ እየፈጠሩ መሄድ ያስፈልጋል። አጥር እየበዛ ከሄደ እንዳንለያይ ከእርስዎ እንደዚያ አይነት የማስተማር ሚና ይጠበቃል፤ እንደሚያደርጉ አውቃለሁ ግን ይጠበቃል። በእኛ በኩል የቀሩ ጉዳዮች ካሉ እያየን እናርማለን። ግን እንደድሮ አይመስለኝም። በጥቅሉ የምናገረው ከድሮ ለውጥ አለ፤ ከቀረ ደግሞ እናሻሽላለን ብዬ ባልፍ ነው የሚሻለው፡፡
ታሪካችንን በሚመለከት በጣም በጣም ወርቃማ ዕድሎች ነበሩን። ኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። አሁን አሳዛኝ ናት። እናንተ እንደምትሏት ሳይሆን አሳዛኝ ሀገር ናት። የሄድንበት ሀገር ሁሉ ከእኛ ይሻላል። ያ ደግሞ ያቃጥላል፤ ያስቆጫል። ምንድን ነው ዕድል ያላችሁ እንደሆነ ክርስትና ከመጀመሪያው ሴንቼሪ ጀምሮ የትኛም ዓለም ሳይስፋፋ የገባው ኢትዮጵያ ነው። ያ ክርስትና ድህነትን ለመምታት፣ ደሃን ወደ ብልፀግና ለማሸጋገር መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ነበረበት። ነበረበት ነው አላገለገለም። የመጀመሪያው እስልምና የገባው ኢትዮጵያ ነው እንደምታውቁት ። ይሄ ጉዳይ ቱል ሆኖ አላገለገለም። ከድህነት ማላቀቅ ነበረበት አልሆነም አላገለገለም ማለት ነው። ጥንታውያን ነን ሲበዛ፤ ታሪክ ያለን መልካም ድላችን የሚያስገርም ሀገር ነን። በዚያ ልክ መጠቀም አልቻልንም። ሥልጣኔ የጎደለን ደግሞ እንዳንባል አየር መንገድ፤ የባንክ ሥርዓት፤ ቴሌኮም፤ ባቡር ከጀመርን 80፣ 90፣ 100 ከዚያም በላይ ዓመት ፈጅቷል። ቆይቷል እኛ ጋር ቴሌኮም።
የኢትዮጵያ ሊቃውንቶች ምዕራቡን ዓለም መጎብኘት ከጀመሩ አራት መቶ ዓመት ሆኖቷል። እንዴት አስችሏቸው ተመልሰው የእኛን ነገር እንዳዩ ግን አላውቅም። በሄድንበት ሀገር ሁሉ የዛሬ መቶ ዓመት፣ የዛሬ ሰማንያ ዓመት ተገነባ የሚባለው ነገርና የእኛ ሁኔታ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው። ለምሳሌ ኮሪደር መገንባት የነበረበት የዛሬ አርባ ዓመት ነበር፤ ዛሬ አይደለም። እዳ ስለወደቀብን ነው እንጂ የእኛ ሥራ መሆን አልነበረበትም። በቅርቡ ማሌዢያ በነበረኝ ቆይታ የገረመኝ ይሄ ነው። ኮሪደር ከገነቡ አርባ ዓመት ሆኗቸዋል። ማሌዢያ በቅኝ ግዛት ውስጥ እያለች ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር ነበረች። ነፃነት አግኝታ እርሷ የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ ግን ገና በጣም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። እናም ያለፈው ስልሳና ሰባ ዓመት ብዙ ነገር ነው ያባከነብን። በሚያስቀናው ሳንቀና፣ በሚያስቆጨው ሳንቆጭ እንደው ወተን እየገባን ነው የመጣነው። ከተቆጨን ደግሞ መደረግ አለበት። መሠራት አለበት እዚህ። እንኳን ኮሪደርና ልማት ቀርቶ ማንኛውም ለውጥ ይጎረብጣል። ሰውን ከልማዱ ማፋታት ከባድ ነገር ነው። የለመደውንና ምቾት ቀጣና ውስጥ ያስገባውን ነገር ከዛ መነቅነቅ በጣም ከባድ ነው። ለዚህ ነው እድገት በእኛ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኖ የቆየው።
መቅናት አለብን። መናደድ አለብን። ለምን ኢትዮጵያ አነሰች ብለን ማዘን አለብን። ማዘን ብቻውን በቂ አይደለም። አቅደን መተግበር አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሞላ ጎደል እኔ ሦስት ሾተላዮች ያሉብን ይመስለኛል። አንደኛው እያፈረሱ መሥራት ነው። ይህ እንደኮሪደር አይደለም። ኮሪደር የፈረሰውን ማፍረስ ነው። እሱ አልነበረም። ላስቲክና ጭቃ አለ ብላችሁ ፈረሰ የምትሉ ሰዎች ካላችሁ አልነበረም። ለምሳሌ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በ1950ዎቹና መጨረሻና 60ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ የእግረኛ ጦር አላት። የአየር ኃይል ግን አልነበራትም። ጎረቤቷ ሞዛምቢክ በቅኝ ግዛት እንደተገዛች የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ተጠይቀው እዛ ሄደው ስድስት ወርና ከዛ በላይ የታንዛንያን አየር ክልል እንዳይጠቁ ይጠብቁ ነበር። ማንዴላን አሠልጠነዋል፣ ዙምባቤን አሠልጥነዋል። ከእሱ በላይ ደግሞ ትናንትና አብራሪና አውሮፕላን ልከን የአንድ ሀገር የአየር ክልልን እንጠብቅ ነበር።
እኛ የተረከብነው አየር ኃይል ግን እንኳን የሰው ሀገር የአየር ክልል ሊጠብቅ ቀርቶ ለራሱም ፈርሶ ነበር። ይህ ትክክል አይደለም። ተቋም ማስቀጠል ያስፈልጋል። ሀገር ማስቀጠል ያስፈልጋል። ለልጆቻችን መቆያ ስለሆነ። ጥንታዊት ሀገር ስለሆነች። እያፈረሱ መሥራት አንዱ ሾተላይ ነው። ሁለተኛው በዕድልና በግዜ መቀለድ ነው። ዕድል ሲገኝ መጠቀም ነው እንጂ ያን እያባከኑ መሄድ ካለፈ በኋላ ላይ ደግሞ ፀፀት ዋጋ የለውም። ዕድልና ግዜን መጠቀም ላይ ችግር አለብን። ብዙ ዕድል አበላሽተናል። ሦስተኛው ሾተላይ ካለፈ በኋላ መቆዘም ነው። አይ እንትና! አይ እንትና! እያሉ ወደኋላ መቆዘም። እሱ አይጠቅምም። እያለ ነው መጠቀም። ከሄደ ለታሪክ ማስተማሪያ ማስቀመጥ ነው። ይህ ጉዳይ በብዙ ጎድቶናል። የዚህ ጉዳይ መሠረት ደግሞ እኔ ያልጋገርኩት እንጀራ አይውጣ፣ እኔ ያልሠራሁት ወጥ ይረር የሚል እሳቤ ነው። በቃ እኔ ካላደረኩ በስተቀር አይሆንም። አሁን ኮሪደር የሚጠላ ነገር አይደለም። ዓለም በሙሉ እያደነቀው እንዴት ኢትዮጵያዊ ይጠላዋል። እኔ ሳላደርገው ነው። ይህ እሳቤ በብዙ እየጎዳን ስለሆነ አርቀን ወደፊት ብንሄድ ይሻላል። ከታሪካችን መማርና የተሻለ ታሪክ ማኖር ስላለብን።
የአካቶ ሀገራዊ ምክክርን በሚመለከት ለተነሳው ሃሳብ የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያውቀው የምክክር ኮሚሽኑ የሚመራው በፓርላማ ነው። እኔ በቀጥታ የማዘው ተቋም አይደለም። ይህ ተቋም ከሠላም ኮሚሽኑ ትምህርት ወስዶ፤ ከድምበር ኮሚሽኑ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የእናንተ አመራር ይጠበቃል። እናንተ ናችሁ የትናንትናውን ገምግማችሁ ነገ ደግሞ እንዳይደገም አርቃችሁ ማስኬድ ያለባችሁ። በእኛ በአስፈፃሚው ጎን የሚፈለግ ድጋፍ ካለ መቶ በመቶ ለማድረግ ዝግጁዎች ነን። ነገር ግን ጥሩ ሙከራ እያደረጉም ይመስለኛል። በማየው ነገር የተቃጠለ ጊዜ ሳይሆን አብዛኛውን ቦታ እያነጋገሩና አጀንዳ እየለዩ ይመስለኛል። ባለን አንዳንድ ነገር እንደምንፈልገው ባይፈጥንም ጅማሮው ጥሩ ይመስለኛል። ተሐድሶ ኮሚሽን አቋቁመናል። በየቦታው የታጠቀ ኃይል አለ። እንጠቀምበት። ካለፈ በኋላ ያስቆጫል። ተሐድሶ ኮሚሽኑ እንዳይሠራ እንቅፋት ከምንሆን ቶሎ ዲ ዲ አር አሳክተን ሰው ከክላሽ ይልቅ ሞር እንዲይዝ አድርገን፣ መኪና እንዲይዝ አድርገን፣ ትራክተር እንዲይዝ አድርገን ብናሠራው ይሻላል።
የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ እንዳያመልጠን መጠቀም አለብን። በቀጣይ ፓርላማው የሚመራው ጉዳይ ስለሆነ የእናንተ ድጋፍ ቢታከል ጥሩ ነው። ችግር ካለ ማረም፣ የጎደለ ካለ መሙላት፣ ድካም ካለ ማጠናከር፤ ዕድልን ግን መጠቀም ያስፈልጋል። ዕድል ካመለጠ በኋላ አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው። ብዙ ግዜ የምታዘበው የእኛ ነገር ጉዟችን የአዞ መንገድ ነው። አዞ ከውሃ ውስጥ ፀሐይ ሊሞቅ ሲወጣ በእግሩ ዱካ እየሠራ ይወጣል። በእግሩ የሠራውን ዱካ ግን በጭራው ያጠፋዋል። ርቆ ከወጣ በኋላ ፀሐይ እየሞቀ አውሬ መጥቶ ሲያጠቃው ተመልሶ ወደውሃው ለመግባት ዱካውን አያገኘውም። በእግሩ የፈጠረውን ዱካ በጭራው ስለሚያጠፋው። እኛ እስከ መቼ ነው መንገዳችንን ራሳችን እያጠፋን መመለሻው እየጠፋን የምንኖረው የሚለውን ጉዳይ ማሰብ ያስፈልጋል። የሠራነውን ጉዳይ መጠበቅ፣ ማስቀጠል ስለሚያስፈልግ።
ብልሹ አሠራር እና ልምምድ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። ፒቲ ሙስና አለ። በሰዓት ሥራ አለመግባት አለ። አድሎ አለ። በጣም ብዙ ችግሮች አሉ። ይኼ እየተቀረፈ መሄድ አለበት። እስካሁን ድረስ ያሳካነው ተቋማዊ ስቴት ኮራፕሽን የለም። እንደ መንግሥት የኢትዮጵያን ሀብት ዘርፈን ሌላ ቦታ አንወስድም። የኢትዮጵያን ሀብት በተቻለ መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ እናፈሳለን። ይሄ ምንም ማስረጃ አያስፈልገውም የሚታይና ዓለም የሚገነዘበው ጉዳይ ስለሆነ ብዙ መናገር አያስፈልግም። ግን ስቴት ኮራፕሽን የለም ማለት፣ ተቋማዊ ኮራፕሽን የለም ማለት ግለሰቦች አይሰርቁም ማለት አይደለም። ሥራ ይፈልጋል። የውርስ ችግሮች አሉብን። ፖሊሲዎቻችን፣ አሠራራችን፣ መዋቅሮቻችን መታረም አለባቸው። ለምሳሌ ሲቪል ሰርቪስ ብዙ ሥራ ይፈልጋል፤ ከልማድ ማላቀቅ ስለሆነ። የማስፈጸም አቅማችንም እንዲሁ ውስንነት አለበት። የዓለም ስሪቷ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል። ከእንደነዚህ ዓይነት ምስኪኖች ነው ኤክስትራክት የምታደርገው። ያን ተቋም ትርፏን ማፍረስ አንችልም። እዚያ ውስጥ ነው እንደምንም ብለን ጥቅማችንን ለማስከበር የምንሠራው። እነዚህን ዓይነት ችግሮች አሉ፤ እዚህም እዚያም። እነርሱን እያረቁ መሄድ ነው ሪፎርም ያልነው።
ታስታውሳላችሁ ፖለቲካል ሪፎርም አደረግን። በሰፈር የነበረውን ብልፅግና ብለን ሰብሰብ አደረግን። እኛ ስንሰበስብ ተቃዋሚዎቹ ቢሰበስቡ ኖሮ ናሬሽን ይገነባል። ፖለቲካል ሪፎርሙ የበለጠ እያደገ ይሄዳል። ኢኮኖሚክ ሪፎርም ቅድም እንዳነሳሁት ነው፤ ዲጂታላይዜሽን፣ ሴክተራል ሪፎርም ግብርና ላይ ያመጣነው። ግብርና ላይ ያመጣነው፣ ቱሪዝም ላይ ያመጣነው ሥራ፣ አሁን ከተማ ላይ የምንሠራው ሥራ እነዚህ ሁሉ ሪፎርሞች የሥራ ከባቢና የሥራ ባሕል ለውጥ ተደምሮ ሲመጣ ብልሹ አሠራርና አድሎ እየቀነሰ ይሄዳል። ሰው እስካለ ድረስ ጥፋት ዜሮ ይሆናል ባይባልም እየቀነሰ ይሄዳል። ለዚህ ነው ብልሹ አሠራርን በጊዜ እየነቃን ማረም ማስተካከል የሚገባን። በሥልጠናም፣ በግምገማም፣ በእርምጃም።
ሥልጠናን ውይይትን በሚመለከት እኛ ወደ ሥልጣን ስንመጣ ቃል ገብተናል። ብልፅግና የሚያደርጋቸውን ውይይቶች በመግለጫ ሳይሆን ከሞላ ጎደል ለሕዝብ የሚያስፈልገውን መረጃ ግልጽ እናደርጋለን ብለን ቃል ገብተናል፤ ታውቃላችሁ ይሄንን። ስንሠለጥን ብዙ ወሬ ይወራል፣ ስንወያይ ብዙ ወሬ ይወራል ይሄን ለሕዝብ እንሰጣለን ብለናል። ምክንያቱም ሕዝብ አይቶ እንዲያርመንም፣ እንዲመክረንም፣ እንዲወያይበትም ጭምር ነው። በድብብቆሽና በመግለጫ ብቻ መሆን የለበትም ጠቃሚ መረጃ ሲኖር በግልጽ መሰጠት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡
ኮሪደር ልማትን በሚመለከት የዛሬ ዓመት ስለ ኮሪደር ልማት ብንናገር አስቸጋሪ ይሆናል ብለን ነው። አሁን ግን ኮሪደር ልማት ማለት ፒያሳ ማለት ነው። ኮሪደር ልማት ማለት ቦሌ ማለት ነው። ይህንን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ከተማ ፎቅ ያለበት ገጠር ነው። ፎቆች የሚታዩበት ገጠር፤ ሽንት ቤት የለም፣ መብራት የለም፣ በየለም የተሞላ ነው፤ መቀየር አለበት። በጣም የዘገየ ሥራ ነው። ከብዙ ሀገራት ኋላ የቀረንበት ሥራ ነው። አንዳንዶቻችን ደግሞ እንደፋሽን ነው፤ አስፋልት ዳር ላስቲክ፣ ቆርቆሮ እያደረግን አስፋልት ማጣበብ፤ ካልጠፋ ቦታ ይሄን የሚያህል ሀገር ተሸክመን፤ ተጋፍጠነዋል፣ ችለነዋል፣ መቀየር አለበት፤ ግን ውጤት እያመጣንበት ነው።
በ20/50 ከተሜነት ወደ 60 ፐርሰንት ያድጋል። አብዛኛው ሰው ከገጠር ከተሜ እየሆነ ይሄዳል። እኛ የነበርንበት ሁኔታ በላስቲክ ላይ ላስቲክ፣ በጭቃ ላይ ጭቃ፤ ምን ከተማ ይባላል። አሁን ካላረምነው በስተቀረ ሕዝብ እየበዛ ሲሄድ ሰርቪስ አቅርቦት ማድረግ ወደማንችለበት ደረጃ ይወስደናል። አጠቃላይ ኢኮኖሚ የት ነው? ከተማ ነው እኮ ያለው። ከተማ አደገ ማለት የሀገር ኢኮኖሚ አደገ ማለት ነው። በከተማ ልማት ትዝ ይላችኋል ከዚህ ቀደም ገጠር ተኮር ነን፣ አርሶ አደር ተኮር ነን ብለን ለገጠሩ አርሶአደር ግብርናውን ምንም ጠብ ሳናደርግ ቆየን። አሁን ደግሞ ገጠርና ከተማ የለም ኮሪደር ልማት እንሠራለን ብለን ባንጀምር እንዴት የሰው ሕይወት ልናሻሽል እንችላለን። ለምሳሌ ኮሪደር ልማት ማለት መንገድ ነው፤ በጣም ሰፋፊ መንገድ እየገነባን ነው አዲስ አበባ ውስጥና በየከተማው።
መንገድ ግንባታ፣ ኢንፍራስትራክቸር ግንባታ አያስፈልግም? ሁለተኛ ኮሪደር ልማት ማለት በየሰፈሩ ትናንሽ ስታዲየም ነው እየገነባን ያለነው። በየሰፈሩ 20 ሠላሳ ገንብተናል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ። በየሰፈሩ ስታዲየም መገንባት ያለውን ፋይዳ የሚያውቅ ሰው ልጆቹ ኳስ ሊጫወቱ አስፋልት ላይ ወጥተው በመኪና የተገጩበት ሰው ይገባዋል። የኛ ልጆች አስፋልት ዳር ኳስ ይጫወቱ ነበር፤ መቆም አለበት እሱ። ልጆቻችን ላይ የምንሠራው በዚህ መንገድ ነው። ትናንሽ ስታዲየም ሠርተን ልጆቻችን እንዲጫወቱ ብናደርግ፤ እናንተም ትላልቅ ሰዎች ጊዜ ሲያገኝ ቢንቀሳቀስ መልካም ነው። አልነበረም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ። ማንኛውም ቦታ ኪስ ቦታ ይባላል፤ ሲሸጥ ይኖራል። ኪስ ቦታ የሚባል ስፔስ እንተው ነው የተባለው፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ እንደምታውቁት ፓርክ የለም። ሰው ወጥቶ ፍሬንድሺፕ፣ እንጦጦ ሳይሆን በየሰፈሩ ውስጥ ትናንሽ ዛፍ፣ ሳር ያለበት፣ ወንበር ያለበት ቦታ አልተለመደም። ሁሉ ቦታ ይቸበቸባል በሊዝ፤ የጠላት ገንዘብ ይመስል። ፓርክ ነው የሠራነው። ዛፍ ነው የተከልነው። አዲስ አበባ ውስጥ 5 ሚሊዮን የማያንስ ሰው እግረኛ ነው። መኪና ያለው አጠቃላይ 1 ሚሊዮን ቢሞላ ነው። ለአንድ ሚሊዮን ሰው መኪና መንገድ ሠርተን፣ ለአምስት ሚሊዮን ሰው እግረኛ መንገድ አለመሥራት እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? ይሄ እኮ አድሎ ነው። ለእግረኞች ንጹሕ የእግር መንገድ የተሠራው የእግር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች፣ የሳይክል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች መኪናም ባይኖራቸው በልካቸው ሰርቪስ እንዲያገኙ ነው። ይሄ እንዴት ስህተት ይሆናል?
በየአስፓልት ዳር ሽንት የሚሸናበት ሀገር እኮ ኢትዮጵያ ነው። በዋና ከተማ ውስጥ ማንም ሰው ምንም ሳይሳቀቅ ልክ እንደ ጥሩ ነገር ቆሞ ያደርገዋል። ይሄን ለመቀየር ሽንት ቤት መሥራት እንደ ስህተት ይሆናል? ሰው ያንን ነገር በክብር ያድርገው፣ ተፈጥሯዊ ነው ያድርገው፤ ያንን ነገር በክብር ያድርገው ማለት እንዴት ስህተት ይሆናል?
እኛ ያፈረስንባቸው ሰፈሮች በቂ መብራት፣ በቂ መፀዳጃ፣ በቂ ፍሳሽ ማስወገጃ አልነበረም። እዚህ እኛ ሰፈር አሁን ሰሞኑን የሚፈርሰው አካባቢ፣ ሰው እዚህ ተቀምጦ ቡና እየጠጣ፣ በአምስት ሜትር ርቀት ውስጥ፣ ካለምንም መሳቀቅ ሌላ ሰው ይፀዳዳል። ይሄን ኑሮ ነው መቀየር የፈለግነው።
ኮሪደሩ ያስፈልገናል፤ ጥፋቱን ቀንሰን፣ ድካሙን ቀንሰን ከስህተት ተምረን፣ ብንጠቀምበት ጥሩ ነው።
አንዳንዶች ለዲሞግራፊ ነው ብለው ይናገራሉ፤ ምን ያድርጉ ይሄን ካልተናገሩ! ሀሳብ የለ! እሺ አዲስ አበባ ለዲሞግራፊ ነው እንበል፤ ጅማስ? አጋሮስ? ጎንደርስ? ሐረርስ? ምንድነው ዲሞግራፊው? ይሄ ሥራ ሁሉም ቦታ ነው ያለው። የሆነ ሰፈር ቢሆን ኖሮ፣ እሺ እንጠረጥራለን፤ ሠላሳ አርባ ከተማ እያፈረሰ ባለበት ሁኔታ የማይሆን ስም ሰጥተን ልማት ከምናደናቅፍ ከቻልን ማገዝ ካልቻልን ደግሞ ዝም ብለን መታዘብ ነው የሚሻለው።
ዓለም ላይ ብቸኝነት የሚባለው ነገር ከፍተኛ አደጋ እየሆነ ነው። አንዳንድ ሀገራት እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ይመድባሉ ሰው በብቸኝነት ራሳቸውን ስለሚገድሉ ከሰው ጋር የሚገናኙበት ለመፍጠር። ዕድገት አንዱ በሽታው እሱ ነው። በጋራ ቡና የለም፣ ምናምን የለም፤ ሰው ብቸኛ ይሆንና፤ አንደኛ መውለድ ይቀንሳል፤ በኋላም ብዙ ሰው ራሱን ይገድላል።
አሁን የምንፈጥራቸው ኢንፍራስትራክቸሮች በጋራ መኖርን ልማዳቸው እንድንኖር የሚያደርግ ነው። ፓርክ ሲሠራ፣ ኳስ ላይ ሲሠራ ይበልጥ ትውውቅ፣ ይበልጥ ዝምድና ይኖራል። ለምሳሌ፤ የፓርላማ አባላት ወሎ ሰፈር አካባቢ የነበረው አፓርትመንት የምትኖሩ የፓርላማ አባላት፤ ትናንት የነበረውንና ዛሬ ያላችሁበትን ተመልከቱት። ልጆቻችሁ ቢያንስ ወጥተው ወክ የሚያደርጉበት ሁኔታ አልተፈጠረም? ይሄ ነገር ጠቃሚ ነው ግደላችሁም፤ ሁላችንም የምንቃወም ከሆነ ልማትን አደገኛ ነው የሚሆነው። ጠቃሚ ነገር ነው፤ ስህተት ካለበት እናርመው። ሰዎች እኮ ሀገራቸውን የጋብቻ ቀለበት እያዋጡ ነው የገነቡት እንኳን ጭቃ ቤት አፍርሰው! የሚፈርስ ካለ እያፈረስን አገር መገንባት አለብን ለልጆቻችን። በዚያ እሳቤ ካላየነው በቀር ነገ ሲጀመር ካደናቀፍን ችግር ነው። አሁን የገጠር ኮሪደር ተጀምሯል። የገጠር ኮሪደር በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። እያንዳንዱ አርሶ አደር በጓሮ የተወሰነ ዶሮ፣ የሚታለብ ላም እንዲኖረው፣ ከመንገድ ዳር ጠጋ እንዲል፣ ቆርቆሮ አጥር እንዳያደርግ፣ ትራኮማው ምኑ ብዙ ነው በሚያንፀባርቅ ነገር፣ በተፈጥሯዊ መንገድ አጥር እንዲያጥር፣ በተቻለ አቅም እርሻ እያደገ ስለሆነ፣ አርሶ አደር ገቢው እያደገ ስለሆነ፣ አርሶ አደር ታውቃላችሁ ቆጣቢ ነው፤ ለክፉ ቀን ነው የሚለው ፣ አርሶ እንኳን ዘር እና በጎተራ ያስቀመጠውን ለክፉ ቀን አይነካም ይርበዋል እንጂ። ይሄ ልማድ ሀብቱ እያደገ ሲሄድም መጠቀም ላይ ችግር አለ። መደበቅ አለ። ማለማመድ አለብን ቤቱን ፀዳ፣ ቀለም መቀባት እንዲችል፣ አልጋ ላይ እንዲተኛ፣ ከከብት ጋር እንዳያድር፣ በጣም ብዙ አርሶ አደር ቤቱ ውስጥ ከብት ያስተኛል። ይሄን ካልቀየርን እንዴት ብልፅግና ይመጣል? ለዚህ የተከበረው ምክር ቤት ቢያግዝ ጥሩ ነው፤ ገና ብዙ ሥራ ነው ያለብንና መደነቃቀፍ እንዳይሆን፤ ነገር ግን አንደኛ ጥናት ያስፈልጋል። ዘሎ ኮሪደር ትክክል አይደለም፤ ጥናት እያጠኑ ስንት ሰው ነው በምን ያህል ሀብት መተካት ይቻላል እያሉ እያጠኑ መሄድ ያስፈልጋል። እየሞከርነው የሚጎል ካለ እንሞላበታለን።
ሁለተኛ ውይይት ያስፈልጋል ከማኅበረሰቡ ጋር፤ ለአንተ ነውና፤ ማወያየት ማነጋገር አያስፈልግም ልንል አንችልም፣ አነጋግረን፣ አወያይተን ነው የምንሠራው። ምክክር ያስፈልጋል፡፡
ሦስተኛ ካሣ መክፈል ያስፈልጋል፤ ከቻልን ቤት፣ ካልቻልን መሬት በምንችለው ካሣ መክፈል ያስፈልጋል። ከቻልን ከቻልን ሠርተን እናስገባለን እንደ አቧሬ፣ ካልቻልን ብንወስደውም ሌላ ቦታ ካሣ እንከፍለዋለን። ይሄ ካልተሳካስ! ቅሬታ የምናዳምጥበት ሥርዓት አበጅተን ያልተመቻቸው ሰዎች ካሉ ቅሬታ እንዲያስደምጡ ደግሞ ችግራቸውን እንዲናገሩ ደግሞ እናመቻቻለን፡፡
ይሄ ሁሉ እንዲሆን እንዳያችሁት ኮሪደር ልማት ከፍተኛ አመራር ነው በየሰፈሩ ወርዶ የሚሠራው። አዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ተሰጥቶት ሰፈር፣ በክልል በዞን ዞን፤ ለምሳሌ ኦሮሚያን ብንወስድ፣ ያለው አስተባባሪ ቀጣና አለው። የጅማ ቀጣና፣ የወለጋ ቀጣና፣ የባሌ ቀጣና ተብሎ ተከፋፍሏል። አማራ ክልል ብትሄዱ እንደሱ ነው፤ የኔም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም የክቡር አፈ ጉባኤውም ኢኒሸቲቮች እነዚህ መልክ እየያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፤ ለዚህ እኮ ነው በየኦፕሬሽኑ ስዞር የምታገኙኝ። ይሄን አድርገን ብንሠራ ጥሩ ነው፡፡
አሁን ጅማ እና ጎንደር ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ ሳይ መጠናከር አለበት ይሄ ነገር። ቆሻሻን፣ ለዓይን የማይመች ነገር መቀየር ለሁላችንም ጠቃሚ ነው፤ ከእኛ በላይ ለልጆቻችን ጠቃሚ ነው። በዚያ መንፈስ ብናይ ጠቃሚ ነው። ሥራ ሲሠራ የሚበላሽ ነገር ደግሞ ካለ ማስተካከል ያስፈልጋል። በዋዛ ይሄን የሚያክል ልማት ሊመጣ አይችልም። አይታችኋል አሁን ከቦሌ መገናኛ ያለውን መንገድ! እስኪ ማታ ማታ ወክ አድርጉበት፤ በጣም እኮ ነው የሚያስደስተው፤ ግን እዚያ ብቻ ሳይሆን በየከተማዎቻችን እንዲሆን ሰፋ አድርገን ማሰብና መሥራት ይኖርብናል። የኮሪደር ልማት ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው፤ ዓለም እየመሰከረ ነው። እኔ ያቃተኝ ነገር፤ እንኳን መጥቶ ያየ ሰው ሄጄ የማገኘው ሁሉ ይጠይቀኛል ይሄን፣ ‹‹ብር ከየት ነው የመጣ፣ ነዳጅ አላችሁ ወይ፣ በሦስት ወር፣ በስድስት ወር የማያነሳ ሰው የለም። እና እባካችሁን እናንተም ብታግዙን ጥሩ ይሆናል፤ እንፍጠን፣ ኋላ ቀርተናል፤ ጊዜ እንዳያመልጠን፣ አብረን ብንተጋ ለማለት ነው፡፡
የመጨረሻው፤ ዲፕሎማሲን በሚመለከት የኢትዮጵያ ፖሊሲ እና ፕሪንሲፕል ከተቻለ ከሁሉም ጋር በሠላም መኖር ነው። ከሁሉም ጋር በትብብር መኖር ነው። ከሁሉም ጋር ሰጥቶ በመቀበል መርሕ መኖር ነው። ከሠላም ትርፋማ ስለምንሆን። መጀመሪያ ብሔራዊ ጥቅማችንን ዲፋይን አድርገናል። አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት፣ ብሔራዊ ጥቅማችን። የእናንተ ምንድነው፣ እንዴት እንተባበር፣ በምን ሒሳብ ነው የምንሠራው፣ ከዚህ ቀደም ድሃ ናቸው፣ በውስጣቸው ችግር አለባቸው፣ ፍላጎታቸውን እንዳሻቸው ማድረግ አይችሉም ብለው የሚያስቡ፣ ከባቢዎች ካሉ አሁን መታረም አለባቸው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፓወር ሐውስ ናት፤ ጥያቄና መልስ የለውም ይሄ፤ ትበለፅጋለች፤ የራሷን ብቻ ሳይሆን የዚህን ኮንቲኔንት ችግር ለመፍታት የራሷን ሚና ትጫወታለች። ይሄን አስቦ ነው ከኢትዮጵያ ጋር መነጋገር እንጂ እንዲያው ገፋ ገፋ አይሆንም፤ ማንም ቢሆን ማለት ነው። አናንቆ፣ አራክሶ፣ ምናምን ድሃ ናችሁ አይሠራም።
ለምሳሌ ስንዴ እያደገ ሲመጣ ስንዴ አለማም የሚለውን እናንተ ውስጥ ለመክተት ከዩክሬን ስንዴ ኢትዮጵያ መጣ የሚል ዜና በአስቸኳይ ዓለም ሁሉ ይናገራል። እየነገሩን ያሉት ተረጋጉ ይሉናል፤ አንረጋጋም፤ ፈጥነን እናለማለን፤ ያን ስብከትማ ሰምተን ኖርን እኮ። አሁን በቃን ድህነት አስጠላን እኛ። መለወጥ እንፈልጋለን። የሚችል ያግዘን የማይችል ደግሞ አይረብሸን ነው። ይሄ እንዲሆን የተከበረው ምክር ቤት መገንዘብ ያለበት ነገር፣ መርከብ በዙሪያው ባለው ውሃ በዙሪያው ባለው ባሕር፣ በዙሪያው ባለው ውዝውዝታ አይሰምጥም። መርከብን የሚያሰምጠው ውሃ መርከብ ውስጥ መግባት ሲጀምር ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ሠላም ወዳድ የጋራ ሕልም ያለን፣ ኢትዮጵያን የምናስቀድም፣ ኢትዮጵያ ከፓርቲ በላይ፣ ከክልል በላይ፣ ከሰፈር በላይ ከሆነችልን ማንም ሰው ኢትዮጵያን በኃይል ማንበርከክ አይችልም፡፡
አሁን ግን ያለው ሁኔታ ቅድም አልፌው ነው እንጂ እንቃወማለን እንታገላለን የሚሉት ሰዎች በሚያሳዝን ሁኔታ ከጠላት ጋር ይሠራሉ። ለጠላት መረጃ ይሰጣሉ የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው ያስፈጽማሉ። ኢትዮጵያውያን ከዚህ መቆጠብ አለብን እኛ፣ የጠላት መሣሪያ መሆን የለብንም። ለሀገር ልማት፣ ብልፅግና ሠላም በጋራ የምንሠራ መሆን አለብን።
ኤምኦኤ በሚመለከት ቻይናን በሚመለከት፣ ለተነሳው ጉዳይ እኛ ከቻይና በጣም ሠላማዊና በትብብር ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት አለን። እኩል ከአሜሪካ ጋር በጣም ሠላማዊ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ዝምድና አለን። ለምሳሌ የኮሚቴ ፎርም ስንሠራ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በጣም አግዘውናል። የክሬተርስ ኮሚቴ ኮቸር የሚያደርጉት ፈረንሳይና ቻይና ናቸው። በጣም አግዘውናል። እኛ የዚኛው ክላስ የዚኛው ክላስ፣ የዚኛው ጎራ የዛኛው ጎራ ተሰላፊ አባል አይደለንም። እኛ የኢትዮጵያ ሕልም ተሰላፊ አባል ነን። ለኢትዮጵያ ሕልም የሚመች ማንኛውም ሀገር ጋር እንሠራለን። ከማንም ጋር አንለጠፍም ከማንም ጋር ሆነን ማንንም አንወቅስም፤ ሠላም ማምጣት ከቻልን እናግዛለን ልማታችንን የሚያግዙ ካሉ አብረን እንሠራለን። ከምዕራቡም ከምሥራቁም ያለን ግንኙነት ሠላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ (በናሽናል ኢንተርስት) መሠረት ያደረገ ነው። በዛ መንፈስ ቢታይ ጥሩ ነው። የትኛውም የምናገለው የምናቅፈው አካል እንዳለ ተደርጎ ባይሳል። ሁሉም ሀገር አግዞን ከችግር እንዲያወጣን በትብብር እየሠራን ነው በተለይ መካከለኛው ምሥራቅ። ቅድም እንደተነሳው መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ኢትዮጵያ ስትከተል የነበረው ፖሊሲ ኮምፕሊትሊ ስህተት ነው። በሁሉም መመዘኛ፣ ቅርብ፣ ጎረቤት ከፍተኛ ሀብት ያለበት ልጆቻችን እየሄዱ ግርድና የሚቀጠሩበትን ቦታ ኢግኖር አድርገን ሌላ ቦታ መሄድ አንችልም። ከነሱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር አለብን። ባሕል ቋንቋ እምነት ያስተሳስረናል በብዙ መንገድ። እውነት ለመናገር መካከለኛ ምሥራቅ ለኢትዮጵያ እድገት እያደረጉ የሚያክል አስተዋፅዖ የሚያደርግ ማንም ሀገር የለም። በፋክትም ከታየ ማለት ነው፣ እና እዛ መልቲ ላተራል ተቋም መግባት ብቻ ሳይሆን ከዓረብ ሀገራት ጋር ያለንን ዝምድና በደንብ መመርመርና በደንብ ጠንካራ ወዳጅነት መፍጠር ያስፈልጋል። ዓለም ከነሱ ጋር እየተራቆተ እየተረባረበ እኛ እኛ ከዚህ ርቀን ብንኖር ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለውም። ገንዘብ አላቸው፣ እውቀት አላቸው፣ ልምድ አላቸው ቅርብ ናቸው። ገቢያችን ናቸው፣ የልጆቻችን የሥራ ቦታ ናቸው። በዚህ ስፕሪት ነው እየተሠራ ያለው፣ የተለያዩ ተቀዋም ውስጥም ንግግር ጀምረናል። ዓረብ ሊግንም ብናገኝ እንገባለን። ስለማይፈልጉን ነው እንጂ እንገባለን በገባንበት ቦታ ድምፃችንን እናሰማለን፡፡
እያየነው ነው፣ እኮ እኛ ሳንኖር ስንቀር ምን እንደሚሠራ እኮ አየነው። አሁን ብሪክስ ሲባል አቅላችሁ እንዳታዩት። አንዳንዶች እንደሚያወሩት አይደለም። በጣም በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ሁሉ ይቅር እኛ ዘራፊ አይደለንም፣ እኛ የሰው ነገር አንገድብም ብለን መናገር እራሱ ትልቅ ጥቅም አለው። ለምሳሌ ከሱማሌ ላንድ ጋር የነበረን ኤምኦዩ ኢትዮጵያ የሶማሌያን ግዛት ልትወስድ ተስማማች የሚል ትርክት ነው መስጠት የተሞከረው። እኛ ግን ከሶማሌ ላንድ ጋር ስንፈራረም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት እንኳን ብለናቸው እምቢ ብለው የሃምሳ ዓመት ሊዝ ነው የፈረምነው። እንዴት ነው የሃምሳ ዓመት ሊዝ መሬት መቀማት የሚሆነው? ብዙዎች እኮ ሃምሳ ዓመት አትፈርሙ፣ መቶ መሆን አለበት፣ ሎንግ ተርም ኢንቨስትመንት ነው እያሉ ስምምነቱ ስላልተሳካ ለሃምሳ ዓመት ነው ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረም ነው እኛ። ግን የሚባለው ኢትዮጵያ ልታስፋፋ ነው። አይደለም በሥልጠናው ላይ አንስቸዋለሁ እዛ ያልነበራችሁ ሰዎች እኛ ከሶማሌያ ቀጥሎ ሁለተኛ ትልቅ የሶማሌ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፣ ወንድሞቻችን ናቸው፣ ከሶማሌ ጋር ምንም አጀንዳ የለንም። እኛ አጀንዳችን ኢኮኖሚያችን እያደገ ነው ሕዝባችን እያደገ ነው፣ ከምፅዋ እስከ ሶማሌ አምስት ሺ ኪሎ ሜትር ነው። ትልቅ ሃብት ነው። ልናለማው አልቻልንም ሌሎች ከሌላ ቦታ መጥተው እንደፈለጉ የሚያደርጉት ትንሽዬ አክሰስ ጋራንቲ ስጡን። እኛ ከፈረስን ሁላችሁም ትጠፋላችሁ ትልቅ ስለሆንን ጥያቄያችን ይሄ ነው። ይህ ጥያቄ የገባቸው አሉ ያልገባቸው አሉ። እንዲገባቸው የሚጠይቁ አሉ፣ የኛ ሥራ ማስረዳት ነው። ከኤርትራም ይሁን ከጅቡቲም ይሁን፣ ከሶማሌም ይሁን ከኬንያም ይሁን ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት ሠላማዊ ጉርብትና ነው። ለኢትዮጵያ የማያዋጣት በሠላም በሰጥቶ መቀበል አብሮ ማደግ ነው። ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ግን ከእንግዲህ በኋላ ኢትዮጵያን ኤክስትራክት እያደረጉ ኢትዮጵያን በሰፈር እያባሉ መኖር አይቻልም። እንደዛ አይቻልም። ኢትዮጵያን አክብሮ የኢትዮጵያን ጉርብትና ወዶ ከኢትዮጵያ የሚደረግ ጥቅም ማንኛውም ነገር ካለ በደስታ ችግር የለውም። በምዝበራ ግን መሆን የለበትም። ከዚህ ውጪ ከምዕራቡም ከምሥራቁም ተባብረን ሀገር መገንባት ነው የምንፈልገው፤ እኛ ቅጥረኞች አይደለንም። ለሆነ ቡድን ተቀጥረን በሱሙኒ ተገዝተን የሆነ ቡድን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች ሳንሆን አርበኞች ነን። ኢትዮጵያን መገንባት እንፈልጋለን።
ይሄን አምኖ ያከበረ ማንም ሀገር በከፍተኛ ደስታ አብረን መሥራት እንፈልጋለን። አሁን ከኤርትራ ጋር አንዳንድ ወሬ ይነሳል። የምንፈልገው ሠላም ነው። ከዛ የከፋ ነገር ካልመጣ በስተቀር በእኛ ኢኒሼቲቭ በኤርትራ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ነገር አይፈጸምም። ጅቡቲ እንኳን እኛ ልንረብሽና ልንነካቸው ቀርቶ የሚነካቸውም ካለ አንቀመጥም። እነሱ ከተነኩ እኛ የለንም። ሱማሌ በሺ የሚቆጠር ሰው ነው እኮ የሞተብን፤ በሺ የሚቆጠር ሰው እኮ ነው የሰዋነው፤ ለጋራ ሠላም ብለን። አሁንም የምንፈልገው እሱን ነው። ሱማሌ አካባቢ መስከን መረጋጋት፤ ናሽናል ኢንተርስት ማስቀደም እንዲችሉ ጊዜ ሰተናል እንታገሳለን። ቀልብ እንዲገዙ ሰብር እንዲያደርጉ እንታገሳለን። ግን ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት። አለም ዛሬ ይስማ! የቀይ ባሕር አክሰስ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል።
በዚህ ጉዳይ ሻይ የምናደርግ የምንደብቅ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። በጦርነት አንፈልግም፤ በኃይል አንፈልግም፤ በቂ ሪሶርስ ነው። በማንኛውም ሕግ፣ በማንኛውም የሀገር ልምምድ ኢትዮጵያ ይገባታል። ብዙዎች እኮ ነውር ነው ይላሉ። 120 ሚሊዮን ሕዝብ መቆለፍ ነውር ነው ይላሉ። አንዳንድ የተገዙ ኢትዮጵያውያን ባይገባቸውም ወይ እኛ ወይ ልጆቻችን ያሳኩታል ጥርጣሬ የለውም። እውነት ስለሆነና ምክንያታዊ ነገር ስለሆነ። ይሄን አስታኮ ግን ነገ ውጊያ ይነሳል ብለው የሚያስቡ ሰዎች አንዋጋም ከማንም ጋር። መዋጋት ፍላጎት የለም።
ሁለተኛው ጉዳይ ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ ሀገራት የሚል ስጋት ያለባቸው ሰዎች አልፎ አልፎ ስለሚነሱ፣ ኢትዮጵያን ማንም ሰው ዛሬ በኃይል መውረር አይችልም። ማንም! ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አለ፤ በቂ። ስንገዛ ስንሸምት የነበርንባቸውን በውጊያ ክፍተት የገጠሙንን ነገሮች ማምረት ጀምረናል። እናመርታለን ሰው አለን፤ ጀግኖች ነን ሰው አንነካም፤ ከነኩን ግን ለማንም አንመለስም። ስጋት የለብንም። በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ብዙም አቅም ባልነበረበት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ዓድዋ ላይ ሄደው አሸንፈው ነፃነት ማስከበር ከቻሉ ዛሬማ፤ ያኔ እኮ አምስት ሚሊዮን ነን። ዛሬ እኮ 120 ሚሊዮን ነን። የጀግንነት ደሙ ደግሞ እንዳለ ነው። እና ስጋት አይግባችሁ ማንም ቢመጣ አሳፍረን እንመልሳለን ማንንም ግን አንነካም እኛ። በዛ እሳቤ መታሰብ አለበት ልማት፤ የውጪ ኢንቨስትመንት፣ ትብብር እንዲመጣ ያስፈልጋል።
ህዳሴን በሚመለከት እውነት ለመናገር ለግብፅ ለሱዳን፣ ትልቅ ድል ነው። ስጋት ነበር ውሃው ሲያዝ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት ነበር። እንደምታዩት ውሃውን ይዘናል። ግድቡ እኮ በነገራችን ላይ አሁን ድልድዩ ታውቃላችሁ ከላይ ያለው ድልድይ ተገጥሟል እኮ። ውሃ ይዘናል፣ ግድቡ አልቋል። ምንም አይነት ችግር በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት አልገጠመም። ምን አልባት ግን ነገ ግብፅ ወይ ሱዳን የሆነ የውሃ ችግር ቢያጋጥማቸው ስላለን ልንለቅላቸው እንችላለን። ባይኖረን ምን እንደርጋለን? ሲቸገሩ ማየት አንችልም። ወንድሞቻችን ናቸው እናግዛለን። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሙሉ ኮሚትመንት አላት፤ ማንንም መጉዳት አንፈልግም። ኢትዮጵያ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት ግን ማንም ማቆም አይችልም። ተሞከረ እኮ፣ በነገራችን ላይ የተከበረው ምክር ቤት ሕዳሴ ግድብ ባለፉት አምስት ዓመታት አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ያዋጣችሁት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሺ የሚቆጠር ሰው ገብረናል። ያላስታጠቁብን እኮ የለም፤ ተዋግተን ነው የሠራነው። ማቆም አይቻልም ማለት ነው። በገንዘብ አይቻልም። በፕሮፖጋንዳ አይቻልም። በጦርነት አይቻልም። ወደፊትም አይቻልም። የምንፈልገውን ነገር ልክ እንደህዳሴ በእኛ ጉልበት በእኛ አቅም በሠላማዊ መንገድ እናሳካለን። ማንም ላይ ጦር የመስበቅ ፍላጎት የለንም። ማንም ኢትዮጵያን እንዲደፍር ግን አንፈቅድም። አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም