አዲስ አበባ ያፈራቻት ታታሪ አርሶ አደር

ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በፋርማሲ የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ሲነር ፋርማሲስት ባለሙያ ናት፡፡ ትምህርቷ እና አስተዳደጓ በመራት የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ወደ ገበያው ይዞ የመቅረብ ሃሳብ እንደ ተግዳሮት የተመለከተቻቸውን ችግሮች ለመፍታት የተጓዘችበት መንገድ ‹‹ነገርን ከስሩ … ›› እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል የገጠማትን የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በተጓዘችበት መንገድ በሺዎች ለሚቆጠሩ እንስቶች የሥራ እድል ለመፍጠር አስችሏታል፡፡

በሀገራችን የምግብ ሥርዓት ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን ነገር ግን እምብዛም ትኩረት ያልሰጠውን ቅመማ ቅመም በስፋት ማምረት ዘርፍ ውስጥ በመግባት በአሁን ሰዓት በከፋ ዞን ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ በቅመም የተሸፈነ የእርሻ ስፍራ እንዲይዝ እና በአካባቢው የሚገኙ እንስቶች እንዲጠቀመቡት አድርጋለች፡፡ በዛሬው የሕይወት ገጽታ አምዳችን የወይዘሮ ራሔል ህሩይ የዳማሲን የመዓዛማ ዘይቶች፣ የቅመማ ቅመም ማምረቻ እና ማቀነባበሪያ ኃ/የተ/የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሕይወት ጉዞ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

የልጅነት ጊዜ እና ትምህርት

ራሄል ትውልድና እድገቷ በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የልጅነት ጊዜዋ የተሟላ ምቹ እና በእሷ አገላለጽ የራሷ ሞግዚትም ጭምር የነበራት በቅንጦት ተይዛ ያደገች ናት፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በላዛሪስት ትምህርት ቤት እንዲሁም ሕይወት ብርሃን ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት አሳልፋለች፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፋርማሲ የትምህርት የተከታተለች ሲሆን በሙያዋም ሲኒየር ፋርማሲስት ናት፡፡

ራሔል አሁን እየሰራች የምትገኝበትን ግብርና ውስጥ ለመግባት የሚያስችላትን የድኅረ ምረቃ ትምህርቷን በአግሪ-ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ያጠናቀቀች ሲሆን ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር በርካታ ስልጠናዎችን ወስዳለች፡፡

ራሔል በልጅነት አዕምሮዋ በአካባቢዋ እና በአስተዳደጓ ታስተውለው የነበረው ባሕላዊ እውቀት አሁን ለምትሰራበት ዘርፍ ልጅነቷ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ትገልጻለች ‹‹በልጅነቴ የሀገራችን ባሕላዊ መድኃኒቶችን እያየሁ ነው ያደጉት እናም እነዚህ መድኃኒቶች ዘመናዊ በሆነ መልኩ ቢሰሩ ብዬ አስብ ነበር፡፡›› የምትለው ራሔል በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች የሚበቅሉ ለመድኃኒትነት፣ ለመዋቢያ አገልግሎት እና በምግብ ውስጥ እንደ ቅመም የሚያገለግሉ እጽዋቶችን በአግባቡ የሚጠቀሙ ባለሙያዎች አሏት፡፡ ነገር ግን እነዚህ ባሕላዊ እውቀቶች ተጠንተው እና አድገው በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ አይስተዋልም፡፡ ይህ ሃሳብ ራሔልን ወደዚህ ዘርፍ እንድትገባ ያደረጋት ነበር፡፡

የተለያዩ ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን በመጠቀም ለውበት መጠበቂያ የሚውሉ መዓዛማ ዘይቶችን ለማዘጋጀት በምታደርገው ሂደት ውስጥ ግን እነዚህን የግብርና ውጤት የሆኑ ግብዓቶች እጥረት መኖሩን ተመለከተች። በዚህም አልተወሰነችም ይህን ችግር ይፈታልኛል ያለችውን መንገድ ጀመረች፡፡

ከግብርና ምርምርና ጥናት ላይ የሚያተኩሩ ተቋማት ጋር ጎራ በማለት ከውጪው ካለው የማምረት ሥራ ባለፈ ከመነሻው የሚያመርቱ አርሷ አደሮችን ሕይወት የማየት አብሮ የመሥራት እና በዛ ሥራ የመሳብ እድል አገኘች ‹‹ በምጓዘው ጉዞ ውስጥ የሚፈጠሩብኝ ጥያቄዎች ይበልጥ ወደ አርሶ አደሩ እንድቀርብ አደረገኝ፡፡ ከዛም የሀገራችን የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ውስጥ የሚሰራ ሰው ጋር ለመተዋወቅ ቻልኩ፡፡›› የምትለው ራሄል በአካባቢው የብዝሀ ሕይወት ያለውን ተፈጥሯዊ የደን ሀብት እና ሥነ ምህዳሩን መጠበቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለገበሬው ሕይወቱ መሆኑን ተረዳች፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ቁጥር መጨምር የቤተሰብ መብዛት አዳዲስ ፍላጎቶችን እና የመኖሪያ ቦታ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ የማይቀር ነው፡፡

በመሆኑም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የእርሻ ባለቤቶች ያላቸውን ሀብት ወደ ጥቅም እና ገቢን ወደ ማስገኘት መቀየር ይገባዋል የሚል እምነት ራሄል ልብ ውስጥ ነበረ፡፡ በመሆኑም ለሥራዋ የጥሬ እቃ ግብዓት ፍለጋ ወደ ገጠር የገባችው እንስት የምትፈልገውን ጥሬ እቃ የሚያቀርቡላት ሰዎችን ወደ መፍጠር እና ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር ሥራ ውስጥ ራሷን አገኘችው፡፡

‹‹በባሕላችን በምንጠቀማቸው የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ሀብታም ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚህም ቅመሞች ግን በአብዛኛው ለምግብነት ብቻ የሚውሉ ናቸው፡፡›› በማለት ገልጻ ይህንን እንደ ፕሮጀክት በመያዝ እነዚህ ግብዓቶች ያለቀላቸው ምርቶች ሆነው ወደ ገበያ እንዲቀርቡ ተጨማሪ ጥናቶችን ለማድረግ ሥራዋን ጀመረች፡፡ ፕሮጀክቱን ከያዘች በኋላ በገበያው ላይ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል?፣ ምርምሮች ላይ ምን ያህል ተሰርቷል ? ፣ ወደ መሬት የማምጣት ሥራ ይህንን ባሕል እንዴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያስ እንዴት በስፋት መሸጥ ይችላል? የሚለውን ወደ ማጥናት ገባች፡፡ በዚህም በደቡብ የሀገራችን ክፍል ያሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶች በቂ ጥናት ተደርጎባቸው ገና ከጫካ ያልወጡ እጽዋቶችን መኖራቸውን ገልጻ የሚታወቁት የቅመማ ቅመም ዝርያዎችም በብዛት እና በሚፈለገው የጥራት መጠን ማምረት ደግሞ ገበያው የሚጠይቀው ነውና ራሔል ለዚህም ሌላ መፍትሔ ማበጀት ይገባት ነበር፡፡

ጉዞ ወደ ግብርና

‹‹የተፈጥሮ ሀብቱ የሕዝቡ ብቻም ሳይሆን የአራዊቱም ጭምር ነበር እነዚህን የቅመማ ቅመም ዓይነቶች በአንድ መሬት ላይ ማምረት የሚል ሃሳብ መጣልኝ፡፡ የራሴ መሬት ይሁን ወይስ ሌላ የሚለው ግን ሌላ ጥያቄ ነበር ነገር ግን በማህበረሰብ ውስጥ አብዛኛው ሰው የራሱ መሬት አለው።›› በዚህ ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ እና የራሷን መሬት መገንባት ተቀባይነቱ አጠያያቂ የሆነባት ራሔል አሁንም ዳሰሳዋን ቀጠለች፡፡ ‹‹አንድ ያስተዋልኩት ነገር ትርፍ መሬት የሚባለውን ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎች ከሚኖሩበት ቤት ጀርባ የራሳቸው ጓሮ አላቸው በጣም የገረመን ግን እነሱ ጓሮ ብለው የሚጠሩት ከግማሽ ሄክታር እስከ አስር ሄክታር የሚያህል መሬትን ነው፡፡›› እንደ አንድ የከተማ ልጅ እንደዚህ ዓይነት መሬት ሰፊ መሬት የተንጣለለ ቤትን የተሰራበት ቦታ እንጂ ባዶ መሬት ለእርሷ አዲስ ነበርና በማህበረሰቡ ውስጥ ተዟዙሯ ባየችው መሠረት እነዚህ የመሬት ባለቤቶችን ወደ ሥራ በማሳተፍ የራሳቸውን ሥራ እንዲሰሩ እና ለእሷ ደግሞ የጥሬ አቅራቢ እንዲሆኑ የሚል ሃሳብ አፈለቀች፡፡

‹‹እኔ እቃውን ተረክቤ ሥራውን ማስኬድ ነው የምፈልገው፡፡ ነገር ግን የሚመረተው ምርት እንዲኖረው የምፈልገው የጥራት ደረጃ ደግሞ አለ።›› የምትለው ራሔል ይህንን ለማሳካት አርሶ አደሮቹ የሚጎላቸውን በማጥናት የቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ እውቀት ፣ በማህበር ማደራጀት ሊያግዙ ከሚችሉ አካላት ጋር ለመሥራት ውይይቶችን ማድረግ ቀጠለች፡፡

ዋናው ዘር ነው

በተፈጥሮ በመሳብ እዚህ የደረሰው የራሔል ሃሳብ 20 አርሶ አደሮችን በማደራጀት ወደ መሬት መውረድ ቻለ፡፡ በዚህም አላበቃም ወደ 300 አድጎ በአምስት ዓመት ውስጥ በያዘው እቅድ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሴት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ አሳክቶ እነዚህን ሴቶች ታሳታፊ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ስያሜውም ዳማሲን የመዓዛማ ዘይቶች የቅመማ ቅመም ማምረቻ እና መቀነባበሪያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ነው፡፡ በከፋ፣ በቤንች ሸኮ በተለያዩ ወረዳዎች እና በሥራቸው የሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ከማህበረሰቡ እና ከአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ ተዘዋውሮ እየሰራ ይገኛል ይህም ከዞን ወደ ዞን በመሸጋገር በጅምር ያለውን ማጠናከር ፣ ዘለቄታ ካላቸው ትልልቅ ገበያዎች ጋር ማስተሳሰር እና እንደ ድርጅት ያለውን አቅም ማሳደግ በእቅድ ተይዘው በሥራ ላይ የሚገኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ራሔል በዳማሲን ያሳተፈቻቸው ሴት አርሶ አዶሮች ተደራጅተው እንዲሰሩ እና ምርቱን እንዲስረክቧት ብቻም ሳይሆን ድጋፍ ማድረግ ወደ ጓሮ የሥራ ቦታቸው ገብቶ ስልጠና መስጠት፣ የሚተክሏቸውን ችግኞች ማዘጋጀት ዘር መምረጥ በዳማሲን የሚሰሩ ናቸው፡፡ ዝንጅብል ፣ ኮረሪማ ፣ ኮሰረት ፣ እርድ ፣ ጤና አዳም ፣ ሮዝመሪ እና ሌሎች ወደ 15 የሚደርሱ ዝርያዎች ላይ ትሰራለች ‹‹ቅመማ ቅመሞች አንድ ሰብል ብቻ አይደሉም ስለዚህ አንድ ላይ መሥራት ያስፈልግ ነበር፡፡ በአንድ መሬት ላይ ለመዝራት የሚታወቁ ዝርያዎችን መጠቀም አስፈላጊ ስለነበር ለዚህም ምርምሮቻችን ላይ መሠረት ያደረገ እንዲሆን እንሰራለን፡፡›› ራሔል የምርምር ሥራዎች ላይ እምነት አላት ነገር ግን እነዚህ የምርምር ሥራዎች ውጤታማነታቸው ወደ መሬት እንዲወርድ ደግሞ ወደ ንግድ ሃሳብ መቀየር አለባቸው የሚል እምነት አላት። ከሰዎች ጋር አውርቶ የመግባባት ፣ የገንዘብ ችግር ፣ የቦታ ችግር ከሚገጥሟት ውስጥ ናቸው ዘሩን ከተለያዩ አካባቢዎች ከወላይታ፣ ከወንዶ ገነት ይሰበሰባል ታዲያ በእጽዋት ምርምር፣ በደን ሀብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ እነዚህን ተቋማት ቋሚ አጋሮች በማድረግ አብራ ትሰራለች፡፡ አንደኛው የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር መዓዛማ ዘይቶች እና እጽዋቶች እንዲሁም ለመድኃኒትነት የሚውሉ እጽዋቶች ላይ የሚውል የምርምር ማዕከል እና በሚዛን ቴፒ የሚገኝ የተለያዩ ቅመማ ቅመምነት ላይ የሚውሉ ሌሎች አዳዲስ ምርምሮችን እያደረገ እጽዋቶችን ይፋ የማድረግ ሥራ የሚሰሩት ይገኙበታል፡፡

ራሔል ከዚህም በተጨማሪ ባሕላዊ እውቀቶች ወይንም በተለምዷዊ በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚገኙ እውቀቶች ቦታ ትሰጣለች ለማሳደግም ሥራዎችን ትሰራለች፡፡ ‹‹ለምሳሌ እናቶቻችን ቂቤን በቤታቸው ሲያነጥሩ የሚጠቀሙት አንዱ እጽዋት ኮሰረት ቢሆን ማንኛውንም የኮሰረት እጽዋት አይጠቀሙም በማሽተት የሚሆነውን ይለዩታል፡፡›› ታዲያ ራሄል ይህን ባሕላዊ እውቀት አልናቀችውም የተሻለ የጥራት ደረጃ ያለው የቅመማ ቅመም የእጽዋት ዝርያ ለመፍጠር እና ለመትከል በከፋ ዞን በየቀበሌው ያሉ እናቶችን ሰብስባ እናቶቹ ባላቸው እውቀት ተክሉን እንዲመርጡት አደረገች ፤ ከዚያም ያን ተክል ችግኝ በማድረግ በድጋሚ የተሻለውን እንዲሁ እንደመርጡ ካደረገች በኋላ የመረጡትን ችግኝ በማባዛት በመስጠት በየጓሯቸው እንዲተክሉት ተደርጓል፡፡ እነዚህም የተወሰኑትን ከምርምር፣ ከእናቶች እውቀት፣ በጫካ ውስጥ የሚገኙ የቅመማ ቅመም ችግኞችንን ደግሞ በምርምር በመታገዝ ሥራዎቿን ማስፋፋት ቀጠለች፡፡

እውቀት በተለያዩ መንገዶች ሰዎች ጋር ይዘራልና ራሔል የምትሰራቸው ሥራዎች ላይ የራሷን እይታ ብቻ እንዲወሰን አትፈቅድም ‹‹እኔ የማምንበትና እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን የሚል እምነት የለኝም የሰዎችን እውቀት ለመቀበል እጥራለሁ ሃሳባቸውን ለመስማት በጣም እፈልጋለሁ መሳሳት ደግሞ ያለ ነው ተሳስተንም አንቀርም እያሻሻልነው እንሄዳለን፡፡››

የማህበረሰቡን እውቀት በማከል በምርምር ሥራ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን በማሳተፍ እና የተለያዩ የተረጋገጡ ኤክስፐርቶች ወደ ቦታው ሲመጡ ስልጠና እንዲሰጥ በመጠየቅ የተሻሉ የጥሬ እቃ ግብዓቶች እንዲመረቱ ማድረግ ችላለች፡፡ በዚህም ቋሚ የችግኝ ጣቢያ በማቋቋም በጥንቃቄ የተመረጡ ችግኞች ጥራታቸውን እንደጠበቁ በብዛት ማምረት የሚያስችል ነው፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ዘር ነው ስለዚህ እነዚህን የችግኝ ጣቢያዎች ከወረዳዎች ተቀብዬ እኔ ማስተዳደር በምችለው አቅም አራት የችግኝ ጣቢዎች አቋቁመናል በአካባቢው ያለ ሴቶችም አሁን ላይ የተሻለ ልምድ አላቸው፡፡››

ሴቶች አርሶ አደሮችን መፍጠር

ራሔል የምታደራጃቸው አርሶ አደሮች በአብዛኛው ሴቶች ናቸው፡፡ ይህስ እንዴት ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄ እሷ የምትለው አላት፡፡ ‹‹ሴት ስለሆንኩ ሴቶችን ብቻ ላሳትፍ የሚል እሳቤ አልነበረኝም እኔ በግሌ ይህንን የጥሬ እቃ የሚያቀርብልኝ ሰው ለማግኘት የራሴን የእርሻ መሬት ማግኘት አልቻልኩም እርሻ ያላቸው ወንዶች አልያም አባወራዎች ደግሞ መሬታቸው ራሳቸውን ቤተሰባቸውን የሚስተዳድሩበት ነው ይህ ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የምሰራውን የሙከራ አልያም በጅማሮ ያለ ፕሮጀክት ላይ በመሆኑ ፍላጎት አላሳዩም፡፡›› ታዲያ ሌላ መንገድ መፈለግ ልምዷ ነውና ለዚህ ምቹ ሆኖ ያገኘችው በአካባቢው ያሉ ሰዎች እንደ ጓሮ የሚጠቀሙበትን መሬት ገጣጥሞ ትልቅ አቅም እንዲፈጠር ማድረግ ነበር፡፡ ‹‹በከፋ ባሕል ጓሮ የሴቶች ነው ያልተጠቀምንበት ሀብት ነው ሴቶች ደግሞ በአብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በቤት ውስጥ ነው ስለዚህ እነዚህን ይህንን መሬት

ብንጠቀም እና ለሴቶች የሥራ እድል ብንፈጥር ለእነሱም ቤታቸውን የሚያግዙበት ነው፡፡›› ሴቶች በዚህ ዘርፍ የራሳቸውን እውቀት የሚያሳድጉበት በራሳቸው ጓሮ እና በቤታቸው በመሆን ምርታቸውን አቅርበው እና ሽጠው ወደ ገበያ በማቅረብ ገቢ የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡

ይህንን ሃሳብ ወደ መሬት ለማውረድ ከአንድ እንስት እስከ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳመን ቀላል የማይባል ሂደትን አልፋለች ነገር ግን በቦታው በጋራ በመሥራት፣ የሰዎችን እውቀት በስፋት በመቀበል እና በመሞከር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተግባብታ እና ተስማምታ ለመሥራት ትጥራለች ፤ ራሄል በገጠር ውስጥ ብቻም አልተወሰነችም ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፕሮጀክቷን በማስተዋወቅ እንዲደግፏት ታደርጋለች፤ ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርባ በመሥራት ዛሬ ያለ የደረሰበት ደረጃ ችላለች፡፡

የሀገር ልጅ በተግባር

ራሔል በሥራዋ ወደማታውቀው የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ በቤንጅ ሸኮ ሁለት ወረዳዎች በከፋ ደግሞ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ እየሰራች ትገኛለች አሁን ያለችበት ደረጃ ሥራዋንም ስኬታማና ጥሩ ሆኖ አግኝታዋለች በዚህም ስለ አካባቢው እና በቦታው ስላሉ የማህበረሰብ ክፍል የምትለው አላት ‹‹ስለዚህ ክልል አንድ መናገር የምችለው ነገር በጣም ትልቅ አቅም አለ፤ ማንም ሰው ከየት ነህ ብሎ አይጠየቅም ሁሉም ሰው የሚያውቀውን ያሳየኛል መሄድ ያለብኝን መንገድ ይጠቁመኛል ይህ ባሕል ያጠነክረኛል፡፡››

‹‹ሥራዬን ለመሥራት አብዛኛውን ጊዜ ሆቴል አድራለሁ ታዲያ ወደ ልጆቼ ደውዬ ካላገኘኋቸው በጣም እጨነቃለሁ የማደርገው ይጠፋኛል ነገር ግን የማልመው ነገር ከእለት ምግብ ያለፈ ነው፡፡›› በማለት ህልሟ ሩቅ መሆኑን እና በቅርቧ ያሉ ሰዎች በደስታን የሚፈጥሩላት እና መልካም የምትላቸው ሰዎች በሕይወት እንድትቀጥል ያደርጓታል፡፡ ‹‹በአንድ ወቅት ወባ ታምሜ ለ25 ቀን አልጋ ላይ አሳልፌ ነበር በዚያን ወቅት ሰዎች ለእኔ ያላቸው ፍቅር በእጅጉ አይቼበታለሁ።›› በማለት ገጠመኟንም ታነሳለች፡፡

ቤተሰብ እና ህልምን ማስኬድ

ራሔል ይህንን ፕሮጀክት ስትመራ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናትም ጭምር ናት፡፡ በዚህ የሥራ እንቅስቃሴዋ ውስጥ አሁን ላይ በሕይወት የሌለውን ባለቤቷን በማሰብ ትጀምራለች ‹‹ሥራዬ ደስታን ይሰጠኝ ስለነበር ባለቤቴ እጅግ በጣም ደጋፊዬ ነበር እዚህ ትደርሳለች ብሎ ያሰበም አይመስለኝም፡፡›› በማለት ታስታውሳለች ወላጆቿም በሕይወት የተመቻቸ አኗኗር መኖር የምትችል ናትና ለምንድነው የምትለፈው የሚል ጥያቄን በተደጋጋሚ ያነሱላታል በጉዞዋ ግን ይደግፏታል ልጆቿም አብዛኛውን ጊዜ ከወላጅ እኗቷ ጋር ስለሚቆዩ ለእርሷ ትልቅ እረፍት መሆኑን ራሔል ታነሳለች። ‹‹የመጀመሪያ ልጄ አሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው ፣ ሁለተኛዋ ልጄ ደግሞ ማትሪክ ተፈታኝ ናት ፣ ሶስተኛው ልጄ ደግሞ ሰባተኛ ክፍል ነው አብሯቸው ያደገ ድርጅት ስለሆነ ይወዱታል፡፡ ››

ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ መቅረብ

‹‹ የተነሳንበት ሃሳብ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ቢዝነስ ማቅረብ ቢሆንም ተቀባይነት ያለው፣ ጥራት ያለው ምርት እንዲሆን ከመነሻው መሥራት የግድ ነበር፡፡›› የአቅርቦት ሂደቱን ማስተካከል ላይ ለመሥራት ወደ እርሻ የገባችው ራሄል ዳማሲን አሁን ያለበት ደረጃ መልካም መሆኑን ታነሳለች፡፡ ‹‹ ብዙ ሥራዎች ቢቀሩትም ገና አሁን ነው ቢዝነስ የመሰለው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡›› አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን በማቅረብ ከሚታወቀው የዩኒሊቨር ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጻ ፤ ድጋፍ በማድረጉ ደግሞ ከዩኤስ ኤይድ ጋር በመሆን በቅርቡ ከእርሻው ጀምሮ አብረው መሥራት እንደሚጀምሩ ገልጻለች፡፡

በተጨማሪም በወረዳው የተሰጣት መካከለኛ እርሻን በመጠቀም በዙሪያዋ 500 አርሶ አደሮችን ይዛ እርድን በስፋት ከትንሽ እስከ ትልቅ በማምረት ከሀገር ውስጥ ገበያ መጀመር በእቅድ የተያዘ መሆኑን ራሔል ትጠቅሳለች፡፡ በቀጣይም በተለያዩ ሀገራት ኤከስፖርት የማድረግ ሂደቶች ያሉ ሲሆን የማምረት አቅምን በማሳደግ በብዛት ፣ በዘለቄታው የማምረት አቅም ላይ በመድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚጠቅም የኤክስፖርት አቅም እንዲኖረው ማስቻል ራሔል አሁንም እየሰራችበት ያለችው ጉዳይ ነው ለዚህም የማስተዋወቅ ሥራን እየሰራች ነው፡፡

የወደፊት ህልሟ ውስጥ በዘርፉ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ አምራቾች እነዚህን ቅመማ ቅመሞችም ሆኑ ለውበት መጠበቂያ የሚያገለግሉ ምርቶች ሰዎች በሚፈልጓቸው መጠን፣ ዓይነት እና ጊዜ ላይ ያለ ምንም ተግዳሮት እና መዘግየት ማቅረብ የሚችል እንዲሆን ነው፡፡

ዘርፉ እምብዛም ባለሙያዎችም ሆኑ አምራቾች በብዛት ያልተሳተፉበት ነውና ራሔል በዚህ ዘርፍ አሁን ላይ የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ የገጠሟትን ችግሮች በመቅረፍ ለሚመጣው ባለሙያም ሆነ አምራች ካለፈው ጊዜ የተሻለ መሆኑን አንስታ ከተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን የመሞከር እድል በመስጠት ከማህበረሰቡ ጋር ተገናኝተው እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ እንዲሁም በቀጣይ የማሰልጠን ሃሳብ ሰዎች የተማሩትን የሚሞክሩበት እንዲሆን ሌላኛው እቅድ ነው፡፡

ራሄል በከፋ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በሥራቸው በሚይዟቸው በርካታ ቀበሌዎች የሚገኙ ሴት አርሶ አደሮችን በማደራጅት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እነዚህ አርሶ አደር ሴቶችም ህብረታቸውን በማጠንከር ሥራቸውን ማሳደግ የሚችሉባቸውን ሥርዓቶች መፍጠር መቻሉን አንስታለች፡፡ አንድ ማህበር በቀላሉ 200 ሴቶችን ሲይዝ አንድ ቀበሌ ውስጥ 40 ሴቶች ሊኖሩ ይችላሉ ከዚያም እነዚህን በቡድን በማደራጀት አንድ ላይ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህም በሥራቸው በርካታ ሴቶችን የያዙ 12 ኮኦፐሬቲቮች ይገኛሉ፡፡

መሠረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት

በዚህ ዘርፍ ችግርን ከመነሻው ለመቅረፍ ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በማቅናት ኑሮዋን ከማህበረሰቡ ጋር አድርጋ የከተመችው ራሔል የአካባቢው ማህበረሰብ ሊሟላለት የሚገቡ ነገር ግን ያላገኛቸው መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀላል የማይባሉ መሆናቸውን ትጠቅሳለች፡፡ ቤንቺ ጨና የሚባል ወረዳ ስር አምስት ቀበሌዎች ሲሆኑ 17 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ምቹ ያልሆነ መንገድ ፤ ሌሎች ቀሪ ቀበሌዎች ደግሞ ምንም መንገድ ያልተሰራላቸው ናቸው፡፡ ‹‹በየቀበሌዎቹ ከ3 ዓመት እስከ 14 ዓመት ያሉ 20 ሺህ ትምህርት ያላገኙ ሕፃናት ይገኛሉ ይህ በጣም አደገኛ እና አሳዛኝ ነው፡፡›› ከዚህም በተጨማሪ የመገበያያ ስፍራ የተደራጀ ገበያ ለአንድ ማህበረሰብ ወሳኝ መሆኑን የምታነሳው ራሔል ይህም አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሳለች፡፡ ‹‹በዚህ አካባቢ ትንንሽ ቆጪ ተብለው የሚጠሩ ገበያዎች አሉ ወደ እዚህ ቦታ ለመሄድ ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ መንገድ መጓዝ አለባቸው፡፡ ›› ይህ ለእናቶች እጅግ ከባድ መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡

በተለያዩ ማህበረሰባዊ ድጋፎች ላይ ተሳትፈው አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉ ተቋማት ደግሞ ወደዚህ አካባቢ መጥተው ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ወፍጮ ቤት፣ የጤና ተቋማትን መገንባት ቢችሉ ትልቅ ገጸ-በረከት መሆኑን አንስታለች፡፡ ራሔል በዚህ አካባቢ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ዘርፎች ጥናት ተደርጎባቸው ተለይተው የተቀመጡ 12 ዘርፎች መኖራቸውን አስታውሳ እነዚህ ተቋማት ቢቋቋሙ እነዚህ ኮፐሬቲቮች ደረጃ የተቋቋሙ እናቶች በራሳቸው ማስተዳደር እንደሚችሉ ገልጻለች፡፡

በአጠቃላይ ሴቶችን እናበቃለን ብለው የሚሰሩ ተቋማት ዝግ የሆነውን አሰራር ብድር ለማግኘት ያለውን ረጅም እና የተወሳሰበ መንገድ ሊቀርፉ ይገባል፡፡ ‹‹እነዚህ ኮፐሬቲቮች ብድር ቢያገኙ ችግሮችን መቅረፍ ይችላሉ መቅረፍ ሲችሉ በጓራቸው የተከሏቸውን በአግባቡ መሰብሰብ እና ማከማቸት ይቻላል ይህ ሲሆን ኤክስፖርት ማድረግ በብዛት ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ የሚለው ጥያቄ መመለስ ይችላል፣ የሥራ እድል ፈጠራውን ማስፋት ይቻላል፣ ያሉትን ማህበራት በማጠናከር ጠንካራ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡›› የሥራ ያደገ የገቢ አቅም ፣ ማምረቻ ቦታዎችን ማመቻቸት የዓለም አቀፉን ገበያ ደፍሮ ለመግባት ያስችላል፡፡ ‹‹ኮኦፐሪቲቮቻችን ተበታትነው ያሉ ከመሆናቸውም በላይ በየቦታቸው ብዙ ችግሮች አሉባቸው በመሆኑም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመዋዕለ ሕፃናት ጭምር አቋቁመናል፡፡

ወይ አልተጠጉን ወይ አልተጠጋናቸው

የቅመማ ቅመም ምርቶችን በጥራት ከመነሻው ለማምረት እርሻን የመረጠችው ራሔል በ2008 ዓ.ም ወደ ስትጓዝ ምንም ሄክታር ያልነበረው ዘርፉ አሁን ላይ የቅመማ ቅመም ምርት በአካባቢው ከሁለት ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቅመም መሸፈን መቻሉን ትገልጻለች፡፡

ራሔል የውበት መጠበቂያ ምርቶችን የተመከለተ ሥራዋን ለማሳካት በምታደርገው ጥናት ጥሩ ልምድ መቅሰም የቻለችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች ፤ ባሕላዊ እውቀቶችን በመጠቀም በሀገራችን የሚገኙ ቅመማ ቅመሞች ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎችም ሆኑ በዘርፉ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች እምብዛም ባልተሳተፉበት ዘርፍ በመግባት በቀጣይ መሥራት ለሚፈልጉም እሷ ከመጣችበት መንገድ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ችላለች፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ የአሰራር ሥርዓቱ ምን ያህል ምቹ ነበር ምንስ መደረግ ይገባዋል የሚለው ላይ ሃሳቧን አካፍላናለች፡፡

‹‹የተለያዩ አካላት ዘርፉ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ይተባበራሉ የምርምር ተቋማትን፣ የብዝሀ ሕይወትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የተነሳንበት ሃሳብ እንደ አንድ የግል ተቋም ለብቻ ማድረግ ከባድ ነው ኢንቨስት የሚደረግበት የገንዘብ አቅም ብድር ለማግኘት ከባድ ነው።» ምክንያቱም የምርጥ ዘር ችግኝ አፍልቶ ለአርሶ አደሮች አከፋፍሎ ፕሮጀክቶች ከግብ ለማድረስ እና ምርቶቹን ለእርሻ ላይ ሰብስቦ ለገበያ አቅርቦ ሥራው የወጣበትን ገንዘብ መተካት እጅግ ከባድ መሆኑን የምታነሳው በሥራ ላይ ያሉ አካላትን ቀርቦ የማነጋገር ሥራን በዘርፉ ያሉ አካላት በአካባቢው አካላት በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ሰዎች በዚህ ዘርፍ ያሉ ድርጅቶችን ማብቃት ላይ በጋራ መሥራት የሚገባቸው መሆኑን ራሔል ትገልጻለች፡፡

‹‹እነዚህ ሴቶች ከሚወስዷቸው ስልጠናዎች ውስጥ እንዴት ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ፋይናንስ ላይ ያተኮረ ስልጠና ወስደው በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲቆጠቡ ተደርጓል፡፡ መቆጠብ መበደር ምን ማለት እንደሆነ አሰለጠናቸው በጣም ጠንካሮች ነበሩ ለመበደር በሚፈልጉበት ጊዜ ግን ኮላተራል ተጠየቁ ይህን መፍታት ከባድ ነበር፡፡ እነዚህ ሴቶች ሞራላቸው እንዳይነካ እኔ ራሴ አበዳሪ መሆን ነበረብኝ፡፡ ››

‹‹ለተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶችም ሆኑ የአሰራር ሥርዓቶች ለማህበረሰብ አቀፍ የንግድ እሳቤ አዲስ ናቸው ለዚህ የሚሆን የአሰራር ሥርዓት በውስጣቸው የለም ስለዚህ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚሰሩ አካላት ቀርቦ ለሚያናግሯቸው ሥራ ፈጣሪዎች ሥራቸውን ዞር ብለው ማየት ለማገዝ ፍላጎት ማሳየት ይገባቸዋል።›› አምስት ሺህ ሴት አርሶ አደሮችን መፍጠር ሰርተው ያመረቱትን እንዲሸጡ ለዛውም ገቢ ማፈላለግ የሚገዛቸው ሰዎች መፈለግ ሳይጠበቅባቸው እንዲሰሩ ማስቻል ቀላል አይደለም የምትለው ራሔል ሴቶችን መደገፍ ማህበረሰብን መደገፍ የሥራ ፈጠራን ማሳደግ ብድር መስጠት በሚል ዓላማ የተቋቋሙ ድርጅት ‹‹ወይ አልተጠጉን ወይ አልተጠጋናቸው››

‹‹አንዳንድ ተቋማት ብድር ለመስጠትም ድጋፍ ለማድረግም ቃል ይገቡልናል በኋላ ግን የምናውቀውን የባንክ ሂደት ያመጡልናል ያ ደግሞ ውጤት የሌለው ነገር ግን በጣም ረጅም ሂደት ያለው ነው፡፡ ይህ አሰራር ሂደት ከምንሰራው ሥራ ከምንመራው የሕይወት ዑደት ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ባለኝ ነገር መሥራት መቀጠልን እመርጣለሁ፡፡›› የምትለው ራሔል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ተቋቁመው ነገር ግን ዝግ የሆነ አሰራር ያላቸው ናቸው በመሆኑም በሥራ ላይ ያሉ አካላትንም ሆነ ሃሳብ ያላቸውን እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ቀርበው ማነጋገር ፖሊሲ አውጪዎችም ቢሆን ይህንን መሰል ጉዳዮችን ወርደው ማየት ይገባቸዋል የሚል ሀሳቧን ታነሳለች፡፡

እውቅናዎች እና አበርክቶዎች

ራሔል ሥራዋን ‹‹ካደረግከው በትክክለኛው መንገድ አድርገው›› የሚለውን መርህ በመከተል ሥራዋን በመሥራት ዘርፉ ላይ ከሚሰሩ የተለያዩ አካላት እና ባለሙያዎች ጋር በጥምረት ትሰራለች በዚህም የአፍሪካ ሴቶች ኔትዎርክ አካል ስትሆን እ.አ.አ በ2021 በአፍሪካ አግሪ ቢዝነስ ሽልማት ላይ አሸናፊ ሆና ተመርጣለች፡፡ በዚህ ኔትወርክ ውስጥ ያሉ በተለያዩ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ሴቶችም ለሥራቸው ያግዛቸው ዘንድ ከኤግዚም ባንክ ብድር እንዲያገኙ መንገዶች ይመቻችላቸዋል፤ ራሔል ይህንን እድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው የሀገር ውስጥ ባንክ አሰራር ግን ዝግ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ‹‹ሰዎች ለምን ሥራዎችሽን እያሳየሽ አስተዋውቅሽ አትሰሪም ይሉኛል፤ እኔ በጓዳ ብዙ ያልሰራናቸው ሥራዎች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡››

በሌሎች መድረኮች ባገኘችው እውቅና ከአራት ዓመት በፊት የዓመቱ ምርጥ የሥራ ፈጣሪ ተብላ የተሸለመች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በቅመማ ቅመም ዘርፍ አማካሪ ታጭታ አገልግላለች። ራሔል ካገኘቻቸው እውቅናዎች ይበልጥ ቦታ የምትሰጠው በኢትዮጵያ ስታርታፖች ውድድር የሚዘጋጁባቸው ቦታዎች ላይ ራሔል በዳኝነት በመሳተፍ ከጀማሪዎች ጋር ልምዷን ታካፍላለች፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You