የሀገር ባሕል ልብሶች ሰዎች አንድን ፕሮግራም ወይም ሁነትን መሠረት አድርገው ይለብሳሉ፡፡ ብዙዎች በዓላትን ጠብቀው እንዲሁም የተለያዩ ፕሮግራሞች ታሳቢ በማድረግ በሀገር ባሕል አልባሳት መዋብና ማጌጥን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ የሀገር ባሕል አልባሳቱ በአንድ ወቅት ተለብሰው ፋሽን የሚያልፍባቸው እና ይሄኛው ለዚህ በዓል ያኛው ለዚህ ዝግጅት ተብለው የሚገደቡም አይደሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሀገር ባሕል ልብሶች እጅግ በተራቀቀ መልኩ የተለያዩ ፈጠራዎችን ታክለውበት የሀገር ልብሶችን ማዘጋጀት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ዲዛይነር ቤዛ ዮሐንስ የሀገር ባሕል አልባሳትን ለየት ባለ መልኩ ይዛ ቀርባለች፡፡ የብራንዷ ስያሜም ቤዛ ሲሆን ቀለል ያሉ ዘመናዊነትን የተላበሱና በየቀኑ መለበስ የሚችሉ የሀገር ባሕል አልባሳትን ማዘጋጀት የቤዛ ብራንድ መለያ ነው የምትለው ቤዛ፤ ዲዛይነር መሆን እና ወደዚህ ሙያ መግባት ከልጅነቷ ጀምሮ የምትመኘው ህልሟ እንደነበር ገልጻለች፡፡ ቤዛ በትምህርት ቤት ቆይታዋ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነርሲንግ ሙያ ትምህርትን ካጠናች በኋላ ለአምስት ዓመት ያህል በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግላለች። ‹‹ተመርቄ ሥራ እንደጀመርኩ የዲዛይኒንግ ትምህርት ማሰልጠኛ ገብቼ የአጭር ጊዜ ትምህርትን ወሰድኩ›› የምትለው ቤዛ የሚያስፈልጋትን ስልጠና እንዳጠናቀቀች ማሽኖችን በማሟላት በቤቷ ውስጥ ለራሷና ለሌሎች ሰዎች ለሰርግ እና ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚሆኑ ልብሶችን በመሥራት ልምድና ችሎታዋን አዳብራለች፡፡ የልጅነት ፍላጎቷ የሆነውንና እጅጉን የምትወደውን ሙያ ከሥራዋ ጎን ለጎን አሳድጋለች፡፡
ቤዛ ብራንድ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜ የቀረው መሆኑን የምታነሳው ቤዛ ለደንበኞቿ የምታቀርባቸው ልብሶች ከተለመደው የሀበሻ ልብስ ቀለል ባለ እና በየእለቱ መለበስ የሚችል መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡ በዲዛይኗ ውስጥ ደግሞ የሀገር ባሕልን የሚያንጸባርቁ ዲዛይኖች እና ቆየት ያሉ ጥልፎች ይንጸባረቃሉ፡፡ በራሷ ፈጠራ መነን፣ ጋቢ እና ሌሎች በእጅ የሚሰሩ የሽመና ውጤቶችን ትጠቀማለች። እነዚህ አልባሳት ታዲያ ከ25 ዓመት እድሜ ጀምሮ ያሉ እንስቶች እንዲለብሱት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የሀገር ባሕል አልባሳቱ ለወንዶች እንዲሁ ለሴቶች በተለያዩ ዲዛይኖች ይዘጋጃል፡፡ ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ የብዙዎች ምርጫ የሆነውን ሰዎች ንግዳቸውን በስፋት የሚያስተዋውቁባቸውን የተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገጾች ትጠቅማለች፤ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚዘጋጁ ሁነቶች፣ የፋሽን መድረኮች ላይ በመሳተፍ ሥራዎቿን ታስተዋ ውቃለች፡፡
አሁን ላይ ቀናት በቀሩትና ልንቀበለው ከደጅ የቆምንለት የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ደግሞ ከብርሃን፣ ከፍካት እና የአዲስ ዓመት ብስራት ከሆነችው የአደይ አበባ ጋር አብሮ የሚነሳ ነው፡፡ በፋሽን ኢንዱስትሪው የሀገር ባሕል ልብስን ለገበያ የሚያቀርቡ ዲዛይነሮች ደግሞ የአደይ አበባን ምሳሌ በማድረግ አዲስ ዓመትን የሚገልጹ የባሕል ልብሶችን ከበዓሉ ቀደም ብለው ያስተዋውቃሉ፡፡
ቤዛ ይህንን የበዓል ወቅት ምክንያት በማድረግ ‹‹አደይ ኮሌክሽን›› በሚል ለአዲስ ዓመት ያዘጋጀቻቸውን የሀገር ባሕል ልብሶች ማስተዋወቋን ጀምራለች፡፡ ‹‹አደይ አበባን መሠረት አድርገው የሚሰሩ ልብሶችን ለመሥራት ቢጫ ቀለምን እንጠቀማለን እሱም ደግሞ የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ተከትሎ የምትወጣውን አደይ አበባ የሚገልጽልን ሲሆን ፍክት ያለ በመሆኑ ብዙዎች ይመርጡታል›› የምትለው ቤዛ፤ እነዚህ በአደይ አበባ ኮሌክሽን ስር ያሉ ልብሶችም ለወጣቶችም ሆኑ ለእናቶች የሚሆኑ ናቸው። ቀለል ያሉ በመሆናቸውም ተወዳጅ ተወዳጅና ተመራጭ ናቸው፡፡ በቤዛ ብራንድ ከዚህ ውጭ ባሉ ወቅቶችም የተለያዩ ዲዛይኖችን እና የተለያየ ቀለም ያላቸው የሽመና ውጤቶችን በመጠቀም በብዙ የቀለም አማራጮች ይገኛሉ፡፡
‹‹የሀገር ባሕል ልብሶቻችን አሁን ላይ ያላቸው ተቀባይነት በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከነበረው ሰዎች የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ያላቸው ልምድ እየጨመረ መጥቷል በተለይ በዚህ ዘርፍ ሴቶች ይበልጥ የሀገራቸውን ባሕል በጣም ይወዳሉ፣ ይጠቀማሉ በሌሎች የሀገር ውስጥ ምርቶች ላይም ፍላጎት ያሳያሉ›› በማለት የሀገር ባሕል ልብሶች በሰዎች ዘንድ ያለውን አቀባበል ያላትን ምልከታ የምታነሳው ቤዛ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደ ችግር የሚያነሷቸውን ሃሳቦችም እንዲሁ ጠቅሳለች፡፡
በሀገራችን የሀገር ባሕል ልብስ ሙያ እና ሥራ ዘርፍ ውስጥ የግብዓት እጥረቶች፣ ከልምድ ከሚሰራው ባሻገር ልምድ የወሰዱ የሸማኔዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ ገልጻ በተጨማሪም አብዛኞቹ ዲዛይነሮች እና በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚፈጥሯቸውን ዲዛይኖች በሌሎች ሸማኔዎች እና የጥልፍ ባለሙያዎች የሚያሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ባለሙያዎች በራሳቸው ስር አድርገው እና ሰፊ የሥራ ቦታን ገንብተው ለመሥራት የቦታ ውስንነት ሌላኛው እንደሆነ ቤዛ ትጠቅሳለች፡፡ በዚህም ምክንያት በቁጥር ብዛት ያላቸውን ምርቶች ለማምረት አንዱ ተግዳሮት መሆኑን አክላለች፡፡
ቤዛ ብራንድ የተለያዩ ዲዛይኖችን ካወጣች በኋላ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ የምትፈልገውን የሽመና ጥራት እና ዲዛይን ለማውጣት ከአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ እና ባህር ዳር በመላክ የምታሰራ ሲሆን ቤዛ ወደፊት ሸማኔዎች እና ባለሙያዎች በማሰልጠን ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በአንድ ቦታ መሥራት የሚያስችላትን የሥራ ቦታ የመገንባት፣ ማሰልጠኛዎችን የመክፈት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመፍጠር እውቅና ያለው ብራንድ መሆን ትልቁ ዕቅዷ ነው፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም