አሁን አሁን መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱና ካልተናገሩ የሌሉ የሚመስላቸው በርካታ ናቸው።የዚያኑ ያህል ደግሞ በግልፅ ከማውራትና ከመናገር ይልቅ ማንሾካሾክ የሚቀናቸው ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
እኔ እንደሚመስልኝ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ማህበረሰብ ሹክሹክታን ስራዬ ብሎ ይዞታል። ፍቅሩን፣ጥላቻውን፣ አድናቆቱንና ሌሎቹንም ስሜቶቹን የሚገለፀው በሹክሹክታ ሆኗል። በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተረው የዚህ ተግባር፤ ዋነኛ ማጠንጠኛው በአመዛኙ ሰው ነው።
የእያንዳንዱ ግለሰብ የማንሾካሾክ ባህሪ የተለያየ መልክ አለው። የሆነ ሰው እልፍ ይበል ብቻ አንዱ ወደ አንዱ ይጠጋና ይኼ ልጅ እኮ! ይቺ ልጅ እኮ፥ ባለፈው ያልኩህ ናት፤ ያቺ እንኳን» እያለ ይንሾካሾካል። በሆነ ባልሆነው፣ ባወቀውም ሆነ ባላወቀው ይዘላብዳል።ድምፁን አቀዝቅዞ እከሌ እንዲህ ነው፤እገሊት እንዲህ የሚልህ ሰው፤እከሌና እከሊት ሲመጡ ለማመን በሚያዳግት ፍጥነትና አክሮባት የውሸት ሳቅ፣የይሁዳ ሰላምታ ሲሰጥ ታስተውለዋለህ።
የተንሾካሿኪነት ባህሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ መልክ እንዳለውና በርካቶችም የተግባሩ ፈፃሚ መሆናቸውን ከወራት በፊት ሶሻል ሳይኮሎጂካል ኤንድ ፐርሰናሊቲ ሳይንስ / Social Psychological and Personality Science /ላይ የታተመው ጥናት ያመለክታል።
«መንሾካሾክ የትም ዓለም ያለ ነው፤አንድ ሰው በአማካኝ በቀን 52 ደቂቃ በማንሾኳሾክ ያባክናል፤በእነዚህ ደቂቃዎችም ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊው፤ከግለሰቡ መልካምነት ይልቅ መጥፎነት፤ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ይቀርባሉ ሲል»አስነብቧል።
ወደ እኛው ስንመለስ ምንም እንኳን የሹክሹክታ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሰው ቢሆንም፤ ተግባሩ ሲያድግ እየተራባና እየተባዛ ሲሄድ ፖለቲካንም ይነካካል።ተሰብስበህ በተቀመጥክበት ድንገት አንዱ አንሾካሻኪ ግራ ቀኝ ገልመጥ ያደርግና«ይሄ መንግስት እኮ፤ይህ ፖርቲ እኮ? ያንሾካሹካል።
በዚህ መልክ ብዙሃኑ ያሰበውን የገባውን ያመነበትን በግልፅ ከማውራት ይልቅ ሲያንሾካሹክ የተመለከተ ታዲያ «ምንድ ነው ግልፅ መናገር አስፈርቶ እንዲህ ያደረገን ? ብሎ ምክንያቱን መጠየቁ አይቀሬ ነው።
ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጡ ሳይኮሎጂስቶች ደግሞ የአንሾካሻኪዎች የማንሿከክ ዋነኛ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ በተለይ ቅናት፤የመበለጥ አሊያም የዝቅተኝነት እንዲሁም እኩይ የመሸነፍ ስሜት የወለደው መሆኑን ያሰምሩበታል።
ከዚህ የምንረዳው ታዲያ መንሾካሾክ ሰውን ከሰው የሚያጋጭ፤ ትዳር የሚበትን፤ ወንድማዊና የጓደኝነት ፍቅርን የሚያሻክር፤ በራስ አለመተማመን የሚሳያድግና ሌላም ብዙ መከራዎችን የሚፈጥር ነው። ይህ ደግሞ በጤነኛ አእምሮ እንዲፈፀም የሚፈቀድ አይደለም።
እናም ምርጫ አለ። ፊት ለፊት ማውራት ካልቻልክ ግን አታንሾካሹክ። ማንሾካሾክ ግን መብትህ ነው።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 2/2011
ታምራት ተስፋዬ