የአርሲው ቢሊሌ

ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ ሳያሳኩት ለማለፍ የማይፈልጉት አንድ ነገር ቢኖር “ለስም መጠሪያ…ብትሞት ለመታወሻ የሚሆንህን ልጅ ውለድ” የሚለውን ውስጣዊ የሕይወት ምክርን ነው፡፡ ከዚህ ከፍ ብለው ጀግና የሻቱ ዕለት ደግሞ “ስምህን የሚያስጠራ…የምታስጠራ ልጅ ይሁን /ትሁን” የምትል መልካም ምኞት ያዘለች ዓረፍተ ነገር ናት፡፡ ታዲያ መጠሪያም ይሁን መታወሻ የሚገኘው ከስሙ ሳይሆን ከሥራው ነው፡፡ ጥሩም ይሁን መጥፎ መሥራትን ሁሉም ሰው ይሠራል፡፡ ቁም ነገሩም በሥራው መጠሪያውን ማግኘቱ ሳይሆን፤ መጠሪያውን ለማግኘት የበቃበት ሥራ ምንነት ነው፡፡ ምክንያቱም መጥፎ የሠራው የሚታወሰው በመጥፎ፣ የሚጠራውም በክፉ ነው፡፡ ጥሩ የሠራውም በሠራው ልክ… የዛሬውን የዝነኞችን ዝናር አንግቶ የምንመለከተውን ወጣት ድምጻዊን በግሌ፤ በሥራው መጠሪያ ስፈልግለት ከሥራዎቹ አንዱ የሆነውን “ቢሊሌ”ን አገኘሁ፡፡ እንደገና ከራሱ በላይ ያስጠራውና እርሱን የወለደው አንድ ድንቅ ማህበረሰብ መኖሩን አስቤ “የአርሲው ቢሊሌ” ስል ልጠራው ፈለኩ። ምንም እንኳን ሴት ብትሆንም “ቢሊሌ” የሚለውን በሰማሁት ቁጥር የሚታወሰኝ የእርሷ የማንነት ነጸብራቅ ያረፈበትን እርሱን ነውና ትልቅ የሠራ መታወሻው ታላላቆች ናቸው። ቢሊሌ ስል ገና ማን ሊሆን እንደሚችል ማወቃችሁ አይጠረጠርም፡፡ ከአርሲ አሰላ የሯጮች መንደር ወጥቶ ስሟን በሙዚቃ ያስጠራውን አንዷለም ጎሳን ለማስታወስ ለማንም ጊዜ አይፈጅም፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስሙ በሁሉም የሙዚቃ አድማጭ ዘንድ ከፍ ብሏል፡፡ የአንዷለም ጎሳ ችሎታ ለመደነቅ በጎሳ አጥር ብቻ አልታጠረም፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ የኦሮምን ባሕልና ቀደም ያሉ ታሪኮች በሙዚቃ ደረጃ ጥንቅቅ አድርጎ በመሥራት የብዙኀኑን ቀልብ ለመሳብ እምብዛም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በውብ የግጥምና ዜማዎቹ፣ ከማራኪ ድምጹ ጋር በማዋሃድ አሸወይናውን እንካችሁ ሲል ይታወቃል። ለ8 ዓመታት ያህል በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲቆይ ተወዳጅነቱን ለማትረፉ ነጠላ ዜማዎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን በ2017 ዓ.ም ግን በዓይነቱ ለየት ያለውን እንቁ አልበም “አያንቱ” በማለት ይዞ መጥቷል፡፡

“ልጅነቴ ልጅነቴ፤ ማርና ወተቴ” እያለ በአሰላ ቦርቆ ያደገው አንዷልም ትውልዱ ግን ከወደ ባሌ ቃሶሃራ ነው፡፡ ቤተሰቡን ተከትሎ ከባሌ አሰላ በመግባት የስመ ጥር ሯጮቹን መንደር ተቀላቀለ፡፡ ብዙዎቹ ከወዲያ ወዲህ ሲሮጡ፤ እርሱ ከወዲህ ሾልኮ ጎበዝ ድምጻዊ ለመሆን በቃ፡፡ የአሰላ አየር መሮጥ ለሚፈልገው ብቻ ሳይሆን ለማቀንቀን ለተመኘውም ለጉሮሮው የማር ወለላ ሆነች፡፡ “ሸጌ ኮቱሜ፤…ዚያዴ ማሎ” እያለ በልጅነት ውስጥ ሆኖ ሲያጉራጉራት “እደግ! ተመንደግ! ድምጽህን የአዕዋፋት ዝማሬ ያድርግልህ!” ብላ መረቀችው መሰል እንዲህ ያለው ብርቱ ድምጻዊ ለመሆን በቅቷል። እንደ ልጅ በልጅነቱ የሰማውን ሙዚቃ ሁሉ ለመድገም በመታተር ስሜት ውስጥ ሆኖ ቢያድግም፤ አስቀድሞ የልጅነት ሕይወቱ የተሳሰረበት ሌላ ነገርም ነበረው፡፡ ከሙዚቃው በፊት ሲሯሯጥለት የነበረው ለእግር ኳስ ነበር፡፡ በነበረው ችሎታ አካባቢውን በመወከል ወጣ ብሎ ማንጠባጠቡንም ጀማምሮ ነበር፡፡ ከመድረክ ፊት ከቆመው ታዳሚ አስቀድሞ ከሜዳው ትሪቭል የተቀመጠው ተመልካች አጨብጭቦለታል። ከማይክ አስቀድሞ የኩባንያም ትሁን የብርጭቆ እጆቹ ዋንጫ ጨብጠዋል፡፡ ከጉሮሮው በላይ ከአንደበቱ በፊት እግሮቹ በልምምድ ዘለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ከቤት እስከ መባረር ያደረሰውን እግር ኳስ ጥሎ ወደ ሙዚቃ የገባበት አንድ የጊዜ ድልድይ አለው፡፡ ታዳጊው ወጣት አንዷለም ጎሳ ከሕይወት ፈረስ ኋላ ተቀምጦ ልጓሙን በመጨበጥ ለቤተሰቡም፣ ደግሞ ራሱንም በጋሪ ሲያስተዳድር ነበር፡፡ ያ ከሞት አፋፍ ደርሶ የተመለሰበትን መጥፎ አጋጣሚ ዛሬም የሚያስታውሰው ትዝታው ነው፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ታዳጊው አንዷለም የፈረስ ጋሪውን ጭኖ ለመውጣት ይሰናዳል፡፡ ዕለቱ የበዓል ቢሆንም ለኑሮ የሚፍጨረጨረው አንዷለም ግን መሥራት እንዳለበት ወሰኗል፡፡ ከሰዓታት ኋላ ያለው የልጇ ሁኔታ የታያት የምትመስለው እናትም፤ በዚህ ቅር ቅር አላት፡፡ “እባክህን አትውጣ…ተው የዛሬን ይቅርብህ” ብላ ብትማጸነውም፤ ለመቅረት አልወደደምና እየነዳ ወጣ፡፡ ከሰዓታት በኋላ ግን የእናት ፍራቻ እውን ሆነ፡፡ አንድ ሁለት እያለ ሲሰግር የነበረው የአንዷለም ፈረስ ሸኾናው መሬት አልቆነጥጥ ቢለው ድንገት ተንሸራቶ ቁልቁል ወደ ገደል ወረደ፡፡ ጋሪው ከፍ ብሎ ወደፊት በአፍጢሙ ተዘቀዘቀ፡፡ ከላይ የተፈናጠጠው አንዷለምም ከታች ከመሬቱ ጋር ተደባለቀ፡፡ ካገኘው ምት ጋር ተጨምሮ ትንፋሹ ተቋርጦ ለአንድ ሰዓት ያህል በድን ሆኖ ጸጥ አለ፡፡ በእነዚያ ደቂቃዎች ውስጥ እርሱን በሕይወት የጠበቀ አልነበረም፡፡ ታሪክ እንዲጽፍ ግን ዕድል ይሁን ተአምር ፈቅደውለት ተርፎ በሕይወት ለመታየት በቃ፡፡

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ የኮካ ኮላ አይድል ብቅ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጹ ሲደመጥ ከቆመበት መድረክ ጀርባ ሲጠብቀው የነበረው ባለጋሪነቱ ነበር፡፡ ያቺን የጋሪ ፈረሱን እየነዳ ባጠራቀማት ገንዘብ አዲስ አበባ ተሳፍሮ የሙዚቃ ጥሪውን ምላሽ ለመስጠት የውድድር መድረኩ ላይ ወጣ፡፡ አንድ የአሊ ቢራን ሙዚቃ ተጫውቶ ሲጨርስ የዳኞቹን ፊት እየተመለከተ የአስተያየት ምላሾቻቸውን በጉጉት ጠበቀ፡፡ ከብዙ አስተያየቶች በኋላ ዳኞቹ ለውሳኔው ተማከሩና፤ ተመልሰህ በሌላ ጊዜ እንደገና እንድትሞክር ተባለ፡፡ ከንግሥናው በኋላ ከወራት በፊት አንድ ሚዲያ ላይ ቀርቦ ተስፋ ስለቆረጠበት ጊዜ ሲጠየቅ “በሕይወቴ ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ የለም፡፡ ወደፊትም አልቆርጥም” የሚል ነበር ምላሹ፡፡ ራሱን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከዚያ ውድድር በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ጀግና መሆኑን ማሳየት መቻሉ በርግጥም ተስፋ መቁረጥ በአንዷለም ሕይወት ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ከዚያ የሞት አጋጣሚ መትረፉ ለዋዛ ፈዛዛ ሕይወት አለመሆኑንም አስረግጦ ያውቃልና የሚጓዝባቸው መንገዶች ሁሉ በቅንነት ደረጃዎች ወደ ታላቅ የስኬት ማማ ይመሩታል። ሲሄድ ሁልጊዜ ከፊቱ ላይ ፈገግታ አይታጣም፡፡ ሰዎችን ሲቀርብም ሆነ ሲቀርቡት በንጽሕ የመልካምነት ልቦና በመሆኑ አውቀው አይጠሉትም፡፡ ከምግባሩ የተመለከቱ፣ ከአንደበቱ የሰሙ ሁሉ ይወዱታል፡፡ አክብሮ መከበር የሕይወቱ አንደኛው መርህ ነውና ጥበብን ባከበራት ልክ አከበረችው፡፡

ከአልበም ቀደም ብሎ ከሠራቸው ሥራዎቹ መካከል አንደኛዋን ነጠላ ዜማውን መጠሪያውን አድርገንለታልና ሳናነሳት ለማለፍ አትሆንም፡፡ ብዙ ጣፋጭ ነጠላ ዜማዎችን ሲያስደምጥ ቢቆይም በወርሃ ግንቦት ያስደመጣት አንዲት ዜማ ግን ለየት ያለች ነበረች፡፡ ይህቺ ዜማም እንዲሁ ነጠላ ተብላ የምትቋጫ ብቻ አይደለችም፡፡ ያደመጠ ሁሉ ያጨበጨበለት የኢትዮጵያ የታሪክ ክፋይ የሆነ ሥራው ነበር፡፡ ሙዚቃው በኦሮምኛ ቢሆንም የኛው ነው ብሎ ወዶ በፍቅር ያደመጠለት ግን ጆሮው ቢቆረጥ ቋንቋውን ለመስማት የማይችለው ሁሉ ነበር፡፡

“ቢሊሌ” ውብ ቆንጆ መልከ መልካም ኮረዳ፡፡ ሲሄድ ከመንገድ ላይ፣ ተቀምጦ በሃሳቡ የሳላት ሴት መስሎ ይሰማን ይሆን…ላላወቅናት ቢሊሌ እሷ አይደለችም፡፡ አንዷለም ጎሳ “ቢሊሌ” ሲል ከጥንታዊ የታሪክ ገጾች መካከል መዞ በሙዚቃው እንደ አዲስ ያመጣት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካዊ ሴት ናት፡፡ በ1820ዎቹ በአጋሮ ስለመወለዷ የሚነገርላት ቢሊሌ እጅግ ቆንጆ፣ ዘለግ ያለች መልከ ንግሥት ዓይነት ነበረች፡፡ ግን የባላባትም ሆነ የነገሥታት የዘር ሀረግ የሌላት ምስኪን የድሃ ልጅ ናት፡፡ በዘመኑ ተጧጡፎ በነበረው የባሪያ ንግድ ከሀገሯ ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን፣ ከሱዳንም ወደ ግብጽ ካይሮ ደረሰች፡፡ ከአውሮፓ ድረስ ለባሪያ ግዢ የመጣው ጌታም ከተመለከታቸው መካከል በቢሊሌ የዓይን ፍቅር ተነደፈ፡፡ እያለም ብዙ የባሪያዎችን የድንጋይ ህግጋት ጥሶም ወደራሱ አስጠጋት፡፡ ወደ ንጉሣዊው ቤተሰብ ከተቀላቀለች በኋላም በፍቅሯ መክነፉን የጨመረው ባለዙፋን የአውሮፓን ቋንቋና ባሕል ብቻም ሳይሆን፤ በነበራት ቅልጥፍናና ዕውቀት የመጨበጥ ብቃቷ ትምህርት እንድትማርም ጭምር አደረጋት፡፡ በዚያ ላይ ንጹሕ፣ ገራገር ስብዕናዋ የማረከው ንጉሥም በስተመጨረሻ ከዙፋኑ ጎን አስቀምጦ ዓለም ሁሉ ተደመመባት፡፡ ከትንሽዬ መንደር ውስጥ ያውም በባርነት ወጥታ፣ ስንቱን መከራና ጭንቅ በመቋቋም፣ ኢትዮጵያዊነትን በለበሰው ስብዕናዋና ውበቷ ቅድመ ዓድዋን በአውሮፓዊው የንጉሥ ልብ ውስጥ ቀረጸች፡፡ ያደረገችውና የሚነገርላት እልፍ ቢሆንም ለዛሬው ዓይናችን ዳግም በሙዚቃው ያነገሳት ላይ ነው፡፡ ሙዚቃው አድማጭ ጆሮ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ብዙዎች መነጋገሪያ አድርገውት ሰንብቷል፡፡ ብዙዎችም እየተቀባበሉት የማህበራዊ ሚዲያውን አጥለቅልቆታል። በኢንተርኔት መረብ ውስጥ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ 2 ሚሊየን እይታዎችን በማግኘት ምን ያህል መወደዱን አስመስክሮለታል፡፡

አንዷለም በአዲስ ዓመት…አዲሱን ገጸ በረከት ለሙዚቃ አፍቃሪያን ሁሉ እንደሚሆን አድርጎ ያማረ የአልበም ሥራውን አምጥቶልናል፡፡ በነጠላ ዜማዎቹ ሲያስደስተው ለነበረው አድማጭ ዓመታትን ተጠቦና ተጨንቆ አሁን የበኩር አልበሙን አበርክቶለታል፡፡ የእርሱን የአልበም ሥራ ሲቋምጡ ለኖሩ ያለፉትን ጊዜያቶች ለማካካስ በሚመስል መልኩ እምብዛም ባልተለመደና ወጣ ባለ አቀራረብ 16 ሙዚቃዎችን በአንዱ አልበም ውስጥ አጭቆበታል፡፡ አልበሙን የተለየ የሚያደርገው በዛ ያሉ ሥራዎችን አንቀልባው ላይ መጫኑ ብቻ ሳይሆን ብዛትን ከጥራት ጋር በእኩል አስማምቶ “ከብዛቱ ጥራቱ” የሚባልለት አለመሆኑ ነው፡፡ ከአንዷ የመጀመሪያ ስንኝ አንስቶ እስከ ሙሉ አልበሙ እንዳያልቅ እየሰሰቱ የሚያደምጡት ዓይነት ነው፡፡ በቀመሱት ቁጥር ድገሙኝ የሚያሰኝ እንጂ በፍጹም ለየትኛውም ዓይነት አድማጭ አያታክትም፡፡ ስለዚህ የአልበም ሥራ ሙያዊ ብስለትና ጥፍጥና በትንሹ ለመቅመስ የሞከርን እንደሆን እኚህ ሁሉ ሙዚቃዎች በታጨቁበት ሙዚቃ ውስጥ አንድም የግጥምና ዜማ ድግግሞሽ አለመስተዋላቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በአልበም ሥራ ውስጥ ከሃሳብ ጀምሮ የሙዚቃ ባለሞያዎች የሚፈተኑበት እምደ መሆኑ፤ በአያንቱ አልበም ውስጥ በርከት ያሉ ዕውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች መሳተፋቸው እንዲህ ካለው እንከን ታድጎታል፡፡ በዓይነትና ይዘታቸው 16ቱም ከሁለት ተከፍለው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አሥር ያህሉ በጥናትና የምርምር ፈለጎች የሚገኙ ፈጠራ አዘል ግብዓቶችን የያዙ ናቸው፡፡ ቀሪ ስድስት ያህሉ ደግሞ በባሕላዊ እሴቶች ታሽተው የተዘጋጁ ሲሆኑ የኦሮሞ ማህበረሰብን ጥንታዊና አሁናዊ ቱባ መገለጫዎችን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የተሠሩባቸውን የሙዚቃ ስልቶች ስናጤን የሀገራችንን ልዩ ልዩ የሙዚቃ ስልቶች ለመጠቀምና ለማካተት የተሞከረበት መሆኑ ያስታውቃል፡፡

የአልበም ሥራው እንዲሁ እንደዋዛ ለመሥራት ያህል ብቻ ታስቦ እንዳልተሠራ ዙሪያ ገባው ይናገራል፡፡ ከታሰበበት ነገር አንዱ ተደማጭነቱ ከሀገር ውስጥ ያለፈ አድማስ እንዲኖረው በማሰብ አሉ የተባሉ ባለሙያዎቹን አካቷል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩን በማሳለጥ ሚኪ ጃኖ፣ ኤፍሬም ብርቅነህ፣ አንተነህ(አቡዝ)፣ እንድይ ቤተ ዜማ በጋራም በግልም ተጠበውበታል፡፡ በእነዚህ ባለሙያዎች የተቀናበሩትን ሙዚቃዎች በአንድ ወደ አልበም የማምጣቱን የማስተሪንግ ሥራ ጥንቅቅ አድርጎ የጨረሰው ደግሞ አንጋፋው አበጋዝ ሾይታ ነው፡፡ የሙዚቃው የጀርባ አጥንት በሆነው በግጥምና ዜማው ኢብራሂም መሀመድ፣ ሞቲ አባ ዳሌ፣ ላሊሳ ኢድሪስ፣ ፋጤ አኒያ፣ ናሆም መኩሪያ፣ ዘርዓ ብሩክ እና ሌሎችም አዋጥተውበታል፡፡ ከአንዷለም የግጥምና ዜማ ቅኝት በስተጀርባ በሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው የሙዚቃውን እስትንፋስ በመዝራቱ ሁለቱን የመሀሪ ልጆችን ጨምሮ ሌሎች ብርቱ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችም ተሳትፈውበታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ታዲያ አልበም የመሥራቱ ሃሳብ በአንዷለም ውስጥ ሲበቅል ድፍን ስድስት ዓመታቶች ሞልተውታል፡፡ ሆኖም ሥራው በተግባር ተገልጦ አያንቱን ለማስደመጥ መባተል ከጀመረ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ሙሉ አልበሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅም 7 ሚሊየን ብር ተቆጥሮበታል፡፡ ይሄው ዛሬ ከዓመታት በኋላ ህልምና ትልሙ እውን ሆኖ በተሳካ ሁኔታ በድል አጠናቆ የድሉን ዜማ አስደመጠን፡፡ ሰው የደገሰውን ሲበሉለት፤ የወለደውን ሲስሙለት ደስ ይለዋልና መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም አንጋፋዎቹንም ጭምር በመጥራት የመጀመሪያውን የድሉን ዜማም በዚያው የምርቃት መድረክ ላይ አቅርቦ በተዋበ ሁኔታ ተመርቆለታል፡፡ በአባገዳዎች እርጥብ በረከት ተመርቆ ለአድማጩ ከተለቀቀው አልበም ውስጥ የተመረጡ ጥቂት ሥራዎች ደግሞ በምስል ተዘጋጅተዋል፡፡

የአርሲው የጥበብ ፍሬ አንዷለም ጎሳ “አያንቱ” በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ላሳደገው ማህበረሰብ ለውለታው ማመስገኛ በሚመስል መልኩ የማህበረሰቡን ባሕላዊና ትውፊታዊ ማንነቶችን ከጫፍ ጫፍ ከፍ አድርጎበታል፡፡ “Qaxaleen Arsii tun na moote” በአንደኛው የአርሲ የታላቅ ሰው ልጅ ውበት ልቡ ሸፍቶና በፍቅር ነዶ እያወደሰ በሚያነግሳት በዚህ ሙዚቃ ውስጥ የአርሲን ባሕላዊ የጭፈራ ስልቶችና የእነርሱ ብቻ የሆኑ ቱባ ማንነቶችን ያንጸባርቅበታል፡፡ በሥራው አርሲዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፤ ከኦሮሚያ ዘሎ በመላው ሀገሪቱ ተወዳጅና ድንበር የለሽ ሆኗል፡፡ “ሰው የሚወደው አንተ ስትወደው ነው፡፡ እኔ ወድጄዋለሁና ሰውም ይወደዋል ብዬ አስባለሁ” ከአልበሙ መለቀቅ ቀደም ብሎ የተናገራት ቃል ነበረች፡፡ በርግጥም በሰውነት እግር ላይ ቆመው፣ ወደውና መርጠው የሠሩት ነገር ሰውን ማስደሰቱ አይቀርም፡፡

የአርሲው ቢሊሌ ቀደም ሲል የኦዳ ሽልማትን አሸንፏል። ገና ብዙ ሽልማቶችም ይጠብቁታል፡፡ በብርታትና ወኔ የዛሬን እንዲመለከት ያስቻለውም ይኸው ሽልማት ስለመሆኑ የተናገረበት አጋጣሚም ነበር፡፡ አንዷለም አሁን ላይ በሥራዎቹ የዝናን ሰገነት ለመርገጥ በቅቷል፡፡ በሥራ አጋጣሚዎች ጎኑ ከቆሙት ባሻገር በእርሱ ደስታቸውን እየገለጹ በፍቅርና አድናቆት የከበቡት መላው የሙዚቃ አፍቃሪያን ናቸው። ስለ ሥራዎቹም ሆነ ስለ ራሱ ማንም ስለ ብሔር፣ ቋንቋ የሚያስታውስ የለም፡፡ ያገኘው ሁሉ በፍቅር ያጅበዋል፡፡ ሊያገኘው የሚፈልግ ሁሉ ያስበዋል፡፡ “ነገሮች ላይ ተጠላልፈህ በጭራሽ እንዳናገኝህ፡፡ እባክህን በርትተህ ሥራልን” በሚሉ በብዙዎች ታጅቧል፡፡ የማናቸውንም ቃላት ቸል ሳይል ስለ አደራዎቻቸው መጨነቁን በመናገር እርሱም “…ማናቸውንም ማሳፈር አልፈልግም፡፡ ብዙ ዓይነት ነገሮች ውስጥ ለመግባት እየገባሁ መጠንከር የምፈልገውም ለዚሁ ነው፡፡ አደራ አለብኝና ሠርቼ ማሳየት እፈልጋለሁ” ሲል ከአንድ ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ አንስቶታል፡፡ ለወጣቱ ሙዚቀኛ ይህ ጅምር እንጂ የስኬቱ መጨረሻ አይደለም፡፡ ገና ብዙ ወደፊት አለውና በብዙው እንደሚያስደምመን ሙሉ የእምነት ተስፋችን ነው፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You