አዲስ አበባ፦ በ2016 በጀት ዓመት ከ47 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች እንዲወገዱ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ተሬሳ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ ክትትል እና ቁጥጥር ከተደረገባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ 109 ተቋማት ጉድለት የተገኘባቸው ሲሆን 87 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 21 ተቋማት ጊዜያዊ እሸጋ እና የአንድ ተቋም ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ክትትል እና ቁጥጥር ከተደረገባቸው የመድኃኒት ተቋማት ውስጥ 16 ተቋማት ላይ ችግር የተገኘባቸው ሲሆን 77 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 38 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ እና አንድ ተቋም ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፤ 90 ሺ 584 ኪሎ ግራም የሚመዝንና ብር ከ47 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ተወግዷል ብለዋል።
ክትትል እና ቁጥጥር ከተደረገባቸው የምግብ እና ጤና ነክ ተቋማት ውስጥ 941 ተቋማት ላይ ችግር እንደተገኘባቸው ገልጸው፤ 855 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 83 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ እና የሶስት ተቋማት ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
አጠቃላይ በዓመቱ የተወገዱ፣ ጊዜ ያለፈባቸውና የተበላሹ ምግቦች 132 ሺህ 250 ኪሎ ግራም በቁጥጥርና የኦፕሬሽን ሥራ በመሥራት 13 ሚሊዮን 345 ሺህ 270 ብር ዋጋ ያላቸውና ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል ነው ያሉት አቶ አሰፋ ተሬሳ።
ብር 6 ሚሊዮን የሚገመት 109 ማዳበሪያ (6500 ኪሎ ግራም) የሚሆን ቅቤ የናሙና ምርመራ በማድረግ በውጤቱም መሠረት ከባዕድ ጋር የተቀላቀለ መሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነና ለጤና አስጊ በመሆኑ እንዲወገድ ተደርጓል ያሉት አቶ አሰፋ፤ 59 ሺህ 936 ኪሎ ግራም የሚመዝን የጤና ነክ ምርቶች (የፅዳትና የንፅህና መጠበቂያ) ግምታዊ ዋጋቸው ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ምርቶች የመጠቀሚያቸው ጊዜ በማለፉ እንዲወገድ መደረጉን ተናግረዋል።
103 ሺህ 500 ብር ዋጋ ያለው 345 ኪ.ግ የበሰበሰና ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ሲፈጭ የተገኘ በርበሬ እንዲወገድ ተደርጎ ተቋሙም የእገዳ እርምጃ እንደተወሰደበት ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም