ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይመስለኛል፤ ከሙዚቃና ጥበባዊ ሥራዎች ውጪ ከ«ፖለቲካ» ሰዎች አንደበት «የኢትዮጵያ አምላክ» ሲባል የሰማሁት። በእርግጥ እድሜዬ በጣት በሚቆጠሩት ሥርዓቶች ውስጥ ተሳታፊም ሆነ ተመልካች የሚያደርግ አቅም ኖሮት አይደለም፤ ያው ሴት ስለሆንኩም ስንት ሥርዓት እንዳየሁ ልነግራችሁ አይቻለኝም። ሂሳብ ልትሠሩ! ብቻ ግን ከአባባ ጃንሆይ ወዲህ በቤተ እምነቶችና በኪነጥበብ ባለሙያዎች ካልሆነ የኢትዮጵያ አምላክ ሲጠራ ሰምቼ አላውቅም ለማለት ነው።
አሁን ላይ ዓለማችን «ሴኪዩላር» መሆንን፤ ወይም ዓለማዊ መንግሥትን የምትደግፍበት ጊዜ ላይ ነን። ነገሩ ለምን መሰልጠን ሆኖ እንደሚቆጠር ባላውቅም፤ እርግጥ መንግሥትና ሃይማኖት የየራሳቸው ኃላፊነት ኖሯቸው መንቀሳቀሳቸው መልካም ነው። ቢሆንም እንደ አገሩ ሕዝብ ማንነት፣ ባህልና አኗኗር መሆን ደግሞ የተሻለው ነው፤ ለኢትዮጵያም አምላኳን እንደ መጥራት።
«ሀ» ከ «ለ» ጋር እኩል ከሆነ እና «ለ» ደግሞ ከ «መ» ጋር እኩል ከሆነ፤ «ሀ» ከ «መ» ጋር እኩል ናቸው፤ በሚለው መርህ ከሆነ ዓለማዊ መንግሥትም በመንፈሣዊው ዓለም መሠረታዊ ሕግ ነው የሚተዳደረው።
ይህም እምነት ይባላል። ሕግ ሲወጣ ሁሉም ሕጉን ያከብራል ብሎ በማመን ብሎም ላላከበረውም ቅጣቱን በማስቀመጥ እንጂ፤ ይህ ባይሆን የዓለማዊ መንግሥት ሕግ ስለተጻፈና ስለተለፈፈ ብቻ እስከዛሬ ያኖረን ነበር? እንደውም ዓለማዊ መንግሥት «ርዕዮተ ዓለም» የሚባል ሃይማኖትና «ህገ መንግሥት» የሚባል መጽሐፍ ያለው መሆኑን ልብ ይሏል!
አንድ ፖለቲከኛ ካለፉት ሳምንታት በአንዱ ስለዚሁ ጉዳይ ሲያብራሩ ነበር። በዚህም «የኢትዮጵያ አምላክ» እያሉ ከላይ ከፈጣሪ መጠበቅ ሳይሆን በዓለማዊ መንግሥት አሠራር መሄድ እንደሚያስፈልግ አጥብቀው ገለጹ። ነገሩን ያነሳሁት ተሳስተዋል ለማለት አይደለም፤ በምንስ አቅሜ እላለሁ። ተሳስተዋል ከማለት ሃሳባቸውን ከሞላ ጎደል አለመቀበል ይቀላል።
በእርግጥ ደስ የሚለው የኢትዮጵያ አምላክ ስለጠራነው ብቻ አይደለም የሰማንም ሆነ የሚሰማን። በፈጣሪ ስም እየተማማልን ለመገዳደል የምንቀጣጠር ብዙ ስለሆንን፤ እውነት ሰምቶን ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። ግን ሲሠራ እናየዋለን፤ ቢያንስ በዝናብ የእኛንም ቁጣና ዱላ፣ የደኑንም እሳት ሲያበርድ አይተናል። በተዓምር ከጉድ ተፍቶን ሰምተናል። በሌሊቱ ምን እንዳለፈ ሳናውቅ ከጎርፍ አምልጠን ተገኝተናል።
የኢትዮጵያ አምላክ ከሌሎች አገራት አምላኮች ይለያል ወይ? የተለየ አይደለም። ብርሃንንም ጨለማንም እንደፈጠረ ሁሉ ማለት ነው። ነገር ግን እኛ እንለያለን ብዬ አምናለሁ፤ ኢትዮጵያውያን ነን። በሩን ደጋግሞ ለማንኳኳት የማንሰለች ስለሆንን፤ የቤቱ ባለቤት ከበሩ ዞር እንድንልለት ሲል በሩን ከፍቶ መልስ ሊሰጠን ይችላል።
ኢትዮጵያውያን ይህን አምነን ጠዋትና ማታ በየእምነታችን አገራችንን ጠብቅልን እያልን ፈጣሪን እንጠይቃለን። ሰላምን በምንለምንላት በአገራችን ስም እንማማላለን፤ በእርሷ እንለማመናለንም። «የኢትዮጵያ አምላክ ይፍረድ!» ስንልም ታድያ በእምነት ነው። አሃ! በቅርብ ጊዜያት ታሪክ ከመጫረስ ያዳነንን ዝናብ ያዘነበልን ማን ሆነና?
ይህ በእርግጥ የሚያስታብይ እንዲሆን አይደለም። የተለየን ነን ስንል በሰውነታችን አይደለም። በተቀበልነው እምነትና አኗኗር ነው። ሁሉም አገራትና ሕዝቦቻቸው ስለራሳቸው እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። እንደውም ከእኛ በላይ አገር ወዳድ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ቸር ደግና ሩህሩህ ሕዝብ ያለባቸው አገራትም እንዳሉ ስንረዳ፤ ይህ ጠባቆት ምክንያቱ የእኛ ግብር እንዳልሆነ ሊገባን ይችላል።
እንደ ኢትዮጵያውያንና እምነት እንዳላቸው ሰዎች፤ ዓለምን የፈጠረ አምላክ አንድ ነው። ልክ በክፍል ውስጥ ሊያስተምር እንደቆመ መምህር፤ ግን ብዙ ተማሪዎች እንዳሉት። እርግጥ ነው መምህሩ ተማሪዎቹን አልፈጠራቸውም፤ በእውቀት ግን ይወልዳቸዋል። በክፍሉ ሰነፍ ተማሪ አለ፣ ጎበዝ ተማሪ አለ፣ ረባሽ አለ፣ ታዛዥ አለ፣ ትዕቢተኛ አለ፣ ትሁት አለ፣ አርፋጅ አለ፤ መምህሩ ተማሪዎቹን እንዳየባቸው ነገር ይጠብቃቸዋል።
ረባሹ ሰነፍ ነው ማለት አይደለም፤ ጎበዙም ትሁት ላይሆን ይችላል። ወይም በጥቅሉ የተማሪዎቹ ጸባይ ወይም ጥረት ብዙ ዋጋ ላያሰጥ ይችላል። በመምህራን ፊት እነዛ ዝርዝሮች ሁሉ ምንም ሊሆኑ ይችላሉ። በቃ! መምህሩ የተሻለ ያውቃልና ለተማሪዎቹ ባሰበላቸው ደረጃ፤ በሚያውቀው እውነት መሰረት ያሰበውን ይተገብራል። ሰነፍ ተማሪ ሰነፍ ስለሆነ፤ ጎበዙም በውጤቱ አይደለም፤ መምህሩ የሚያውቀው ሌላ ነገር ይኖራል።
በአገራችን ስለሃይማኖትና እምነት ማውራት እንደ ሌሎች አገራት የሚያሳቅቅበት ጊዜ ላይ አልደረስንም። እንኳን አሁንና በቀደመ የፖለቲካ ሥርዓት በአደባባይ ሃይማኖትን እያወገዙ በእኩለ ሌሊት በየቤተ እምነቱ የሚሄዱ ሰዎችን ታሪክ እናውቃለን። ኢትዮጵያውያን ነን፤ ከዚህ ወደየትም መሸሽ አንችልም። ያው ምግባራችን ገልጦ ባያሳይም እንኳ፤ አገራችን አሁንም የእምነትና የሃይማኖተኞች አገር መሆኗ አያጠራጥርም። ያውም የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ተጣምረው ቤተሰብ የሚመሠርቱባት አገር።
እንደ እምነታችን የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል። የአርበኞችንና የሰማዕታትን፣ የታጋዮችንና የጓዶችን ትግልና መስዋዕትነት የሚቀናቀን አይደለም። «እርሱ ባይረዳችሁ ኖሮማ እናንተ ጣልያንን አታሸንፉም ነበር» ስንባል በኩራት እንቀበላለን እንጂ አንገት አንደፋም። እምነት ያላቸው ሕዝቦች ቀና ብሎ በጤና ለመሄድም የአገራቸውን አምላክ ያመሰግናሉና፤ ቀድሞም ሲወጡ «በአገሬና በእምነቴ የመጣ…» ብለው ነው። በሁለቱ አይደራደሩም! የኢትዮጵያ አምላክና ኢትዮጵያውያን ይተዋወቃሉ።
እናም «የኢትዮጵያ አምላክ ይፍረድባችሁ!» የተባሉና መልዕክቱ የተገባቸው መጥኔ ለእነርሱ ነው። ቢዘገይም ዝም ሳይል በዝናቡ እሳት ሲያጠፋ ስላየን! ክብሪት የሚጭሩ ስለጣቶቻቸውና ስለእጆቻቸው ቢያስቡ መልካም ነው። እምነት ቀላል መሣሪያ አይደለም። ምንም ያህል ዓለማዊ ብንሆንና ምክንያታዊነትን በሚገባው ቦታ ላይ ረስተንና ዘንግተን «ሎጂክ» ማህበራዊ ኑረታችን እንዲቀናቀን ብናደርግም፤ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያውያን ነን። እምነትም ሃይማኖትም አለን፤ ይህ ደግሞ ፋሽን አይደለም፤ ማንነት ነው። ላለፉት እልፍ ዓመታት አልተቀየረም፤ አሁንም የደበዘዘ ቢመስል እንኳ አይቀየርም።
ወይም በዚህ ሃሳብ አትስማሙ ይሆናል፤ ተሳስቼ ይሆን? አላውቅም። አለመቀበልም ይችላል። ይህን ግን ልበል! ፖለቲካው ውጥንቅጡ የወጣ ነው፤ ዘንድሮና አምና እንኳ ይለያያል። ፓርላማው ገና ብዙ ጽዳት የሚፈልግ ይመስላል፤ ጠርቶ አልጠራም። ኑሮው ሽቅብ መውጣትን ሙያ አድርጎት በዚህ በኩል ያዋክበናል። ገንዘብ ከሃዲ ነው፤ ትናንት ዳቦ ገዝቶ ያበላን የነበረ ፍራንክ ዛሬ ልብስ መጥቀሚያ መርፌ እንኳ አይገዛም።
እኛም «ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት…» እንደሚለው ብሂል ዓይነት ጸባይ አለን፤ የወደድነው ሲመጣ፤ «እንኳን ደህና መጣህ» ከማለት ይልቅ «መች ነው ተመልሰህ የምትሄደው?» ብሎ መጠየቅ ይቀናናል። ዛሬ ያመሰገንናቸው የወታደሮቻችን መሣሪያዎች ከዓመትና ዓመታት በፊት እኛው ላይ ተደግነው ያውቃሉ፤ «የገደለው ባልሽ… የሞተው ወንድምሽ»ን ተርተንማል። እንግዲህ ሳይለወጥ የቆየ ማን ነው? ያልተቀየረውስ? የኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ይመስለኛል። «አቤት» ያለ ጊዜ! እኛን ነው ማየት! ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
ሊድያ ተስፋዬ