የሀውቲ ታጣቂዎች በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት አደረሱ

የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃታቸውን የአሜሪካ ጦር ገለጸ። የአሜሪካ ጦር በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ መርከቦችን ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በቀይ ባሕር ላይ አጥቅተዋል ብሏል።

ጦሩ እንደገለጸው ከሆነ ጥቃት የደረሰባቸው መርከቦች የሳዑዲ ሰንደቅ ዓላማ ስታውለበልብ የነበረችው አምጃድ እና የፓናማ ሰንደቅ ዓላማ ስታውለበለብ የነበረችው ብሉ ላጉን ናቸው። ሀውቲዎች ሰኞ ምሽት ብሉ ላጉንን በበርካታ ድሮኖች እና ሚሳይሎች ማጥቃታቸውን ያመኑ ሲሆን ስለሳዑዲ መርከብ ጉዳይ ግን ምንም ያሉት ነገር የለም።

የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ ሀውቲዎች ሁለቱን መርከቦች በሁለት ሚሳይሎች እና ድሮን ዒላማ ማድረጋቸውን እና መምታታቸውን ገልጿል። ሁለቱም መርከቦች ነዳጅ ጭነው ነበር ያለው የአሜሪካ ጦር መግለጫ ጥቃቱን “ሀውቲዎች የፈጸሙት ኃላፊነት የጎደለው የሽብር ድርጊት” ሲል ገልጾታል። ሮይተርስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው መርከቦቹ በሚመቱበት ወቅት ተቀራርበው ሲጓዙ ነበር። የደረሰው ጥቃት ቀላል በመሆኑ መርከቦቹ ጉዟቸውን መቀጠላቸውም ተገልጿል።

ሁለት ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የጫነችው የሳዑዲዋ አምጃድ መርከብ ባለቤት የሆነው ሳዑዲ ናሽናል ሺፒንግ ግሩፕ ባሕሪ ስለጉዳዩ አስተያየት አለመስጠቱን ዘገባው ጠቅሷል። ብሉ ላጉን የሚያስተዳድረው የግሪኩ አስተዳዳሪ ሲ ትሬድ ማሪን ኤስኤ በተመሳሳይ ስለጉዳዩ መልስ አልሰጠም። የሱዝማዝ ታንከሯ የመጨረሻ የመጫን አቅሟ አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንደሚሆን ተገልጿል።

የሳዑዲዋ መርከብ በቀጥታ ዒላማ ተደርጋለች ላይሆን እንደሚችል ዘገባው ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የዓለም ትልቋ ነዳጅ አምራች ሳዑዲ ዓረቢያ ሀውቲዎች መርከቦችን ዒላማ ለማድረግ በግዛቷ ላይ ሲተኩሱ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተመለከተቻቸው ነው። ሳዑዲ ዓረቢያ ምስቅልቅል ካስከተለው የየመን ጦርነት ራሷን ለመነጠል እየሞከረችም ነው።

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ከባለፈው ኅዳር ወር ጀምረው ጥቃት እያደረሱ ያሉት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነው ማለታቸው ይታወሳል። ሀውቲዎች እስካሁን በፈጸሟቸው ጥቃቶች የሰጠሙ መርከቦችም አሉ። ሀውቲዎች ይህን ጥቃት የማያቆሙት በጋዛ ተኩስ ሲቆም ነው ብለዋል።

አሜሪካ እና አጋሮቿ ሀውቲዎች እያደረሱት ያለውን ጥቃት ለማስቆም የመን ውስጥ ዘልቀው በመግባት የሀውቲ ይዞታዎች ቢደበድቡም፣ ጥቃቱን ማስቆም አልቻሉም ሲል አል ዐይን ዘግቧል።

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You