የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል አንድነትንና ወንድማማችነትን ባጠናከረ መልኩ በድምቀት ተከበረ

ቢሾፍቱ፡ኢሬቻ መልካ” በ”ሆራ ፊንፊኔ” እና “ሆራ አርሰዲ” በዓል አንድነትንና ወንድማማችነትን ባጠናከረ መልኩ በርካቶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፥ ኢሬቻ ቱሉና ኢሬቻ መልካ በመባል ይታወቃል።

ኢሬቻ ቱሉ በበልግ ወቅት በተራራማ ቦታ ላይ ለፈጣሪ ተማጽኖ የሚቀርብበት ነው። የክረምቱ ወቅት አልፎ ብራ ሲተካ የሚከበረው ደግሞ ኢሬቻ መልካ በመባል ይታወቃል፡፡

የጉጂ አባ ገዳ ጃርሶ ዱጎ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መሳተፋቸው ወንድማማችነትን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

እንደሚቻል የገለጹት አባገዳው፤ ሠላም የሕይወት መሠረት በመሆኑ ሁሉም ለሠላም ሊሠራ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በበዓሉ የታየው አብሮነት፣ አንድነትና ወንድማማችነት ከበዓሉ በኋላም ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ከጂማ ዞን ሊሙሰቃ ወረዳ የመጣችው ወጣት ረሃ ሙዘሚል እንደተናገረችው፤ የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል በርካታ የኦሮሞ ሕዝብና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተሳተፉበት በመሆኑ ለየት ያደርገዋል።

ኢሬቻ ፍቅር አንድነትና ሠላም የታየበት መሆኑን የገለጸችው ወጣቷ በኢሬቻ የታየው አንድነት ከበዓሉ በኋላም ሊቀጥል ይገባል ትላለች።

በበዓሉ ላይ የሀገር ውስጥ ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት መጥተው በበዓሉ መታደማቸው እንዳስደሰታት በመግለጽ፤ በዓሉን በማስተዋወቅ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መሥራት እንደሚገባ ተናግራለች።

ከጫንጮ ከተማ የመጡት አቶ ሙዳ ቦረናገዲ በሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ አርሰዲ የተከበረው የኢሬቻ በዓል አንድነት አብሮነትና ፍጹም ሠላም የታየበት ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ አቃፊ በመሆኑ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ጋር አብሮ እየኖረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል ኢሬቻ ኦሮሞ ብቻ እያከበረ የነበረ ቢሆንም አሁን የሁሉም በዓል መሆን መቻሉን ይናገራሉ።

ኢሬቻ ባሕልና እሴቱን ጠብቆ ማቆየት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በዓሉ የተለያዩ የሀገር ውስጥ የውጪ ቱሪስቶችን በመሳብ የቱሪዝሙን ዘርፍ እንደሚያነቃቃ ይገልጻሉ።

ከአዳማ ከተማ የመጣችው ቤተልሔም ግርማ በበኩሏ እንደተናገረችው:-የኢሬቻ በዓል ሠላም ፍቅርና አንድነት የታየበት ነው ።

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በበዓሉ ላይ መታደማቸው የባሕል ልውውጥ ለማድረግና የእርስ በእርስ ትስስርን እንደሚያጠናክር በመግለጽ፤ በዓሉ የአንድነት በመሆኑ ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክርም ትናገራለች።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ኢሬቻ ለባሕላችን ህዳሴ በሚል መሪ ሀሳብ በሆራ አርሰዲ ትናንት በድምቀት ተከብሯል።

 

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You