ሠላምና ትብብርን የሚያጎለብቱት በዓላት

ሃይማኖታዊ ሥርዓትና በሕዝባዊ ትዕይንቶች ደምቀው የሚከበሩ በዓላት ሠላምን የሚሰብኩ፤ ጥላቻን የሚጠየፉ፤ መነቃቀፍ፤ መጠላለፍ፣ መገዳደልን ለሰው ልጅ ይቅርና ለዱር ፍጥረታት የማይመኙ፤ የአንድነት፤ የእኩልነት፤ የፍትሕ ቅኝትና ዜማ፤ ውዳሴና በረከቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ ሳቢ የበዓላት የአከባበር ሥርዓት፣ ጣፋጭ የበዓል ማድመቂያ ዜማዎች፤ የተጣላን አስታርቆ፣ የተበተነውን ሰብስቦ፣ የተቸገረውን መጽውቶ፤ ሀገር የሚያፀናና ትውልድን የሚያሻግር ትውፊት ያላቸው የበርካታ በዓላት ባለቤት ነች። በጋራ በዓላት እንዳሉ ሁሉ የሙስሊምን በዓል ኦርቶዶክሱ አድምቆ፤ የኦርቶዶክስ በዓላትን ወንድም ሙስሊሙ አጅቦ፤ በኢሬቻንም ደምቆና በጋራነት የሚያከበር ማኅበረሰብ መኖሩ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም።

በዓላትን ለማክበር ደግሞ ሠላም ወሳኝ ነው። ከሌለ ሀገርም፤ ሕዝብም፤ ሃይማኖትም የለምና ወንድማማችነት፣ ለሠላም ዘብ መቆምና መተባበር አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።

የኢትዮጵያ የአደባባይ የሃይማኖትና ሕዝባዊ በዓላት ዓለም የሚታደምባቸው፤ ከመሆን አልፈው ነፃነታቸውንና ሠላማቸውን እንደዓይን ብሌን በማየት ሊያውኳቸው የሚሞክሩ ተግባራትን፤ ዝርፊያዎችን፤ ንጥቂያዎችን፤ ማታለሎችን በመከላከል ማሳተፉ የሁልጊዜም የቤት ሥራ ነው።

የጀሞ ደብረ ሠላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ መላከብርሃን ሙላት ክበቤ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ስለሠላም የሚሰብኩ፤ የሰው ልጅ እኩል በመሆኑ ማንም የበላይ ማንም የበታች አለመሆኑን የሚያስተምሩ፤ ሠላምን የሚያውጁ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ያሏት ትልቅ ሀገር ናት ይላሉ። በመሆኑም ታሪካቸው የሆኑ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላትን በሠላም ማከበር ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ።

በዓላት አስተምህሮአቸው አንድነት፤ ይቅርባይነት፤ መከባበር፤ ፍቅርና መዋደድ ነው፤ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላትን ይዘታቸውን፤ ትውፊታቸውን ጠብቀን፤ አስተምህሮታቸውን አክብረን ማሳለፍ አለብን ሲሉ ይናገራሉ።

ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተከበሩ የመጡ በዓላት ናቸው፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ በሠላም እንዲከበሩ ማኅበረሰቡ ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ያስረዳሉ። በበዓላት ጊዜ የሚፈጠሩ ግጭቶች በዓል አክባሪውን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሚጎዱ በመሆናቸው በ2017 ዓ.ም የምናከብራቸው በዓላትን ሠላማቸው የተጠበቀ ማድረግ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በሀገሪቱ የተከሰቱ የሠላም መደፍረሶች ሕዝቡ ስለሠላም አስፈላጊነት የሚረዳበትን መንገድ ላይ በአግባቡ ባለመሠራቱ የመጣ ነው የሚሉት አባ መላከብርሃን፤ በሀገሪቱ ከማዕዘን እስከ ማዕዘን ፍፁም የሆነ ሠላም ለማምጣት ከልብ መሥራት የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በሠላም ዙሪያ ውጤት ለማምጣት ከልብ መሠራት እንዳለበት ያስረዳሉ።

በ2017 ዓ.ም የሚከበሩ በዓላት ትውፊታቸውን በጠበቀ መልኩ በሠላም እንዲከበሩ የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው፤ የሃይማኖት አባቶች ሠላምን ማስተማር፤ ወጣቱም የሃይማኖት አባቶችን በማክበርና መልዕክታቸውን በመስማት ሠላምን ማስከበር እንዳለበት ይጠቁማሉ።

የሀገር ሽማግሌዎች፤ ወላጆች ልጆችን ማስተማርና ሥነምግባር እንዲኖራቸው ማረቅ አለባቸው ያሉት የሃይማኖት አባቱ፤ እርስ በእርስ እየተረዳዱ ችግሮችን የማለፍ ጥበብን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ነው የሚገልጹት።

የሃይማኖት አባት የሆኑት ሀጂ ተሻለ ኪሮ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖትና ሕዝባዊ በዓላት ሠላም የሚያውጁ፤ ስለ በአብሮነትና ለኅብረ ብሔራዊነት አንድነት የተመቹ ናቸው ይላሉ።

ሠላም ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እድገት የሚጫወተው ሚና ትልቅ ነው፤ እኔና ለእኔ ብቻ የሚለው ሃሳብ ሀገር ያጠፋል፤ በመሆኑም የጋራ ተጠቃሚነትን በማጎልበት እኛነትን ማጎልበት ለሰላም ወሳኝ ድርሻ አለው ሲሉ ያስረዳሉ።

ልማትን ለማስቀጠል፤ በዓላቶችን በአንድነት፤ በፍቅር ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ ቤተ-እምነቶችና ብሔር ብሔርሰቦች በዓላትን እንደየባሕልና ወጋቸው ተሰባስበው በጋራ ሊያሳልፉ እንደሚገባም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

በዓላት በአንድ ማዕድ የሚያቋርሱ፤ በደስታና በመከራ ጊዜ በአብሮነት ለመቆም መነሻ የሆኑ የአንድነት ጌጦች ናቸው ያሉት የሃይማኖት አባቱ፤ በዓላት ዛሬም ነገም ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ማድረግ የሁልጊዜም የቤት ሥራ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በ2017 ዓ.ም የሚከበሩ ሃይማኖታዊና የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት ሠላማቸው በተጠበቀ መንገድ እንዲከበሩ ወጣቱ በብሔር፤ በቋንቋ፤ ሳይለያይ በአንድነት መቆም አለበት ሲሉ አስረድተዋል።

ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻገረ የመጣውን አንድነት መጎልበት እንዳለበት አንስተው፤ በዓላት ሲከበሩ የአንዱን ሠላም አንዱ የሚጠብቅበትን አካሄድ ማጠናከር፤ የኢኮኖሚ አቅም ያነሳቸውን የመደገፉ ልምድ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታሉ።

ሳቁንን ደስታውን በጋራ በማድረግ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላትን የፍቅር ማድረግ እንደሚገባም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በቀጣይ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትንም ትውፊታቸው ሳይሸረሸር፤ ይዘታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ፤ የሃይማኖት አባቶች ከፖለቲካና ከፅንፈኝነት ነፃ ሆነው ዜጎችን ላይ የሠላም አዋጅ ማወጅና በሠላም የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ዓለም ለማክበር በጉጉት የሚናፍቃቸው ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ላይ ረብሻ የሚያነሳ ሰው በእምነት የጎደለ ነው፤ ሁሉም እንደየሚከተለው ሃይማኖት እምነቱን አጥብቆ ሠላምን መከተል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በ2017 ዓ.ም የምናከብራቸው በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፤ ሁሉም ማኅበረሰብ በእኔነት ስሜት ሠላምን ማስከበር ይገባዋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላት የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌቶች ናቸው ያሉት ደግሞ የፊንፊኔ ቱሌማ አባ ገዳዎች ሰብሳቢ ሰቦቃ ለታ ናቸው።

ዘመን መለወጫ፤ መስቀል፤ ኢሬቻ፤ ኢድአልፈጥር፤ ጥምቀትና ሌሎችም ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ሠላምን የሚያስተምሩ፤ አንድነትን የሚያፀኑ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገትን የሚያስመዘግቡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በዓላት ፍቅርና ሰላምን በማስተማር አንድነትን አፅንተዋል፤ አንዱ ለአንዱ በችግርና በደስታ እንዲቆም ጠንካራ ባሕል ገንብተዋል። ባሕላቸውንና ትውፊታቸውን ለማስቀጠል ትውልዱ መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ሠላም ካለ ሀገር፤ እምነት፤ እድገት፤ ባሕል አለ፤ ሠላም ለሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ ነው፤ ወጣቶች በቀጣይ በሚከበሩ በዓላት ላይ ሠላም የማስከበር ሥራ መሥራት አለባቸው ይላሉ።

በ2017 ዓ.ም የሚከበሩ በዓላት ልክ እንደወትሮው ሠላምን የሚያውጁ፤ በዩኒስኮ የተመዘገቡ፤ የአንድነት፤ የፍቅር፤ የመከባበር፤ የአብሮነት መገለጫችን በመሆናቸው በሠላም እንዲከበሩ ሁሉም መሥራት እንዳለበት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You