በውጣ ውረድ ያልተበገረ ስኬታማ የሕይወት ጉዞ

‹‹ቆራጥነት እና በዓላማ መጽናትን ሰዎች ከእርሷ ሊማሩ ይገባል›› ሲሉ ባለቤታቸው ይመሰክሩላቸዋል። በልጅነታቸው ተወልደው ያደጉባትን ከተማ፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የሚወዱትን ትምህርታቸውን እና ትምህርት ቤታቸውን ትተው ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡ የተሳቡበት ትምህርት እና ለሱ ሲሉ የከፈሉለት ዋጋ ዛሬ ላይ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡

በልጅነታቸው የመሰረቱትን ትዳር የትምህርት ፍላጎታቸውን ሳይጫን፤ ትዳራቸው ለልጅነት ሕልማቸው ይበልጥ ድጋፍ ሆኖላቸዋል፡፡ ሕልማቸውን ማሳካት፣ የትዳር ሕይወታቸውን ማሳመር እንዲሁም ልጆቻቸውን በስኬታማ መልኩ ማሳደግ ችለዋል፡፡

ለትምህርት የነበራቸው ፍቅር እና የተጓዙበት መንገድም ወደ አስር የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ጆርናሎችን እስከማሳተም አድርሷቸዋል፡፡ የተለያዩ ተቋማትን በብቃት መርተዋል፣ በመምህርነትም ረጅም ዓመት አገልግለዋል፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ስርዓት ትምህርትን ቀርጸዋል። በተጨማሪም የሚሰሩበትን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን መዋቅር ሰርተዋል፡፡ እኒህ ትጉህ ሴት ዶክተር አብረኸት መሓሪ ናቸው፡፡ በዛሬው የሕይወት ገጻችን የዶክተር አብረኸት መሓሪ የሕይወት ጉዞ ልናጋርችሁ ወደናል፡፡ መልካም ንባብ …

ልጅነት በብዘት ከተማ

ትውልዳቸው በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ውስጥ የምትገኝ ብዘት የምትሰኝ አውራጃ /ቦታ ናት። ለወላጆቻቸው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ ፈጣን እና በትምህርታቸው ጎበዝ ነበሩ፡፡ ለዚህም ማሳያ እድሜቸው ለትምህርት ደርሶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጀመሩ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ያለውን በመምህራኖቻቸው ምስክርነት እና በእሳቸው ውጤት በወቅቱ በነበረው የትምህርት ስርዓትና ሕግ አንዳንድ ክፍል እያጠፉ ወደቀጣዩ ክፍል ሊሸጋገሩ ችለዋል፡፡ ‹‹ በልጅነቴ መሆን እፈልግ የነበረው የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት እና በትምህርቴ ስኬታማ ሴት መሆን ነበር፡፡ ከዚያም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ቢዝነስን የምታንቀሳቅስ ሴት መሆን የዘወትር ሕልሜ ነበር፡፡ ›› የሚሉት ዶክተር አብረኸት ወላጆቻቸው በንግድ ስራ የተሰማሩ መሆናቸውንም በማስታወስ ነው።

በአብዛኛው የሀገራችን ገጠራማ ክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ከተማ ተጉዘው እና ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ለመማር ይገደዳሉ፡፡ ዶክተር አብረኸትም የስድስተኛ ክፍልን ትምህርታቸውን እንደጨረሱ የቀጣዩን ክፍል ትምህርት ለመማር ከአዲግራት ከተማ 37 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ዋናው አውራጃ መጓዝ ነበረባቸው፡፡

በዚያም ሁለት ታናናሽ ወንድሞቻቸውን ይዘው ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በሳምንቱ መጨረሻም ወደቤተሰቦቻቸው በማቅናት ለሳምንታት የሚሆናቸውን ቀለብ ይዘው በመመለስ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ ታላቅ እህት እንደመሆናቸው ጠዋት ለወንድሞቻቸው ቁርስ አዘጋጅተው ሲመለሱም ቀድመው ወደቤት በመግባት የሚቀመስ እያዘጋጁ ይጠብቋቸዋል፡፡

በሚማሩበት ትምህርት ቤትም ወላጆቻቸው በገዙላቸው ብስክሌት ይመላለሳሉ፡፡ ትምህርት ልጅነታቸው የሰጡለት ሕልማቸው ነበር፡፡ የእረፍት ክፍለጊዜያቸውን እንደሌሎች ተማሪዎች ከእኩዮቻቸው ጋር ሳይሆን ከመምህራኖቻቸው ጋር ነበር የሚያሳልፉት። የአብረኸት ወላጆች በንግድ ስራ ውስጥ ያሉ ነበሩና ለልጆቻቸው ወጪዎችን ለመሸፈንም ሆነ ትምህርታቸውን ለማስተማር ጥሩ ገቢ ነበራቸው፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በብዙ መልክ የተሻለ ኑሮን እንዲኖሩ መደገፍና ማገዝ የሁሉም ወላጅ ተግባር ነው፡፡ ልጅን መዳር እና ለወግ ማብቃት የቤተሰብ የዘወትር ሕልም ነው፡፡ ዶክተር ልጅ በበነበሩበት ግዜ እና ዘመን ደግሞ ልጅን ሳይጠነክር መዳር የተለመደ ባሕል ነበር፡፡ ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸውን ለዘመናት ከኖሩበት ባሕል እና አስተሳሰብ ጋር ማስታረቅ ይከብዳቸዋል፡፡ የዶክተር አብረኸት ወላጆች እና ከልጃቸው ጋር አለመስማማት ውስጥ የገቡትም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡

ልጅህን ለልጄ

ትዳር ሰዎች በሕይወታቸው ሊያሳኩት ከሚገባ አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ታዲያ በአሁን ሰዓት ሙሉ ሙሉ ቀርቷል ለማለት ባይቻልም ከዓመታት በፊት ግን ሴት ልጆች ልክ እንደ አሁኑ እድሜያቸው ለትዳር ደርሶ፣ ፍላጎታቸው ተጠይቆ ሳይሆን ቤተሰብ ለቤተሰብ ተጠያይቆ ልጅህን ለልጄ በሚል ልጆቻቸውን ለትዳር ያጫሉ። በትዳር የመዛመድ ጥያቄ የቀረበላቸው የሴት ቤተሰብም በሀሳቡ ከተስማሙ እና ዝምድናውን ካመኑበት ጥያቄውን ተቀብለው ለልጃቸው ባል የሚሆነውን ሰው በእጮኝነት ተቀብለው ቃል ይገባሉ፡፡

አብረኸትም በዚህ ባሕል ውስጥ ማለፍ የግድ ብሏቸው ነበር፡፡ በአሁን ሰዓት የትዳር አጋራቸው የሆኑትን በእጮኝነት ወላጆቻቸው ሲመርጡላቸው ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበሩ፡፡ ጊዜው ደርሶ ትዳር ለመመስረት ሲበቁም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ መረጃ ለሙሽራዋ ለአብረኸት እንግዳ መረጃና በፍጹም የማይስማሙበት ነበር፡፡

‹‹ በጊዜው ለማግባት በፍጹም ፍቃደኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም ትምህርቴን መማር እፈልግ ነበር፡፡ እንደማገባ ከተነገረኝ ጊዜ ጀምሮ በጣም አለቅስ ነበር፡፡ በሰርጌ ቀንም ተደብቄ ለመጥፋት ሞክሬ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ›› የሚሉት አብረኸት ከዚያ በፊትም ልጃችሁን ለልጃችን የሚል ጥያቄ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለቤተሰቦቻቸው ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ወላጆቻቸው ግን ‹‹ቅድሚያ ትምህርቷን ትማር ››በማለት ሲመልሱ አይተዋል፡፡ የአሁኑ ባለቤታቸው የአቶ ክንፈ ግርማይ ቤተሰቦች ግን ዶክተር አብረኸትን ትምህርታቸውን እንዲማሩ እንደሚያግዛቸው ለወላጆቻቸው ቃል በመግባት ጋብቻ እንዲፈጸም እንዳደረጉ ያስታውሳሉ፡፡

የሰርጉ ቀንም ሲደርስ እሳቸው በጣም አዝነው እያለቀሱ እንደነበረም ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ ቃል እና ትዕዛዝ መውጣት ስለማይችሉ ጋብቻው ተፈጸመ፡፡ ባለቤታቸው አቶ ክንፈ ቃላቸውን በማክበር ትምህርት እንዲማሩ ፈቅደው ያስተምሯቸው ነበር፡፡

ዶ/ር አብረኸት የሀገር አቀፍ ፈተናን በሚወስዱበት ጊዜ የመጀመሪያ ልጃቸውን ነፍሰጡር ነበሩ። ነገር ግን ሕልማቸው የነበረውን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችል ውጤት በጊዜው አላመጡም፡፡ ግን የመጀመሪያ ልጅ እናት መሆን ችለዋል ፤ የልጃቸውን ስምም ‹‹ ሐቨን ›› ብለው ሰየሙት ቃሉ የትግርኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጓሜውም መመኪያዬ የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደእኩዮቻቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ባይችሉም ልጀቻቸው ግን መመኪያቸው መኩሪያቸው መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡

በአዲስ ስፍራ የሕይወት ጉዞና ሕልም

የአብረኸት ባለቤት አቶ ክንፈ ስራቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነበርና ኑሯቸውን ከትግራይ ክልል ወደ አርሲ ነገሌ አደረጉ፡፡ በመሆኑም የአብረኸት ወደፊት ኑሮም የተወለዱበት እና ያደጉበትን አከባቢ ትተው ወደ ነገሌ ሄዱ፡፡ ከባለቤታቸው ጋርም በዚያው መኖር ጀመሩ። ዶክተር አብረኸት ወደ ማያውቁት ቦታ ሕይወትን ለመጀመር ሲያስቡ እንደተጓዥ ሻንጣቸውን አላዘጋጁም፤ ይልቅስ ደብተሮቻቸውን ይዘው ነበር ከትውልድ ሀገራቸው የወጡት፡፡ ከዚያም በሻሸመኔ ያጡትን የዪኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ለማሻሻል ወደኋላ ተመልሰው የመሰናዶ ትምህርታቸው በድጋሚ ከተማሩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ ኮሌጅ መማር የሚያስችላቸውን ውጤት አሳኩ፡፡

በዚህ መሀል አብረኸት (ዶ/ር) ሁለተኛ ልጃቸውን ወልደው ነበር፡፡ ከዚያም ትምህርታቸውን ለመቀጠል ልጆቻቸውን ይዘው ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አደረጉ፡፡ በአዲስ አበባም ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ ብዙዎች የትዳር ሕይወት እና ራስን በትምህርት የማሻሻል ሕልምን ማስቀጠል አልታደልንበትም አልያም በእኩል ማስኬድ አልቻልነውም ሲሉ ዶ/ር አብረኸት ግን በኮሜርስ የንግድ ስራ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲማሩ ሶስተኛ ሴት ልጃቸውን ነፍሰጡር ነበሩ፡፡ ‹‹ሴት ልጄን እንደወለድኩ በዘጠነኛው ቀን ከአራስ ቤት ወጥቼ ፈተና ተፈትኛለሁ።›› የሚሉት ዶክተር አብረኸት የሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመረቁ ፡፡

ዶክተር አብረኸት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ በኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን የስራ ሕይወት ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡ በስራ ቦታቸው የነበራቸው ቆይታ እጅግ መልካም እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ትምህርታቸውን ለመተው ግን አልቻሉም፡፡ በመሆኑም በመስሪያ ቤቱ ለሰባት ዓመት ያክል ካገለገሉ በኋላ በዲግሪ ፕሮግራም ትምህርታቸውን ለመቀጠል ከስራ ቦታቸው ፍቃድ ጠይቀው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በቀን መርሀ ግብር ለመማር አመለከቱ፡፡

በዚህ ጊዜ ዶክተር አብረኸት የአራት ልጆች እናት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ትምህርት ሕይወታቸውን የሰጡለት ለራሳቸው ቃል የገቡበት ጉዳይ ነው፡፡ በባለቤታቸውም ለአማቾቻቸው ቃል የገቡበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት ትምህርት ለሚወዱት ባለቤታቸው ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ዶክተሯ እንደሚሉት ‹‹ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረን ለልጆቻችን ሞግዚትና የቤት ውስጥ አጋዥ ቀጥረን፡፡ እኔ ከዩኒቨርሲቲው ወደ ቤቴ የምመለሰው እሁድ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ለልጆቼ የሚፈልጉት ነገር እንዳይጎልባቸው እጠነቀቃለሁ፡፡ ››

እንዲህ እያለ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ፡፡ በኋላም ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው ተመራቂ ተማሪዎችን አወዳድሮ የመቅጠር እድል ተወዳድረው ፈተናውን በማለፍ የዩኒቨርሲቲው መምህር እና የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ ነገር ግን በስራቸው ላይ ብቁ ሆኖ መገኘት የማይደራደሩበት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹የአመራር ብቃቴን ያዳብርልኛል›› ያሉትን የዴቨሎፕመንታል ማኔጅመንት ትምህርት በዚያው መማር ቀጠሉ፡፡

በዚያ ብቻ ግን አላበቁም፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመማር ከስራ ቦታቸው ፍቃድ ጠይቀው ቀን ቀን እያስተማሩ ግማሽ ቀን ደግሞ በፋይናንሻል ማኔጅመንት በሚያስተምሩበት ተቋም ውስጥ ተማሩ፡፡ ‹‹ ትምህርቱን እንደጨረስኩ ሙለ ሙሉ ለማስተማር ፍላጎት ስለነበረኝ ለኢንስቲትዩቱ ያለኝን ፍላጎት አሳወቅኩ ፡፡ ›› ዶክተር አብረኸት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ያጠናቀቋቸው ትምህርቶችን ያላቸውን የስራ ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰው ሀብት አስተዳደር ስራ ውስጥ በኃላፊነት የማገልገል እድሉን አገኙ፡፡ የዩኒቨርሲቲውም መዋቅር እንዲሰሩ ጥያቄ ቀረበላቸው ፤ ለአንድ ዓመት ያክልም በሰው ሀብት ስራ ክፍል ውስጥ በመሆኑ የዪኒቨርሲቲውን መዋቅር ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በሊደርሺፕ እና ጉድ ገቨርናንስ የትምህርት ሞጁል አስተባባሪ፣ አማካሪ እንዲሁም መምህር ሆነው በኢንስቲትዩቱ ውስጥ መስራታቸውን ቀጠሉ ፡፡

የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀው በሚያስተምሩበት በዚህ ወቅት የጥናትና ምርምር ወይም የሪሰርች ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። የኢንስቲትዩቱ የሊደርሺፕ አመራር ዳይሬክተር ለመሆን የቀረበውን የውድድር መስፈርት አሟልተው እና ተወዳድረው በማሸነፍ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ ፡፡

በስራቸው ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢንስቲትዩቱ የሚመጡ ምሁራንን እንዲሁም የስራ ኃላፊዎች የማግኘት እድል ነበራቸው፡፡ ከቀረቡላቸው የተለያዩ ሀገራት ጥሪዎች መካከል የአዘርባዣን አምባሳደር በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተማሪዎችን ለማነጋገር በመጡበት ለዶክተር አብረኸት የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል በአዘርባጃን እንዲማሩ እድሉን ሰጧቸው፡፡ የትምህርት እድሉ የቀረበው በኢንስትዩቱ ውስጥ ለሚገኙ ሶስት ተወዳዳሪዎች በመሆኑ ዶክተር አብረኸት ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመወዳደር እና የአንደኛ ደረጃ በመያዝ ከሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው

ጋር በመሆን በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለማጥናት በአዘርባጃን እድል አገኙ ፡፡

ቤተሰባዊነት

የዶክተር አብረኸት ልጅነት ለትምህርት፤ የወላጆቻቸው ሀሳብ እና በቀደመው ባሕል ደግሞ ወደ ትዳር መመስረት አምርቷቸው ነበር ፡፡ በ14 ዓመታቸው ትዳርን ሲመሰርቱ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበሩ፡፡ አሁን ላይ የአራት ልጆች ወላጅ ናቸው። በትምህርታቸው ደግሞ አንድ ዲፕሎማ፤ ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፤ አንድ ሁለተኛ ዲግሪ እና አንድ ሶስተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ እነዚህ የትምህርት ደረጃዎች፤ ከ20 ዓመት በላይ የቆየ የማስተማር እና የአስተዳደር የስራ ልምድ ልጆች ከወለዱ በኋላ ያረጋገጧቸው ስኬቶች እና የተጓዙበት መንገድ ነው። ታዲያ ይህ ጉዞ በአንድ እናት እይታ እንዴት ይገለጻል፤ ምን ያህል ከባድ ነው ማሳካትስ ለሌሎች የሚቻል ነው ወይ? ተብሎ መጠየቁ የማይቀር ነው፡፡ ዶክተር አብረኸት እንዲህ ይላሉ ‹‹ ከባለቤቴ ጋር ስንጋባ እስከመጨረሻው እኔ እስፈለኩ ድረስ ትምህርት ሊያስተምረኝ ቃል ስለገባ በማንኛውም መንገድ ላይ ደጋፊዬ ነው ፡፡ ይህንን ሁሉ ትምህርት ስማርም የቤቴን ነገር ችላ የምል አይነት ሴት አይደለሁም ፡፡ ›› በማለት የነበራቸውን የሰዓት አጠቃቀም ይገልጻሉ፡፡ በየዓመቱ የጥቅምት ወር ሲሆን ለቤታቸው የሚያስፈልጋቸውን አስቤዛ ለአንድ ዓመት ያክል የሚሆናቸውን አስፈጭተው አዘጋጅተው ያስቀምጣሉ ፡፡

ተምሳሌት

ዶክተር አብረኸት የአራት ልጆች እናት ናቸው። ከ20 ዓመት በላይ የቆየ የስራ ልምድ አላቸው፡፡ ልጆቻቸው የእርሳቸውን ፈለግ የተከተሉ ናቸው፡፡ ‹‹በልጅነቴ ስለወለድኳቸው አብረን ስንወጣ እህታቸው እንጂ እናታቸው አልመስልም፡፡ ›› የሚሉት ዶክተር አብረኸት፤ ለልጆቻቸው አርአያ መሆን መቻላቸውን አንስተው ጎበዝ ተማሪዎች እንደነበሩ ይገልጻሉ። ልጆቻቸው በአጠቃላይ በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን በትምህርታቸው እናታቸውን ፈለግ በመከተል ሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ድረስ የቀጠለ ልጅ አላቸው። በአብዛኛው ልጆቻቸው ትምህርታቸው በውጭ ሀገር ተከታትለው በስራ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

ታዲያ ዶክተር አብረኸትም ነፍሰጡር በሆኑበት ጊዜም ሆነ ወልደው ትምህርታቸውን አላቋረጡም፡፡ ልጆቻቸው የውጭ ሀገር የትምህርት እድል አግኝተው ከቤት ሲወጡ፤ ዶክተሯ ከባለቤታቸው ጋር ቤት ውስጥ ቀሩ፡፡ ከዚህ ወዲያ ‹‹የሚያለቅስ፤ የማሳድገው ሆነ የማዝለው ልጅ የለኝም፡፡›› በማለት ራሳቸውን አበርትተው ቀጣይ ትኩረታቸውን ራሳቸውን በትምህርት ማሳደግ እና ስራቸው ላይ አድርገዋል፡፡

‹‹ የመጀመሪያ ልጄ ከሀዋይ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ ሶስተኛ ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) ይዟል፡፡ በአሜሪካን ሀገር እየሰራ ይገኛል፣ ሁለተኛ ልጄ በሳይኮሎጂ ተመርቃ በሚኖሶታ በስነ-ልቦና አማካሪነት እየሰራች ትገኛለች፣ ሶስተኛ ልጄ እንዲሁ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ እየሰራች ሲሆን የመጨረሻው ልጄ ፊዝዮቴራፒስት በመሆን እየሰራ ይገኛል እና ልጆቼ በጣም ያግዙኛል፡፡ አንዳንዴም መማር አይበቃሽም እንዴ ይሉኛል ››

የማይታለፉ የሚመስሉ ቀናት

‹‹በሕይወት ውስጥ የማይታለፍ ችግር አለ ብዬ አላስብም፡፡›› የሚሉት ዶክተር አብረኸት ዓላማቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚወዱትን ትምህርታቸውን መቀጠል እና ማጠናቀቅ ነበርና የተንገዳገዱባቸውን ጊዜያት ያስታውሳሉ ፡፡ ‹‹ ባገባሁበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወቅት ነበርና እና ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተማሪዎች መካከል ስለነበርኩ በወቅቱ ያን ውጤት ማምጣት ባለመቻሌ ያለቀስኩትን መቼም አልረሳውም፡፡ ››

ሌላኛው ፈተና ደግሞ በስራው ዓለም ላይ የገጠማቸው ፈተና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች ኮርፖሬሽን የሰራተኛ ማሕበር ተወካይ በነበሩበት ወቅት የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ በስራ ባልደረባቸው በቀረበላቸው የሀሰት ደረሰኝ እንዲያወራርዱ ተጠይቀው ነበር፡፡ ይህንንም ሃሳብ ውድቅ በማድረጋቸው ሌላ ባለሙያ ለመምረጥ በሚደረገው ምርጫ ላይ ስማቸውን የማጥፋትና በሀሳባቸው ከማይስማሙ ሰራተኞች በተለያየ መንገድ ትንኮሳ ይደርስባቸው ነበር፡፡ በምርጫው ወቅት በተደረገ ስብሰባ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራዎችን ለማስኬድ ከሰራተኞች የተሰበሰበን ገንዘብ አሳልፌ አልሰጥም በማለታቸው ይሄ ሁሉ በደል እንደደረሰባቸው ለኦዲተሮች እና ለኃላፊዎች አስረድተው ያን ወቅት ማለፋቸውን ይገልጻሉ ፡፡

ዶክተር አብረኸት ማንኛውንም ፈተና አልፈዋለው የሚል ሀሳብ አስቀድመው ለራሳቸው ነግረውታል። በአዘርባጃን የፒ.ኤች.ዲ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ባቀኑበት በተሰጣቸው እድል ትምህርታቸውን ተምረው ቢጨርሱም በሀገሪቱ ሕግ ግን እንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲሁም የሀገሩን የአዘርባጃን ቋንቋ ተምረው መፈተን የግድ ይላቸው ነበር፡፡ ይህ መረጃ አስቀድሞ ያልነበራቸው አብረኸት ለአንድ ዓመት በራሳቸው ወጪ ቋንቋውን ተምረው ተፈትነው ዲግሪያቸውን ሊቀበሉ ችለዋል፡፡

አመራርነት እና ሴትነት

ስራቸውን ሲጀምሩ በመምህርነት የጀመሩት ዶክተር አብረኸት ያጠኑት የፋይናንስ ትምህርት በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገለገሉበት ኃላፊነት የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊነት ነበር፡፡ በስራቸው አንድ መርህ አላቸው፡፡ ‹‹በእውቀት አምናለሁ ከትምህርት ባሻገር የተለያዩ መጽሀፎችን አነባለሁ፡፡ ሴቶች በአመራርነት ዘመናቸው ምን ሊገጥማቸው ይችላል? የሚለውን በስራዬ እንዳልሳሳት የሚጠቅመኝን አነባለሁ፡፡ ›› ባጠኗቸው የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እንዲሁ የመመረቂ ጽሁፎቻቸውን በተቋማት በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ የሴቶች ሚና ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ‹‹ ሌላው ሰዎች በስራቸው ራሳቸውን ለማሳደግ ወደ ላይ ወደ ኃላፊዎቻቸው ሳይሆን ከጎናቸው ካለ ሰው መማር ስራቸውን በየጊዜው መገምገም ይገባቸዋል፡፡ አብሯቸው ከሚሰራ ሰው ጋር በፍቅር እና በመረዳዳት መስራት ይገባቸዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ሴቶች ወደ አመራርነት ሲመጡ ይፈራሉ አቅም ኖሯቸውም ውድድር በሚኖርበት ጊዜ ራሳቸውን ያገላሉ፡፡ ያ መሆን የለበትም ውስጣቸው ሙሉ መሆን አለበት፡፡ በራስ መተማመን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሰው ልጅ የትም ሊያደርሰው የሚችለው ያለው በራስ መተማመን ነው፡፡ ውስጣቸው ሙሉ እንዲሆን ደግሞ ማንበብ እና መመራመር ያስፈልጋል፡፡ ›› ይላሉ፡፡

ዶክተር አብረኸት ኃላፊነት ሲሰጣቸው አመራር ምን ቁልፍ ነገሮችን ማሟላት አለበት? መሪዎች ለምን ይወድቃሉ? የሚለውን በማንበብ እና የማኔጅመንት ትምህርትን በመማር የአመራርነት ብቃታቸውን በማሳደግ ላለፉት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

ዶክተሯ የማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ ሲሆኑ ለተከታታይ 12 ዓመታት በፋይናንስ ስርዓት የማማከር ስራ ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የስርዓተ – ጾታ እና ሴቶችን የማሰልጠን ስራ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ በዚህም ልምዳቸው ሴቶች ራሳቸውን ለማብቃት እና ወደፊት ወጥተው ለመታየት ፍርሀት እንዳይዛቸው ራሳቸውን ማብቃት ላይ እንዲሰሩ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፡፡

ዶክተር አብረኸት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ክፍል በኃላፊነት ሲሰሩ፤ አርብ አርብ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለ15 ደቂቃ ያክል ስራን በጋራ የመገምገም ልምድ አላቸው። በወቅቱ በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ የሚገኙት መምህራን ይህ ጉዳይ ምቾት አልሰጣቸውም፡፡ ዶ/ር አብረኸት ምንም እንኳን በወቅቱ ኃላፊ ቢሆኑም የነበራቸው ግን ሁለተኛ ዲግሪ ብቻ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ያስታውሳሉ።

ጥናትና የምርምር ውጤቶች

ዶክተር አብረኸት መምህር ሆነው ላለፉት 20 ዓመታት አገልግለዋል፣ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ በዳይሬክተር ደረጃ የመምራት እድልም አግኝተዋል። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተማሪዎች የሚሰሯቸውን የመመረቂያ ጽሁፎችም እንዲሁ በማማከር ስራ ተሳትፈዋል፡፡ አሁንም በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በጾታ እኩልነት ፣ በክላስተር ዙርያ፣ በማኑፋክቸሪክ፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ከአስር በላይ የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችን ሰርተዋል፡፡ እነዚህን የጥናት ውጤቶችም ለማቅረብ በተለያዩ ሀገራት ላይ ተዘዋውረዋል፣ ስልጠናዎችን ለመውሰድ በስራ አጋጣሚ በርካታ ሀገራትን ለማየት ችለዋል፡፡

መምህርነት

‹‹ማስተማር እጅግ በጣም ነው የምወደው፡፡ እውቀትን ማስተላለፍ የሕሊና እርካታ አገኝበታለሁ፤ ብዙ እንዳነብ አድርጎኛል፡፡ ልምድም አገኝበታለሁ፡፡ ከተማሪዎቼ የጎደለኝን እሞላለሁ፡፡ ከሰዎች እተዋወቃለሁ እስካሁን ድረስ ቤተሰብ የሆንኳቸው ተማሪዎች አሉኝ፡››

ዶክተር አብረኸት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ለ20 ዓመታት ሲቆዩ በማስተማር ረጅም ዓመት ልምድን አካብተዋል፡፡ ከሀገር ውስጥም ከውጭም የተለያዩ የስራ እድል ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው አንድም መምህርነትን በመውደዳቸው አንድም ደግሞ ሀገራቸውን በጣም በመውደዳቸው እና ከሀገር ለመውጣት ባለመፈለጋቸው አሁንም ድረስ በማስተማር ስራ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አጋርነት በተግባር

ዶክተር አብረኸት ባለፉት ዓመታት በነበራቸው የስራም ሆነ የትምህርት ስኬታቸው እዚህ የደረሱበት ደረጃ በቤታቸው ያለው ሰላም እና የባለቤታቸው ያልተቋረጠ አጋዥነት መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ‹‹ ባለቤቴ በንግድ ስራ ውስጥ የተሰማራ በመሆኑ በትምህርት ብዙም አልገፋበትም፡፡ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ብቻ ነው የተማረው፡፡ ነገር ግን በጣም ደጋፊዬ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው አንድን ሕልሙን ለማሳካት እና ያሰበበት ለመድረስ በመጀመሪያ በቤቱ ውስጥ ሰላም፣ መግባባት መረዳዳት ሊኖረው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ምንም እንኳን ቆራጥ ብንሆን ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ በቤታችን ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት እና አጋራችን የጉዟችን ደጋፊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ቤታችን ሰላም ሲሆን ነው ውጪ ባለን ስራ ስኬታማ ልንሆን የምንችለው፡፡ ››

የዶ/ር አብረኸት ባለቤት አቶ ክንፈ ግርማይ ይሰኛሉ፡፡ ለዚህ ቃለመጠይቅ ስለባለቤታቸው ያላቸው የእርሳቸውን ሀሳብ አካትተነዋል ታዲያ የነበራቸውን ትውውቅ እንደዚህ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ ልጆች ሆነን አንድ አካባቢ ስለነበርን አብረን ተምረናል፡፡ እኔ ደግሞ የሚማር ሰው በጣም ነው የምወደው፡፡ በዛ ላይ እኔ እንኳን ባልፍ ስለልጆቼ ሳስብ እሷ መማር እንዳለባት አምንበታለሁ፡፡ ››

አቶ ክንፈ በቤታቸው ውስጥ ያሉ የቤት ሰራተኞቻቸው ጭምር ሁለተኛ ዲግሪ እንዲይዙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ባለቤታቸው አብረኸት ትምህርታቸውን እየተማሩ ከጎን ልጆች እየወለዱ ነበርና ባለቤታቸው ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ ተከታትለው ያስመዘግቧቸው ነበር፡፡ ባለቤታቸውን እንደሚያስመዘግቡ ያዩ ሰዎች እንዴት ፈቀዱላቸው በማለት እጅግ እንደሚገረሙ ያስታውሳሉ ፡፡

ለዶክተር አብረኸት ዓላማ መሳካት የአቶ ክንፈ ሚና የሚናቅ አይደለም፡፡ ባለቤታቸው የዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲካተተሉ እሳቸው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ለዓመታት የፊልድ ስራቸውን ትተዋል፡፡

ዶክተር አብረኸት ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሚማሩበት ወቅት አቶ ክንፈ ልጆቻቸውን ትምህርትቤት በማድረስ፤ ሁኔታቸውንም በመከታተል ለዶክተር ሀሳብ ያቀሉላቸው ነበር። በባለቤታቸው የትምህርት ውጤትም እጅግ ይኮሩባቸዋል ፡፡ ‹‹ ልጅ እየወለዱ መማር ፣ ማህበራዊ ሕይወት መምራት፣ ስራ መስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህን ሁሉ አቻችላ ነው የኖረችው፡፡ በይበልጥ ደግሞ ቆራጥ ናት ከዓላማዋ ዝንፍ አትልም፡፡ ››የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን እና ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You