በተፈጥሯዊ ግብዓቶች የተነከሩ የሀገር ባህል አልባሳት

በምትሰራቸው አልባሳት ደንበኞቿ ምቾት እንዲሰማቸው ትፈልጋለች። ፋሽን የሚለው እሳቤ ለእሷ ተፈጥሮ እና ምቾት የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ይገባዋል የሚል ትርጉም አለው። ዲዛይነር ሜሪያም ሰብለ።

‹‹ሜሪያም አስቴቲክስ›› የተሰኘ ሃሳቤንና ምልከታዬን ይገልጹልኛል ያለቻቸውን ዲዛይኖቿን በሀገር ባህል ልብሶች ላይ በማሳረፍ ስራዎቿን ለገበያ በማቅረብ ደንበኞችን ማፍራት ችላለች።

‹‹አስቴቲክስ›› የሚለው ቃል ውበት የሚል ትርጓሜ እንዳለው ጠቅሳ፣ ሜሪያም በስራዋ ውበትን ከተፈጥሮ ጋር በማጣመር በተፈጥሮ ላይ ያላትን እይታ በምትሰራቸው የሀገር ባህል ልብሶች ላይ በማሳረፍ ልብስ ብቻም ሳይሆን ታሪክን ጭምር የሚያስተላልፉ ስራዎችን ታዘጋጃለች።

‹‹የስራዎቼ ሁሉ መነሻ ተፈጥሮ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ሊለብሳቸው እና ሊዋብባቸው ይችላል›› ትላለች።

ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ በሜሪያም አስቴቲክስ የሚገኙት አልባሳት ከሀገር ባህል ፈትሎች የሚሰሩ ናቸው። ለየት የሚያደርጋቸውም በተለዩ ተፈጥሯዊ ግብዓቶች ተነክረው ተፈጥሯዊ ቀለም እንዲኖራቸው ተደርገው በመዘጋጀታቸው ነው። አልባሳቱ የልደት ፕሮግራም ያላቸው፣ የእርግዝና ጊዜያቸውን በፎቶ ማስቀረት የሚፈልጉ እናቶች፣ ወጣቶች ለተለያዩ ቤተሰባዊ የመዝናኛ ቀናቸው ላይ የሚመርጧቸው ሲሆኑ፣ ቀለል ያሉና ውበትንም የሚያጎናጽፉ መሆናቸውን ትናገራለች።

ዲዛይነሯ በዚህ ስራ ላይ አራት አመት ያህል ቆይታለች። ወደዚህ ስራ ከመግባቷ በፊት በተማረችው የሆቴል ማኔጅመንት ሙያ ለስድስት አመት ያህል ሰርታለች።

ወደዚህ የፋሽን ዲዛይን ስራ እንድትገባ ያደረጋት አጋጣሚም የኮቪድ ወረርሽኝ መሆኑን ጠቅሳ፣ እንቅስቃሴዎች በተገደቡበት በእዚያ ወቅት ሜሪያም በቤቷ ውስጥ የምታሳልፈውን ነጻ ጊዜ ለመጠቀም ስታስብ የራሷን ስራ መጀመር ያለባት መሆኑን አመነች። ፍላጎቷ ምን ላይ እንደሆነ በመመርመርም ጥናቶች ማድረግ ጀመረች።

ለተፈጥሮ ቅርበት ያላት ሜሪያም ይህን የፋሽን ኢንዱስትሪ ጥሩ ሆኖ አገኘችው። ምንም እንኳን ዲዛይነር የመሆን ፍላጎት አልነበራትም፤ ይሁንና ከፋሽን ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞች ይስቧት እንደነበር ታስታውሳለች።

በዚህም ከመደበኛ ስራዋ ጎንለጎን ስራዋን ማስኬድ እና ቢዝነሱ በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማድረግ መስራቷን ቀጠለች። ‹‹መደበኛ የሙሉ ቀን ስራ እያለኝ የራሴን ቢዝነስ ማስኬድ በጣም ከብዶኝ ነበር›› የምትለው ሜሪያም፤ የቀድሞ ስራዋን ትታ ሙሉ ለሙሉ በራሷ ስራ ላይ ለማተኮር ለመወሰን ተቸግራም ነበር። ‹‹በፊት በምሰራበት ቦታ የሚከፈለኝ ደመወዝ ፣ የምሰራበት ክፍል ጥሩ ስለነበር ስራዬን ሙለሙሉ ለማቆም እርግጠኛ አልነበርኩም›› ስትል ገልጻ፤ በሂደት ስራዋን ማስተዋወቋን ቀጥላ በሰዎች ዘንድ ተቀባይት ማግኘቱን ተመለከተች። ይህ ስራዋ ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆን ሙሉ ትኩረቷን በእሱ ላይ ለማድረግ ወስናም ወደ ቢዝነሷ ገባች።

ለተፈጥሮ ባላት ቅርበት ቀሚሶችን በቀለም፣ ጃኬቶችን ደግሞ በጌሾ፣ በእርድ እና በቀይ ሽንኩርት በመንከር ታመርታለች። በራያ፣ ሰቆጣ እንዲሁም በቦረና አካባቢ በቂቤ እና ተፈጥሯዊ በሆኑ ግብዓቶች የሚነከሩ ልብሶች ስለመኖራቸው መረጃው እንዳላት የምትገልጸው ሜሪያም ‹‹የሀበሻ ልብሶቻችን የተለመዱ እና ነጭ ናቸው፤ አሁን ላይ ሰዎች በጣም የሚፈልጓቸው እና በዋጋም እየተወደዱ የመጡት የተነከሩት ናቸው፤ ስለዚህ እንዴት የሀገራችንን አልባሳት በተፈጥሯዊ መልኩ በማቅለም መጠቀም እንችላለን የሚለው ሃሳብ ወደ ንክር የሀበሻ ልብሶች ማዘጋጀት እንድመጣ አደረገኝ›› ስትል ገልጸለች።

በሜሪያም አስቴቲክስ የሚሰሩ የሀበሻ ልብሶች በፋሽን ኢንዱስትሪው ‹‹earth tone›› የተሰኘ የቀለም ስያሜ ያላቸው ማለትም ከመሬት እና ከአፈር ጋር ተቀራራቢ የሆነ የቀለም አይነት ያላቸው ናቸው። ከማንኛውም የቆዳ ቀለም አይነት ጋር አብረው የሚሄዱ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ በተለይም ለሀበሻ የቆዳ ቀለም ተስማሚ መሆናቸውን

ሜሪያም ትገልጻለች።

ሜሪያም ግብዓት በአህጉረ አፍሪካ በሴኔጋል እና ማሊ ሕዝቦች ተሸምነው የተዘጋጁ እና በባህላዊና ተፈጥሯዊ መንገድ ትርጉም ያላቸው ስዕሎች ያረፉባቸውና የጀግንነት መገለጫ የሆኑ አልባሳትንም በግብአትነት እንደምትጠቀም ትገልጻለች። ‹‹ባደረኳቸው ጥናቶች እነዚህ አልባሳት በቀጥታ ተፈጥሮን የሚገልጹ እና ታሪክን የሚያንጸባርቁም ሆነው ስላገኘኋቸው የማሊን ጨርቆች ከሀገራችን ጨርቆች ጋር በማጣመር እሰራለሁ።›› ስትልም ታብራራለች።

የሜሪየም አልባሳት ምርቶች በተፈጥሯዊ ግብዓቶች የተነከሩ መሆናቸውን የሚያውቁ ደንበኞቿ ለአልባሳቱ

ያላቸው አቀባበል ለየት ያለ መሆኑን ትገልጻለች ። ‹‹አልባሳቱ በሽንኩርትና በጌሾ የተነከሩ ናቸው ስንላቸው ብዙዎች ቀድመው ልብሱን ያሸቱታል፤ ምንም ሽታ እንደሌለው ከነገርኳቸው በኋላ ግን መረጃው የሌላቸው ሰዎች በጣም ይገረማሉ፤ ይወዱታል›› ስትል ትገልጻለች።

አንድ በተፈጥሯዊ ግብዓት የተነከረ ልብስ የሚያልፈውን ሒደት አስመልክታ ስታብራራም። ቀለም የመንከሩ ሂደት የሚከናወነው ከመሸመኑ በፊት በክሩ መሆኑን ጠቅሳ፣ ክሩ ከሚፈለገው ግብዓት ጋር ተደባልቆ በውሀ ከተዘፈዘፈ በኋላ ለአራት ቀንና ከዚያ በላይ ይቆያል፤ በሙቅ ውሃ ቀለሙ እንዲዋሀድም ይደረጋል›› ትላለች።

የሚፈለገውን አይነት ቀለም ከያዘ በኋላ ሽታው እንዲወጣና ልብሱ ላይ እንዳይቀር በባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚታጠብም ተናግራ፤ እሷ ይህንን ተቀብላ በደንበኞቿ ፍላጎት እና ዲዛይን መሰረት አልባሳቱን ትሰራላቸዋለች። የሀበሻ ልብሱ የሚኖረው ተፈጥሯዊ ቀለም በመሆኑ ተጠቃሚዎች ቤታቸው ወስደው ሲያጥቡትም ሆነ ጸሀይ ላይ ሲያሰጡት ቀለሙ እንደማይለቅ ሜሪያም ትገልጻለች።

ሜሪያም አዳዲስ ዲዛይኖችን ትፈጥራለች፣ ስራዎቿን ማህበራዊ ገጾችንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም በራሷ በሚገባ ታስተዋውቃለች። የስፌት ስራውን የሚያከናውኑላት ሁለት ሰራተኞችም አሏት።

ሜሪያም አስቴቲክስ የወደፊት እቅዱ ሙለሙሉ ተፈጥሯዊ በሆኑ ግብዓቶች የተነከሩ የሀበሻ ልብሶችን ለየት ባለ መልኩ ማዘጋጀት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ይህንን የሚያከናውኑላት ባለሙያዎች እንዳሏት ገልጻለች።

‹‹ሙለ ለሙሉ ተፈጥሯዊ አልባሳትን ለማዘጋጅት በሽንኩርት ሲሆን፤ የሽንኩርት ቅርፊት፣ እርድ ሲሆንም እርድ፣ ወዘተ መሰብሰብ ያስፈልጋል። አሁን ላይ ያን ሒደት ማከናወን እንደማትችል ጠቅሳ፣ ወደፊት ሙሉ ለሙሉ በተፈጥሯ ግብዓት የተነከሩ ልብሶችን ማዘጋጀት እፈልጋለሁ ብላለች። ታዋቂ የፋሽን ዲዛይነር በመሆን በአፍሪካም ሆነ በሌሎች ሀገራት ስራዎቿን የማስተዋወቅ እቅድም አላት።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You