የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ሌላ ምዕራፍ

የምሥራቅ አፍሪካ ከዋክብት አትሌቶች ለረጅም ዓመታት በተለይም በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ስፖርቱን ወደፊት በማራመድ ዘመን የማይሽራቸው ታሪኮችን አኑረዋል:: ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እያሳዩት የሚገኘው ብቃትም የሰው ልጅ የአቅም ጥግ ገደብ እንደሌለው እያስመሰከረ የማይቻል ነገር እንደሌለ አረጋግጧል::

በ19ኛው ክፍለዘመን ወንዶች ማራቶንን ለ3 ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች በሚቀሩት ሰዓት ያጠናቅቁ ነበር:: ከመቶ ዓመት በኋላ ግን ይህ ሰዓት ተሻሽሎ ከ2 ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል:: ለዚህም የምሥራቅ አፍሪካ ከዋክብት አትሌቶች የተጫወቱት ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል::

የወንዶች ማራቶን ክብረወሰን ባለፉት ሃያ ዓመታት ብቻ አስር ጊዜ ተሻሽሏል:: ከነዚህ ክብረወሰኖች ውስጥ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የሁለቱ ባለቤት ሲሆን ሰባት ያህል ክብረወሰኖች በኬንያውያን አትሌቶች ተሻሽለዋል:: ይህም የምሥራቅ አፍሪካ የርቀቱ ኮከቦች የማያባራ ፉክክር ማራቶንን ዛሬ ለደረሰበት ታላቅነት እንዳበቁት ማሳያ ነው::

የሴቶች ማራቶንን በተመለከተ ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓለም ክብረወሰን ሌላ መልክ ነበረው:: እኤአ 2003 ላይ እንግሊዛዊቷ ታሪካዊ አትሌት ፓውላ ራትክሊፍ በለንደን ማራቶን በ2:15:25 አዲስ ዓለም ክብረወሰን ካስመዘገበች ወዲህ ለሁለት አስርተ ዓመታት ገደማ የሴቶች የማራቶን ክብረወሰን ለውጥ አልታየበትም:: 2019 ላይ ግን ኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌ በቺካጎ ማራቶን 2:14:04 በማጠናቀቅ ቆሞ የነበረውን የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን አንድ ርምጃ ወስዳዋለች:: ይህ በሴቶች ማራቶን የማይቻል የሚመስለውን ክብረወሰን በይቻላል የለወጠ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነበር:: ያም ሆኖ የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ልክ እንደወንዶቹ በጥቂት ዓመት ልዩነት ዳግም ሳይሰበር ለመቆየት ተገዷል::

ከአራት ዓመታት በላይ ሳይሻሻል የቆየው የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ዳግም እስኪሰበር ሌላ ሁለት አስርተ ዓመታት አልጠበቀም:: ከአራት ዓመት በኋላ በ2023 የበርሊን ማራቶን ብዙዎች ለማመን በተቸገሩበት አስደናቂ ብቃት ኢትዮጵያዊቷ ብርቅዬ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ከአራት ደቂቃ በላይ በማሻሻል በ2:11:53 አዲስ ክብረወሰን ለመጨበጥ በቃች:: ይህም በሽርፍራፊ ሰከንዶች ለማሻሻል ከብዶ የነበረውን የርቀቱን ክብረወሰን በሩጫው ዓለም ሰፊ በሚባል ልዩነት ማሻሻል እንደሚቻል ከማሳየቱም በላይ የርቀቱ ኮከብ አትሌቶች የተሻለ ሰዓት እንዲያስቡ ትልቅ ተነሳሽነትን ፈጥሮባቸዋል:: ይህም ተነሳሽነት በሴቶች ማራቶን ታሪክ ከአንድ ዓመት በኋላ ሌላ አዲስ የማራቶን ክብረወሰን ለአትሌቲክሱ አበርክቷል::

ባለፈው ዓመት የወንዶች ማራቶን ክብረወሰንን ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕተም በ2:00:35 ሰዓት ያሻሻለበት የቺካጎ ማራቶን ከትናት በስቲያ ለ46ኛ ጊዜ ሲካሄድ ኬንያዊቷ ሩት ቼፕጌቲች 2:09:56 ሰዓት በማጠናቀቅ አምና በትዕግስት የተያዘውን ክብረወሰን ከሁለት ደቂቃ ባልተናነሰ ሰዓት በማሻሻል የሴቶችን የማራቶን ክብረወሰን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግራዋለች::

ለዚህ አዲስ ምዕራፍ መከፈት በፉክክሩ ሚና ከነበራቸው አትሌቶች አንዷ ኢትዮጵያዊቷ ሱቱሜ አሠፋ 2:17:32 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ስትሆን ሌላኛዋ ኬንያዊት ኤሪን ቺፕታይ 2:17:52 በመግባት ሦስተኛ፣ ኢትዮጵያዊቷ ቡዜ ድሪባ 2:20:22 በሆነ ሠዓት አራተኛ ሆነው ፈጽመዋል::

50ሺ የሚጠጉ ተሳታፊዎች በተካፈሉበት የቺካጎ ማራቶን በወንዶች የዓለም ክብረወሰን አልተመዘገበም:: የ27 ዓመቱ ጆን ኮሪር 2:02:43 በመግባት አንደኛ በመሆን ሲያሸንፍ 2:04:39 በሆነ ሠዓት የገባው ኢትዮጵያዊ መሐመድ ሆሠይዲን ኢሣ ሁለተኛ፣ ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ በሦስተኛነት ማጠናቀቅ ችለዋል::

ሴቶች ማራቶንን ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች ለመጀመሪያ ጊዜ ማጠናቀቅ የቻሉት እአአ 1979 ሲሆን፤ በ2ሰዓት ከ19 ደቂቃ ርቀቱን ለመሸፈን ደግሞ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል:: እአአ ከ1970ዎቹ ወዲህ ባሉት ዓመታት አዳዲስ ክብረወሰን የተመዘገበባቸውን ጊዜያት ስንመለከትም አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን የሚያጠናቅቁበት የሰዓት ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል::

ማራቶንን ከ2ሰዓት በታች ለማጠናቀቅ በወንዶች በኩል ከሚደረገው ጥረት እና ከፍተኛ ፉክክር አንጻር በሴቶች በኩል ከጥቂት ዓመታት በፊት ርቀቱን ከ2ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች ለማጠናቀቅ የሚደረገው ጥረት እምብዛም ሊባል የሚችል ነበር:: ይሁንና ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ቀድሞ ከነበረው ሰዓት ከሦስት ደቂቃ በላይ ማጠናቀቅ አሁን ላይ ሌላ የርቀቱን ፈጣን ኮከብ እንደፈጠረው ሁሉ በቅርብ ዓመታትም አዲስ ነገር ተስፋ እንዲጠበቅ አድርጋል::

የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋም ገና ወጣት ከመሆኗ በተጨማሪ ካላት ጽናትና ብቃት አንጻር ይህን ሰዓት አሻሽላ ክብረወሰኑን ዳግም በእጇ ለማስገባት ከወዲሁ የቤት ሥራዋን እንደምትጀምር ይጠበቃል::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You