በዓለም ላይ በርካታ የቅንጦት እቃዎች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። አንዳንዶቹ እቃዎች ለመደበኛ የእለት ተዕለት ኑሮ አስፈላጊ ቢሆኑም ለቅንጦት ተብለው ከፍተኛ ገንዘብ ሲፈስባቸውና በተለየ ሁኔታ ሲሰሩም ይስተዋላል። ከነዚህም ውስጥ የሰማዩ በራሪ አውሮፕላን ይጠቀሳል። አውሮፕላን በዚህ ዘመን ዓለምን በማስተሳሰር ያለው ፋይዳ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል። በዚህ ዘመን ከአንዱ ጫፍ ወደሌላው የዓለም ጫፍ ለሚደረገው ጉዞ አውሮፕላን የአንበሳውን ድርሻ ይጫወታል። እንደቀደሙት ተጓዦች ማጄላንና ክርስቶፈር ኮሎምበስ ሰዎች በእግር ኳትነው ዓለምን ማግኘት ዛሬ ላይ የሚታሰብ አይደለም። በሰዓታት ልዩነት ከአንዱ አህጉር ወደሌላው አህጉር መሸጋገር የተለመደ ነው።
በዚያው ልክ ታዲያ አሁን አሁን እነዚህ አውሮፕላኖች ከመጓጓዣነት አገልግሎት አልፈው ቅንጦት እና የሀብት መገለጫም ሲሆኑ ይስተዋላል። በዚህም በርካታ ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ፈሶባቸው ለአገልግሎት የሚውሉት አንዳንድ አውሮፕላኖች ቅንጡ መኖሪያ ቤት ወይም ቢሮ እንጂ አውሮፕላን ናቸው ለማለት የሚከብዱ ናቸው። ጥቂቶቹን እናስተዋውቃችሁ።
የመጀመሪያው ቅንጡ አውሮፕላን ኤርባስ 380/Airbus 380/ የተባለው የዓለማቸን ግዙፉ የግል አውሮፕላን ሲሆን የዓለማችን ውድ አውሮፕላን በሚልም ተመዝግቧል። ይህ አውሮፕላን 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ነገስታትን ታሳቢ በማድረግ የተሰራ ነው። የዚህ አውሮፕላን ባለቤት የሳውዲው ልዑስ አለዋድ ቢን ታላ አል ሳኡድ ሲሆኑ የዚሁ አውሮፕላን ሞዴል የሆነ የሲንጋፖርና የኤሜሬትስ አውሮፕላንም ይገኛል። ይህ አውሮፕላን ለህዝብ ማመላለሻነት ሲውል እስከ 800 ሰዎችን ማጓጓዝ ይችላል።
ይህ የልዑሉ አውሮፕላን ‹‹በአየር ላይ የሚሄድ ቤተመንግስት›› የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። አውሮፕላኑ አራት የቤተሰብና የፀሎት/መስገጃ ክፍልም አለው። ኮንሰርት የሚካሄድበት ክፍል፣ የእንግዶች መቀበያ እና ለሎች በርካታ ዘመናዊ ክፍሎችም ያሉት ነው። ከዚህም ባሻገር ዘመናዊ የውበት መጠበቂያ ክፍሎችም አካቷል።
ሁለተኛው ውድ አውሮፕላን ደግሞ ቦይንግ 747-8 ቪአይፒ (Boeing 747-8 VIP) የተሰኘ ሲሆን ረጅሙና በትልቅነቱም በዓለም ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ነው። ይህ አውሮፕላን 367 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያወጣል። በውስጡም ቅንጡ የሆኑ ሆቴሎችና መዝናኛዎች እንዲሁም የእንግዶች መቀበያ ቢሮዎች አሉት።
ሶስተኛው ውድ አውሮፕላን ቦይንግ 757 (Boeing 757) ይሰኛል። ይህ አውሮፕላን አንድ መቶ ሚሊዮን የሜሪካን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከሚገኙ ዘመናዊ አውሮፕላኖች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። 43 መቀመጫዎች ያሉት ይህ የግል አውሮፕላን እያንዳንዱ መቀመጫ ቴሌቪዥን እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራ ነው። ከዚህም ባሻገር አንድ ሺ የሚሆኑ ፊልሞችና 2500 ሲዲዎችም አሉት።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 1/2011