ሆሳዕና:- በምክክር ሒደቱ ለሰላምና ለሀገር ግንባታ መሰረት የሆኑ ሀገር በቀል እውቀቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛል ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለስድስት ቀናት የተካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ መጠናቀቅ አስመልክቶ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ለሰላምና ሀገር ግንባታ መሠረት የሆኑ ሀገር በቀል እውቀቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
ኮሚሽኑ አጀንዳ ሲያሰባስብ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጸሎትና ምክር በማስቀደም ነው ያሉት ዶክተር ዮናስ፤ በምክክሩ ሒደቶችም ሀገር በቀል እውቀቶችንና ጥናቶችን በማካተት እየሠራ ነው ብለዋል።
በሀገር በቀል እውቀቶች በሚመሩ ውይይቶች ላይ ቀድሞ ጥላቻን የሚያስተጋቡ አካላትን ማለዘብ ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል።
ሕዝቡ ለሰላም ከግጭት ይልቅ የሚያዋጣን ምክክር ነው የሚለውን ግንዛቤ እየተረዳ መሆኑን አመላክተው፤ ስለሰላምና ሀገር ግንባታ በይበልጥ ለመሥራት ሀገር በቀል እውቀቶች በስፋት መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል።
እንደ ሀገር በተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ስለምክክር አስፈላጊነት፣ አካታችነት፣ አቃፊነት አወንታዊ አመለካከት እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመው፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ሕዝብን ወክለው የተገኙ ተሳታፊዎች በባለቤትነት ስሜት መሳተፋቸው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ እስካሁን በከተማ አስተዳደርና በክልል ደረጃ በተደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር መድረኮች ጉዳዩ ይመለከተኛል በማለት በእኔነት ስሜትና ባለቤትነት የጋራ ውይይቶች ተካሂደዋል። ይህም ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ተስፋ እንዳለው አመላካች ነው።
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሀ ግብር የምክክሩ አስፈላጊነት የታየበትና ሰላማዊ እንደነበር ተናግረዋል።
ምክክር አላማው ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት አውድ መፍጠር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በክልሉ በተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ስኬታማ እንዲሆን ጥረት ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም