አዲስ አበባ፡– በሲዳማ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ100 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በክልሉ ሥራና ክህሎት ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የ2017 ሴክተር ጉባዔ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ያሉትን አቅሞችና አማራጮችን በመጠቀም የወጣቱን የሥራ ዕድልና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቷል።
በዓመቱ ወጣቶችን ወደ ሥራ ከማስገባት ባለፈ በሥራ ላይ ያሉትን በመደገፍ ወደ ባለሃብትነት እንዲሸጋገሩና ኢንዱስትሪውን እንዲቀላቀሉ የማድረግ ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዕውቀት መር የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በክልሉ ቴክኖሎጂን በመረዳት፣ በማላመድና በማሻገር የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማፋጠን የሚያግዝ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያስተዋውቅ ክልል አቀፍ ምክር ቤት እንደሚቋቋምም ገልጸዋል።
በዚህም በአዲስ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕቀፍ መሠረተ ልማትን የማስፋፋትና የክልሉን የኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥን ውጤታማ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።
የክልሉ የሥራና ክህሎት ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሐገረጽዮን አበበ እንደገለጹት፤ ክህሎት ያለው፣ የበቃና አመለካከቱ የተቀየረ ዜጋ ወደ ሥራ ለማሰማራት ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
ኮሌጆቹ ከመደበኛ ሥልጠና በተጨማሪ ገበያ ተኮር አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶችን ለሥራ እንዲያበቁ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ለሚፈጠረው የሥራ ዕድል ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦትና ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷል።
ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር አሠሪና ሠራተኛን ማገናኘት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳካት ሥልጠና በመስጠት ግንዛቤ መፍጠር በዓመቱ ከተያዙ ዋና ዋና ግቦች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ በራሳ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግሥት ያቀደውን ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባር ለማገዝ ኮሌጁ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በመደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ከማፍራት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍና ቴክኖሎጂ የማሸጋገር ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርቶችን ወደማምረት እንዲገቡ የማገዝና ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ወጣቶችን የማዘጋጀት ሥራም እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በመድረኩ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት እውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም ውይይት ተደርጓል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም