አዲስ አበባ:- ተቋምን ብሎም ሀገርን ለማገልገል በቅድሚያ ጥብቅ በሆነ ሙያዊ ዲስፕሊን መታነፅ ያስፈልጋል ሲሉ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠልጣኝ የበረራ አስተናጋጆችን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
አዛዡ በዚህ ወቅት ሀገርን ብሎም ተቋምን ለማገልገል በቅድሚያ የሀገር ፍቅር ስሜት ከዓላማ ፅናት ጋር መላበስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የእርስ በእርስ መደጋገፍን እንደባሕል መያዝ እንደሚገባ እና ከፋፋይ ከሆኑ ጎጂ አስተሳሰቦችም መራቅ ወሳኝ ነጥብ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበረራ አስተናጋጆች ውስጣዊ አንድነታቸውን ይበልጥ በማጎልበት ከብሔርተኝነት ከሃይማኖት አክራሪነት እንዲሁም ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ራሳቸውን ማራቅ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስተንግዶ ኃላፊና አሠልጣኝ መምህርት ወይዘሮ መሠረት ገላየ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተሰጠው ሃገራዊ ተልዕኮ ባሻገር እየሠራ ያለው የልማት ሥራ ለሌሎችም ተቋማት መልካም አርዓያ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህ የተቋሙ ስኬት ሚናቸውን ለተወጡ የሠራዊቱ አመራሮች እና አባላት ትልቅ ክብር እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዕለቱም የአየር መንገዱ የበረራ መስተንግዶ ሠልጣኞች የኢትዮጵያን አየር ኃይል ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም