ከዓለም ዋና ዋና ከሚባሉት ስድስቱ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቺካጎ ማራቶን ከነገ በስቲያ ይካሄዳል፡፡ መነሻውን በግራንት ፓርክ በማድረግ በታላላቆቹ የቺካጎ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የሚካሄደው ውድድር ዘንድሮ ለ46ኛ ጊዜ ሲካሄድ 50 ሺ የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንደሚሮጡ ታውቋል፡፡ ከሕዝባዊው ሩጫ ባለፈ አጓጊ የሆነው የታዋቂ አትሌቶች ፍልሚያም የኢትዮጵያ እና ኬንያ የማራቶን ከዋክብት አትሌቶችን ያገናኛል፡፡
ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የቺካጎ ማራቶን ባለፈው ዓመት የዓለም ክብረወሰን መሰበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ከወራት በፊት በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕቱም የሰው ልጅ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የማጠናቀቅ ብቃት ያለው መሆኑን ያረጋገጠው በዚህ መድረክ ነበር፡፡ የዘንድሮው ውድድርም ለዚህ ድንቅ አትሌት መታሰቢያ ሆኖ ይካሄዳል፡፡ በውድድሩ እንደሚካፈሉ ያረጋገጡ አትሌቶችን ብቃትና ያላቸውን ሰዓት ተከትሎም ከባድና ፉክክር እንደሚኖር ከወዲሁ ተገምቷል።፡
የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዓይን በጎረቤታሞቹ ሃገራት ኮከብ አትሌቶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፤ በርቀቱ ልምድ ያላቸውና በበርካታ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ድልን በመቀዳጀት ብቃታቸውን ያስመሰከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ብርሃኑ ለገሰ፣ ዳዊት ወልዴ፣ አምደወርቅ ዋለልኝ፣ ጀማል ይመር እና ሁሰዲን ሞሃመድ በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡
ባለው ፈጣን ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ የሚመራው አትሌት ብርሃኑ በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበው 2:02:48 ሰዓት በቺካጎው ፉክክር ፈጣኑ አትሌት አድርጎታል። የሁለት ጊዜ የቶኪዮ ማራቶን ቻምፒዮኑ ይህ የቺካጎ ማራቶን ተሳትፎው ሁለተኛው ነው፡፡ በዚህ የፈረንጆች ዓመት የሮተርዳም ማራቶን ተሳትፎው ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ቢሆንም በቺካጎ ውጤታማ ለመሆን በሚያስችለው ብቃት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዳዊት ወልዴ ለአሸናፊነት በሚደረገው ጠንካራ ፉክክር ለአሸናፊነት ትልቅ ግምት የተሰጠው ኮከብ ነው፡፡ ዳዊት ምንም እንኳን በቫሌንሲያ ማራቶን ያስመዘገበው 2:03:48 የሆነ የግሉ ፈጣን ሰዓት ከብርሃኑ በአንድ ደቂቃ የዘገየ ቢሆንም ቀላል ግምት የሚሰጠው አትሌት አይደለም፡፡ በኬንያ በኩል ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል የአሸናፊነት ግምት ያገኘው እአአ በ2019 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊው አሞስ ኪፕሩቶ ይገኝበታል። አትሌቱ የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊ መሆኑ ደግሞ በዚህ ውድድርም ለውጤት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ቪንሰንት ጌቲችም ከተጠባቂዎቹ አትሌቶች ተርታ የተቀመጠ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶንን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ፈታኝ ፉክክር እንደሚኖር ከወዲሁ መገመት ይቻላል። በተለይም በቺካጎ ማራቶን የሁለት ጊዜ አሸናፊ (2021 እና 2022) መሆን የቻለችው ኬንያዊቷ ሩት ቺፕጌቲች ፊቷን ዳግም ወደ ውድድሩ መመለሷ ተጠባቂ እንድትሆን አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከቺካጎ ማራቶን በሚስተካከለው የቶኪዮ ማራቶን በቅርቡ አሸናፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ ከበደ በቀላሉ ልትበገር የማትችልና ለኬንያዊቷ አትሌትም አስፈሪ ተፎካካሪ እንደምትሆን ይጠበቃል። ውድድሩን ይበልጥ ተጠባቂ ያደረገው ደግሞ ከሱቱሜ ባለፈ እንደ ደጊቱ አዝመራው፣ አሸቴ በከሪ፣ ሕይወት ገብረኪዳን እና ቡዜ ድሪባን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የማራቶን ኮከቦች የውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ነው፡፡
በቶኪዮ ማራቶን 2:15:55 የሮጠችው ሱቱሜ በዓመቱ ከተመዘገቡ የርቀቱ ፈጣን ሰዓቶች ቀዳሚውን ስትይዝ፤ በሂውስተን ግማሽ ማራቶን ውድድርም በተመሳሳይ በአሜሪካ ከተካሄዱ ውድድሮች በርቀቱ እጅግ ፈጣኑን ሰዓት የግሏ ማድረግ ችላለች፡፡ ይህም የአትሌቷን ወቅታዊ ብቃት የሚጠቁም ሲሆን፤ በቺካጎ አሸናፊ በመሆን ታጠናቅቃለች ተብሎ ይጠበቃል። ጠንካራ የአሸናፊነት ፉክክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት ሱቱሜ እና ቺፕጌቲች እርስ በእርስ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ እአአ በ2019ኙ የኒውዮርክ ማራቶን እንዲሁም በ2021 ደግሞ በለንደን ማራቶን ተፎካክረዋል፡፡ ከነገ በስቲያ የሚካሄደው የቺካጎ ማራቶንም ለሁለቱ አትሌቶች የአሸናፊዎች አሸናፊ ፉክክር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም