በቴሌቪዥን መስኮት የሚወጣው የሙዚቃ ድምፅ ምን ያህል ሰዎችን የማዝናናት ብቃት እንዳለው እርግጠኛ ባልሆንም ድምፁ ግን አሁንም ቀጥሏል። አንዲት ወጣት ቢያንስ አስር ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ፋሽን ልብሶችን እየቀያየረች የተቀረፀችው ምስል ተቀነባብሮ በክሊፑ ውስጥ ቀርቧል። በሙዚቃው ውስጥ ምን አይነት ሚና እንዳለው በውል የማይታወቀው ወጣትም በስፖርት የዳበረ የሚመስለውን በጉርድ ሸሚዝ የተወጠረ ጡንቻ እያሳየ ኮስተር ብሎ ከጎኗ ይንጎማለላል። አልፎ አልፎም ከአረንጓዴ መስክ ላይ ተቀምጠው እሷ በእሱ እቅፍ ውስጥ ገብታ ትታያለች። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የቤቱና የመኪናው ውበት ጎልቶ ይታያል።
ይህ ከጥቂት ወራት በፊት የተለቀቀ አዲስ ነጠላ ዜማ ነው። ይህ ነጠላ ዜማ ለምን እንደቀረበና ምን አይነት አላማ እንዳለው ምናልባት ከሙዚቀኞቹ ወይም ከዘፋኟ ውጭ የሚያውቀው ያለ አይመስለኝም። እውነት ለመናገር ልጅቷ ዘፋኝ ለመሆን የሚያስችል ድምፅም ሆነ የአቀራረብ ስልት አላት ለማለት ከባድ ነው። እንደው አንዳንዴ በሙዚቃ ውድድሮች ላይ ለቀልድ ብለው ወይም በቴሌቪዥን ለመታየት ሲሉ ብቻ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን አስታወሰችኝ።
አንድ ወቅት በኢትዮጵያ አይዶል ሾው ላይ ለቀረበ አንድ ተወዳዳሪ በወቅቱ ዳኛ የነበረው ሰርፀፍሬ ስብሃት ተወዳዳሪው “ዘፈን” ካቀረበ በኋላ የተሰማውን ስሜት የገለፀበት መንገድ ሁሌም ትዝ ይለኛል። ተወዳዳሪው መድረክ ላይ ወጥቶ ለዛ በሌለው ድምፁ ብልግና የተቀላቀለበትና ከኢትዮጵያዊ ስነምግባር የወጣ ግጥም በማቅረቡ “ምነው አንዳንዴ እኮ ማፈር የሚባል ነገር አለ፤ ሰው ፊት ዝም ብሎ እንዲህ አይነት ፀያፍ ነገር ይቀርባል እንዴ” ሲል በምሬት ገልጾ ነበር።
ታዲያ ይህ ውድድር ስለሆነ ዳኛው በግልጽ የተሰማውን ለመናገር እድሉን አግኝቷል። ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ያለከልካይ የሙዚቃ ክሊፕ እየሰሩ ያልተገራ ድምጻቸውንና ያልተከረከመ አንደበታቸውን የሚያሰሙንን “ዘፋኞች” እና ይህንን ተቀብለው ያለከልካይ የሚያስተጋቡትን የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተመለከተ እኛ ለማን ምሬታችንን እናቅርብ ይሆን?
እውነት ለመናገር አሁን አሁን እድሜ ለሚዲያ ነፃነትና ለዘርፉ እድገት ምስጋና ይግባውና አንዱ ሲሰለቸን ወደ ሌላው ጣቢያ እየቀያየርን የማየቱ እድል ስለተፈጠረ እንጂ በአንዳንድ ጣቢያዎች በሚቀርቡት ክሊፖች እየተማረርን ወዴት እንሄድ ነበር?
አብዛኞቹን ክሊፖቻችን የሚያመሳስላቸው ነገር ደግሞ የሚቀረፁበት ቦታ ነው። ቪላ ቤትና ዘመናዊ መኪና የብዙ ክሊፖች ግዴታ እስከሚመስል ድረስ ክሊፕ ውስጥ አይጠፉም። በተለይ ከመኪናዎቹም ሆነ ከቤቱ ውበት እና ውድነት ጋር የማይመጣጠን ቁመና ተይዞ በዚያ ሁኔታ መቀረፅ ለምን የሚል ጥያቄን ያስነሳል፤ በይዘቱም ላይ የተአማኒነት ጥያቄን ያጭራል። የሚገርመው ደግሞ አንዳንዶቹ የቆመ የሰው መኪና አጠገብ የተቀረፁ እስከሚመስል ድረስ መኪናው ሲቆም እንጂ ሲንቀሳቀስ አይታይም። ዘፋኞቹም በመኪናው የውጭ አካል ላይ ተደግፈው እንጂ ወደ ውስጥ ሲገቡ ወይም ሲነዱ አይታዩም። ቤቱም ቢሆን ለክሊፑ የተከራዩት ቤት እንጂ ባለክሊፖቹ የሚኖሩበት አለመሆኑ ድባቡ ያስታውቃል።
ታዲያ በዚህ አይነት ሁኔታ የኛ ባልሆነ ነገር ለምን መጨነቅ እንደመረጥን አይገባኝ። ፍቅርን ለመግለፅ ከሆነ በደሳሳ ጎጆም ውስጥ ፍቅር አለ። የግድ ቤትና መኪና ከሌለ ፍቅር አይኖርም ማለት ነው?
ሴቶቹ በሚሰሩት ክሊፕ ላይ አጫዋች ወይም ፍቅረኛ ሆነው የሚቀርቡት ደግሞ በአብዛኛው ስፖርተኛ ወንዶች ናቸው። መልከ መልካም ወንዶችም ይመረጣሉ። በተቃራኒው ደግሞ ወንዶቹ በሚሰሩት ክሊፕ ላይ ፍቅረኛ ወይም ጓደኛ ሆነው የሚሰሩት ሴቶች ቆንጆዎች ናቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ “ፍቅረኛሞች” ተብለው የቀረቡትን ጥንዶች ሁኔታ ለተመለከተ የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። እውን እነዚህ ሁለት ሰዎች በዚህ ደረጃ የተቀራረበ ስነልቦና ይኖራቸዋል? የሚል ጥያቄንም ያጭራል።
ሌላው ደግሞ የድምጽ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሙዚቀኞች እንኳንስ ለሙዚቃ ይቅርና ለመስማትም የሚዘገንን ድምጽ ይዘው በቴሌቪዥን መስኮት ሲወጡ ማየት ከባድ ነው። የሚገርመው ደግሞ ለነዚህ ሰዎች የሙዚቃ ክሊፖችን የሚሰሩ አቀናባሪዎች ይህንን እያዩ መስራታቸው ነው። በርግጥ እነሱ በክፍያ እንደሚሰሩ ይታወቃል። ነገር ግን “እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እንደሚባለው ምናለ ትክክለኛውን ነገር ነግረዋቸው በአጭሩ ሌላ ሙያ እንዲፈልጉ ቢያግዟቸው የሚለው የሁል ጊዜ ጥያቄዬ ነው።
የልብስ መቀያየርም በአብዛኞቹ ክሊፖች ውስጥ የግዴታ የሆነ ያልተፃፈ ህግ ይመስላል። አንዳንድ “ዘፋኞች” በአንድ ክሊፕ ውስጥ እስከ 20 ጊዜ ልብስ ሲቀያይሩ ተመልክቻለሁ። የሚገርመው ደግሞ አብዛኞቹ የሚቀያይሯቸው አልባሳት ከሙዚቃው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸውና ከኛ ባህልም ጋር የማይሄዱ መሆናቸው ነው።
ውድ አንባቢዎች! እንደው ግን እነዚህን የአገራችንን ክሊፖች እስኪ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። እንደው አንዳንዶቹ እኮ በሙዚቀኞች ስም ሙያውን የሚያራክሱ ናቸው። በርግጥ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የደረጃ መለያየት መኖሩ ግድ ነው። ግን በዚህ ደረጃ መለያየት ሲኖርና በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ለመታየት ሲባል እንዲህ ሙያውን የሚያራክስ ተግባር ሲፈፀም ትክክለኛ ባለሙያውም ዝምታን መምረጥ ያለበት አይመስለኝም። አየር ሰዓት አገኘሁ ወይም ገንዘብ አለኝ ብሎ በሙያ መቀለድ መቆም አለበት ብዬ አስባለሁ።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም በተቻለ መጠን ለሙያው ትኩረት መስጠት ያለባቸው ይመስለኛል። ሙዚቃ ተገኘ ተብሎ ደረጃውን ያልጠበቀና የባለሙያውንና የሌሎች ለሙያው ቅርበት ያላቸውን ዜጎች የሚጎዱ ስራዎችን አየር ሰዓት ሰጥቶ ማስተናገድ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም። እናም ለሙያው ክብር እንስጥ!!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 1/2011
ወርቁ ማሩ