ዲዛይነር ሜሪያም ሰብለ ትባላለች፡፡ በአሁን ሰዓት ‹‹ ሜሪያም አስቴቲክስ ›› የተሰኘ ሀሳቤንና ምልከታዬን ይገልጹልኛል ያለቻቸውን ዲዛይኖቿን በሀገር ባህል ልብሶች ላይ በማሳረፍ ስራዎቿን ለገበያ ታቀርባለች።። ሰዎችን መሳብ እና ደንበኞቸ ማፍራትም ችላለች፡፡
በስራው ላይ አምስት ዓመት የቆየችው ሜሪያም ወደዚህ ስራ ከመግባቷ አስቀድሞ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በሆቴል ማኔጅመንት ነበር፡፡ በስራው ውስጥም ለስድስት ዓመት ያክል ቆይታለች፤ ታዲያ ወደዚህ የፋሽን ዲዛይን ስራ እንድትገባ ያደረጋት አጋጣሚ የተፈጠረው የኮቪድ ወረርሽኝ የዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ ይፋ ተደርጎ እንቅስቃሴዎች በተገደቡበት ወቅት ሜሪያም የራሷን ስራ ለመስራት ፍላጎቷን በመመርመር የራሷን የተለያዩ ጥናቶች ማድረግ ጀመረች።
ለተፈጥሮ ቅርበት ያላት ሜሪያም ይህን የፋሽን ኢንዱስትሪ ጥሩ ሆኖ አገኘችው፡፡ በዚህም ከመደበኛ ስራዋ ጎን ለጎን የፋሽን ስራው ላይ ትኩረት ማድረግ እና ቢዝነሱን በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማድረግ መስራቷን ቀጠለች፡፡ ‹‹ መደበኛ የሙሉ ቀን ስራ ኖሮኝ ከዛ ደግሞ የራስን ቢዝነስ ማስኬድ በጣም ከባድ ነበር።›› የምትለው ሜሪያም የራሷን ስራ ከመጀመሯ በፊት ተቀጥራ ለስድስት ዓመት የሰራች ሲሆን ከዚህ ጊዜ በኋላ የቀድሞ ስራዋን ትታ ሙሉ ለሙሉ ወደ ራሷ ስራ ለማተኮር ለመወሰን የተቸገረችበት ጊዜም ነበር፡፡
‹‹በፊት በምሰራበት ቦታ የሚከፈለኝ ደሞዝ፣ የምሰራበት ክፍል ጥሩ ስለነበር ስራዬን ሙሉ ለሙሉ ለማቆም እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ ›› ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች፡፡ ሜሪያም የራሷን ስራ ከጀመረች አራት ዓመት ያክል ጊዜ ቆይታለች፡፡ ‹‹ የ2016 ዓ.ም ራሴን የፈተሽኩበት አቅሜን ያየሁበት እና ብዙ ነገር የተማርኩበት ነው እና ማንኛውም ሰው የራሱን ስራ ለመጀመር ሲያስብ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ መሆን አይጠበቅበትም አንድ ትልቅ ነገር ለመጀመር ስናስብ ደግሞ የፍርሀት ስሜት ማስተናገድ የተለመደ በመሆኑ ወደኋላ ሊያስቀረን አይገባም፡፡ ›› ትላለች፡፡
ሜሪያም ከዚህ ቀደም የምትሰራበት የራሷ ሱቅ ከመሀል ከተማ ራቅ ያለ በመሆኑ በ2016 ዓ.ም ውስጥ አንዱ እቅዷ ይህንን ሱቋን ወደ ሌላ አማካኝ ወደሆነ ቦታ መጥቶ መክፈት ነበር፡፡ ይህንንም አሳክታዋለች። በዚህም እቅዷ የነበረውን ደንበኞችን ማብዛት ሽያጮቿን መጨመር እና ስራዋን የምታስተዋውቅበትን የማህበራዊ ገጽ ላይ ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ በዚህ ዓመት ያሳካቻቸው ናቸው፡፡ ሜሪያም ከስራዋ ባሻገር የተለያዩ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ መጎብኘት አብዝታ የምትወደው በመሆኑ በአሁን ሰዓት በግል ስራዋ ላይ በማተኮሯ ብዙም ጉብኝት ማድረግ አልቻለችም፡፡
ሜሪያም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማኅበረሰብ የተሻለ ቦታ ለመድረስ እና የተሻሻለ አስተሳሰብ ያለው ለመሆን መማር ምርጫ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡ በአሁን ሰዓት ከመደበኛ የትምህርት ስርዓት ባሻገር ሰዎች ፍላጎታቸው ያደረበትን ዘርፍ በመምረጥ እና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ትምህርቶችን በመውሰድ በራሳቸው ስራ ላይ ተሰማርተው ገንዘብ መስራት ጀምረዋል፡፡ ሜሪያም በዚህ ዙርያ ከብዙ ወጣቶች ጥያቄዎች ይደርሷታል፡፡ ‹‹ ብዙዎች ሳይማሩ ገንዘብ መስራትን እንደትልቅ ነገር በማየት ትምህርትቤት ገብቶ መማር ግዴታ ነው ወይ እያሉ ይጠይቁኛል፡፡ ›› ነገር ግን እንደ ሀገር ለምንሰማቸው አንዳንድ መልካም ያልሆኑ ዜናዎች በሴቶች ላይም ሆነ በሰዎች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ምክንያቱ አለመማር ነው፡፡ መማር ማለት ደግሞ ማገናዘብ በመሆኑ ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡ ‹‹ ሴቶች ራሳቸውን በኢኮኖሚም ሆነ በአመለካከት ልቀው ለመገኘት መማር ትልቁ መሳርያቸው ነው፡፡ ›› ትላለች፡፡
ሜሪያም በ2017 ዓ.ም የራሷን ቢዝነስ ማስፋፋት እና ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ፤ ራሷን በእውቀት ማሳደግ እና የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘት በእቅዷ ውስጥ ያለ ነው፡፡
ሌላኛዋ በስራ ላይ የምትገኘው እንስት አይናለም እሸቱ ትባላለች፡፡ አይናለም ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ብዙውን ግዜ ወንዶች ተሰማርተውበት በሚገኘው በሊስትሮ ስራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች ፡፡ ‹‹ ወደ ስራው ስገባ የወንድ የሴት ስራ ነው ብዬ በፍጹም አላሰብኩም፡፡ ›› የምትለው አይናለም በዚህ ስራ ላይ አንድ ዓመት ያክል ጊዜ በአራት ኪሎ አካባቢ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
አይናለም ትውልዷ በሰላሌ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ በሰው ቤት ውስጥ ተቀጥራ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል ሰው ቤት ስትሰራ ከቆየች በኋላ የራሷን ትዳር መሰረተች፡፡ ስራዋንም ትታ የቤት እመቤት ሆና ለተወሰኑ ዓመታት ከቆየች በኋላ ባለቤቷን ለማገዝ ወስና ወደ ሊስትሮ ስራ ገባች፡፡ እሷ ጋር ጫማቸውን ለማስጠረግ የሚመጡ ሰዎችም እንደሚያደንቋትና እንደሚያበረታቷት ትገልጻለች፡፡
አይናለም የሁለት ልጆች እናት ስትሆን የመጀመርያ ልጇ የአምስት ዓመት፤ ሁለተኛ ልጇ ደግሞ የሶስት ዓመት ሲሆኑ ልጇን ለማሳደግ እና ትምህርት ቤት ለመላክ ይህ የሊስትሮ ስራ ጥሩ ሆኖ አግኝታዋለች ፤ የ2017 ዓ.ም እቅዷም ልጆቼን ማሳደግ ነው ስትል ትገልጻለች፡፡ አይናለም የሊስትሮ ስራዋን ዘወትር የምታከናውነው በአራት ኪሎ አካባቢ ሲሆን መኖርያዋ ግን በእንጦጦ ማርያም ሰፈር ነው፡፡ ታዲያ ጠዋት የልጆቿን ምግብ አዘጋጅታ ከ12 ሰዓት በኋላ በስራዋ ላይ ትገኛለች ፤ ማታም እንዲሁ እንደምታስተናግደው ሰው በማየት ስራዋን እስከ ምሽት 12 ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት በመስራት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ወደቤቷ ታመራለች፡፡ አይናለም በስራ ቀኗ በከተማችን እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት እና ቦታው ላይ ደንብ ከቦታቸው የሚያስነሷቸውን ተቋቁማ ስራዋን ሰርታ እና የምታገኘውን ገንዘብ ቆጥባ የቤት ኪራይ፣ የታክሲ ወጪ እና የልጆቿን ትምህርት ቤት ትሸፍናለች፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ናት ፡፡
አይናለም የራሷን የንግድ ስራ መጀመር የወደፊት እቅዷ እንደሆነ ገልጻ ነገር ግን በራሴ አቅም ሰርቼ መለወጥ ስለምችል የሰዎችን እርዳታ አያሻኝም በማለት ጠንክሮ መስራት የሚያስገኘውን ለውጥ እንደምትተማንበት ትገልጻለች፡፡ በ2017 ዓ.ም በዚሁ ስራዋ በመቀጠል ሌሎች የተሻሉ ስራዎችን የመስራት እና ለልጆቿ የተሻለ ሕይወትን መስጠት የአይናለም እቅዷ ነው፡፡
በጤና ተቋማት ውስጥ ሴቶች ከሚመረጡበት የስራ ሙያ እና እምብዛም ትኩረት የማይሰጠው ነገር ግን ወደጤና ተቋም የሚመጡ ታካሚዎችን በመንከባከብ እና ቅርባቸው በመሆን ብዙ ዋጋ የሚከፈልበት ሙያ ነው የነርሲንግ ሙያ፡፡ ሲስተር ውብታዬ ገዳ ይባላሉ በነርሲንግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን የያዙ ሲሆን ሲኒየር ነርስ ሆነው በማገልገል 10 ዓመትን አገባደው ወደ አስራ አንደኛው እየተጠጉ ነው፡፡ ‹‹ የነርሲንግ ሙያ መሰጠትን እና ከልብ የሆነ ፍላጎትን ይጠይቃል፡፡ እርዳታ ፈልጎ ወደ ሆስፒታል የሚመጣን ሰው ለመርዳት ቅንነት ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡ እንደዛ ካልሆነ በስራው ላይ ለመቆየት በጣም ይከብዳል፡፡ ›› በዚህም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በጤና ተቋማት ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ሲሰማ ቦታው ላይ የሚሰሩት ሰዎች ሙያውን ይወዱታል ወይ የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል ትላለች፡፡ በዚህም ሴቶች የተሻሉ ሲሆን በስራ ቆይታዋ ነፍሰጡር ሆነው፤ ከወለዱ በኋላም በዚሁ ስራ ላይ ሰዎችን በማገልገል ያሳልፋሉ፡፡
ሲስተር ውብታዬ የአንድ ልጅ እናት ስትሆን የምትሰራው በጃንሜዳ ጤናጣቢያ ላይ ለአስር ዓመት ያክል ቆይታለች አሁንም በስራው ላይ ትገኛለች፤ በስራዋም ደስተኛ መሆኗን ትገልጻለች ፡፡ እንደ የጤና ባለሙያ አምሽቶ መስራት፤ በጠዋት መግባት እና አዳሪ ሆነው በተቋሙ ውስጥ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ታዲያ ይህ ስራ ለአንዲት ቤተሰብን ለምትመራ ሴት አይከብድም ወይ ብለን ላቀረብንላት ጥያቄ ‹‹ በቤት ውስጥ ያለ የትዳር አጋርም ሆነ አብሮ የሚኖር ሰው አስቀድሞ መረዳት እና ማገዝ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ድንገተኛ በሆኑ አደጋዎች አልያም እርዳታ በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ ከቤታቸው ተጠርቶ መሄድ ስላለ ሙያውን መረዳት ያስፈልጋል›› ትላለች፡፡ ሲስተር ውብታዬ መኖርያዋ ለምትሰራበት ቦታ ቅርብ በመሆኑ የሚኖራትን የስራ ጫና በእጅጉ እንደሚቀንስላት ትገልጻለች፡፡
ሴቶች አንድ ጊዜ ወደ ትዳር ከገቡ እና የራሳቸውን ሕይወት ከመሰረቱ በኋላ በትምህርት ራሳቸውን ማሳገድ ይልቅ ምናልባት ለቤተሰባቸው ቅድሚያ በመስጠት ትምህርታቸውን ላይቀጥሉ ይችላሉ ወይዘሮ ውብታዬ ለዚህ የራሷን እና የስራ ባልደረቦቿን ጥንካሬ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ እኔ ስራ እንደጀመርኩ ነበር ዲግሪዬን የተማርኩት ነገር ግን በምሰራበት ቦታ የነበሩ ሴቶች ትዳር መስርተው ልጆች ኖሯቸው ነፍሰጡርም ሆነው ጭምር የማታ እና የርቀት እየተማሩ ትምህርታቸው ይማራሉ፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ የሚያመጡት ውጤትም የተሻለ ነበር፡፡ ›› በማለት የሴቶቹን ጥንካሬ ትገልጻለች፡፡ ይህ ደግሞ ሴቶች ከልባቸው ከፈለጉ ማሳካት እንደሚችሉ እና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ትላለች፡፡
ሲስተር ውብታዬ 2016 በስራዋ ጥሩ የሚባል ዓመትን እንዳሳላፈች ገልጻ ቀጣዩን የ2017 ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ለጃንሜዳ ጤና ጣቢያ ሰራተኞች እንዲሁም ለቤተሰቦቿ መልካም አዲስ ዓመትን እንዲሁም እንደ ሀገር መልካም ነገር የምንሰማበት እና የስኬት ዓመት እንዲሆን ተመኝታለች፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም