የኢትዮጵያ መለያ – ጳጉሜን

ኢትዮጵያ በዓለም ብቸኛዋ የ13 ወራት ፀጋ ባለቤት ናት፡፡ የዘመን አቆጣጠሯን ከዓለም ልዩ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ በነሐሴና በመስከረም ወራት መካከል የምትገኘው የ13ኛዋ ወር ጳጉሜን ባለቤት መሆኗ ነው።

በጳጉሜን የመስከረም መምጣት ምልክት የሆኑ አደይ አበባዎች በብዛት ይታያሉ፤ የክረምቱ ብርታትም እየቀነሰ ይመጣል።

ጳጉሜን የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው፡፡ በግእዝ “ወሰከ ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ ጳጉሜን ወርም ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ ናት።

የጳጉሜን ወር እንደየዘመን አቆጣጠሩ የተለያዩ ቀናትን ትይዛለች። በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዘመነ ዮሐንስ ስድስት የጳጉሜን ቀናት ፤በዘመነ ሉቃስ፣ ዘመነ ማቴዎስና በዘመነ ማርቆስ ደግሞ ወሯ አምስት ቀናት አሏት።

ምዕራባዊያኑ ኢትዮጵያ በጳጉሜን ወር ለብቻ ያስቀመጠቻቸውን ቀናት በየወራቶቻቸው ውስጥ ተጨማሪ ቀን አድርገው ይጠቀሙባቸዋል። ኢትዮጵያውያን ግን በልዩ ሁኔታ 13ተኛ ወር አድርገናታል፡፡ ታዲያ ይች የጳጉሜን ወር እንዴት መጣች ምንስ ትርጉም ትሰጣለች? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የስነፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ጌትነት ፈለቀ (ዶ/ር) ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

የጳጉሜን ወር በየዓመቱ የምናስባት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የተሰጠች ስጦታ ናት የሚሉት የስነፈለክ ተመራማሪው፤ ወሯ በዘመን ቀመር ውስጥ ስትካተት ታስቦበትና ተለክታ የተገኘች መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ዶክተር ጌትነት ገለጻ፤ በቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ትንተና መሰረት በአንድ ዕለት ውስጥ 24 ሰአት ከ21 ደቂቃ ከዜሮ ነጥብ አራት ሰከንድ አለ፡፡

በቀመሩ መሰረትም በአንድ ቀን ውስጥ 21 ደቂቃ ከዜሮ ነጥብ አራት ሰከንድ ትርፍ ይመጣል፡፡ የተገኘው ትርፍ ሲደመር የጳጉሜን አምስት ቀናትን ያመጣሉ። ይህ ቀመር በ600 ዓመት ውስጥ ደግሞ አንድ ቀን ጳጉሜን ሰባት ቀን ታደርጋታለች ይላሉ።

በግሪጎሪያን ዘመን አቆጣጠር በአንድ ወር ውስጥ ከ28 እስከ 31 ቀናት ሲኖራቸው፤ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ደግሞ 30 ቀናትን በማድረግና ቀሪ ቀናትን በመቀመር የጳጉሜን ወርን አስገኝቷል ሲሉ ያስረዳሉ።

ቀናቶቹም ወቅቶችን ለመረዳትና ለማወቅ እንዲሁም ዓመት ከመጀመሩ በፊት በዓመቱ ያሉ በዓላትን ለመቀመር እንደሚረዳ ጠቅሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠርና የጳጉሜን ቀናቶች ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም ለየት የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ዶክተር ጌትነት እንደሚገልጹት፤ ከታሪካዊና ቀደምት ሀገራት ውስጥ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት መሆኗ፤ ሀገሪቱ በሳይንስ በቀደምትነት ረዥም ርቀት ሂዳ እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ጳጉሜን የአዲስ ዓመት መጀመሪያ፣ መንደርደሪያና መሻገሪያ፣ተስፋ የሚሰነቅባትና የምናቅድባት፤ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የተበረከተች ስጦታ ነች ሲሉም ዶክተር ጌትነት ይገልጿታል፡፡

አሁን ላይ በዘመናዊ ሳይንስ ብዙ በመጓዝ ሳተላይት የማምጠቅ ደረጃ ላይ ብንደርስም፤ ጥንት የነበረው ዕውቀት መሄድ በሚገባው ፍጥነት እየሄደ አይደለም ያሉት ዶክተር ጌትነት፤ እንደሀገር ለመቀጠል ያሉን እሴቶቻችን፣ ባህሎቻችንና ማንነታችንን ማጠናከር ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ዘመን አቅጣጠርን ጨምሮ ብዙ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በማስገባት ትውልዱ በአግባቡ እንዲረዳቸው ማድረግ ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያን ቀናቶችና ስያሜያቸውን ከነትርጓሜአቸው ጠንቅቆ ማወቅ፣ ታሪክን፣ ባህልና ወግን ጠብቆ ማቆየት፣ የአባቶችን ዕውቀት ማሳደግና ማንነታችንን ማስቀጠል ብሎም ለዓለም ማሳወቅ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲሉ ዶክተር ጌትነት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You