ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በግፍ ለተገደሉ ከፍተኛ አመራሮች የኀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በሀገራችን ከፍተኛ የጦር እና የሲቪል አመራሮች ላይ በተፈፀመው ህገ-ወጥና ዘግናኝ ፋሽስታዊ ግድያ የተሰማቸውን ጥልቅና ልባዊ ኀዘን ገልጸዋል።
አንድ ዓመት ባስቆጠረው የለውጥ ጉዞና የመደመር ጎዳና ላይ እያለን በጓዶቻችን ላይ የተፈፀመውን ልብ ሰባሪ ጥቃትና ሀገራችን የገጠማትን ብርቱ ፈተና ስናስብ ልባችን በከፍተኛ ኀዘን የሚደማው ያለምክንያት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰማእታቱ እንደ አለት የፀኑ፣እንደአልማዝ የጠነከሩ፣ሀገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የማገልገል ዓላማን ያነገቡ፣ ዓላማቸውን ሳያሳኩ አንገታቸውን ላለማዞር የቆረጡ፣ይህንንም በተግባር ያረጋገጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ነበሩ ብለዋል።
ከዚያ በላይ ልብን የሚያደማው እነዚህ ሰማዕታት የለውጡ የምስራች ገብቷቸው የሚገኘውን ሀገራዊ ዋጋ ተረድተው እኛንም ወደታያቸው ራዕይ ሊወስዱን አቅም የነበራቸው ግንባር ቀደም የለውጡ ታላሚዎች መሆናቸውን ስናስብ ነው ነገሩ ከምንጊዜውም የቀደመ ከምናስበውም ውጪ ልብ የሚያደማ ሆነብን ሲሉ ገልጸዋል።
ሰማእታቱ ሀገርን አንድ ማድረግ፣ህዝብንም በሰላምና በዴሞክራሲ ጎዳና መውሰድ ከባድ መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ ተረድተው ነበር ብለዋል። ሆኖም ግን ትግሉ ከሰውነት በታች ከወረዱ፣ ከስልጣን ውጪ ሌላ የማይታያቸው፣ ከመግደል ውጪ ሌላ ዕውቀት ካልዞረባቸው፣ ከጉልበት ሌላ መፍትሔ ከማይታያቸው፣ ከግል ጥቅም ባሻገር ለማየት ከማይችሉ ጋር እንደሚደረግ ተረድተነው ነበር በማለት በመግለጫቸው አትተዋል።
ታላቂቱን ሀገር ማሳነስ፣የከበረውንም ህዝብ ማዋረድ ለግስጋሴያችን ልጓም፣ለመንገዳችን እንቅፋት ማኖር ሙያ የሚመስላቸው እዚህም እዚያም አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዴሞክራሲ ህዝብ ያተርፋል፤ እነሱ ግን ይከስራሉ፤ ከስልጣኔ ህዝብ ይጠቀማል፤ እነሱ ግን ይጎዳሉ፤ ከህብረ ብሄራዊነት ሀገር ይበለጽጋል፤እነሱ ግን ይደኸያሉ፤ በፍቅርና በይቅርታ ኢትዮጵያ ትታከማለች፤እነሱ ግን ይታመማሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለህዝብና ለሀገር መሥራት የሚችል ብርቱ ልብ፣ሰብዓዊ አንጀት፣ጠንካራ ክንድ፣ አርቆ አሳቢ አዕምሮ፣ አመዛዛኝ ህሊና፣ ጠቢብ ልቦና የላቸውም። አርበኝነታቸው ለአሉባልታና ለሀሜት፣ ጀግንነታቸው ለሴራና ለነገር፣ ጉብዝናቸው ለተንኮልና ለጭካኔ ነው።
በአዕምሯቸው ካለው ሃሳብ ይልቅ በወገባቸው ያለው ዝናር፣በልባቸው ካለው ጥበብ ይልቅ በእጃቸው ያለው ሽጉጥ የሁሉም ነገር መፍትሔ ይመስላቸዋል። ሃሳቡን ማሸነፍ ሲያቅታቸው፣ሃሳቢን ለማጥፋት ተነሱ፤ አዕምሮ ሲጎድላቸው፣ባለአዕምሮን ለማጥፋት ቆረጡ፤ጥበብ ሲሰፋባቸው ጠቢባኑን ለማስወገድ ፈጠኑ፤ሀገር ወደ ዘመነ አብሮነት ስትጓዝ እነሱ ተቃራኒውን መረጡ፤በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ የተጠላውን መንገድ እንደተከተሉ አስምረውበታል።
ሴረኞቹ ዓላማቸው ሦስት ነገሮችን ማሰናከል መሆኑ ወለል ብሎ እንደሚታይ የዘረዘሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንድ በኩል የለውጡን ሐዋርያት በመግደል ለውጡን ማስቆም፣በሌላ በኩል ህዝባችንን በተሳሳተ ምስል እርስ በርሱ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ማድረግ፣በሦስተኛ ደረጃም የፀጥታ ኃይሎቻችንን ሞራል እና ክብር በመንካትና አንድነቱን በጎጥ በመከፋፈል ሀገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነበር ብለዋል።
በሂደቱም ጀግኖቹ እንዲህ በቀላሉ ማጣት እንደ እግር እሳት ይለበልባል፣እንደጎን ውጋት ያሳቅቃል በማለት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የተሰው ጀግኖችን ለማግኘት ስንት እንደደከመች፣ስንት እንደተሳለች፣ስንት ወጥታ እንደወረደች በማይረዱ በገዛ ልጆቿ ልጆቿን ማጣቷን እንስተዋል። በአገር እየኖሩ በአገር እየከበሩ ሀገር በማይገባቸው የልጅ ደመኞች ውድ ልጆቿን መቀማቷን ጠቅሰዋል።
ያን የመሰለ ሀገርን የካደ ሰንካላ ክፉ ምኞት ሲጀምርም የከሸፈና የተሸነፈ አስተሳሰብ በመሆኑ ህዝባችን በተለመደ አገር ወዳድነትና በፅኑ የአርበኝነት መንፈስ በእንጭጩ አምክኖታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሩና በወገኖቹ ጥቃት የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአባቶቹ እንደለመደው ከሀገሩ ልጆችና ከጀግኖቹ ጋር በአንድነት በመቆም ክፉውን ሴራ አክሽፎታል ብለዋል።
በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ፖለቲከኞቻችን በአንድነትና በፅናት በመቆም ኢትዮጵያዊነት እንደጥሬ ወርቅ ተፈጥሮ እንደ ጥሩ ወርቅ ነጥሮ እንደማይወጣ ዳግም መረጋገጡንና ክልሎች በጋራ በመቆም በመደጋገፍ የመኖርን ፋይዳ ማሳየታቸውን አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደገለጹት ሀገር በተስፋና በደስታ ዘመን ብቻ ሳይሆን በመከራና በችግር ዘመናትም ውስጥ እንደምታልፍ ከታሪክ ብቻ ሳይሆን ከመኖርም የምንረዳው ሐቅ ነው። ምንም እንኳን ሃሳበ ስንኩላን ሲነገራቸው ባይሰሙም፣ሲመከሩ ባያዳምጡም ምህረትና ይቅርታ ባይገኝላቸውም፣የሀገራችን ጠላቶች ደግመው ደጋግመው መገንዘብ የሚኖርባቸው አንድ ዘላለማዊ እውነት ሀገራችን አእላፋት አዝማናትን አልፋ አሁን በምትገኝበት የታሪክ ምዕራፍ የደረሰችው ጉዞዋ በፀጥታና በሰላም ውስጥ ብቻ ስለነበር አይደለም።
ጨለማውንም እየገለጠች፣ ጉዳባውንም እየተሻገረች፣ማዕበሉን እያለፈች፣አቀበቱን እየዳኸች፣ በእሳትና በአውሎ ንፋስ መካከል እየሰነጠቀች በመጓዝ ጭምር አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ቀጥና የማትበጠስ፣ተዳፍና እሳቷ የማይጠፋ፣ተናግታ የማትፈርስ፣ተናውጣ ስሯ የማይበጠስ ሀገር ናት ብለዋል።
ህግ አክባሪ ዜጎቻችን ደግሞ ደጋግሞ በተለያዩ መድረኮች የህግ የበላይነትን ለማጠናከር መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ሲመክሩ በጥሞና እንዳደመጡ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግደል መሸነፍ ነው ስንል የሃሳብና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሉዓላዊ ሃሳብ እንጂ በጥይት እንደማይሸነፍ በመረዳታችን ነበር ብለዋል።
እንደእነሱ የፀብ ብረት መወልወልና ባሩድ መቀመም ስለማንችል ሳይሆን ታላቁ ጀግንነት ፍቅርና ይቅርታ፣እርቅና ሰላም ስለሆነ እንደሆነ አብራርተዋል።
በሀገሪቱ አንድነት እና ሉአላዊነት፣ዘላቂ ጥቅምና ክብር ላይ ድርድርም ሆነ ትዕግስት ፈፅሞ አይኖረንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያለቀስን ብንቀጥል የጓዶቻችንና ዓላማ አናሳካም፤ ተስፋ ብንቆርጥ የጓዶቻችንን ሰንደቅ ከፍ አናደርገውም ሲሉ ገልጸዋል። ይልቁንም የገጠመን ፈተና እንዳይደገም አድርገን የህገ-ወጥነትን በሮች ሁሉ እንዘጋለን ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያደረሰን መግለጫ ያመለክታል።
ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011