“ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን የጋራ ትርክቶች በርካታ ናቸው” – ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያንን ከሚያለያዩ ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ የጋራ ትርክቶች በርካታ ናቸው ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተናገሩ።

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ለኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን የጋራ ትርክቶች በርካታ በመሆናቸው ለትብብር ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ ለኢትዮጰያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቅርሶች እንዲሁም የቀደሙ ታሪኮች የጋራ መገለጫ ብቻ አይደሉም ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በየትኛውም አካባቢ ያሉ ባህሎች፣ ወግና ልማዶች እንዲሁም የተለያዩ እሴቶች አብዛኛዎቹ የተቀራረቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

እንደ ልጅ ዳንኤል ጆቴ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያን ከሚያስተሳስሯቸው በርካታ የተፈጥሮ ጉዳዮች በተጨማሪ የቀደሙ አባቶች የወጠኑት አንድነት ለዛሬም መሠረት የሚጥል ነው።

ያለፈው አንድነት በራሱ በጊዜውም ሆነ ለአሁን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ቢሆንም አዲሱ ትውልድ በትክክል ስላልደረሰው የተዛባ አመለካከት ሊስፋፋ እንዲሁም በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳይኮን አድርጎታል ብለዋል።

ከመንግሥታት መቀያየር ጋር ተያይዞ በህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የደረሰው ጉዳት አለ ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ በተለይ አንድ ብቻ አመለካከት፣ ባህል፣ እምነት እንዲሁም ቋንቋ መጽናት አለበት በሚሉ ኃይሎች በመኖራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ሊሻክሩ እንደቻሉ አብራርተዋል።

ልጅ ዳንኤል አክለውም፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በርካታ የድል ታሪክ መጻፋቸውን አንስተዋል። በየወቅት የስልጣን ሽሚያና የውስጥ ለውስጥ ግጭቶች ቢኖሩም የቋንቋ አለመግባባት ሳይገዳቸው የውስጥ ልዩነት ወደ ጎን በመተው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተዋድቀው ድል ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ትውልዱ የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር የሚችለው ሀገሩን በሚገባ ሲያውቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ አባቶች ሠርተውት ያለፉትን ሀገር አኩሪ ጀብድ በአግባቡ ማወቅና በእራሱ መንገድ መተግበር ይኖርበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ ጀግኖች አርበኞች ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል፤ ይህን ዕውነታ ትውልዱ በተገቢው መንገድ መገንዘብ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የሀገሩን ዕውነታ በአግባቡ የተረዳ ትውልድ አንዳንድ ኃይሎች የሚያሴሩትን የመከፋፈል ተግባር በማክሸፍ አንድነቱን ማስቀጠል ይችላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢትዮጵያ የሚታዩ አላስፈላጊ ጉዳዮችን ፈር ለማስያዝ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የአርበኞችን የድል ታሪክና የአባቶችን ተጋድሎ እንዲሁም ለሀገር ዕድገትና አንድነት የሠሩትን በርካታ ሥራዎች የአሁኑ ትውልድ በሥራ፣ በትምህርት፣ የሀገርን አንድነት እና ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች መድገም እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You