ከሜዳሊያ ጀርባ ያሉ ሙያተኞች

ስፖርት ለበርካታ በሽታዎች መፍትሔ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ለታካሚዎቻቸው አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የጤና ተቋምም አካላዊ እንቅስቃሴን ከሰው ወደ ሰው ለማይተላለፉ ነገር ግን ገዳይ ለሆኑት እንደ ስኳር፣ የልብ ሕመም፣ ስትሮክ፣ ደምግፊት እንዲሁም የመገጣጠሚያና አጥንት ሕመሞች የሕክምና አማራጭ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በአንጻሩ ዘርፈ ብዙ የሆነው ስፖርት መድኃኒት ብቻም ሳይሆን የጉዳት ምክንያትም ነው፡፡ አስገራሚው ደግሞ ከጉዳት በቶሎ ለማገገም ቀጥተኛው መፍትሔም ስፖርት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ስፖርትና ሕክምና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ሊባሉ ይችላሉ፡፡

ከሕክምና መስኮች መካከል አንዱ የሆነውና በየጊዜው እድገቱ እየጨመረ የመጣው የስፖርት ሕክምና የተዋወቀው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ የስፖርት ክለቦችም በዋናነት በስብስባቸው ከሚያካትቷቸው ሙያተኞች መካከል ሕክምና ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በእርግጥም ከበርካታ ሜዳሊያዎች ጀርባ ጀግና የሕክምና ባለሙያዎች አሉ፤ እነዚህ ሙያተኞች ለአትሌቱ ስኬታማነት ቁልፍ ቢሆኑም በሚገባቸው ልክ አልተዘመረላቸውም፡፡ ባለንበት የፉክክር ዓለም አትሌቶች ከገጠማቸው የጤና መጓደል በቶሎ አገግመው ወደ አቋማቸው እንዲመለሱ በማድረግ የማይተካ ሚና አላቸው። በስፖርት ሜዳ የሚገጥሙ ዘግናኝና አትሌቱ ዳግም ወደ ውድድር የመመለስ ዕድሉን አጠራጣሪ ያደረጉ ከባድ ጉዳቶችን ድል በመንሳት ዳግም ለውድድር መድረክ በማብቃትም መተኪያ የላቸውም፡፡

የዘመናዊውን የኦሊምፒክ ምሥረታ ተከትሎ በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ አትሌቶችን ለመርዳት በሚል የተጀመረው ሕክምናው በሂደት አስፈላጊነቱ እየጎላ እና በቡድን ውስጥ ያለው መሠረታዊነት በመጨመሩ ዘርፉ የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ በቀደሙት ዓመታትም ጉዳት ያስተናገዱና ሕመም የገጠማቸው ስፖርተኞችን ይረዱ የነበሩት የሕክምና ባለሙያዎች በዘርፉ የተለየ ሥልጠና ያልወሰዱ ጠቅላላ ሐኪሞች ነበሩ። ነገር ግን በስፖርት ውስጥ ሕክምናን የሚጠይቁ ጉዳዮች ከሌሎች የሕመም ዓይነቶች የተለዩ በመሆናቸው የተለየ እይታ ሊያገኙ ችለዋል፡፡

ስፖርት ሕክምናን ከሌሎች የሕክምና ዓይነቶች ነጥሎ በመመልከት የመጀመሪያዋ ሃገር ጣሊያን ስትሆን እአአ በ1958 አንስቶም ይህንኑ በሥራ ላይ ስታውል ነበር፡፡ በቀጣይም የአውሮፓ ኅብረት ስፔሻሊስት ሐኪሞች ማኅበር በአሕጉሪቱ ተመሳሳይ ሥልጠናዎችን በመስጠት የስፖርት ሕክምና እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በሕክምና ትምህርት ክፍሎቻቸው ውስጥ ሐኪሞች በስፖርት ሕክምና ሥልጠና አግኝተው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህ ወቅትም በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች በመላው ዓለም የሚገኙ ሲሆን፤ የስፖርት ሕክምና ማኅበር በመመሥረትም በተለይ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ይሠራሉ፡፡

ይህ ዘርፍ በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት ትልቅ እመርታ ያሳየ ሲሆን፤ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ብቻም ሳይሆን የስፖርት ሕክምና ተቋማትም ተስፋፍተዋል፡፡ የስፖርት ሕክምናን ምንነት ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈም በየጊዜውም በርካታ ጥናቶችን በመሥራት እንዲሁም የሕክምና ዘዴዎችን በድረገጾች አማካኝነት በመለዋወጥ ዘርፉ ይበልጥ እንዲጠናከርና እንዲዘምን ሆኗል። ስፖርት በቴክኖሎጂ እና በገንዘብ አቅሙ እየፈረጠመ መምጣቱን ተከትሎም ታላላቅ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች የሕክምና ባለሙያዎችን በግላቸው በመቅጠር ጭምር አቅማቸውን በምን መልክ መጠቀም እንደሚችሉ በሳይንሳዊ ዘዴ ይታገዛሉ፡፡

የስፖርት ሕክምና ዋነኛ ዓላማው የተጎዱና ሕመም የገጠማቸው አትሌቶችን በመርዳት ወደጤናቸው መመለስ ብቻም አይደለም። ይልቁንም አትሌቱ የብቃቱን ጥግ አውጥቶ እንዲጠቀምና ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ጥረት የሥልጠና ቡድኑ ባለሙያዎች ድምር ቢሆንም ጤናን በሚመለከት ግን ከሐኪሞች ባለፈ ፊዚዮቴራፒስቶች፣ የሥነምግብ ባለሙያዎች እንዲሁም ዕውቅና ያላቸው የሥልጠና ባለሙያዎች በጥምረት ይሠራሉ፡፡ የእነዚህ ሙያተኞች ተግባር የተለያየ ቢሆንም አንዳቸው ያለሌላኛቸው ግን ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እንደ ስፖርተኛው የጉዳት ዓይነትና ሁኔታ መድኃኒት ከማዘዝ እስከ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና የደረሰ ሕክምና ሊደረግ ይችላል፡፡ በዚህም የወጌሻዎች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎች እንዲሁም የሥነምግብ ሐኪሞች ከሥነልቦና ምሑራን ጋር በመሆን ስፖርተኛውን ዳግም ለሥልጠና እና ውድድር ያበቃሉ፡፡

ብርሃን ፈይሳ

 

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You