ከባዱ ክረምት አልፏል። ዝናቡም ምድርን አረስርሶ ሄዷል። አበቦች ምድርን አልብሰዋል። ወንዞች ገመገሞችም ከውሃ ሙላት ጎድለዋል። በደመና የተሸፈነው ሰማይም ጠርቶ ኩልል ያለች ፀሐይ መውጣት ጀምራለች።
ይህ ሁሉ የሚሆነው በኢትዮጵያ በወርሐ መስከረም ነው። በዚህ ወር በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ እና ሌሎች በዓላትን በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል። በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው። እኛም ኢሬቻ በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው ቢሾፍቱ ተገኝተናል።
በቢሾፍቱ የሚከበረው የኢሬቻ ሆራ አርሰዲ ዓመታዊ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉም ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የመጡ እና በባሕል አልባሳት ያሸበረቁ አባ ገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሕጻናት ታድመዋል።
በምዕራብ ጉጂ ዞን የሀዮ አባገዳ የሆኑት ኤባ ዴማ ከምዕራብ ጉጂ ድረስ በመምጣት የኢሬቻ ሆራ አርሰዲ ዓመታዊ በዓል ሲታደሙ አግኝተናቸው፤ ስለበዓሉ አከባበርና አጠቃላይ ሁኔታ የተሰማቸውን ጠይቀናቸዋል።
እንደ አባገዳው ገለጻ፤ ኢሬቻ አንድነት እና ፍቅር የሚታይበት ለፈጣሪም ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው።
ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ታዳሚዎች ያለልዩነት በፍቅር እና በአንድነት በጋራ በመሆን ፈጣሪን ሲያመሰግኑ በማየታቸው እንደተደሰቱም ተናግረዋል። በዓሉም በኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱን ላሳለፈ ፈጣሪ የሚቀርብ ታላቅ የምስጋና በዓል መሆኑንም ገልፀዋል።
ወጣት ለገሠ ዱርሳ በበኩሉ በዓሉን ለመታደም ከሰበታ መምጣቱን ተናግሯል። ኢሬቻ የክረምቱ ውሃ ሙላት ሲያልፍ ቤተሰብ ከቤተሰቡ የሚገናኝበት በመሆኑ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርበት ገልፀዋል።
በዓሉ ላይ ደማቅ አለባበስ ለብሳ ያገኘናት ወይዘሪት ሀወኒ ዲዳ የወለጋ ተወላጅ መሆኗን ገልፃ የሆራ ፊንፊኔ በዓል አክብራ የሆራ አርሰዲን በዓል ለማክበር በቢሾፍቱ እንደተገኘች ተናግራለች።
በየዓመቱ በዓሉን ለመታደም እንደምትመጣ ገልፃ በዋዜማው ታዳሚዎች በጋራ መሆን የሚጨፍሩት ጭፈራ እና የሚለብሷቸው አዳዲስ ዲዛይን ያላቸው አልባሳት በዓሉን በጉጉት እንድትጠብቀው እንደሚያደርጋት ተናግራለች።
ወጣቶች ባሕላቸው እንዲጠብቁ እና በዓሉን የሚያጠለሽ ነገር ሲያዩ እንዲከላከሉ መልዕክቷን አስተላልፋለች።
የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል በጣም ደማቅ እና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ተከብሯል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም