የመስከረም ወር የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትም የሚስተናገዱበት ነው። ዘንድሮም መስከረም ሃያ አምስት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም መስከረም 26 በቢሸፍቱ ሆራ አርሰዴ በዓላት በድምቀት ተከብረዋል፡፡
እነዚህ በአላት ሲከበሩ በየአካባቢው የሚገኘው ሕዝብ ለእንግዶች ከፍተኛ አቀባበል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመንግሥት በኩል በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች በመከናወናቸው በዓሉ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በአዲስ አበባም ሆነ በቢሸፍቱ እየተከናወኑ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባም ሆነ በቢሸፍቱ የአልባሳት ገበያ ደምቆ ታይቷል፡፡
በተለያዩ ቦታዎችም የጽዳት እንቅስቃሴና አካባቢ የማስዋብ ሥራዎችም በስፋት ተከናውነዋል። ይህ እንግዲህ በዓሉን ለማክበር በግለሰብ ደረጃ ከሚደረገው ዝግጅት ባለፈ መሆኑ ነው። ለመሆኑ ይህ ዘመናትን የተረሻገረ ሕዝባዊ በዓል በሕዝቦች መካከል አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን ያለው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል ስንል አቶ ድሪቢ ደምሴን አነጋግረናል። አቶ ድሪቢ ደምሴ የሜጫና ቱለማ መረዳጃና ልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ የኦሮሞ ባህል ሃይማኖትና የገዳ ሥርዓትን የተመለከቱ አራት መጻህፍቶችንም ጽፈዋል። በተጨማሪ የተለያዩ ጥናቶችንም ያከናወኑና በመሥራት ላይ የሚገኙም ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ኢሬቻ ምን ማለት ነው ?
አቶ ድሪቢ፤ ኢሬቻ ማለት ፈጣሪን ለማመስገን ለምለም ሳርና አበባ ከአንደ ቦታ አንስቶ ሌላ የተባረከ ቦታ በማስቀመጥ ለአምላክ ምስጋና የሚቀርብበት ሥርዓት ማለት ነው። የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ቀን የተለያየ ቢሆንም በሁሉም የኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ የሚከበርም ነው። አንዳንድ ቦታዎች ስያሜው ኢሬቻ ሲባል በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ኢሬሳ ይባላል። ኢሬቻ በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚከናወነውና እየታወቀ የመጣው በወንዝና ዳርቻ እና ተራራ ለይ ብቻ የሚደረገው ሳይሆን በሰርግ ሥነሥርዓት ለይ፤ ልጅ ሲወለድ፤ ለእርሻ አዲስ ማሳ ሲወጣም ይደረጋል። ፈጣሪ ለምለም ሳር ዝናብ መሬትና መሬቱ ያፈራውን እና ሌሎችንም «ይህንን ሁሉ ሰጥተህ ለዚህ ላደረስከኝ አምላክ ከሰጠህኝ ነገር ለይ ለክብርህ ትንሽ ነገር አደርጋለሁ እንደ ማለት ነው።»
ኢሬቻ በኦሮሞ ባህበረሰብ ዘንድ መከበር የጀመረበት ትክክለኛ ጊዜ ባይታወቀም ብዙ ሺ ዓመታት እንዳሳለፈ ይታወቃል። ኢሬቻ ብቻ ሳይሆን የገዳ ሥርዓትም በኋላዊ አምልኮውም ተመሳሳይ ነው። አሁን በድምቀት ሰው በብዛት እየተገኘበት በባህላዊ አልባሳትና በሌሎች ነገሮች አሸብርቆ መከበር የጀመረው ግን በ1990ዎቹ ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነው። በፊት ከአዲስ አበባ በጣት የምንቆጠር ሆነን ለማክበር ስንሄድ ብዙ መከራ ይገጥመን ነበር። በተደጋጋሚም ለመታሰር እና ለመደብደብ በቅተናል። ይህ ሁሉ መስዋእትነት እየተከፈለ ነው እሬቻ አሁን ላለበት ደማቅ አከባበር የበቃው። ለዚህ ደግሞ የቱለማ የገላን ጎሳዎች ትልቁን ደርሻ ስለተወጡ ሊመሰገኑ ይገባል። እነሱ እዚሁ አዲስ አበባ ስር ሆነው ባህላችንን አንለቅም ብለው በመጠበቃቸው ሲደበደቡበት፤ ሲዋረዱበት ሲሰደቡበትና ሲታሰሩበት ኖረዋል። ባእድ አምልኮ ነው እየተባለ ማህበረሰቡ ብዙ መስዋእትነት እንዲከፍል ተደርጓል። እኔ ራሴ በዚሁ የተነሳ ኢሬቻ አከበርክ ተብዬ ከመታሰር ባለፈ በእስር ቤት ልዩ ክፍል ውስጥ እንድቆይም ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡– የኢሬቻ በአል ከሃይማኖት ጋር ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው።
አቶ ድሪቢ፡– በመሠረቱ የኦሮሞ ማህበረሰብ ክርስትናነ እአስልምናን ከተቀበለ ረዥም ዘመን አስቆጥሯል። ክርስትናም ሆነ እስልምና ሃይማኖቶች የራሳቸው መመሪያ ከሚለው ውጪ ያለውን በሙሉ ካፊር ነው ባእድ ነው ይላሉ። እውነታው ግን ኢሬቻም ዋቄ ፈታም ሀገር በቀል መሆናቸው ነው። በእርግጥ ባእድ አምልኮ የሚሉት ከሃይማኖቱ አስተምህሮ መመሪያ የወጣ በአንድ ፈጣሪ አምላክ የማያመልኩ ለማለት ነው።
በዚህ አይነት ኢሬቻ ለአንድ ሺ ዓመት የሚያክል ጊዜ ባእድ አምልኮ እየተባለ ጥሩ ያልሆነ የሚያጠለሽ ስም ተሰጥቶት ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች የእኔ ባህል የእኔ መገለጫ ነው ከማለት ሲታቀቡ ይስተዋላል። ይህም ሆኖ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ኦሮሞ ሲተገብረው የኖረው ነው ። አሁን ደግሞ ከ1990ዎቹ ዓም መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ የተማረ ከሚባለውና በመንግሥት ሠራተኝነት ካለው የማህበረሰቡ ተወላጅ ጀምሮ ባእድ አምልኮ አለመሆኑ፤ የኦሮሞ መገለጫ ባህል መሆኑን ማስተማር ስንጀምር ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል። ይህን አጠናክረን የምንቀጥለው ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል። እሬቻ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኬንያም እየተከበረ ይገኛል። ከአፍሪካም ተሻግሮ በአሜሪካ አውሮፓና ሌሎች የዓለም ሀገራትም ሲከበር እየተመለከትን ነው። ይህንንንም ተከትሎ የኦሮሞ ባህል እየታወቀ እንዲመጣ በር ከፍቷል። አለባበስ የምግብ አይነቶችና ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎችና የኦሮሞ ሕዝብ ማንነትን የሚገልጹ ነገሮችም አብረው እየወጡ እንዲታወቁ ሆነዋል። በጥቅሉ እሬቻ ለኦሮሞ ሕዝብ የሰላም የአንድነትና የልማት ምልክቱ ነው። የአንድነት ሲባል በእሬቻ ቀን ህጻን ሽማግሌ ወንድ ሴት ሁሉም እኩል አንድ ላይ የሚቆሙበት ነው። እነዚህ ሁሉ በአንድ ለይ ሆነው ወደ ጸሀይ መውጫ ምስራቅ በመቆም ፈጣሪን የሚለምኑበት ነው። በኦሮሞ ባህል የምርቃትና የእርግማን ቦታ የተለያዩ ናቸው። አባቶችም በምርቃ ቦታ ሆነው እርግማን አያስተላልፉም በእርግማን ቦታ ሆነውም ምርቃት አያስተላልፉም። ኢሬቻ የምርቃት የሰላም የመልካም ምኞት ቦታ ነው። የየትኛውም በሃይማኖት ተከታይ ሊታደምበት የሚችለው ነው። ይህንንም ባለፉት ጊዜያት አይተናል።
አዲስ ዘመን፡– በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወን የኢሬቻ በዓል አካበባር ምን ይመስላል ?
አቶ ድሪቢ፡–መጀመሪያ እሬቻ የሰላም ነው ሲባል ቂም ያለበት የተኮራረፈ እና የተቀያየመ ሰው እሬቻን አያከብርም። ይሄ በአባ ገዳዎች በቃሉ የሃይማኖት መሪዎች የሚነገርና የሚያስቀስፍም ነው። በመሆኑም ኢሬቻ ከመድረሱ ሁለት ሳምንት አስቀደሞ የሀገር ሽማግሌዎች የተቀያየማችሁ ሰዎች አላችሁ ወይ ? ተራራ ልንወጣ ነውና መጥታችሁ ሰላም አውርዱ ተብሎ እንዲነገር ያደርጋሉ። ይህንንም ተከትሎ ተቀያይሞ ተኳርፎ የነበረ አባቶች ጋር ቀርቦ የበደለው ክሶ እንዲታረቁና ይቅር እንዲባባሉ ይደረጋል።
ከዚህም ባለፈ እሬቻ የሚከበርበት ቦታ ወንዝም ሆነ ተራራው ላይ ሲደረስ ምን አልባት ከቀናት በፊት የታረቁ እና እንደገና የተጣሉ፤ ወይንም የዛን ቀንም ዋዜማ ቢሆን የተጣሉ ሰዎች ካሉ አበባና ሳሩን ቁጭ ከማድረጋቸው በፊት አባ ገዳው ወይንም አባ መልካው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይቆምና እንዲህ ይላል። የተቀያየማችሁ ሰዎች የላችሁም ወይ ? ምስጋናችንን ጸሎታችንን እንዳታረክሱብን ካላችሁ «ጾታን ከምድር እውነታን ከፈጣሪ መደበቅ አይቻልምና» እኛ ባናያችሁ ፈጣሪ ያያችኋልና ውጡልን ይላሉ። በዚህ ጊዜ ቅያሜ ያላቸው ሁለቱም ወይንም አንዱ ወገን ይወጣል። አንዱ ወገን ወጥቶ ሌላኛው ከቀረ እርቅ ላይ እንዴት ትቀራለህ ተብሎ ሌላ ቅጣት ይጠብቀዋል። በመሆኑም ይህንን ጥሪ ሰምቶ ራሱን የሚሸሽግ አይኖርም ቅር ያለው ሁሉ ወጥቶ አስቀየመኝ ያለውንና የተቀየመበትን ነገር ይናገራል። በዚህ አይነት ሂደት ታልፎ ሁሉም የበዓሉ አክባሪ በንጹህ ልብ የሚታደምበት ይሆናል።
አከባበሩ በመጀመሪያ ህጻናት ልጆች ይሄዳሉ ቀጥሎ የደረሱ ልጅገረዶቸ ፤ ከዛ ያገቡ ሴቶች አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ከዛ ወጣት ጎረምሳዎች ፎሌ የሚባሉት መጨረሻ እየጨፈሩ ይሄዳሉ። ከዚያ በፊት ግን ከሳምንት ጀምሮ መንገዱና አካባቢው ለበአሉ አከባበር እንዲመች ተደርጎ ይስተካከላል የማጽዳትም ስራ ይከናወናል። በመጨረሻ መልካው ላይ ሰደረስ አባ ገዳዎች ከፍ ያለ ለቦታ ለይ ይወጡና መልእክት ያስተላልፋሉ። በዚህ ግዜ ሁሉም ሰው እሬቻውን ውሃ አስነክቶ ፊቱን እና ወደራሱም ረጨት አድርጎ እጁን ስሞ ፈጣሪን አመስግኖ ይመለሳል። ምስጋናው የሚደረገው በክርስቲያን በሙስሊም ወይንም በየትኛውም እምነት ተከታይ ሊሆን ይችላል ። ዋናው ቁም ነገር ግለሰቡ ዝናብ ዘንቦ ፤ምድር ለምለም ሆኗ እህል በቅሎ አበባ ማበቡ የሚያስደስተው በዚህም እጠቀማለሁ ብሎ የሚያስብ ሁሉ ለፈጣሪው ምስጋናውን ማቅረብ ይችላል። ለዚህ ነው እሬቻ ሃይማኖት አይደለም፤ የሃይማኖት ልዩነት አያደርግም፤ የትኛውንም ሃይማኖትም የሚቃረን አይደለም የምንለው።
የሚከበረውም በተለያያ ሥፍራ ለማህበረሰቡ ቅርብ በሆነበት ቦታ ሁሉ ይደረጋል። ቀኑም የተለየየ ሊሆን ይችላል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት «አሊዋቶ» የሚባል ነገር አለ። «አሊዋቶ» ማለት ነገሮች ሁነቶች በፍጥነት የሚለዋወጡበት ወቅት ማለት ነው። ከዓመቱ አስራ ሁለት ወራት ውስጥ በሶስቱ ወሮች የሚቀያየሩ ነገሮች በዘጠኝ ወር አይቀያየሩም ይህን የሚያደርገው ሰው ሳይሆን በተፈጥሮ ሂደት ማለት ነው። ሀምሌ መጀመሪያ ላይ ዝናብ ሲጥል የደረቁት ምንጮች ውሃ ማፍለቅ ይጀምራሉ፤ ምድር ይጨቀያል የደረቀው ሳርና ተክል ይለመልማል ወንዙ ይሞላል ይደፈርሳል። በነሀሴ አጋማሽ ጩልሌ ከማደሪያው አይወጣም ጊዜውም የጸጥታ ይሆናል። ይህም አልፎ ደግሞ በሶስተኛው ወር ማለትም መስከረም ሲገባ ነገሮች ተለዋውጠው ብርሃናማ ይሆናል ከዚያም ዘጠኙን ወር ጸሀያማ ሆኖ ይቀጥላል። ይህ እንደ አካባቢው ይለያየል ። ለምሳሌ በምስራቅ ሀረርጌ የሚደረገው እሬቻና ደምቢዶሎና ግምቢ ከሚደረገው ይቀድማል። ዝናቡም የሚቀንስበት ጊዜ ስለሚለያይ ወንዙም ስላልጠራ ጭቃው ጠፈፍ ስላላለ ማለት ነው። ወደ ፊት ግን ሁኔታዎች ሲስተካከሉ በጥናትና በውይይት ለይ በመመርኮዝ አንድ ቀን የሚከበርበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ይገመታል።
በአዲስ ዘመን፡– የእሬቻ በዓል መከበር ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ለቀሪው ማህበረሰብ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ?
አቶ ድሪቢ፡– የእሬቻ በዓል በየትኛውም ቦታ ቢሾፍቱንና በአዲስ አበባን ጨምሮ ሲከበር በርካታ ገጸ በረከቶችን ሊያስገኝ የሚችል መሆኑ መታወቅ አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ በዓሉ ሕዝባዊ እንደመሆኑ የታዳሚው ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር በየቦታው የሚፈጠሩ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ደግሞ በአብዛኛው ተጠቃሚ የሚያደርጉት በዓሉን የሚያከብሩትንና የሚታደሙትን ሳይሆን በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ ያሉትንና ሌሎችንም ነው።
ይህንን በትንሹ ለመቃኘት ብንሞክር ለእሬቻ በዓል ከባህላዊ አልባሳትና ለበዓሉ ከሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ጀምሮ ከፍተኛ የገበያ ልውውጥ ይኖራል። በዓሉን ለማክበር በሚደረገው እንቅስቃሴም ከትንንሽ ሱቆች ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት እድል አላቸው። በዚህ ረገድ በሚጠበቀው ደረጃ እንዳልተሠራበት ግልጽ ነው። በጣም ብዙ መሥራት የሚጠበቅ ይሆናል። ይህም ሆኖ በቢሾፍቱ ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ እንቅስቃሴ አለ። ዛሬ ላይ ቢሾፍቱ እንደ እስልምናና ክርስትና ሃይማኖታዊ በዓላት የደራ ገበያና የሰው እንቅስቃሴ እየተስተዋለ ነው። ምግብ ቤቶች ቤታቸውን አካባቢያቸውን አጽድተው ተዘጋጅተው እየጠበቁ ቀኑን መቼም ከሚያገኙት በላይ ገቢ እየሰበሰቡበት ነው።
ይሄ በአዲስ አበባ የለም። ምክንያቱ ከአመለካከት ችግር ወይንም በዚህ ደረጃ በከተማዋ መከበር ከጀመረ ቅርብ ጊዜ ስለሆነው ይሆናል። ምንም ይሁን ምን ግን በቀጣይ ሊስተካከል የሚገባው ነው። የሚዘጉ ሆቴሎችና የንግድ ማእከላት ክፍት መሆንና አገልግሎት በመስጠት እነሱም ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። የከተማዋ ነዋሪዎችም እንቅስቃሴ እንደሌሎች በዓላት ዋዜማ ደማቅና ሰላማዊ እንዲሆን እንጠብቃለን። በእርግጥ እንዲህ አይነት ነገሮች ለከተማዋ አዲስ በመሆናቸው በአንድ ጊዜ ሁሉም ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቀስ በቀስ ግን ሁሉም ነገር ይስተካከላል የሚል እምነት አለን።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች እንዳሉ ሁሉ የኦሮሞ ብሄረሰብም ተወላጆችም የሌሉበት ቦታ የለም። በዚህ መነሻነት ኢሬቻ በበርካታ ቦታዎች እንዲከበር ቢደረግ የበርካታ ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይቻላል። በተጨማሪ ይሄ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንግሥትንም ተጠቃሚ የሚያድርግ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሃላፊዎችም በዓሉ በሰላም እንዲከበር በማድረግ ረገድ ሃላፊነት አለባቸው።
ኢሬቻ ከማህበራዊ ፋይዳው ባለፈም ማህበረሰብን በማቀራረብ ሰላም በመፍጠር ረገድ ሰፊ ጠቀሜታ አለው። በመጀመሪያ ደረጃ በራሱ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ሰላም መፈጠር አብሮነትና አንድነት መጠናከር ሌላውንም ማህበረሰብ የሚያበረታታ ይሆናል። ሁለተኛ የኦሮሞ ማህበረሰብ ከየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን ያልተጋባውና ያልተዋለደው ብሄር ጎሳ የለም። ኢሬቻን ተከትሎ የሚፈጠረው ሰላም እነዚህን ሁሉ የሚነካ እነዚህን ሁሉ የሚያቀራርብና የሚያስደስት ነው።
አዲስ ዘመን፡– የኢሬቻ በዓል ሕዝብ የኦሮሞ ሕዝብ እሴቶች ፤ ማንነት የሚባሉትን ምን ያህል ይወክላል ? ምን ያህልስ ለመጠበቅ ይረዳል ?
አቶ ድሪቢ፡– የኦሮሞ ሕዝብ የሚታወቅበት የራሱ ማንነቶች አሉት። ምንም ማዳላት ሳይኖር ሰውን በሰውነቱ የሚቀበል ነው። በእንግዳ ተቀባይነትም ቢሆን የተመሰከረለት ታሪክ ያለው ነው። ደግነት የዋህነት መረዳዳት አጠቃላይ ሠብዓዊነት የኦሮሞ ሕዝብ ለሺህ ዘመናት የኖረባቸው መለያዎቹ ናቸው። የኦሮሞ ማህበረሰብ በሕዝብ ቁጥር ብዛትም በያዘውም ቦታ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካም ትልቅ ቦታ ያለው ነው ። ኬንያ ውስጥ ሶስት ኪሎ ሜትር ገብተን ገበራ የሚባሉ የኦሮሞ ጎሳዎች አሉ። ወደ ህንድ ውቅያኖስ አካባቢም ለሙ የሚባሉ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች አሉ። በዓሉ ሲከበር እነዚህ ሁሉ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ በር ይከፍታል።
መቀራረብ መነጋገርና አብሮነት ደግሞ ሰላም ያመጣል። በባህልም እንደ እቃ ሁሉ መበዳደርና መዋዋስ አለ። በዚህ ሂደት አንዱ የአንዱን አያራክስም፤ አንዱ ሌላውን አይንቅም። ሰው የመሰለውን ያደርጋል እኔ ያልሁትን ብቻ ሁን እኔ የምልህን ብቻ አድርግ ማለት ራሱ ሀጢያት ነው። እሬቻ በዚህ ደረጃ መከበሩ ወይንም ሌሎች ፍቼ ጨንበላላ ጊፋታን የመሳሰሉ ባህሎችም እንዲወጡ በር ከፍቷል። ይህ ማህበረሰቡ ራሱን እንዲሆንና እርስ በእርሱም እንዲከባበር ያደርጋል። ማንነቱን የሚያከብርና የሚጠብቅ ሕዝብ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም በማህበራዊ ኑሮውም የተዋጣለት እና ተጠቃሚ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– የኢሬቻ በአል የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት ረገድ ምን ፋይዳ አለው ?
አቶ ድሪቢ፤ ኢሬቻ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ግንባታ እና አብሮነት ዓይነተኛ ሚና ያለው ቅርስ ነው ከላይ እንዳነሳሁት የኦሮሞ ሕዝብ ክረምት አልፎ ፀደይ ሲመጣ፤ በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ ሲገናኝ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና ያቀርባል። ይህ ለብዙ ሺህ ዘመናት ሲከናወን የቆየ ሀገራዊ ትውፊት ነው። ኢሬቻ ፈጣሪ (ዋቃ) ለሰው ልጆች ለሰጠው የሚመሰገንበት ልዩ በዓል ነው። ኢሬቻ «ዝናብ አዝንቦ ለሰጠው ውሃ፤ እንዲበቅል ላደረገው አዝመራ፤ ከክረምት ጨለማ ወደ ፀሐያማ ወቅት ስላሸጋገርከን እናመሰግናለን» እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል ነው።
ይህ የኢሬቻ ባህላዊ እሴት እና አከባበር ሥነ-ሥርዓት በሀገራችን ወንድማማችነት እንዲጠናከር፣ አብሮነት እንዲጎለብት እና ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ኢሬቻ ከማመስገን አልፎ አንድነት የሚፀናበት ሀገራዊ ሀብት ነው። በኢሬቻ ዕለት ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚሳተፉ የአንድ ሀገር ልጆች በአንድነት የሚሰባሰቡበት፤ በፍቅር የሚደምቁበትና የሚጠያየቁበት በዓል ነው። ኢሬቻ በአንድ ቦታ፤ የአንድ ሀገር ልጆች ተሰባስበው ሀገራዊ እሴታቸውን የሚያዳብሩበት የኅብረት መገለጫም ነው። ኢሬቻ እንደ ሀገር ካሉን ቅርሶች አንዱ ሲሆን የማይዳሰስ ቅርስ ተደርጎ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አካል ተደርጎ የተመዘገበ የሀገር ሀብትም ጭምር ነው።
ኢሬቻ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙት ከመሆኑም በላይ ሴቶች፤ ወንዶች፤ ሕፃናት፤ ወጣቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች በውብ አለባበስ ደምቀው የሚያከብሩት የውበት በዓል በመሆኑ ከፍተኛ የቱሪዝም መስህብ እየሆነ የመጣ ሀብታችን እየሆነ ነው። አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር ተይዞ በአባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች «መሬሆ» እየተባለ ውብ ዝማሬ የሚሰማበት የኢሬቻ በዓል የተለያዩ አካባቢ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራ እና ዘፈን የሚያሳዩበት ባህላዊ የጥበብ መድረክም በመሆን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ ይጫወታል።
ይህ ባህላዊ እና የሰላም የእብሮነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት በመሆኑ፤ የቱሪዝም ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ማክበር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የኦሮሞ ምሁራን እና ልሂቃን ሊሠሩት የሚገባ በርካታ ሃላፊነት አለባቸው ። በዓሉ ለሺህ ዓመታት በተጽእኖ ስር ስለቆየ በርካታ ነገሮቹ ተበርዘዋል። ይህንን ነገር ለማስተካከል መረጃ በመሰብሰብና ከአባቶች በመጠየቅ አሰባስቦ በማጠናቀርና ምርምርና ጥናቶችን በማካሄድ እንዲጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ኢሬቻ በዓል ሲከበር ከአክባሪውና ከታዳሚው ምን ይጠበቃል ?
አቶ ድሪቢ ፤ ይሄ ቀላል ነገር ነው። እያንዳንዱ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅም ሆነ ሌላው ኢሬቻ ለምን እንደሚከበር ካወቀ እንዴት ማክበር እንደሚኖረበት ይገባዋል። ኢሬቻ ምስጋና ነው ! ኢሬቻ ፍቅር ነው ! ኢሬቻ እርቅ ነው ! ኢሬቻ ሰላም ነው ! ኢሬቻ አብሮነት ነው! ። በመሆኑም በዓሉ በሚከበርበት ወቅትም ሆነ ለበዓሉ በሚደረጉ ዝግጅቶች እና እንቅስቃሴዎች እነዚህን ነገሮች መላበስ ብቻ በቂ ነው።
እስከዛሬም ድረስ እሬቻን ለማክበር ወጥቶ በእሬቻ በዓል ላይ ታድሞ ክፉ ነገር ሠርቶ የሚያውቅ የለም። በሰላም ተሰብስበን በሰላም ተመራርቀንና ተመሰጋግነን የምንለያይበት ነው። በዚህ ረገድ በዓሉን ለማክበር በሚደረጉ ዝግጅቶችም ሆነ በበዓሉ ቀን የሚታደሙ የኦሮሞ ወጣቶችን ላመሰግን እወዳለሁ። በእርግጥ ቅድም እንዳነሳሁት እስካሁን ስለበዓሉ በበርካታ ሰዎች ዘንድ በቂ ግንዛቤ ስለሌለና ከሃይማኖት ጋር በማያዝ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ሲወሩ እንሰማለን። ይህ በጊዜ ሂደት የሚስተካከል ይሆናል። ይህም ሆኖ በዓሉን ከሚያከብረው ሕዝብ እንደ ትናንቱ በሰላም በፍቅር በአብሮነት መንቀሳቀስ የሚጠበቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፤ ስለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።
አቶ ድሪቢ ፤ ለሁላችንም መልካም በዓል ይሁንልን። እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
ራስወርቅ ሙሉጌታ አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም