በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የወረዳ ተወካዮች አጀንዳዎችን ለይተው አጠናቀቁ

ሰመራ፦ በአፋር ክልል እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲወያዩ የነበሩት የወረዳ የህብረተሰብ ክፍል ወኪሎች አጀንዳዎቻቸውን አደራጅተው ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የሦስት ቀኑን ሂደት እና የቀጣይ ቀናት ሁነቶችን አስመልክቶ ኮሚሽኑ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሃመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ከሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ህብረተሰቡን ወክለው ሲወያዩ የቆዩት ከ800 በላይ የሚሆኑት እነዚህ ተሳታፊዎች ከሰፊ ውይይት በኋላ በሀገር ደረጃ መግባባት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል ያሏቸውን አጀንዳዎች በስፋት ተመካክረው ለይተዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን በአደራ ተረክበው በቀጣይ ቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚወያዩ 54 ወኪሎችን መምረጣቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ አጠቃላይ ሂደቱን ስንገመግመው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወክለው የመጡ ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፤ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ የወጣበት ሆኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥትም በተለያየ መንገድ ድጋፍ ማድረጉን ያደነቁት ኮሚሽነሯ፤ ለሂደቱ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።

በቀጣይ ቀናት ስለሚኖሩ ቀሪ መርሃግብሮች የተናገሩት ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በበኩላቸው፤ ከቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳ ደረጃ በተደረገው ውይይት የተመረጡ 54 ተወካዮች የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማህበራት፣ የመንግሥት አካላት እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ከተካተቱበት የባለ ድርሻ አካላት ስብስብ ጋር በመሆን በአምስት ቡድኖች ተከፍለው በመወያየት አጀንዳዎችን እንደሚያዘጋጁ ገልፀዋል።

አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉ ቀጥሎ እስከ ሰኞ በሚኖረው ጊዜ እንደ አፋር ክልል በሀገር ደረጃ ለሚደረገው ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች እና ተወካዮች ተመርጠው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ ባወጣው መርሃግብር የአጀንዳ ልየታና የአጀንጃ ስብሰባን በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ አቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሂደቱ እንደታሰበው አልሄደም። በመስከረም ወር የበዙ የበዓላቶች መኖር፣ አንዳንድ ሀገራዊና የፖለቲካ ፓርቲ ስብሰባዎች መደራረብ ኮሚሽኑ ባቀደው መሠረት እንዳይጓዝ አድርጎታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በተከታታይ እያካሄደ ይገኛል።

እስካሁንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መድረኮችን አካሂዷል።

ተስፋ ፋሩ

አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You