በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ይገኛል:: ከተማዋ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ በኩል ይታይባት የነበረውን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት እያስቻለ ነው:: በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የከተማዋን ዋና ዋና ማዕከላትና የቱሪስት መስሕቦችን ደረጃቸውን በጠበቁ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገዶች የማገናኘት ሥራዎች ተከናውነዋል:: ለእነዚህ አካባቢዎች የማይመጥኑ ግንባታዎችን እንዲወገዱ ተደርገው ቦታዎቹን በአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የታክሲና የአውቶብስ ተርሚናሎች፣ ፋውንቴኖች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ካፌዎችና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ወዘተ ተተከትውባቸዋል::
ልማቱ በሚያልፋባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕንጻዎች ቀለም፣ አጥርና የመሳሰሉት አንድ አይነት እንዲሆኑ፣ በዋና ዋና መንገዶች የሚገኙ ንግድ ቤቶች በመስታወት፣ በመብራት፣ ወዘተ. በወጣላቸው ደረጃ መሠረት እንዲለሙ ተደርጓል:: መሠረተ ልማቶች በመሬት ውስጥ እንዲያልፉ የተደረገ ሲሆን፣ የመንገድ መብራቶች ለአካባቢው ብቻም ሳይሆን ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን የሚያላብሱ እንዲሆኑ ተደርገዋል::
ይህ የከተማዋን ገጽታ በሚገባ የገነባ፣ በመሠረተ ልማት በኩል የነበረባትን መሠረታዊ ችግር የቀየረ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በቅርቡ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ተሸጋግሯል:: ይህም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች መተግበር ጀምሯል::
የኮሪደር ልማቱ ወደ ክልል ከተሞችም እንዲዘልቅ ተደርጓል:: ልማቱን ወደ 31 በሚደርሱ ዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ለመተግበር በከተሞቹ ተነሳሽነት እየተሠራ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል:: ሀገር አቀፍ የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ከሚካሄዱባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባን ጨምሮ በሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሻመኔ፣ ጅማ፣ ነቀምቴ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ቡታጅራ፣ ሆሳዕና፣ ቦንጋ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ፣ ሶዶ፣ ማያ፣ ዲላ፣ ድሬዳዋ፣ ሮቤ፣ ሰመራ፣ ሀዋሳ፣ ይርጋለም፣ ኮምቦልቻ፣ ወራቤ፣ ሚዛን አማን፣ አርባምንጭ ይገኙበታል::
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ አማን አሰፋ(ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየተከናወነ ያለው አንደኛ የተረሱ ወይም ያረጁ የከተማዋን አካባቢዎች ማደስ የፕሮጀክቱ አካል በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሥራ ኮሪደርን ብቻ ሳይሆን ያረጀ የከተማን አካባቢ ማደስ የሚለውንም የፕሮግራሙ አንዱ አካል ማድረጉን ጠቁመዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ሁለተኛው የልማቱ አካል የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸውን መንገዶች ደረጃ ማሳደግ እና የእንቅስቃሴ ቅልጥፍናን መጨመር የሚለው ነው። የከተማዋ የኮሪደር ልማት እውን እስኪሆን ድረስ በከተማዋ የእግረኛም ሆነ የተሽከርካሪ መንገድ ተቀላቅሎ የሚታይበት ነበር፤ የመኪና መንገድ በማስፋት ዘና ያለ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ፣ የእግረኛ መንገድን ማስፋትና ምቹ ማድረግ፣ የብስክሌት መንገድ መክፈት እና የከተማ ውበትን መጨመር፣ እይታን ግልፅ ማድረግ በኮሪደር ልማቱ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ:: ከተሞች የሚታወቁበት የራሳቸው የሆነ የከተማ ምልክት እንዲኖራቸው ማድረግም ሌላ በልማቱ የሚከናወን ተግባር ነው።
ይህ የኮሪደር ልማት ሲሠራ ከክፍተት ነፃ ነው ማለት አይቻልም ያሉት አማን (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ ላይ የታየው ክፍተት በአዲስ አበባው ቀጣይ የኮሪደር ልማትና በክልል ከተሞች የኮሪደሪ ልማት ላይ ዋጋ እንዳያስከፍል ምርጥ ተሞክሮዎች እየተቀመሩ እንደሚከናወን አስታውቀዋል::
አማን (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ለሀገራዊ የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ሥራ ሰፊ ተሞክሮ ይወሰዳል። በምርጥ ተሞክሮ ደረጃ ከሚወሰዱት መካከል በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ በመዲናዋ የተደረገው ወደ 47 ኪሎሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥራ የተቀላጠፈ መሆን አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀ ነበር። ከዲዛይን አኳያም ከነውስንነቱ አካባቢዎችን ሊመጥን የሚችል ዲዛይን አለው። እነዚህም እንደ ምርጥ ተሞክሮ ይወሰዳሉ። ሥራው በአነስተኛ ወጪ የተከናወነ ነውና የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነት ሌላው ሊወሰድ የሚገባ ምርጥ ተሞክሮ ነው::
ድክመቶቹን ማረሙ እንዳሉ ሆኖ ሁለተኛ ፕላን እንዳይደረግ እና ዳግም አፍርሶ መሥራት ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ ለብዙ ዓመታት በሚሆን መልኩ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን ባለሙያው አስታውቀዋል:: ድክመት አያጋጥምም ተብሎ እንደማይወሰድ እና መሰል ችግር በማንኛውም ፕሮጀክት ሊኖር እንደሚችልም ጠቅሰው፣ የጥራት ችግሮች መልሰው እንዳያጋጥሙ እስከ አሁን ከተካሄደው የኮሪደር ልማት ትምህርት የሚወሰድ መሆኑንም አስታውቀዋል:: ለማንኛውም ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የኮሪደር ልማት ሥራውን ተሞክሮ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የልማት ተነሺዎች ከኖሩበት አካባቢ እንዲነሱ ሲደረግ ቀድሞ ይመሩ የነበሩትን ሕይወት በማይቀንስ መልኩ መፈጸም እንዳለበትም አስታውቀው፣ የቆዩበትን የኑሮ ዘይቤ በማያናጋ ሁኔታ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የማንሳቱ ሥራ መፈጸም ይኖርበታል ሲሉም መክረዋል::
በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ለሚነሱ ሰዎች በቂ ካሣ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ጠቅሰው፣ ለከተማ ልማት ተነሺዎች ካሣ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ዘላቂ ማቋቋሚያ ሊሆን የሚችል ሥራም መሠራት አለበት ሲሉ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ተነሺው እንዲኖር የሚደረግበት ቦታ ያለውን አዋጭነት ጨምሮ በተቻለ መጠን ማኅበራዊ ኑሮውን በማይነካ መልኩ ተጠንቶ እና ተገምግሞ በተጠና መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለበትም ያመለክታሉ።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሲታይ ዘመናዊ የእቅድ አተገባበርን የተከተለ ነው ያሉት አማን (ዶ/ር)፣ ለባለ ይዞታ የልማት ተነሺዎች ተለዋጭ ቦታ ሲሰጣቸውም ይከተሉት የነበረው የኑሮ ዘይቤ እንደ እድር፣ እቁብ እንዲሁም የመተዳደሪያ ሥራዎቹን የሚያሳጣ ነው ወይስ አይደለም የሚሉትን እና ዘላቂ አማራጮችን ከግንዛቤ ያስገባ ጥናት መካሄዱንም አመልክተዋል።
አማን (ዶ/ር) እንደባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ የኮሪደር ልማቱን በአዳዲስ ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚያደርጉ አካላትም በቅድሚያ የጠራ ፕላን ማዘጋጀት አለባቸው ይላሉ። ፕላን በሚያዘጋጁት ወቅትም በዓይን በሚታየው ግንባታ ላይ ብቻ ማተኮር እንደሌለባቸውም አስታውቀው፣ ግንባታው ምን ነገሮችን ይዞ እንደሚመጣ በየትኛው መሬት እንደሚቀመጥ እና በመቀመጡ ምን ውጤት እንደሚያመጣ ዕቅዱ ተግባራዊ ሲደረግ ምን የተሻለ ትርፍ እንዳለው በታቀደ መልኩ መሥራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የከተማ ፕላን በከተማው ላይ የሚለማ ወይም ወደ ከተማዋ ዳርቻ የሚሰፋ ሊሆን ይችላል ሲሉም ባለሙያው ገልጸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሁኔታ ከዚህ አንጻር ሲታይ በከተማው ላይ የሚለማ መሆኑን ይናገራሉ። በሌሎች ከተሞች ግን እንደ ሁኔታው ከከተማ ውጪ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ በኮሪደር ልማት ሥራው በልማት የሚነሳ አካል ካለ ቀደም ተብሎ ኅብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ለእዚህም ውይይት ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል:: የሚነሳውን ማኅበረሰብ የማሳመን ሥራ ከተካሄደ በኋላ ወደ ማንሳቱ ሥራ መግባት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን ሥራው ከቅሬታ ነፃና ውጤታማ እንደሚሆን አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሦስተኛነት መታየት ያለበት ምንጊዜም መታሰብ የሚገባቸው የዚህ ዓይነት የከተማ ልማት ሥራዎች፣ ለ50 እና ለ60 ዓመታት የሚሠሩ መሆናቸው ነው:: በመሆኑም ለቅንጅት ሥራ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል:: ቅንጅት ሲባል ጉድጓድ ሲቆፈር ያለውን ቅንጅት ብቻ የሚመለከት አይደለም፤ በከተማ ልማት በኩልም በሚካሄዱ የመምራት፣ የማስተባበር እና የምርምር ሥራዎች ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ መፈጠር ይኖርበታል። ቅንጅት ከፕላን ጀምሮ እስከ አፈፃፀም ግምገማ ይዘልቃል።
የኮሪደር ልማቱ የመሠረተ ልማት ፕላን በመሆኑም ይህ የሚመለከተው አካል ፕላን የሚያደርገው ነው። በመሠረተ ልማቱ ውስጥ የውሃ፣ የመብራት እና የቴሌኮም፣ ወዘተ መስመሮች አሉ፤ በመሆኑም የፋይበር ኬብል፣ የኮፐር ኬብል ያካተቱ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ይከናወናሉ። እነዚህን የሚያስፈፅም እና የሚዘረጋ አካል አለ። እነዚህን መዘርጋት ሲያስፈልግ ቦታ ከማመላከት ጨምሮ የእነዚህ ተቋማት ቅንጅት ያስፈልጋል።
አማን (ዶ/ር) በሀገሪቱ በዋነኛነት 31 ከተሞች ለኮሪደር ልማቱ ተነሳሸነት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፣ እንደ አርባምንጭ ከተማ በመሳሰሉት ከተሞች የተጀማመሩ ሥራዎች እንዳሉ አስታውቀዋል። ለእነዚህ ከተሞችም የአቅም ግንባታ እና የክትትል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቅርቡም ለከተሞቹ ስትራቴጂ ዲዛይን በማድረግ የአፈፃፀም መመሪያ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።
ከዚያ ባሻገር የኮሪደር ልማት ሲሠራ ምን ምን ነገሮችን ማካተት አለበት? ይዘቱ ምን መሆን ይኖርበታል? የሚሉትን መመልከትና የቴሌኮም፣ የውሃ፣ የመብራትና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ቅንጅት አንዱና ትልቁ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህ ሥራዎች ወጥና በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ አንዱን መሠረተ ልማት ለመሥራት አንዱን የማፍረስ ችግር ለማስቀረት የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥልጠና እንደሚሰጥ አሰታውቀዋል።
ይህንን የሚሠሩ አማካሪ ድርጅቶችም ምን ምን ማሟላት እንዳለባቸው በሚቀጥለው ፕሮግራም በማዘጋጀት ወደ ተግባር እንደሚገባም ጠቁመዋል። እንደ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዘንድሮ ቅድሚያ የተሰጠው የ2017 እቅድ የኮሪደር ልማት መሆኑን ጠቅሰው፣ አተገባበሩም ክትትል እንደሚደረግበት አስታውቀዋል:: የኮሪደር ልማቱ ዲዛይን ሲደረግ እንዲሁም ወደ አፈጻጸም ሲገባ የቅንጅት ጉዳይ ታሳቢ እንደሚደረግበት አመላክተዋል።
ከ31 የክልል ከተሞች ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኞቹ ወደ ተሟላ ትግበራ አልገቡም ሲሉም ጠቅሰው፣ የተቀሩትም ወደ ልማቱ እንዲገቡ ለማድረግ የከተሞች የአተገባበር ስልት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የክትትል፣ የቴክኒክ ድጋፍ ሥራውን ከእስከአሁኑም በላይ በማጠናከር እንደሚሠራ ገልጸው፣ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር ዲዛይን ሲሠራ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ምልከታ እንዲደረግበት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በሀገራዊ የኮሪደር ልማት ሥራው የፋይናንስ ምንጩ በዋናነት የሚገኘው ከመንግሥት የፕሮጀክት በጀት መሆኑንም ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ በራሱ ፋይናንስ ልማቱን ማካሄዱን በአብነት አንስተዋል። አዲስ አበባ ራሱን ችሎ ሌሎችን እየደገፈ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ሌሎች ከተሞችም ከሚሰበስቡት ገቢ 45 በመቶ በላይ የሚሆነውን ለልማቱ እንዲያውሉ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዳዲስ አገልግሎቶችን ያካተተውን የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማትን አስመልክተው በቅርቡ ሲገልጹ፤ ‹‹ከተማችንን የማስዋብና የመቀየር ከፍተኛ መሻትና ጥማት አለን። ከተማችንን ደግሞ የምንሠራው እኛ ነን፤ ሌላ የሚሠራልን ሰው የለም፤ ሌላው አስተያየት ሊሰጥ፣ ሊተች ይችላል እንጂ የኛን ሀገር ማንም አይሠራልንም›› ብለዋል። መንግሥት ለሕዝብ ቃል በገባው መሠረት ሁኔታዎች ምቹ ባይሆኑም፣ በከፍተኛ ትጋት ያማረ ሥራ መሥራት መቻሉን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ በቅርቡም ግንባታው ስለተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ፤ የኮሪደር ልማቱ በስምንት ኮሪደሮች እንደሚካሄድ ማስታወቃቸው ይታወሳል:: የኮሪደር ልማት በአጠቃላይ 2817 ሄክታር የቦታ ስፋት ሲኖረው 132 ኪሎሜትር ርዝመት ይሸፍናል:: ለቀበሌ ቤት ተነሺዎች ምትክ ቤቶች ተዘጋጅተዋል::
ተነሺዎች ያላቸው ማኅበራዊ ትስስር እንዳይበተን በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ ይደረጋል ሲሉ ከንቲባዋ ጠቅሰው፣ ከ500 በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆችም ለነዋሪዎቻቸው ዝግጁ መደረጋቸውን አስታውቀዋል::
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንደገለጹትም፤ በአንደኛው ዙር የኮሪደር ልማት ለአንድ ሺህ የልማት ተነሺዎች ስምንት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ካሳ ተከፍሏል። 50 ሄክታር ምትክ ቦታ ተሰጥቷል፤ ለ50 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በዚህ ሥራም ከ52 ኪሎሜትር በላይ የተሽከርካሪ መንገድ፣ ከ96 ኪሎሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ 100 ኪሎሜተር የብስክሌት መንገድ፣ አራት የእግረኛ መሿለኪያ ቦታዎች ተገንብቷል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም