– የሲዳማ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተጠናቀቀ
ሐዋሳ፡-በትግራይ እና በአማራ ክልሎች የምክክር ሥራዎች ከተከናወኑ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በመጪው ጥር ወር እንደሚከናወን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። በሲዳማ ክልል ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲደረግ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ትናንት ተጠናቋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በሲዳማ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በትግራይና በአማራ ክልሎች የሚከናወኑ ክልላዊ የምክክር ሥራዎች ከተሠሩ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በቀጣዩ ዓመት በጥር ወር ይካሄዳል።
በአሁኑ ጊዜ ኮሚሽኑ በክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተሰበሰቡ አጀንዳዎች ወሳኞቹ ተመርጠው በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ምክክር እንደሚደረግባቸው አመላክተዋል።
ምክክሩ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚኖርበት አይደለም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በምክክር ያሉትን ችግሮች በመፍታት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክሩ ሕዝቦች በሁሉም አጀንዳዎች ላይ መፍትሔ የሚፈልጉበት መሆኑን ጠቁመው፤ መፍትሔ በማይገኝባቸው ላይ ሕዝቡ እንዲወስን የሚደረግበት የምክክር ሂደት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ትልልቅ ተቋማት ሀሳባቸውን በተደራጀ መልኩ ለኮሚሽኑ እያቀረቡ መሆኑን የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ማንኛውም የውይይት አጀንዳ ያለው ወገን ያለውን አጀንዳ ለኮሚሽኑ ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሲደረግ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ውጤታማ እንደነበረ ገልጸው፤ ለሂደቱ መሳካት አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
የሲዳማ ክልል የባለድርሻ አካላት ወኪሎች የክልሉን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ አስረክበዋል። በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ከአምስቱ ባለድርሻ አካላት የተመረጡ 25 የባለድርሻ አካላት ወኪሎች የሲዳማ የክልልን አጀንዳዎችን አደራጅተው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።
በሲዳማ ክልል በተከናወነው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከ900 በላይ የሚሆኑ ከሲዳማ ክልል ከሚገኙ 45 ወረዳዎች የተመረጡ የማኅበረሰብ ወኪሎች፣ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች እና የታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም