አዲስ አበባ፡– 14ኛው የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ የሕግ ባለሙያዎች በአፍሪካ ደረጃ ተሳትፏቸው እንዲጨምር እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አስታወቀ። ጉባዔው ከጥቅምት 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር 14ኛው የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባዔን ዝግጅትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ 14ኛው የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባዔ ከጥቅምት 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።ጉባኤውም በኢትዮጵያ መካሄዱ የሕግ ባለሙያዎች በአፍሪካ ደረጃ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ያግዛል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንትና የኅብረቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧን ገልጸው፤ ጉባዔው በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን የሕግ ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ሂደት የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ፤ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሕግ ባለሙያዎች አውቀታቸውን እንዲያጎለብቱና በአፍሪካ ደረጃ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛል።
ዝግጅቱን ለማስተባበር የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ሲሆን ጉባኤው ኅብረቱንና ባለሙያውን የሚወክል እንዲሆን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ ሙያው የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲሆንና ጠበቆች ሥራዎቻቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ጉባዔው ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታው በቢዝነስ ሕግ፣ በድንበር ዘለል የሕግ አተገባበር በተመለከቱ ርዕሶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለሙያውና ለባለሙያው እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ለሀገር ገጽታ ግንባታ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ማኅበሩ ስድስት ሺህ 700 በላይ አባላት አሉት ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የሕግ ጥራት ለማስጠበቅ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሕግ ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ዕውቀት እንዲያገኙና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች በሀገር ውስጥ ተገድበው ሳይቀሩ ዓለም አቀፍ አሠራር ልምድ እንዲወስዱ ያስችላል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ጠበቆች ፍትሕን በማጎልበት በሀገር የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ውስጥ የሚኖራቸው አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ነው።
የጉባዔው የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ዘውድነህ በየነ በበኩላቸው፤ የጉባኤው በሀገር ውስጥ መካሄድ ኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያውያን ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች እንዲሁም አጋር አካላት የነቃ ተሳተፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
ኅብረቱ በ54 የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የጠበቆች ማኅበራትን ያቀፈ ሲሆን፤ በጉባዔው ከ300 በላይ የሚሆኑ ምሑራን፣ ጠበቆች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሀገራት ተወካዮች እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመላክቷል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም