ዜና ሐተታ
ከርቀት ላስተዋለ ሰው መለስተኛ ከተማ ከሚመስለው የሼድ ስብስብ ውስጥ አንዱ የእነ አቶ ፉአድ አባተማም ሼድ ነው። እነአቶ ፉአድ፣ ነዋሪነታቸው በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ፣ በዳለቲ ወረዳ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም አምስት ሆነው በመደራጀት በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርተዋል።
በወቅቱ ወደሼዱ ያስገቡት ጫጩት ሁለት ሺህ 200 እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ ፉአድ፤ ተደራጅተው የዶሮ ልማት ከጀመሩ አንድ ዓመት እንዳልሞላቸው ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ጫጩቶቹ በማደጋቸው እንቁላል ለመጣል እየተዘጋጁ ሲሆን፣ ጅምር ላይ እንደመሆናቸው ምርቶቻቸውን በስፋት ለገበያ እንዳላቀረቡም ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደዶሮ እርባታ ከመግባታቸው አስቀድሞ በመንግሥት በኩል አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደዋል። በወሰዱት ሥልጠና ግንዛቤያቸው ከፍ በማለቱ ምርጫቸው ወዳደረጉት የዶሮ ልማት ውስጥ መግባት ችለዋል። በዳለቲ ወረዳ በሚገኙ ሼዶች የመሠረተ ልማቱ የተሟላ ነው። በእያንዳንዱ ሼድ የራሱ የመብራት ቆጣሪ እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ በዚህ በኩል ምንም ችግር የለባቸውም። ችግር ሆኖ የሰነበተው ግን የዶሮ መኖ ጉዳይ ነው ይላሉ::
በተለይም እርባታውን እንደጀመሩ አካባቢ ለዶሮዎቹ መኖ ያመጡ የነበረው ካሉበት አካባቢ ርቀው በመሄድ በመሆኑ ወጪያቸውን ከፍ ሲያደርግና ጉልበታቸውን ሲያባክን እንደቆየ ያስረዳሉ። መኖውን ከአዳማና ከቢሾፍቱ እንደሚያመጡ ጠቅሰው፤ ሌላው ቀርቶ ከባሕርዳር ጭምር መጥተው ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህ ደግሞ ከዋጋውም ሆነ ከአቅርቦቱ አኳያ ችግር ሆኖብን ሰንብቷል ነው ያሉት።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ ገና ጅማሬ ላይ ቢሆንም የዶሮ መኖ የሚያዘጋጅ ሌላ ሼድ በቅርባችን ሥራ በመጀመሩ ርቀን መሔድ ሳይጠበቅብን ከዛ መውሰድ ጀምረናል ሲሉ ጠቁመዋል፤ በቅርበት ከማግኘታቸው በተጨማሪ በዋጋም በኩል የተሻለ ሆኖ ማግኘታቸውን ጭምር አመልክተዋል። ከዚህ የተነሳ ለወራት ያህል ሲፈትናቸው የነበረው የመኖ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘቱን ገልጸዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በእስካሁኑ ሒደት ምርታቸውን የሚሸጡት በየራሳቸው እንጂ በአንድ ማዕከል ሲሸጥ አላዩም። ይሁንና በቀጣይ የገበያ ትስስር ሊፈጠር የግድ የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ በእርባታው ዘርፍ የተሰማሩ ሼዶች በርከት ያሉ እንደመሆናቸው ሰፋ ያለ ገበያ ፈላጊ ናቸው። ይህን ሁኔታ ለማመቻቸት በመንግሥት በኩል እየተነጋገሩበት እንደሆነ ተገንዝበዋል።
እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የተመረተውን ምርት ሁሉ በመሸጡ በኩል ያጋጠመ ችግር የለም። ይሁንና እንደ ችግር ሊነሳ የሚችለው ነገር የውሃ መቆራረጥ ማጋጠሙ ሲሆን፣ ከሌላ ቦታ ለማስገባት ሲሞከር ደግሞ ወጪው ከፍ ያለ ይሆንብናል። ስለዚህ በውሃ በኩል ያለው ችግር ቢታይልን ጥሩ ይሆናል። የወደፊት እቅዳችንም በዚሁ ዘርፍ አስፍቶ መቀጠል ነውና በአሁኑ ወቅት በማኅበር ተደራጅተው እየሠሩ ናቸው።
በዚሁ ዳለቲ ወረዳ የወተት ከብት እርባታ ላይ “ሰሚራ፣ ሐሰንና ጓደኞቻቸው” በሚል ማኅበር ስም ከተደራጁ ጓደኞቻቸው አንዱ አቶ አብዱራሃማን ሐሰን ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የተደራጁት ከልጆቻቸው ጋር ነው። ወደሥራ ከገቡ ስድስት ወር ያህል አስቆጥረዋል። የሚታለቡ እና የማይታለቡ በጥቅሉ ወደ 17 ያህል ላሞች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል ሰባት ያህሉ ጊደሮቸች ናቸው። ጊደሮቹ ገና በመሆናቸው ብዙ ወተት የላቸውም፤ እንዲያም ሆኖ በቀን እስከ 95 ሊትር ወተት ያገኛሉ። ከአንዲት ላም ከ15 ሊትር እስከ 20 ሊትር ወተት በቀን ማግኘትም ይችላሉ።
ድጋፍ እየተደረገልን ይገኛል የሚሉት አቶ አብዱራህማን፣ ቀደም ሲል እንደ አንድ አርሶ አደር በቤታቸው የሀበሻ ላሞች እና አንድ የፈረንጅ ላም እንደነበራቸው ያስረዳሉ። ይህን ጥረታችንን አይተው እንደ ቤተሰብ እንድንደራጅ ሁኔታዎችን ስላመቻቹልን ከልጆቼ ጋርም ተደራጀሁ ይላሉ፤ ወደሥራ ከመግባታቸው በፊትም ተገቢ ሥልጠና መውሰዳቸውን ያመለክታሉ።
አቶ አብዱራሃማን እንደሚገልጹት፤ በተሠራው ሼድ ውስጥ ሥራ ሲጀምሩ በቤታቸው ከሚያደርጉት ጋር ያለው ልዩነት ሰፊ ነው። ከጠባብ ዓለም ወደተሻለ ስፍራ በመምጣታቸው ውጤታማ መሆን ጀምረዋል። በነበራቸው ጥቂት ላሞች ላይ ከስንቄ ባንክ ብድር በመውሰድ የፈረንጅ ላሞችን መግዛት ችለዋል። ገና በጥቂት ወራት ውስጥ ልዩነቱን ማስተዋል ጀምረዋል።
ሥራው ጠንክሮ ለሚሠራ ሰው በጣም አትራፊ ነው። በዚህ ሥራ የተሰማራ አካል ኪሳራ ደርሶብኛልና ወደቤቴ ልመለስ የሚልበት ምንም ምክንያት የለም። እስከጣሩ ድረስ ውጤታማ የሆነ ተግባር ነው። ለላሞቹ አግባብነት ያለውን ምግብ እስካቀረብን ድረስ ወተት ይሰጡናል ብለዋል። ለሌሎቹም አርሶ አደሮች ከልጆቻቸው ጋርም ሆነ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን ተደራጅተው ቢሠሩ ያተርፋሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የከብቶች መኖ በቅርብ ማግኘት መጀመራቸውንና ከብቶቻቸው እንዳይታመሙም የጤና ክትትል እንደሚደ ረግላቸው ተናግረዋል። እንደችግር የጠቀሱት ከሼድ ውጭ ሰፋ ያለ ቦታ አለመኖሩን ሲሆን፣ ከብቶች በባሕሪያቸው አንድ ቦታ ብቻ ሲቆሙ እግራቸው ስለሚታመም ወደ ውጭ ወጥተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ሰፋ ያለ ቦታ ያስፈልጋል ብለዋል።
የገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ስንታየሁ ሲሳይ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ያወረደውን ኢንሼቲቭ ሙሉ ለሙሉ በመውሰድ እና ከሕዝቡ ጋር በመመካከር ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ከመንግሥት፣ ከባለሀብቱና ከሕዝቡ ጋር በመሆን 106 ሼዶች መሠራቸውን ገልጸው፤ የሼዶች መሠራት ዋና ዓላማ ለወጣቶቻችን፣ ለሥራ አጦቻችንና ለአርሶ አደሮቻችን የሚሆን ሥራ ለመፍጠር በማሰብ ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በእያንዳንዱ ሼድ የተለያዩ ማኅበራት ያሉ ሲሆን፣ ልማታቸውን በማቀላጠፍ ላይ ናቸው። የልማት ማኅበራቱ መሠረተ ልማቱ እንዲሟላላቸው ጥረት ተደርጓል። ባሉት ሼዶች ውስጥ የተቀናጀ የከተማ ግብርና በሙላት የሚካሔድባቸው ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የወተት ከብት እርባታ፣ የዶሮ እርባታ፣ የአሳማ እርባታ፣ የንብ እርባታ፣ የከብት ማደለብ፣ የበግና ፍየል ማደለብ፣ የእንስሳት መኖ ማምረቻ ተጠቃሽ ናቸው። ከየሼዶቹ በየጊዜው እንቁላሉ፣ ዶሮው፣ ወተቱ፣ የደለበ በሬው፣ በጉና ፍየሉ እየወጣ ለገበያ ይቀርባል። ማርና አሳማውም እንዲሁ ለገበያ የሚቀርብ ምርት ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ኢንሼቲቩን ለማስፋት ባለፈው የሠራነውን አይነት አራትና አምስት ያህል የተቀናጀ የከተማ ግብርና ክላስተር ለመሥራት እቅድ ይዘናል ይላሉ። ሥራውም የተጀመረ ሲሆን፣ 40 ነጥብ ሦስት በመቶ ላይ መድረስ መቻሉንም ያመለክታሉ። በቀጣይ የሚሠሩ ሼዶች በብሎኬት የታገዙ እንደመሆናቸው የተሻሉ ይሆናሉ። ይህን በመከተል ሸገርን፣ ኦሮሚያን እንዲሁም ኢትዮጵያን ጭምር የማልማት መስመር ውስጥ ነን ማለት ይቻላል ብለዋል።
ልማቱ እየተቀላጠፈ ያለው በክላስተር እንደመሆኑ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታው ምቹ ነው፤ በውሃና መብራት ዙሪያ ያለውን ችግርም ከስር ከስር በመፍታት ላይ እንገኛለን። በቀጣይ ደግሞ የፈረንጅ ላሞች ወጥተው መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም