የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር (IAAF) የዓመቱን በተመልካች የተነሳ ምርጥ ፎቶ ይፋ አደረገ።
በየዓመቱ በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮች በዓለማችን የፎቶ ጋዜጠኞች ተነስተው ለውድድር ከሚቀርቡ ፎቶዎች በተጓዳኝ የሚካሄደው በተመልካች የተነሱ ምርጥ ፎቶዎች የዘንድሮ ውድድር እንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል።
በዚህ ውድድር ከመላ ዓለም በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች በመመልከት ስተቱን በፎቶግራፍ ያስቀሩ ተመልካቾች በማህበራዊ ድረ- ገፅ ፎቷቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ አራት የዓመቱ ምርጥ የፎቶ ጋዜጠኞችም አሸናፊውን መርጠዋል። በዚህም መሰረት አንድሪው ስሚዝ ያነሳው የሞህ ፋራህ ፎቶ ግራፍ አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል።
አሸናፊ ሆኖ መመረጡን ተከትሎም ስሚዝ፤ «ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ የምናገርበት ቃላት ማግኘት አልቻልኩም፤ ይህን ፎቶ ለማግኘትም ሃምሳ ያህል ሙከራዎች አድርጌአለሁ» ብሏል።
የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኑ ሞ ፋራህ ጀግና አትሌትና ሁሌም ቢሆን የሚደነቅበት አትሌት መሆኑን የተናገረው ስሚዝ፤ በእርሱ ፎቶ አሸናፊ መሆኑ ደግሞ አጋጣሚውን ልዩ እንደሚደርገው ተናግሯል።
የዓመቱን ድንቅ የተመልካች ፎቶ ግራህ ይፋ ያደረጉት የመራጭ ኮሚቴው አባላትም፤ ስሚዝ አስደናቂ በሆነ መልኩ የሞህ ፋራህን እንቅስቅሴ በፎቶ ግራፍ ማስቅረቱንና የተነሳበት አቅጣጫና ሰዓት አስገራሚ እንደነበር መስክረዋል።
አዳም ስሚዝ የዘንድሮው ምርጥ የተመልካች ፎቶ ግራፍ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ሁለት የዳይመንድ ውድድሮች ላይ እንዲታደም ነፃ የትራንስፖርትና የመግቢያ ዕድል አግኝቷል።
እ.ኤ.ኣ በ2017/18 የውድድር ዓመት በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮች በዓለማችን የፎቶ ጋዜጠኞች ተነስተው ለውድድር ከቀረቡት 70 ፎቶ ግራፎች መካከል የኢትዮጵያዊው አትሌት የሰሎሞን ባረጋ የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ግራፍ አሸናፊ መሆኑ አይዘነጋም። ይህ ፎቶ የተነሳውን በስፔናዊው ጋዜጠኛ ፍሊክስ ሳንቼዝ በ2018 በስፔን በተደረገው የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ነው፡፡
ዘገባው የዓለም ዓቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው።